Saturday, 20 October 2018 14:13

ቻቺ ታደሰ የት ጠፋች? ምን እየሰራች ነው?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

    “የመጣሽበት ዓላማ ሲገለጥልሽ ብዙ በጎ ነገሮችን ታስቢያለሽ”

   • ለጥምቀት በጎንደር የሚቀርብ የሦስት ቀን ኮንሰርት ለማቅረብ አቅዳለች
   • ከታዋቂ ኤርትራዊት ዘፋኝ ጋር ለማቀንቀን በዝግጅት ላይ ናት
   • በቴልአቪቭ የባህልና የንግድ ኤክስፖ እያዘጋጀች ነው

   ለረዥም ጊዜያት ከመድረክ ጠፍታ የከረመችው ዝነኛዋ ድምጻዊት ቻቺ ታደሰ፤ትላልቅ ዕቅዶችንና ፕሮጀክቶችን ቀርጻ እየተንቀሳቀሰች መሆኗን ለአዲስ አድማስ ተናግራለች፡፡ ከአንድ ወር በኋላ በእስራኤል ቴልአቪቭ የባህልና የንግድ ኤክስፖ ለማካሄድ በዝግጅት ላይትገኛለች፡፡ ምን ዓይነት ኤክስፖ? የጥምቀት በዓልን ምክንያትበማድረግ የሦስት ቀናት ኮንሰርትም በጎንደር ለማቅረብ እየተሰናዳች መሆኑን ቻቺ ታደሰ ትገልጻለች፡፡ እነማን የሚያቀነቅኑበት? እኒህን ጨምሮ በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከድምጻዊት ቻቺ ታደሰ ጋር በስፋት አውግታለች፡፡ እነሆ፡-

    እንደው የት ነው ጥፍት ብለሽ የከረምሽው?
እንግዲህ በስራም በቤተሰቤም ምክንያት ውጭ ስለምመላለስ ተረጋግቼ አንድ ቦታ አልሆንኩም፡፡ በዚህ ምክንያት ሰው ሁሉ አድናቂዎቼ፤ “ከኤርፖርት ጀምሮ ቻቺ የት ጠፋሽ? በጣም ነው የምንወድሽ-- ስራዎችሽ ቆንጆ ናቸው---” እና ብዙ ብዙ ይሉኛል፡፡ በዚህም በጣም ነው ደስ የሚለኝ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ለእኔ ምን ያህል ፍቅርና ናፍቆት እንዳለው በዚህ ስለምረዳው----እኔ ከበፊት ጀምሮ እስከ መጨረሻው የነበሩ አልበሞቼን ስሰራ እጅግ በጣም ተጠንቅቄ ነው የምሰራው፡፡ ለምን ካልሺኝ----በድምፅ መዝፈን ብቻ ሳይሆን በዘፈን ግጥሞችሽ ውስጥ በምታስተላልፊያቸው መልዕክቶች ብዙዎችን ልታገኚ--- ብዙዎችን ልታስተምሪና ልትለውጭ ትችያለሽ፡፡ እኔም እንደዚህ ተጠንቅቄ በመስራቴ ይመስለኛል ከህዝቡ አድናቆትና ፍቅርን ያገኘሁት፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ብዙ ጎበዝ ጎበዝ የሆኑ ወጣት ፕሮዲዩሰሮችና ፀሐፊዎችም እየመጡ ስለሆነ ብቅ ማለቴ አይቀርም፡፡
ያው ቤተሰብ ስለመሰረትኩኝ ለቤተሰብም ጊዜ ስለሚያስፈልግ ጠፍቼ ነበር፤ በተለይ ልጄን ለማሳደግ ስል ከብዙ ነገር ጠፍቼ ነበር፡፡ ልጄ አሁን 13 ዓመት ሆኗታል፡፡ ባለቤቴም አሜሪካ አትላንታ በስራ ላይ ስላለ፣ ከቤተሰቤ ጋር በርከት ያለ ጊዜ ለማሳለፍ ስለፈለግሁኝ ነው፡፡ ልጆች ላይ ከስር ጀምሮ አብረሽ ሆነሽ በቅርቡ ካልሰራሽ ስለሚያስቸግር፣ ያንን ጊዜ ከቤተሰቦቼና ከልጆቼ ጋር ነበር የማሳልፈው፡፡ ልጄን ለዝግጅትም ሆነ ለሙዚቃ ስጓዝ፣ ጠብቁልኝ ብዬ አልሄድም፤ ይዣት ነው የምጓዘው፡፡ ከኔ ጋር ቅርበቱ ኖሯት እንድታድግ የሰራሁት ስራና የሰጠሁት ጊዜ ፍሬውን በእሷ ላይ እያየሁት ነው፡፡ በስፖርት፣ በእውቀትና በትምህርት፣ በመፅሐፍት ማንበብ ላይ----በሁሉ ነገር ጥሩ ሆና አድጋለች፡፡ ሌላውም ቤተሰብ ለልጆቹ፣ ካለው ስራ ገታ አድርጎ፣ ልጆቹን በቅርብ ቢያሳድግ ጥሩ ዜጋ ያፈራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ብዙ ኢትዮጵያዊያን፤ የእኔን ሲያዩና አሁን የምሰጠውን ቃለ ምልልስ ሲያነቡ ይማሩበታል ብዬም አምናለሁ፡፡
በቅርቡ ደግሞ የመጀመሪያ ልጅሽን በሞት አጥተሻል፡፡ ተፅናናሽ --?
