Saturday, 20 October 2018 14:15

ማህበራዊ ንቅዘትን በወኔ የተፋለመው ወጣት

Written by 
Rate this item
(4 votes)

   (“ዘ ያንግ ክሩሴደር”)
 የመጽሐፉ ርዕስ- “ዘ ያንግ ክሩሴደር”
 ደራሲ- ሰለሞን ኃይለ ማሪያም
 የገጽ ብዛት - 220
 ሒሳዊ አስተያየት - በተሾመ ብርሃኑ ከማልበደራሲ ሰለሞን ኃይለማሪያም ‹‹ዘ ያንግ ክሩሴደር›› (ማህበራዊ ንቅዘትን በወኔ የተፋለመው ወጣት) በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ተደርሶ፣ በ2003 ዓ.ም በኮድ ኢትዮጵያ ለህትመት የበቃው መጽሐፍ፤ በ2010 ዓ.ም ወደ ጀርመንኛ ለመተርጎም በቅቷል፡፡ መጽሐፉ ወደ አማርኛ ከመተርጎሙ በፊት ወደ ጀርመንኛ ተተርጉሞ ለንባብ መብቃቱ የሚገርም ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ በኢትዮጵያዊ ደራሲ የተጻፈና ያነሳው ርዕሰ ጉዳይ ትምህርታዊ ከመሆኑ አንጻር፣ ይህን የሥነ ጽሁፍ ሥራ በመገምገም እግረ መንገድም ማስተዋወቅ  ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡  

የመጽሐፉ መጠንሰስ
በነሐሴ ወር 2003 ዓ.ም ላይ ኮድ ኢትዮጵያ እና ኮድ ካናዳ የተባሉ አጋር መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ ዕድሜያቸው ከ12-18 ለሆኑ ወጣት አንባቢያን የሚመጥን የልቦለድ ታሪክ (የስነጽሑፍ) ውድድር አዋጅ ያስነግራሉ፡፡ ተወዳዳሪዎች  የሚያቀርቡት የልቦለድ ሥራ፤ ከዘመኑ ማኅበራዊ  ሕይወት ጋር የተዛመደ፣ ወጣቶች የማህበረሰቡ አባላት በመሆናቸው፣ በአፍላ ዕድሜያቸው ፊት ለፊት የሚጋፈጡት የማህበራዊ ሕይወት ቀውስ ፈተና ምን እንደሚመስል  የሚያንጸባርቅ  ወይም በሀገሪቱ ማህበራዊ ለውጥ እንዲያመጣ ታስቦ መዘጋጀት እንዳለበት የሚያሳስብ ነበር- የውድድር መመሪያው፡፡
ደራሲ ሰለሞን ኃይለ ማሪያም፤ ይህንን የውድድር መመሪያ ከመረመረ በኋላ ተልእኮው የማህበረሰቡን ቁስል ማወቅና የማህበራዊ ጠንቁን ዓይነት፣ ምንነት፣ ስፋትና ጥልቀት መጠቆም ብቻ ሳይሆን መፍትሔው ምን እንደሆነ ለመጠቆምም ውድድሩ መልካም አጋጣሚ የፈጠረለት ይመስላል፡፡ በዚያ ወርቃማ አጋጣሚም፣ በደራሲው ውስጥ ሲብሰለሰል የኖረው ማህበራዊ ንቅዘት፣ አድማሱ ስዩም ብሎ በቀረጸው ዋነኛ ገጸ ባህርይው አማካኝነት መፍሰስ ጀመረ፡፡

ታሪኩ
አድማሱ የተባለው ዋነኛ ገጸ ባህርይ፣ ገና ከልጅነት ዕድሜው ጀምሮ ወደ ሥራ ዓለም እስከ ተሰማራበት ጊዜ ድረስ ሙሰኝነትን የተዋጋ ቅን ዜጋ ነው፡፡ ተማሪ ሳለ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄድ፣ ሰዎች የተፈጨ በርበሬን ከደቀቀ ጡብ ጋር እየቀላቀሉ ለሽያጭ ሲያዘጋጁ ይመለከትና፣ ለፖሊስ ይጠቁማል። ይህም በጓደኞቹ ዘንድ እንዲታወቅና መልካም አርአያ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በሁለተኛ ጊዜ የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ጉቦ እየተቀበሉ፣ መጠኗ አነስተኛ በሆነች ክፍል ተጨናንቀው ምን እንደሚያደርጉ  ይገነዘብና፣ ያንን አሳፋሪ ተግባር ያጋልጣል፡፡ የርዕሰ መምህሩም ጉዳይ በአድማሱ ጥቆማና ክትትል  ወደ ወላጅ ኮሚቴ ቀርቦ ከሥራቸው  ይባረራሉ፡፡ አድማሱ የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን ጨርሶ በአንድ ዕቃ መለዋወጫ መሸጫ መደብር ሲቀጠርም፣ አጭበርባሪዎች ይገጥሙትና፣ ፊት ለፊት ተጋፍጦ፣ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ያደርጋል፡፡
ይሁንና በሕይወት የሚገጥምን ፈተና ፊት ለፊት ተጋፍጦ ማለፍና በአሸናፊነት የመወጣት ጉዞ  አልጋ ባልጋ ሊሆን አይችልም፡፡ ለህብረተሰቡ ጥቅም ሲል  በጀግንነት በመታገሉ ሊያሸልመው፣ ሊያስመሰግነውና ሊያስከብረው ሲገባ በሐሰት መረጃ ይወነጀላል። በዚህም ብዙ  እንግልት ይደርስበታል፡፡ ሆኖም  የሚገጥመውን ፈተና በጽናት  ይወጣዋል፡፡
ከካበተ የሕይወት ልምዳቸውና ዕውቀታቸው የሚያካፍሉት የገነተ ልዑሉ የምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ሽማግሌው አቶ ንጋቱ፤ በአድማሱ ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ ይዘው እናገኛቸዋለን፡፡ ያለ ማቋረጥ በመለወጥ ላይ በምትገኘው ዓለም ውስጥ እራስን ከለውጡ ጋር አስማምቶ መጓዝ፣ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ  መሆኑን ከምሁሩ አንደበት እንገነዘባለን፡፡ ስለ ቤተሰብ ምጣኔ፣ ራዕይ ስላላቸው ወጣቶችና ፊት ለፊት የሚጠብቃቸውን የሕይወት ፈተና እንደምን ተጋፍጠው ድል እንደሚያደርጉት መጽሐፉ አቅጣጫ ያመላክታል፡፡

የልቦለዱ ጭብጥ
ታሪኩ የሚፈጸመው በመዲናችን አዲስ አበባ ልዩ ልዩ ስፍራዎች ሲሆን ዘመኑም ያለንበት ነው፡፡ የታሪኩ ምንጭም በማህበራዊ ንቅዘት የተዘፈቀው ህብረተሰብ ነው፡፡ የመጽሐፉ ዋነኛ ጭብጥ፤ ማህበራዊ ንቅዘት ለእድገታችን ጸር ነውና እንዋጋው፣ ወደዚህም የውጊያ መስክ ነገ ኃላፊነትን የሚረከበውን ወጣት ትውልድን አስገብተን፣ በለጋ ዕድሜው በማሰልጠን፣ በደመ ነፍስ ሳይሆን በስልት እንዲዋጋው እናስችለው በሚል መሠረታዊ ሐሳብ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ጋናዊው ደራሲ አርማህ፤ ‹‹ዘ ቢዩቲፉልስ አር ኖት የት ቦርን›› (ቆንጆዎቹ ገና አልተወለዱም) በሚል ርእስ እ.ኤ.