Saturday, 20 October 2018 14:17

ኢትዮ-ኤርትራ የሙዚቃ ኮንሰርት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)


    “ኤሊያስ አድቨርታይዚንግ ፕሮሞሽንና ኤቨንት” ከኢትዮ ኤርትራ የሙዚቃ ኮንሰርት አዘጋጅ ኮሚቴ ጋር በመተባበር በመጪው ጥር 11 ቀን 2011 ዓ.ም በጊዮን ሆቴል የኢትዮ-ኤርትራ የሙዚቃ ኮንሰርትን እንደሚያዘጋጁ ታውቋል፡፡ አዘጋጆቹ ባለፈው ረቡዕ  በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል በሰጡት መግለጫ፤ የሙዚቃ ኮንሰርቱ ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች በፖለቲካዊ ቀውስ በትስስር ከኖሩበት ህይወት ለ20 ዓመታት ተለይተው ከቆዩ በኋላ በቅርቡ ዳግም የተፈጠረውን ግንኙነት ምክንያት በማድረግ፣ የአገራቱንና የህዝቦቹን ወዳጅነት ይበልጥ ለማደስና ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ ተነግሯል፡፡  
ታዋቂ የኢትዮጵያና የኤርትራ አርቲስቶች በሚሳተፉበት በዚህ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ይታደሙበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው የዝግጅቱ አስተባባሪ አርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ)፤ መንግስትም እውቅና ሰጥቶ የትብብር ደብዳቤ መፃፉን አስታውቋል፡፡ ከኮንሰርቱ ቀደም ብሎ ባሉት ቀናትም ኪነ ጥበባዊ አውደ ርዕይ፣ በተለያዩ የሙያ መስክ ላይ የተሰማሩ የሁለቱ አገራት ምሁራን በኪነ ጥበብ ዙሪያ የሚያቀርቡት ጥናታዊ ፅሁፍ፣ የኢትዮ-ኤርትራ አርቲስቶች የልምድ ልውውጥና በቀጣይ አብሮ የመስራት ምክክር፣ የባህልና ቱሪዝም ሲምፖዚየምና ሌሎችም ዝግጅቶች የፕሮግራሙ አካል እንደሚሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከአዲስ አበባው ኮንሰርት በመቀጠልም ከስድስት በላይ የሆኑ የኢትዮ-ኤርትራ አርቲስቶች በአዲስ አበባ፣ በአስመራና ምፅዋ የሙዚቃ ኮንሰርቶች በተከታታይ ያቀርባሉ ተብሏል፡፡

Read 4364 times