አዎ ተፅናንቻለሁ፡፡ እኔ ሁሌም ከእግዚአብሔር ጋር ቅርብ ነኝ፤ በህይወቴ ሁሉ እግዚአብሔር አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ እንኳን አሁን በቤተሰብ ተከብቤ፣ ድሮም ብቻዬን እያለሁ፣ ሁሉን ነገር አሳልፌ የምሰጠው ለእግዚአብሄር ነው፡፡ እኔ ያለሱ ሀይል የለኝም፡፡ ሁሌ ጠዋትም ማታም ስፀልይ፣ “ሁሉ ያንተ ነው ውሰድ፤ ስደክም እርዳኝ ደግፈኝ” እላለሁ፡፡ ልጄን አጥቻለሁ፤ እንደ እናት ልጅን ማጣት ከባድ ቢሆንም የእርሱ ፈቃድ ነውና ለምን ወሰዳት? ለምን አጣኋት?---አለማለቴ ብዙ እንዳልጎዳ ረድቶኛል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ይሰጣል እግዚአብሔር ይወስዳል፡፡ እግዚአብሔርን አጥብቄ ስለያዝኩኝ በርትቻለሁ፤ ለተጨነቁልኝ አብረውኝ ላዘኑ ሁሉ በጣም አመሰግናለሁ፤ ፈጣሪ ያክብርልኝ ለማለት እወዳለሁ፡፡   
“በአፍሪካዊነታችን እንኩራ” ከተሰኘው የመጨረሻ አልበምሽ በኋላ ድምጽሽ መጥፋቱን ተከትሎ፣ “ሀይማኖቷን ቀይራለች” ተብሎ ተወርቷል፡፡  እውነት ነው?
እኔ በእርግጥ የጠፋሁበትን ዋና አላማ ቀደም ብዬ ገልጫለሁ፡፡ ሀይማኖት ከመቀየር ጋር ተያይዞ የሚነሳው ውሸት ነው፤ እኔ ሀይማኖት ተከታይ አይደለሁም፡፡ እግዚአብሔርን አመልካለሁ፣ እፈራለሁ አከብራለሁ። የፈጠረኝን አምላክ፤ ከዚህ ዓለም በላይ ትልቅ ሆኖ ስለማየው፣ በልጁ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በጣም አምናለሁ፡፡ ለእኔ ሀጢያት እሱ ሞቷል፡፡ ሀጢያተኛ የነበርኩትን እኔን ማስተዋል እንድችል፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን ያመጣኝ እሱ ነው፡፡ መፅሐፍ ቅዱስን በደንብ ተከትያለሁ፤ የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራትና ማክበር ነው ይላል፡፡ እግዚአብሔርን ማክበር መፍራት፣ በአዲስ ብርሃን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መጠጋትና ማመን ማለት፣ ለእኔ ሀይማኖት መከተል አይመስለኝም፡፡ ይሄ ለእኔ አዲስ ሳይሆን ከድሮም ጀምሬ እየኖርኩበት ያለ ነገር ነው፡፡
በመፅሐፍ ቅዱስ በገላትያ ውስጥ የአመፃ ፍሬዎች ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ አንዱ ዘፈንና ዘፋኝነት ነው፡፡ እና መዝፈንና እግዚአብሔርን ማምለክ አይጋጭም? ዘፈንስ ሀጢያት አይደለም ትያለሽ?