አ በ1968 ለንባብ ባበቃው መጽሐፉ፣በወቅቱ የነበረውን ማህበራዊ ንቅዘት እንዳሳየውና ካሜሩናዊው ደራሲ ፈርዲናንድ ኦዮኖ፤ «ቦይ» ወይም «ዘ ሐውስ ቦይ» በተሰኘው መጽሐፉ፤ የነጮችን ደካማ አስተሳሰብ እያዋዛ እንደሚተቸው ሁሉ፣ ሰለሞንም እያዋዛ ማህበራዊ ሕጸጻችንን ሊነግረን ይሞክራል፡፡ «ዘ መኒይ ኦርደር» የተሰኘ መጽሐፍ የጻፈው ሴኔጋላዊው ደራሲ ዑስማኔ ሰንባኔ «ኒው ዮርክ ታይምስ» እና «ታይምስ» ከመሳሰሉ መጽሔቶች ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ ሲናገር፤ «ያደረግሁት ነገር ቢኖር አፍሪካውያን ያልተገሰሰ ድንግል የኪነ ጥበብ ሐብት በውስጣቸው እንዳላቸው ማሳየት ነው፤ መቸም አንድ ሰው ሲፈጥር አገሩን እንጂ ዓለምን እያስተነተነ አይፈጥርም። በመሠረቱም በአፍሪካ ውስጥ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉት አፍሪካውያን እንጂ አሜሪካዊያን ወይም ፈረንሳውያን ወይም ሩሲያውያን ወይም ቻይናውያን ሊሆኑ አይችሉም፡፡» ብሏል፡፡ ሰለሞን ኃይለማሪያም በመጽሐፉ ያሳየን ይህንኑ ነው፡፡  
የመገምገሚያ አውድ
በመሠረቱ፣ በሀገራችን ያለው ማህበራዊ ንቅዘት ምን እንደሚመስል ለማወቅ ሩቅ መሄድ አያስፈልግም። አንድ ህጻን ልጅ ለመላክ መደለያ በመስጠት ይጀመራል። በትምህርት ቤት ‹‹ካስኮረጅከኝ ይህን አደርግልሃለሁ›› በሚል ይቀጥላል፡፡ “የሚያስፈራራኝን ከመታህልኝ ገንዘብ ከየትም አምጥቼ እሰጥሃለሁ” ወደሚል የሚታለፈውም በልጅነት ዘመን ነው። በቤት ብቻ ሳይሆን በጎረቤት፣ በቀበሌ፣ በመንደር፣ በትምህርት ቤት በመደለያ፣ በጉቦ፣ በሸፍጥ፣ አስመስሎ በመንገርና በማስመሰል የሚታዩ፣ የሚሰሙና የሚደረጉ ብዙ ማህበራዊ ህጸጾች አሉ፡፡  እድሜ ከፍ እያለ በሄደ መጠን የማህበራዊ ቀውሱ ዓይነትና መጠን እያደገ እንደሚሄድም አያጠያይቅም፡፡
የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ባቀረበው አንድ የታተመ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ እንደጠቆመው፤ «ጉቦ» ለሚለው ቃል አዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት፤ «ፍርድን ለማጣመምና ሐሰትን ዕውነት ለማስመሰል ለሐሰተኛ ዳኛ የሚበረከት መማለጃ ነው፡፡ ስለሆነም ጉቦ በስጦታም ሆነ በበረከት፣ በእጅ ማራሻም ሆነ በጉርሻ፣ በምልጃም ይሁን በደጅ ጥናት፣ በማሞገስም ሆነ በማሞካሸት፣ የቅዱሳን ሁሉ ቅዱስም ሆነ የብፁአን ሁሉ ብፅእ አድርጎ በግልም ሆነ በጋራ ማቅረብ፣ የማይገባን ጥቅም ለማግኘት ከሆነ፣  ዞሮ ዞሮ ሕገ ወጥ ድርጊትን ለመሸፋፈንና ፍርድን ለመገምደል የሚያገለግል ማህበራዊ ንቅዘት ከመሆን አያልፍም» ሲል ፍቺውን ከእነ ማብራሪያው ይሰጣል፡፡  
