Saturday, 20 October 2018 14:13

ከቴአትርና የፊልም ‹‹ግምገማ›› ባሻገር

Written by  ቢንያም ወርቁ
Rate this item
(2 votes)

 እንደ አንድ የቴአትርና የፊልም አፍቃሪና ባለሙያ፣ መስከረም 26 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀትር በኋላ፣ የሰማሁት ዜና ለእኔ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ከ27 ዓመት በኋላ ቴአትርና ፊልም ከአዲስ አበባ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የሳንሱር ማነቆ በመገላገላቸው ለኢንዱስትሪው ትልቅ የምስራች ነው፡፡
ፊልሞችና ቴአትሮች እንደ ትምህርት ቤት ዕውቀት የሚሰጡ፣ እንደ ቤተ እምነት ሥነ ምግባር የሚያስተላልፉ፣ እንደ የህክምና ተቋማት የሚያክሙ፣ እንደ መዝናኛ ቦታ የሚያነቃቁ፣ እንደ ገበያም የሚያተርፉ ናቸው፡፡ ወደድንም ጠላን ወጣቶች ከትምህርት ቤትና ከቤተ እምነት የሚያገኙትን ትልቅ ቁም ነገር ከፊልምና ከቴአትር ያገኙታል፡፡ ከፋም ለማም ሙያው ክፍተትን ይሞላል፡፡
ሆኖም፣ በሀገራችን ከሥዕል፣ ከሙዚቃና ከሥነጽሑፍ፣ በአጠቃላይ ከሚነበቡና ከሚታዩ የጥበብ ውጤቶች አንጻር እንደ ቴአትርና ፊልም ጥበባት የተበደለ አልነበረም፡፡ አሁን ቢሮው፣ ግምገማን ማቆሙና ህገ መንግስቱን ብሎም ሰው በመሆን ብቻ ልናገኘው የሚገባን መብት መሆኑን አምኖ እንከኑን ማስወገዱ የሚያበረታታ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ዘመን ቴአትርና ፊልም/ሲኒማ/ ከላይ ከተቀረፈው ችግር ውጪ በርከት ያሉ ችግሮች አሉባቸው፡፡ እናም እነሱም በነካ እጅ ቢታሰቡ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ። እርግጥ ቀጥዬ የማነሳቸው አንዳንድ ነጥቦች የአዲስ አበባ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊነት ባይሆኑም፣ ቢሮው ችግሩን ከተረዳው በሚመለከታቸው አካላት ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላልና ሌሎች ጉዳዮችን በዚሁ አጋጣሚ ላነሳ ፈለግሁ፡፡

1   የቴአትር የአዳራሽ ኪራይ ነገር
ቴአትር ቤቶች ቴአትር ሰርተው ለህዝብ እንዲያሳዩ፣ታዳሚውን እንዲያዝናኑና እንዲያስተምሩ ነው የሚከፈቱት፡፡ ቴአትር ቤቶች ቴአትር ካልሰሩ ቴአትር ቤትነታቸው ቀርቶ የመሠብሰቢያ አዳራሽ ብቻ ይሆናሉ፡፡ ህብረተሰቡም ከቴአትር የሚያገኘውን ጥቅም ያጣል፡፡
እንደሚታወቀው፤ የሀገራችን ቴአትር ቤቶች በቀጠሯቸው ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን ከውጭ ባሉ ኢንተርፕራይዞችና ክበቦች በጋራ የመሥራት የቆየ ባህል ነበራቸው፤ አሁንም አላቸው፡፡ ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ የቴአትር ቤቶች የአዳራሽ ኪራይ ዋጋ መናር የቴአትር ባለሙያዎችን የሚያበረታታ አይደለም፡፡ በዚህ ዘመን ቴአትር ቤት ተከራይተው የሚያሳዩ ኢንተርፕራይዞች ገቢያቸው የአዳራሽ ኪራዩን መክፈል ስለማያስችል ከኪሳቸው ተጨማሪ እየከፈሉ በመሥራት ላይ ናቸው፡፡
አንዳንድ ቴአትር ቤቶች ተከራይ ስላጡ አዳራሾቹ ሳይሰራባቸው ወራት አልፈው ዓመታት እየተቆጠሩ ነው፡፡ እንደ አዲስ አሁን በተፈጠረው መልካም አጋጣሚ የቴአትር ተመልካች ለመፍጠርና የነበሩትን የቴአትር ተመልካቾች ለመመለስ የአዳራሽ ኪራይ ጉዳይ ታስቦበት ሊስተካከል ይገባል፡፡