አኔ ዘፈን ሀጢያት ነው ብዬ አላምንም፣ ዋናው ምን ዓይነት ዘፈን፣ ለምን አላማ ነው የምትዘፍኚው የሚለው ነው፡፡ ጥያቄው አሁን ሰው ያልተረዳው አንድ ነገር፣ በአርት ህይወት ውስጥ ስትኖሪ እንዲሁም ዘፈንም ሆነ ፊልም ስትሰሪ፣ ከምንድን ነው የተነሳሳሽው የሚለው ነው፡፡ የምዘፍነው ለአገር ነው? ለክለብ ነው? ለጭፈራ ነው? ወይስ ህዝብና አገርን ለማስተማር ነው?-- የሚለው መለየት አለበት፡፡ ስለ አፍሪካዊነት፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ እኩልነት ስለ ሴቶች ጥንካሬና ኃላፊነት መዝፈን ምኑ ላይ ነው ሀጢያት የሚሆነው? እስቲ ንገሪኝ? በህፃናት መብትና ደህንነት ላይ ብትዘፍኚና መልዕክት ብታስተላልፊና የማህበረሰቡን አመለካከት ብትቀይሪ፣ እኔ ሀጢያት ነው አልለውም። አሁን ሄደሽ በኦርቶዶክስም በፕሮቴስታንትም ስለ ዘፈን ብትጠይቂ፣ የሚነግሩሽ ከላይ ያልኩሽን ነው፡፡ ዘፈን እንዳዘፋፈንሽና እንደምትጠቀሚበት ጉዳይ እንጂ ሙሉ ለሙሉ ሀጢያት ነው ብሎ መደምደም ተገቢ አይመስለኝም፡፡ በአጠቃላይ እኔ የጠፋሁት በጊዜ ማጣት እንጂ በሀይማኖት እንዳልሆነ እንድትነግሪልኝ እፈልጋለሁ፡፡ አሁን ወደ ስራዬ እመለሳለሁ፡፡ ስመለስ በጥሩ ሀሳብ፣ በጥንካሬና በብርታት እንዲሆን ስለምፈልግ፣ ያንን ዝግጅት እያደረግሁ ነው፡፡ ወጣቱን የሚያስተምር የሚለውጥና ጥሩ ስራ ካልሰራሁ በቃ ፉርሽ ነኝ፡፡ ለአገሬ ለህዝቤ የሚጠቅም ስራ ካልሰራሁ፣ በእግዚአብሔርም አይን በጥሩ አልታይም፣ በህዝቡም ከበሬታ አላገኝም፡፡
በበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ እንደምትሳተፊ  ይታወቃል፡፡ በሀረር በዴሳ በጅብ ከተበላው ህፃን ድጋፍ ጀምሮ ያደረግሻቸውን የበጎ አድራጎት ስራዎች በአጭሩ ብታብራሪልኝ …
 በጎ አድራጎት ማለት ከእግዚአብሔር ሀሳብ ጋር የሚገናኝ ነው፤ቅድምም ያልኩሽ ለዚሁ ነው። እግዚአብሔርን ስታክብሪና ማንነትሽ ሲገባሽ፣ ቃሉን ስትረጂ፣ የመጣሽበት ዓላማ ሲገለጥልሽ ብዙ በጎ ነገሮችን ታስቢያለሽ፡፡ እኔም ይሄ ገብቶኛል ብዬ ስለማምን፣ በተቻለኝ አቅም በጎ ስራዎችን በመስራትና ሰዎችን በማገዝ አምናለሁ፡፡ እርግጥ ነው መቶ ሚሊዮን ህዝብ እለውጣለሁ፣ አበላለሁ አልልም፡፡ ነገር ግን እንዳግዘው የተሰጠኝ አንድ ሰው እንኳን ቢሆን፣ ያንን ሰው ተከታትዬ ሲለወጥ ማየት ለእኔ ደስታ ነው። ሰው በእግዚአብሔር ፊት እኩል ነው፤ ክብር ነው። ጊዜና ሁኔታዎች አንዱን ከፍ፣ አንዱን ዝቅ ሊያደርግ ይችል ይሆናል እንጂ፡፡ የበዴሳውም ህፃን እኔ ጋ ሲመጣ እኔ ፈልጌው አይደለም፡፡ እኔ ተፈልጌ ነው የመጣው። ይህንን ልጅ ወደኔ ያመጣው የእግዚአብሔር አላማ ምንድነው? ብዬ ነው፣ እስከ መጨረሻው ያደረስነው። በዚህ ልጅ ብዙ ዶክተሮች ረድተውኛል፣ ብዙ ተጨንቄበታለሁ፡፡
አሁን ልጁ ምን ደረጃ ላይ ነው?