ይህንኑ ቃል ዌብስተር የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ መስረቅ፣ መዝረፍ፣ ማጭበርብር፣ ማታለል፣ ከፍተኛ እምነት የተጣለበትን ዳኛ ወይም ባለሥልጣን ኃላፊነቱን እንዲዘነጋ የሚሰጥ ሽልማት ስጦታ ውለታ፣ ወዘተ በማለት ያፍታታዋል፡፡ ብላክስ ሎው የተባለው የታወቀ መዝገበ ቃላት ደግሞ (አነስተኛም ይሁን ከፍተኛ) በሕጋዊ ኃላፊነት ያለን ባለሥልጣንን (በአንድ ጉዳይ ላይ ያለውን) አመለካከት፣ አስተሳሰብ በተፅዕኖ ለማሳመን ሲባል ማንኛውንም ዋጋ ያለውን ነገር በስጦታ፣ በበረከት፣ በድርጎ፣ ወይም በሌላ መልክ መስጠትና መቀበል እንደሆነ ይገልጸዋል፡፡ እንደዚሁ በሌላ መዝገበ ቃላት ትንታኔ፤ «የራስ ያልሆነን ሀብትና ንብረት በተለያየ መልኩ መውሰድ» ማለት ሲሆን በቀጥታ እኪስ ውስጥ ዘው ብሎ ባይገባ፣ ቤት ሰርስሮ ሳጥን ሰብሮ በድፍረት ባይሰርቅ፣ አሳቻ ቦታ ቆሞ ባይነጥቅ፣ የዚያን ከዚህ አምጥቶ የማይሆነውን «ይሆናል»፣ የሚሆነውን «አይሆንም» በሚል ወይም ልብን አፍዝዞና አደንግዞ ባይወስድ፣ ጉቦ የራስ ሀቅ ያልሆነን ሀብት፣ ንብረት ወይም ሌላ መንፈሳዊ ስጦታን በሥልጣን ተጠቅሞ መቀበል፣ መስረቅ፣ መዝረፍ፣ ማጭበርበርና ማታለል መሆኑን ያብራራል፡፡
በርግጥም መንግሥት የጣለበትን ከፍተኛ ኃላፊነት ዘንግቶ ሥልጣኑን ለሕዝብ ዕድገትና ብልፅግና ማዋል ሲገባው የራሱን ጥቅም የሚያሳደድ ከሆነ፣ በቢሮ ውስጥ ከመቀመጡ በስተቀር ጫካ ከገባ ወንበዴ፣ ጨለማን ተገን አድርጐ ቤት ከሚሰረስር ሌባ፣ አካባቢውን በቁጥጥር ሥር አድርጐ ከሚዘርፍ ነጣቂ፣ የሰው ኪስ ከሚገባ ሞሽላቃ ሌባ ሊለይ አይችልም፡፡ ጉቦ በጉልተኛው ሥርዓት መተያያ፣ እጅ መንሻ፣ ፊት መፍቻ፣ ጉርሻ፣ ወዘተ የወግ ስሞቹ ሲሆኑ መደለያ፣ መማለጃ፣ መሸንገያ፣ ወዘተ የሐሜት መጠሪያዎቹ ነበሩ፡፡ የማዕረግ ስሞቹ ደግሞ አመኃ፣ ገፀ በረከት፣ ሙገሳ፣ ውደሳ፣ ቅደሳ፣ በመባል ይታወቁ ነበር፡፡ ማስታወሻ፣ መታሰቢያ፣ ስጦታ--- የሚሉት ደግሞ ከቁልምጫ ስሞቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ «የመንግሥት ገቢን የሚሰበስብ ባለሥልጣን ማር የፈሰሰበት ምላስ» የሚል የህንዶች ተረት ይጨመርበታል፤ «ተሹሞ የማይበላ ተጥዶ የማይፈላ የለም» የሚል የአገራችንን አባባልም ይጠቀሳል፡፡ «ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል» ተብሎም እንደ ትልቅ ነገር አዋቂ ተብዬዎች በምክር ስም የሚሰጡት ምሳሌያዊ አነጋገር ነው፡፡
ሥነ ጽሁፋዊ ውበት
ምንም እንኳን ድርሰቱ ያነሳው ጭብጥ  ጠንካራና መረር ያለ ቢሆንም በውብ ቋንቋና ተጀምሮ እስኪያልቅ ስሜትን ሰቅዞ በሚይዝ የአተራረክ ሥልት በመቅረቡ ተነባቢና ተወዳጅ ሊሆን በቅቷል፡፡ ለሽልማት የበቃውም ሆነ በሌላ ቋንቋ ለመተርጎም የታደለው አንድም በዚህ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ በእርግጥም የተደራሲውን  ስሜት ጨምድዶ ካልያዘ፣ የታሰበለትን ግብ ከቶ ሊመታ አይችልም፡፡
ደራሲው ማነው?