2   የቀረጥ ነገር
በሀገራችን ከመኪና እና ከጥቂት የቅንጦት እቃ ከሚባሉ፣ ግን መሠረታዊ ከሆኑ ቁሳቁሶች ውስጥ የሚመደበው ቴአትርና ፊልም፣ ከፍተኛ ቀረጥ በመክፈል  የሚታወቅ ሙያ ነው፡፡ መንግስት ለሙያው ምንም አይነት እገዛ ሳያደርግ ከሌላው ንግድ በተለየ መልኩ፣ ገና ትርኢቱ ለህዝብ ሳይቀርብ፣ በከፍተኛ ቀረጥ ትኬት ቆርጦ ያስከፍለዋል፡፡ ሙያተኛው፣ለትርኢቱ ቁሳቁስ ሲገዛ ለመንግስት ይከፍላል፡፡ ለባለሙያ ሲከፍል ይከፍላል፡፡
በአጭሩ አንድ ኢንተርፕራይዝ ሁሉም ለፍቶ ከሚያስገባው በላይ ለመንግስት ክፍያ ይፈጽማል፡፡ እርግጥ ትርኢቱ /ፊልሙ፣ ቴአትሩ/ ተመልካች ካለው ትርፍ ሊያገኝ ይችል ይሆናል፡፡ ካልሆነ ግን በገዛ እጁ እዳ ውስጥ ይገባል፡፡ የእነ ኬንያን የእነ ናይጄሪያን ወይም የህንድንና የአሜሪካን ልምድ በመቃኘት፣ የሀገራችንንም የጥበብ ሥራ፣ ከቀረጥ የመሰብሰብ ሂደት ሊስተካከል ይገባዋል፡፡

3  ለኢንዱስትሪው ጠቃሚ የሚሆኑ ዕቃዎች ከውጭ የማስገባት ጉዳይ
 በ1950ዎቹ የወጣ ህግ፣ የውጭ የባህል ወረርሽኝ ለመከላከል በሚል ሰበብ ከፍተኛ ቀረጥ ተጥሎበት የነበረው የፊልም ቀረጥ ዛሬ ድረስ ቀጥሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶክተር)፣ ከቴዎድሮስ ተሾመ ጋር በመሆን በደራሲነት የተሳተፉበት ‹ሶስት ማዕዘን› የተሰኘው ፊልም፣ የተቀረፀበት ሬድ ካሜራ በአሁኑ ጊዜ ጉምሩክ ተዘግቶበት ይገኛል፡፡ የቴዎድሮስ ሬድ ካሜራ በቀረጥ የተያዘበት ጉዳይ በጣም ብዙ ታሪክ ስላለው እሱ ላይ ጊዜ ማጥፋት ቢሆንም፣ ለኢንዱስትሪው መስፋፋት ጠቃሚ የሆኑ ቁሳቁሶችን ከውጭ ሀገር ማስመጣት ቀላል እንዳልሆነ ማሳያ ይሆናል፡፡
አንድ ባለሙያ፣ ለፊልም ሥራ ሁለት ካሜራ ይዞ ከውጭ ሀገር ቢገባ፣ የጉምሩክ ሰራተኞች አንዱን ነጥቀውት ሌላውን ካሜራው ከገዛበት በርካታ እጥፍ ገንዘብ ይጠይቁታል፡፡ በአጭሩ የሀገራችን መንግስት ካሜራ ሳይሰራ እርስዎ ገዝተው ካመጡት ከሰራውም ከሸጠውም የበለጠ ገንዘብ ይሰበስባል፡፡ በነገራችን ላይ አንድ ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ፣ ከውጪ ሀገር ሁለት ካሜራ ይዞ ሲገባ ቀረጥ አይከፍልም፡፡ ዲያስፖራውን ማበረታታት ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ኢትዮጵያዊ የፊልም ባለሙያ በማያዋጣ ገበያና ፈጽሞ በመንግስት በማይበረታታበት ሀገር ከአንድ ካሜራ በላይ ይዞ መግባት አይቻልም፡፡
የኪነ ጥበቡ ባለሙያ፣ ለሀገሩ ጠብ የሚል ነገር እንዲሰራ የመጣው መንግስት ሁሉ ጥሪ ያስተላልፋል። ግን ሙያተኛው ጠብ የሚል ነገር እንዲሰራ ምንም አይነት እገዛ አያደርግም፡፡ የሀገራችን ፊልሞች በውጪ ሀገር የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ ሲቀርቡ በጥራት ደረጃቸው ማለትም በካሜራ፣ በመብራት፣ በድምፅ ወዘተ ቴክኒኮች፣ ከሌላው ሀገራት ጋር ለመወዳደር የማይችሉ ናቸው፡፡ ግና በዚህ ችግር ውስጥም ሆነው፣ በትወና ብቃታቸው ጥሩ ስም ያገኙ ተዋንያን አሉን። ለዚህ ማስረጃም ‹የሶስት ማዕዘኑ› ሳምሶን ታደሰ እና ‹የሎሚ ሽታዋ› ኤልሳቤጥ መላኩ ከሌሎች አፍሪካውያን ተዋንያን ጋር ተወዳድረው ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል።
ስለሆነም መንግስት በተቻለ ፍጥነት ይህ የቀረጥ ማነቆ እንደ ኬንያ ወይም ጋና፣ ሴኔጋልና ናይጄሪያ የማበረታታት ሥራ ቢሰራ ሙያውም ሙያተኛውም ተደጋፊ ይሆናሉ፡፡  