አሁን ፈረንጆች በጉዲፈቻ እያሳደጉት፣ ፔንሴልቬኒያ ወደ መቶ ሺህ ዶላር የሚያወጣ ህክምና ተደርጎለታል፡፡ አፍንጫውን አጥቶ ነበር፡፡ በአንድ በኩል ደግሞ መንጋጋው ወልቆ ነበር፡፡ የፔንሴልቬኒያ ዶክተሮች ረጅም ሰዓት የወሰደ ቀዶ ጥገና አድርገው፣ ጥሩ ገፅታ ያዘ፡፡ ከዚያም “ቻቺ የልጁ ህክምና አለቀ፤ ምን ይሁን?” ሲሉኝ፣ “አይ እኛ ፊቱን ብቻ ሳይሆን ህይወቱንም መቀየር አለብን፤ አሁን ባለው የቤተሰቦቹ የኑሮ ሁኔታ መልሰን ኢትዮጵያ ካመጣነው ህይወቱ አይለወጥም፤ ቤተሰቦቹ በዝቅተኛ ኑሮ ላይ ያሉና ሌሎች 6 ልጆቻቸውን ተፍጨርጭረው የሚያሳድጉ ናቸው፤ ስለዚህ ወደ ቤቱ ቢመለስ ፊቱ እንጂ ህይወቱ አይቀየርም” አልኩኝ፡፡ እዛ የነበሩ በመንፈሳዊ ህይወታቸው ጠንካራ የሆኑ ቤተሰቦች፤ “እናንተ እዚህ ካደረሳችሁት እኛ ቀሪ ህይወቱን እንለውጣለን” ብለው እያሳደጉት ነው፡፡ አሁን ሀይለኛ እግር ኳስ ተጫዋች፣ የተዋጣለት ዋናተኛ ሆኗል፡፡ ልጁን ብታይው፣ ከነጮች እህትና ወንድሞቹ ጋር በጥሩ ህይወት ላይ ይገኛል፤ የእኔ አላማ ልጁ በምቾት ውስጥ ሆኖ አገሩን፣ ወገኑን፣ ባህሉንና ማንነቱን እንዲረሳ አይደለም፡፡ የዘጠኝ ዓመት ልጅ ነው፤ ከኢትዮጵያ እንዴት ሆኖ እንደወጣ ያውቀዋል፡፡ ነገ ደግሞ ተለውጦ፣ ወደ ሀገሩ ተመልሶ፣ በጎ ሰው ሆኖ፣ አገሩን ወገኑን ቤተሰቡን እንዲጠቅም ነው ፍላጎቴ፡፡
በእስራኤል ቴልአቪቭ ከተማ የሚካሄድ ትልቅ የባህልና የንግድ ኤክስፖ እያዘጋጀሽ መሆኑን ሰምቼአለሁ፡፡ እስኪ ስለ ሁኔታው  አብራሪልኝ---?
