Saturday, 19 May 2012 10:35

የወተት እጥረት ተፈጥሯል!

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(0 votes)

ካሳንቺስ አካባቢ የምትኖረው ወ/ሮ ሔዋን” የአንድ አመት ህፃን ልጅዋን የላም ወተት ነበር የምታጠጣው፡፡ ሆኖም መኖሪያ ቤትዋን ስትቀይር ከወተት አከራዮችዋ ጋር በመራራቁዋ ልጅዋን የታሸገ የላስቲክ ወተት ለማጠጣት እንደተገደደች ትናገራለች፡፡ የላስቲክ ወተቱን የምትገዛው ከቤቷ አጠገብ ካለ ሱቅ ቢሆንም እንደፈለገችው አታገኝም፤አንዳንዴ ደሞ  የገዛችው ወተት ስታፈላው ይበጣጠሳል፡፡ ከሁሉም በላይ ያማረራት ግን የወተት ዋጋ በየጊዜው መጨመሩ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ከወር በፊት በሰባት ብር የምትገዛው ግማሽ ሊትር ወተት አሁን አስር ብር መግባቱን የምትገልፀው ሔዋን” ዋጋ የጨመረበት ምክንያት ምን እንደሆነ ማወቅ አልቻልኩም ብላለች፡፡ ቢሆንም  ለልጁዋ ስትል መግዛቱዋን አልተወችም፡፡

የወተት አቅርቦት እጥረት እንዳለ የሚናገሩ ከብት አርቢዎች” የከብቶች ቀለብ በመወደዱ  ላሞቹ በቂ ምግብ እንደማያገኙና ወተታቸውም እንደቀነሰ ይገልፃሉ፡፡በጐሮ ሠፈራ አካባቢ ከወንድሞቻቸው ጋር 80 ላሞች የሚያረቡት አቶ አያሌው ጓንጉል”  ለሁለት የወተት ፋብሪካ ድርጅቶች በቀን 160 ሊትር ወተት ያቀርባሉ - ሊትሩን በ9 ብር፡፡ ለአካባቢያቸው ሰዎች ደግሞ በቀን 25 ሊትር ወተት ያከፋፍሉ እንደነበር ይናገራሉ - ሊትሩን በ12 ብር፡፡ አሁን ግን  የላሞቹ መኖ በመወደዱ በቂ ቀለብ አያገኙም የሚሉት አቶ አያሌው” በዚህም የተነሳ የወተት አቅርቦታቸው በመቀነሱ ወተት ለፋብሪካዎች ብቻ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡ አገራችን ወተት የሚፈስባት አገር ናት ብትባልም ወተት የማያገኙ በርካታ ህፃናት መኖራቸውን አቶ አያሌው ይናገራሉ፡፡

የአንድ ሊትር ወተት ዋጋ 20ብር መግባቱን አስመልክቶ የተጠየቁት አቶ አያሌው” የወተት ዋጋ የጨመረው አከፋፋዮች በፈጠሩት ችግር ነው ይላሉ - የዛሬ 10 ዓመት ሊትሩ አንድ ብር ከሃምሳ የነበረ ወተት 20 ብር መግባቱን በመጠቆም፡፡

ቀድሞ ከፋብሪካው ወተት ተቀብለው የሚያሰራጩ አከፋፋዮች በኮሚሽን ይሰሩ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ አያሌው” አሁን  አሰራሩ መቀየሩን ጠቅሰው” አከፋፋዮቹ ከፋብሪካ ተቀብለው በፈለጉት ዋጋ ነው የሚሸጡት ይላሉ፡፡

ለከብቶች መኖ በየወሩ እስከ 70 ሺህ ብር እንደሚያወጡ የሚናገሩት አቶ አያሌው”  ወጪውና ገቢው ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡ በደንብ ያልተቀለበች ላም በቂ ወተት እንደማትሠጥ ጠቁመው” ቀድሞ ለፋብሪካዎቹ ከሚያቀርቡት በተጨማሪ ለ13 ቤተሰብ አንድ አንድ ሊትር ወተት ያከፋፍሉ እንደነበር ገልፀዋል- አሁን ግን ሲተርፍ ብቻ እንደሚሰጣቸው በመጥቀስ፡፡

አስር ላሞች ያላቸውና በጉርድ ሾላ አካባቢ የሚኖሩት አቶ ሞገስ በበኩላቸው” ቀደም ሲል ለወተት ፋብሪካ አንድ ሊትር በ9 ብር 25 ያስረክቡ እንደነበር ገልፀው” አሁን ስለማያዋጣቸው ለነዋሪ  ሊትሩን በ10 ብር እንደሚሸጡ ይናገራሉ- የወተት ፋብሪካዎች የሚሸጡበት ዋጋ ግን በጣም መወደዱን  በመግለፅ፡፡