4  የማበረታታት ጉዳይ
በናይጄሪያ አንድ ሰው ፊልም ሲሰራ መንግስት ድጎማ ያደርግለታል፡፡ በአንዳንድ ሀገራት ፊልም ሠሪው ወጪውን እስኪመልስ ተጠብቆ በኋላ ግብር እንዲከፍል ይበረታታል፡፡
የአንዳንድ ሀገራት መንግስት ደግሞ የፊልሙን ድርሰት አንብቦ፣ ድርሰቱ ለሀገርና ለወገን ይጠቅማል ብሎ ካመነበት፣ ፊልሙን ለመስራት የሚፈጀውን ወጪ ሙሉ ለሙሉ መንግስት ይሸፍናል፡፡ ለፊልም ሥራ ባንኮች የሚያበድሩበት አሠራር ያላቸው ሀገራት አሉ፡፡
እኛ ሀገር ሙያው የተተወ ነው፡፡ የሲኒማና የቴአትር ቤቶች፣ በየኮንዶሚኒየሙ አቅራቢያ ሊገነቡ ይገባል። በየአካባቢው መመልከቻ አዳራሾች ሊገነቡ ይገባል። በእንግሊዝ አንድ ሰው ከቤቱ ወጥቶ 20 ሜትር እንደተጓዘ ሲኒማ ቤት ያገኛል፡፡ ይህን የምለው፣ በኛ ሀገር እንዲህ ይሁን የሚል የየዋህ ህልም እያለምኩ ሳይሆን፣  ቢቻል እንደ ት/ቤት፣ ሆስፒታል ሁሉ ሲኒማና ቴአትር ቤቶች ሊገነቡና ወደዚህ ሙያ ለሚገቡ ባለሀብቶች፣ የቦታ ሽያጭ ማበረታቻ መደረግ አለበት፡፡  
በነገራችን ላይ የመጀመሪያው ቴአትር ቤት ሀገር ፍቅር ነው፡፡ ቀጥሎ የአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር፣ ራስ ቴአትርና ሜጋ እንዲሁም የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ይከተላሉ። ዛሬ ራስ ቴአትርና ሜጋ አንፊ ቴአትር ፈርሰው፣ የቀሩን ጥቂቶች ናቸው፡፡ ለ100 ሚሊዮን ህዝብ ያሉን ቴአትር ቤቶች ከህፃናት ቴአትር ጋር አራት ብቻ ናቸው፡፡ እነርሱም ከዘመኑ ጋር አብረው እንዲሻሻሉ ስላልተደረገ፣ በወጣቱ የሚመረጡ መዝናኛ ቦታዎች አይደሉም፡፡ ስለሆነም በአዲስ አበባ ስር ያሉትም ሆነ በፌደራል መንግስት ሥር ያለው ቴአትር የተሻለ መንገድ እንዲከተሉና አዳዲስ እንዲሰሩ ማበረታቻ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

5.የቲኬት ሽያጭ ጉዳይ
የመንግስት ቴአትር ቤቶች ትልቅ ችግር የትኬት ሽያጭ ነው፡፡ ለምሳሌ ሀገር ፍቅር አካባቢ ያለ አንድ ካፌ አንድ ቡና 5 ብር ሊሸጥ ይችላል፡፡ ከጎኑ ያለው ደግሞ 10 ብር ሊሸጥ ይችላል፡፡ ሰው የሚስማማው ቦታ ገብቶ ሊጠቀም ይችላል፡፡ አንድ የልብወለድ ወይም የኢ-ልብወለድ ደራሲም ለመጻፍ የፈጀበትን ጊዜ፣ የገፅ ብዛቱን፣ ያሳተመበትን ወረቀት ጥራት ተንተርሶ የመፅሀፉን ዋጋ ያወጣል፡፡           
50 ሰው የሚሳተፍበት የቴአትር ሥራ እና በ2 ሰው የሚተወን ቴአትር የመግቢያ ዋጋው እኩል ነው፡፡ ይህ የአዲስ አበባ ካቢኔ ያስቀመጠው ነው፡፡ ካቢኔው ባላመረተው ምርት ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ ሊገደድ አይገባም፡፡ የከተማው ሕዝብ የመረጠው ካቢኔ ህዝቡን የጠቀመ ስለሚመስለው በትንሽ ገንዘብ እንዲዝናና በቀናነት ሊከራከር ይችላል፡፡ ነገር ግን የተመረተው ቴአትር ኪሳራ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ ስለሆነም እንደ ማንኛውም ንግድ አምራቹ ገቢና ወጪውን አገናዝቦ ያዋጣኛል ያለውን የትኬት ዋጋ ለመወሰን መብት ሊሰጠው ይገባል፡፡