በመጪው ዲሴምበር 3 እና 4 እስራኤል ቴልአቪቭ፣ የባህልና የንግድ ኤክስፖ ይካሄዳል፤ ይህ ፐሮጀክት ላለፉት 3 ዓመታት ስለፋበት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ የኤክስፖው ዋና አላማ ምንድን ነው ካልሺኝ፣ በእስራኤል ከ140 ሺህ በላይ ቤተ እስራኤላዊያን ይገኛሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ከአሜሪካ ቀጥሎ ብዙ ኢትዮጵያዊያን የሚኖሩባት ከተማ እስራኤል እንደመሆኗ፣ ለምን “የኢትዮጵያ ቀን” ተብሎ አይሰራም ከሚል ሃሳብ የመጣ ነው፡፡ ከነዚህ 140 ሺህ መካከል 40 ሺህ ያህሉ እዚያው እስራኤል ተወልደው ያደጉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ስለ ማንነታቸው፣ ስለ ባህላቸው--- ለምንስ አያውቁም? በሚል ነው ስራውን የጀመርኩት። እነዚህ እዚያው የተወለዱ ቤተ እስራኤላዊያን እንዲህ ዓይነት የባህልና የንግድ ኤክስፖዎችና ፌስቲቫሎች በተወለዱበት አካባቢ ሲዘጋጅ፤ ኢትዮጵያን የማወቅ የማየትና የመመርመር ብሎም ስለ መነሻቸው የማወቅ ጉጉት ያድርባቸዋል፡፡ ማንነታቸውን ባህላቸውን ካወቁ ደግሞ በማንነታቸው ኮርተው ይኖራሉ፤ ከማንነት ግጭት ይወጣሉ-- በሚል ተነሳስቼ፣ ይህን ለማሳካት ነው ሶስት ዓመታት የፈጀብኝ፡፡ ለምን ይህን መስራት ፈለገች? ምንድነው ዓላማዋ? በሚል በእስራኤል በኩል ብዙ ማጣራቶች ተካሂደው፣ እኔም ብዙ በሮችን አንኳኩቼ፣ የኢትዮጵያ መንግስትም ባደረገልኝ እገዛ፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት፣ የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎችም አጋሮቼ ሆነው እየሰራን ነው፤ ፍላጎቴና አላማዬን ተቀብለውና አምነውበት፡፡ አሁን ብዙ ሂደቶችን እያገባደድን ነው። በቀጣዩ ዓመት መስከረም 17 እዚህ መስቀል ሲከበር፣ በእስራኤልም “የኢትዮጵያ ቀን” ተብሎ በድምቀት እንዲከበር ተስማምተናል፡፡
ከሌሎቹ ቀናት መስቀልን (17)ን ለምን መረጣችሁ?
እንግዲህ መስቀል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በማይዳሰሱ ቅርሶች ዘርፍ የተመዘገበና የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲጠበቅ እውቅና የተሰጠው በዓል እንደመሆኑ፣ ብዙ ኢትዮጵያውያን ያሉበት እስራኤል ውስጥ በዓሉም በድምቀት እየተከበረ፣ ቀኑም የኢትዮጵያ ቀን ተብሎ ተሰይሞ እንዲቀጥል ነው የመረጥነው። አሁን ለመንደርደሪያ እንዲሆን ብለን በራሳቸው በእስራኤሎች ጥያቄና “ኢንተርናሽናል ኤክስፖርት” በሚባለው ትልቅ ድርጅት አጋርነት፣ ዲሴምበር 3 እና 4 የባህልና የንግድ ኤክስፖ ይካሄዳል ማለት ነው፡፡ እንደነገርኩሽ፤ የእስራኤሉ “ኢንተርናሽናል ኤክስፖርት” የተባለው ይህ ድርጅት፤ በስሩ አስመጪና ላኪ የሆኑ ትልልቅ ኢንቨስተሮችን ያቀፈ፣ ግዙፍ የመንግስት ድርጅት ነው፡፡ በእኔ በኩል፤ “ሩትስ ኢቨንትስ” የተባለ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ያቋቋምኩት ድርጅት አለ። ሁለቱ በጋራ ኤክስፖውን በኮንቬንሽን ሴንተር ያዘጋጃሉ። አንዱን ቀን ኤግዚቢተሮች እየመጡ ኤክስፖውን የሚጎበኙ ሲሆን፣ እኛ ደግሞ ከዚህ የተለያዩ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ኢንቨስተሮችን ይዘን እንሄዳለን፡፡ ሁለተኛው ቀን ቢስነዝ ቱ ቢዝነስ (B to B) ውይይትና የሁለቱ ሀገራት ባለሀብቶች አብረው የሚሰሩበትን መንገድ በውይይት ያዳብራሉ ማለት ነው፡፡
በምን  ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ኢንቨስተሮችን ነው የምታሳትፉት?