“ፋብሪካዎች ከእኛ ሊትሩን በ9 ብር እየገዙ አይብና ቅቤ አውጥተውለት በ20 ብር መሸጣቸው ተገቢ አይደለም” ይላሉ - አቶ ሞገስ፡፡

ከወተቱ የሚወጣውን አይብና ቅቤ ፋብሪካዎቹ እንደሚሸጡት የሚናገሩት አቶ ሞገስ” ትርፋቸው ይሄ ሊሆን ይገባል እንጂ የወተት ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ማድረግ የለባቸውም ብለዋል፡፡

“የዛሬውን አያድርገውና የኢትዮጵያ ልጆች ከላም ጡት ወተት ጠብተው ነው ያደጉት” የሚሉት አቶ ሞገስ” የላሞች መኖ መወደድ ስራቸው ላይ ችግር እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ - በወር ለ10 ላሞች 8 ሺህ ብር የቀለብ እንደሚያወጡ በመግለፅ፡፡  የወተት ምርት እጥረትንና የዋጋ መናገርን የፋሚሊ ወተት ማርኬቲንግ ሃላፊ ወ/ሮ አልማዝ ወንድሁን ሲናገሩ፤ በቂና ጥራቱ የተጠበቀ ወተት ለማቅረብ መንግስት ለከብት አርቢዎች የራሳቸው ቦታ በመስጠት ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡

ከገበሬዎች አንድ ሊትር ወተት ከ9 ብር እስከ 12 ብር እንደሚገዙ የተናገሩት ወ/ሮ አልማዝ፤ ወተት በጥራትና በንፅህና መያዝ ስላለበት አወዳድረው እንደሚገዙ ገልፀዋል፡፡ ግማሽ ሊትር በሰባት ብር ለአከፋፋዮች እንደሚያቀርቡ ገልፀው በአንዳንድ ቦታዎች ግን እስከ አስር ብር ድረስ እንደሚሸጥ ማየታቸው እንዳስገረማቸው ተናግረዋል፡፡

የቦራ ወተት ሃላፊ እንደሚሉት፤ በፆም ጊዜ የወተት ፍላጐት ስለሚቀንስ ግዢያችን በግማሽ ይወርዳል፤ አቅራቢዮቻችን ደግሞ እንደሌላው ጊዜ እንድንወስድላቸው ያስገድዱናል፤ እኛ ደግሞ ስለሚያከስረን መቀበል አንችልም፤ በዚህ ምክንያት ደንበኝነታቸውን ያቋርጣሉ፡፡ የአሁኑ የወተት እጥረት የተፈጠረውም በዚሁ ምክንያት ነው ይላሉ - ሃላፊው፡፡ ከአቅራቢዎች ሊትሩን 11 ብር ገዝተው ለአከፋፋይ ግማሽ ሊትር በሰባት ብር እንደሚሸጡ የገለፁት የቦራ ወተት ሃላፊ፤ ሆኖም ነፃ ገበያ በመሆኑ በዚህ ዋጋ ለምን አልሸጥክም ማለት አንችልም፤ ከሚገባው በላይ ዋጋ የጨመሩ አከፋፋዮች ካሉ ግን ውላችንን እናቋርጣለን ብለዋል፡፡ የግብርና ሚኒስቴር ህዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ አቶ ማህመድ ሸምሱ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል በነበረው ፋት ኤንድ ማውዝ ዲዝዝ (አፍ ከእግር) እየተባለ በሚጠራው በሽታ ምክንያት አቅርቦት ቀንሶ ነበር፤ አሁን ግን ይህ ችግር ሙሉ በሙሉ ተቀርፎ ወተት በብዛት እያገኘን ነበር፤ ሆኖም ከዝናብ ጋር በተያያዘ ችግር የመኖ እጥረት በመፈጠሩ አቅርቦት መቀነሱን እናውቃለን ብለዋል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል መምጣታቸውን የሚናገሩት ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ያደሳ” ወተት የሚገዙት በቡና ለመጠጣት ቢሆንም በፈለጉ ጊዜ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልፀዋል፡፡ በአገራችን ወተት እንደፈለግን ነው የምንጠጣው ያሉት ወ/ሮ ኤልሳቤጥ “ ወተት እንደ ወርቅ በላስቲክ ታሽጐ መሸጡ እንዳላስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡  ከማነሱ መወደዱ አሳስቦኛል  ብለዋል - ወይዘሮዋ፡፡

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚጠቁመው” አገሪቱ (በ2010/11ዓ.ም) 4.1 ቢሊዮን ሊትር ወተት አምርታለች፡፡ በአገራችን ከሚገኙ 53 ሚሊዮን ከብቶች ውስጥ 10.5 ሚሊዮን የሚታሰቡ ላሞች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከአንድ ላም የሚገኘው የወተት መጠን በ17 በመቶ ቀንሷል -ከአምናው፡፡

 

 

 

Read 14404 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 12:33