ደራሲው ሰለሞን ኃይለማሪያም በ220 ገጾችና በ29 ምዕራፎች ከፋፍሎ፣ ድርሰቱን  ውድድሩን ላዘጋጀው ለኮድ ኢትዮጵያ  ያቀርባል፡፡ ‹‹ዘ ያንግ ክሩሴደር›› የሚል ርዕስ የሰጠው የልቦለድ ሥራውም አንደኛ ይወጣና የበርት ሽልማት ድርጅት በአፍሪካ የአሸናፊነት የምስክር ወረቀትና የገንዘብ ሽልማት ያገኛል፡፡ ይህ መጽሐፍ ወደ ጀርመንኛ የተተረጎመ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ አታሚዎች ታትሞ በኬንያ፣ በኡጋንዳ፣ በታንዛኒያና እና በሱዳን የመጻህፍት መደብሮች ለሽያጭ ቀርቧል። አማዞን የተባለው የኢንተርኔት ገበያም በዲጂታልና  በሕትመት ለአንባቢያን አቅርቦታል፡፡ በሀገራችን ብዙም ባይታወቅም  በሜጋ አሳታሚና አከፋፋይ እንዲሁም በዩኒቨርሳል መጻሕፍት መደብር ይገኛል፡፡
ሰለሞን ኃይለማሪያም የተወለደውና ያደገው አዲስ አበባ ውስጥ ሲሆን ደራሲ፣ ተርጓሚ፣ የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ነው፡፡ በተጨማሪም ለቪኦኤና ቢቢሲ ኮረስፖንደንት ሆኖ ሰርቷል፡፡ በኢትዮጵያ ተቋቁሞ የነበረው ፔን ኢንተርናሽናል የተባለ የስነጽሑፍ ክበብ ፕሬዚደንት በመሆንም አገልግሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከቤተሰቡ ጋር በካናዳ ይኖራል፡፡ ደራሲው “ላቭ ኤንድ አንዛይቲ” የተሰኘ መጽሐፍም ለአንባቢያን አድርሷል፡፡ የበርት አዋርድ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ተሸላሚ ለመሆንም በቅቷል። እ.ኤ.አ በ2016 እና 2017 የጻፋቸው የአጫጭር ልቦለድ መድበሎችም የተደነቁለት ሲሆን የተወሰኑት ሥራዎቹም  ወደ ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛና ስዊድንኛ ተተርጉመውለታል፡፡
እንዴት ወደ ጀርመንኛ ተተረጎመ?
ሰለሞን ኃይለ ማሪያም ‹‹ዘ ያንግ ክሩሴደር›› በሚል ርእስ የጻፈው ልብወለድ መጽሐፍ  በአንድ አውስትሪያዊ ደራሲ እጅ ይገባና የመነበብ ዕድል ያጋጥመዋል፡፡ በአጻጻፍ ውበቱና በታሪኩ የተሳበው ሔልሙት ኤ ናይደር፤ ወዲያው ወደ ጀርመንኛ ተረጎመውና ለህትመት በቃ፡፡ ወደ አማርኛ ግን እስካሁን አልተተረጎመም፡፡  
በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እምነት፣ መጀመርያውኑ ድርሰቱ በአገር ውስጥ  ቋንቋዎች ቢጻፍ፣ ያም ባይሆን ደግሞ ወዲያው በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ቢተረጎም መልካም ነበር፡፡ አሁንም የመጽሐፉ ትምህርታዊ ፋይዳው ከግምት ውስጥ ገብቶ፣ በሀገር ውስጥ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ፣ በሥርዓተ ትምህርቱ ቢካተት ጥሩ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

Read 1091 times