ዘርፎቹ በርካታ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በአግሪካልቸር፣ በአስመጪና ላኪ፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በቡናና የቅባት እህል ላይ የተሰማሩ፣ በኮሚዩኒኬሽን፣ በኬሚካል፣ በባህልና በአስጎብኚነት፣ በኢንዱስትሪ፣ በህክምና መሳሪያና በመድኃኒት አስመጪነት እና በሌሎችም ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ይሳተፋሉ፡፡ ይህ ለአገራችንም ለራሳቸው ለኢንቨስተሮቹም ሆነ በቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ ለመሆን ትልቅ እድል የሚፈጥር ነው። የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋናው አጋሬ ሆኖ እየሰራ ነው፡፡
እስራኤልና ኢትዮጵያ ከንግሥት ሳባና ንጉሥ ሰሎሞን እንዲሁም ከምኒልክ መወለድ ጀምሮ ከ3 ሺህ ዓመት በላይ የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው አገራት ናቸው፡፡ በኤክስፖው ታዲያ ምን አዲስ ነገር ይጠበቃል?
የሁለቱ አገራት ታሪክ አንቺም እንዳልሽው የረጅም ጊዜ ነው፤ ተዋልደናል፤ ንግሥት ሳባን ንጉሥ ሰሎሞን ሲያያት ልቡ በፍቅር መቅለጡን ነው ታሪክ የሚናገረው፤ ይህን ያህል ቁንጅና ውበትና ክብር ያለን ህዝቦች ነን፡፡ ይሁንና ከዚህ የተወሰዱት ወንድምና እህቶቻችን እዛ ከሄዱ በኋላ የወለዷቸው እዛው የተማሩ ልጆች፤ ምንጫቸውን ስር መሰረታቸውን ብዙ አያውቁም፤ ነገር ግን ማወቅ አለባቸው፡፡ “ሩትስ ኢቨንትስ” አላማው ይሄ ነው፡፡ ራሳቸውን ማወቅ የሚጀምሩት ደግሞ አካባቢያቸው ላይ ከሚካሄድ ሁነት መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስለዚህ ባህላቸውን፣ ማንነታቸውን፣ የአገራቸውን ምግብ፣ ቋንቋ፣ አልባሳት እዛው የተወለዱበት በጥቂቱም ቢሆን ሲመለከቱ ይበልጥ የማወቅ ጉጉት ያድርባቸዋል ይጎበኛሉ፤ አገራቸው ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ይመጣሉ፡፡ በብዙ መልኩ ኢትዮጵያን ይጠቅማሉ፤ ከማንነት ጥያቄ ይድናሉ፡፡ ይሄን እጠብቃለሁ፣ ይሄ ቀላል እንዳይመስልሽ፡፡ ታሪኩም ግንኙነታችንም መረሳት የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ ለእኔ ዳግማዊት ኢየሩሳሌም ናት፣ ከጎንደር እስከ ላሊበላ ብዙ ታሪክ ያለን ህዝቦች ነን፡፡
መጪውን የጥምቀት በዓል ምክንያት በማድረግ እስራኤላዊያን፣ ጃማይካዊያንና ኢትዮጵያዊያን ሙዚቀኞች የሚያቀነቅኑበት የሦስት ቀን ኮንሰርት በጎንደር ከተማ ለማቅረብ እየተዘጋጀሽ ነው፡፡ ኮንሰርቱ የእስራኤሉ ፕሮጀክት አካል ነው ወይስ---?
