Print this page
Saturday, 27 October 2018 09:29

ነገ በአማራ ክልል ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች ይካሄዳሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

     የፌደራል መንግስት ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ጉዳት እያጋጠማቸው ላሉት የጣና ኃይቅና የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ትኩረት እንዲሰጥ እንዲሁም የማንነት ጥያቄ በሚያነሱ ዜጎች ላይ
የሚደርስ የኃይል እርምጃ እንዲቆም የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ በጎንደር፣ በደብረ ታቦር፣ በባህር ዳር፣ በወልዲያና በሌሎች የአማራ ከተሞች ይካሄዳል ተብሏል፡፡  የጎንደሩ ሰላማዊ ሰልፍ “በአማራ ወጣቶች ማህበር በጎንደር” አስተባባሪነት እንደሚካሄድ የማህበሩ ሊቀመንበር ወጣት ይሁኔ ዳኛው ለአዲስ አድማስ የገለፀ ሲሆን ሰልፉን  አስመልክቶም ከከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽ/ቤትና ከፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ምክክር ተደርጎ፣ እውቅና መገኘቱን ጠቁሟል፡፡ በእንቦጭ አረም የተወረረው የጣና ኃይቅ አስቸኳይ እልባት እንዲያገኝ፣ በላዩ ላይ በተሰራው መጠለያ ምክንያት አደጋ የተጋረጠበት የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት በአስቸኳይ  ይጠገን ዘንድ የፌደራል መንግስት ትኩረት እንዲሰጠው በሰላማዊ ሰልፉ እንጠይቃለን ያለው ወጣት ይሁኔ፤ በራያ፣ በወልቃይትና በሌሎች አካባቢዎች የአማራ ማንነት ጥያቄን ያነሱ  ዜጎች ምላሽ እንዲሰጣቸውም የምንጠይቅበት ይሆናል ብሏል፡፡ ሰላማዊ ሰልፉን ፍፁም ሰላማዊ ለማድረግ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ሰፊ ውይይት መደረጉንም አስታውቋል፡፡  ደብረ ታቦር የሚካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ከሚያስተባብሩ ወጣቶች አንዱ የሆነው ወጣት ጌታቸው ለሰልፉ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብሏል፡፡ በባህርዳርና በወልዲያ ከተሞችም ተመሳሳይ
አላማ ያለው ሰልፍ በተመሳሳይ ጊዜ ይካሄዳል ተብሏል፡፡ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች በነገው እለት ይካሄዳሉ የተባሉትን ሰላማዊ ሰልፎች በተመለከተ ከክልሉ መንግስት ለማረጋገጥ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡ ለአማራ መንግስት የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በተደጋጋሚ የስልክ ጥሪና አጭር መልዕክት ብናደርግም ምላሽ አላገኘንም፡፡


Read 6952 times