6. የብድር አገልግሎት
አንድ የኪነ ጥበብ ውጤት በትክክል ተጠንቶ ከተሠራ አትራፊ ነው፡፡ ስለሆነም፣ መንግስታዊ ተቋማትና የንግድ ባንኮች፤ ቴአትርና ፊልም አዋጭ መሆናቸውን አውቀው፣ ለሙያውና ሙያተኛው የብድር ስርዓት ሊዘረጉለት ይገባል፡፡ በዚህ ዘመን አንድ ከያኒ ለጥበብ ሥራ ብድር ቢፈልግ፣ ለመንግስት ሌላ የብድር እቅድ የሚያስገባበት አጋጣሚ ነው የሚስተዋለው፡፡ ከቤት ውጪ ንብረት እንደ መያዥያ በማይቆጠርበት ጊዜ ከቤት ብቻ ሌሎች አማራጮች ሊኖሩ፤ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትና ባንኮች ደግሞ አዋጭ ለሆነው ዘርፍ ትንሽዬ በር ሊከፍቱለት ይገባል።

7 ዞሮ ማሳየት
በቀደመው ዘመን እንደ መላኩ አሻግሬ፣ ማቲዎስ በቀለ፣ ጥላሁን ጉግሳ አለሙና ሌሎች በርካታ የኪነ ጥበብ ሰዎች ቴአትርን፣ ከአዲስ አበባ ይዘው በመውጣት፣ በየክልሉ እየገቡ የነገውን ተመልካች በጊዜአቸው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ እነ ሀይሌ ገብረሥላሴ፣ አሰላ ከተማ ፊልም መጥቶ ባያይ ኖሮ፣ ገንዘብ ሲያገኝ ሲኒማ ማምረትና ሲኒማ ቤት ለመገንባት ባልተነሳ ነበር።
አብዛኛው የኪነ ጥበብ ባለሙያ፣ በልጅነቱ ያለበት ድረስ ቴአትር ስለሄደለት በጥበቡ ተለክፎ የተከበረ ባለሙያ ወጥቶታል፡፡ ዛሬ ግን ይህ አይነቱ አሠራር አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ወድቋል፡፡ የህዝቦችን ከህዝቦች ግንኙነት ለማቀራረብ፣ ከኪነ ጥበብና ከስፖርት የተሻለ አማራጭ የለም፡፡ እና መንግስት ከኪነጥበቡ ማሕበረሰብ ጋር ተመካክሮ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት፣ ወጣቱን ለማንቃትና እርስ በእርስ ለማስተሳሰር ተጓዥ የቴአትርና የፊልም እንቅስቃሴ ያስፈልጋል፡፡

8 የሙያ ማህበራት ሚና
የቴአትርና ፊልም ግምገማ ሲያቆም፣ የቴአትርና የፊልም ባለሙያዎች ትልቅ ነፃነት ያገኙ ቢሆንም፣ ማህበራት በተለይ ፊልምን በተመለከተ የጥራት ጉዳይ ላይ ተሰባስበው ሊሰሩ የሚገባበት ሰዓት ላይ የደረስን ይመስለኛል፡፡ በሌላው አገር፣ ለምሳሌ በእንግሊዝ፣ የፊልም ማህበሩ፣ ባለፊልሞች በፍላጎታቸው ፊልሞቻቸውን ደረጃ የሚያስወጡበትና ለደረጃ የሚያሳዩበት ስርዓት ዘርግተዋል፡፡ አንድ ፊልም ከአንድ ፊልም ይለያያል፡፡  ልክ አንድ ሆቴል ባለ አምስት ኮከብ ነው፤ ይህኛው ባለ አራት ኮከብ ነው፤ እንደሚባል ያለ ማንም አስገዳጅነት ባለሙያዎች ከፈለጉ ፊልምን ደረጃ የሚወጣበት ስርዓት ለመፍጠር ምክክር የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን፡፡
ፊልሞቻችን እንዲያድጉ የመንግስት እገዛ ከተደረገበት የፊልም ማህበራትም ትልቅ ሃላፊነትን ለመወጣትና ሙያውን ከፍ ለማድረግ በጋራ የሚቆሙበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ የማህበራት መሪዎች የምክክር መድረክ አዘጋጅተው፣ ለባለሙያዎች ጥሪ እንዲያደርጉ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡
ኪነጥበብ ለዘላለም ይኑር!!


Read 1207 times