ትክክል ነሽ፤ የእስራኤሉ ፕሮጀክት አንዱ አካል ነው፡፡ እኔ ለምሳሌ አንድ አልበም ስሰራ ቼይኑ ከየትኛው ጋር መያያዝ አለበት የሚለውን አስባለሁ። አሁንም በቀጣዩ ዓመት ሴፕቴምበር 28 (መስከረም 17) ለመጀመሪያ ጊዜ በምናዘጋጀው “የኢትዮጵያ ቀን” ኢትዮጵያን ነው የምናስተዋውቀው፡፡ ለማን? ለቤተ እስራኤሎች፤ ቤተ እስራኤሎቹ ደግሞ አብዝተው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ለጥምቀት ነው፡፡ ስለዚህ እዛው ተወልደው ያደጉ በእስራኤል ትልልቅ ዝና ያላቸው፣ የቤተ እስራኤል አቀንቃኞችን “ኢትዮጵያ ሄዳችሁ ከኢትዮጵያዊያን አርቲስቶች ጋር ኮንሰርት መጫወትና በጎንደር ህዝብ መታየት አለባችሁ፤ መነሻችሁ ስረ መሰረታችሁ ጎንደር ነው” አልኳቸው፡፡ ለምን በጥምቀት ጎንደር ላይ ኮንሰርት ተዘጋጀ? ነጮቹ እስራኤሎች ለጥምቀት ሲመጡ፣ የበለጠ ማንነታችንን አቅማችንን፣ ክብራችንን፣ የጥንትነታችንን፣ ባህላችንን---አውቀው ይመለሳሉ፡፡ ከዚያ በእስራኤል የኢትዮጵያ ቀንን ስንሰይምና ጥምቀትን ስናከብር፣ ይበልጥ አክብሮትና አድናቆት ይኖራቸዋል፡፡ ይሄንን ትስስር ስሰራ፣ በኢትዮጵያ የባህላዊ ዘፈን ተጫዋቾች አብረው ከቤተ እስራኤሎቹ ጋር ያቀነቅናሉ፣ ወደፊት አብረው የመስራት አጋጣሚውንም ይፈጥራሉ  ማለት ነው፡፡
ለአገራችን አርቲስቶችም ወደ ውጭ ሄዶ የመሥራቱ አጋጣሚ ይከፈትላቸዋል?
ትክክል ነሽ፡፡ ብዙ የእኛ አገር አርቲስቶች ለምን በአገር ውስጥ ተገድበው ቀሩ የሚለው ታሪኩ ብዙ ነው፤ አሁን እዚህ ማውራት አንችልም፤ ነገር ግን የጎንደሩ ኮንሰርት በመጠኑም ቢሆን አጋጣሚውን ይፈጥርላቸዋል፡፡
ለምንድነው ተገድበው የቀሩት? ለምንስ እዚህ ማውራት አንችልም?
ጥቂቱን ልናገር፡፡ አንደኛ ሁሉም ሙዚቃ ለኢትዮጵያ ብቻ ተብሎ የተሰራ ነው፡፡ ሁለተኛ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው ስራ ለመስራት ደረጃውን የጠበቀ የሪከርዲንግ ስቱዲዮ የለንም፤ ማስተር ለማድረግ እንኳን ውጭ እየተላከ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሙዚቃችንን እንኳን ለዓለም ለአፍሪካ ገበያ እንኳን ለማቅረብ የተመቻቸ ነገር የለንም፡፡ ነገር ግን የእኛ አርቲስቶች ከኮንሰርት ጀምሮ ከውጭዎቹ ጋር ከተገናኙ፣ አርቲስት ወደ እስራኤል ከሄደ፣ ቀስ በቀስ ይለወጣል፡፡ ብቻ ብዙ ሀሳብና እቅድ አለን፤ እግዚአብሔር ይጨመርበት፡፡
አንቺስ ከህዝቡ ጋር ዳግም የምትገናኝበት አዲስ ስራ አላሰብሽም?
እውነት ለመናገር እሰራለሁ፡፡ እንዳልኩሽ ደህና ደህና ፕሮዲዩሰሮችን በቸርችም በሌላውም በኩል እያገኘሁ እየተነጋገርኩ ነው፡፡ ሌላው በጃኑዋሪ 16 በእስራኤል ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይካሄዳል፣ በእኛ ጥር 8 ወይም 7 ማለት ነው፡፡ እናም ከምርጫው ቀደም ብሎ የሽልማት ስነ ስርዓት ያዘጋጃሉ፤ ለትልልቅ ሰዎች እውቅና ይሰጣሉ፤ እዛ ላይ ተገኝቼ እንዳቀነቅን ጋብዘውኛል፡፡ ይሄ ደግሞ ትልቅ ግብዣ ነው፤አሁን የጀመርኩትንም የስራ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው፡፡
ኢ-ሜይል ሲልኩኝ “በኢትዮጵያ የታወቀችና በዓለም የኢትዮጵያን ሙዚቃ ያስተዋወቀች፣ ሂዩማኒቴሪያል አክቲቪስት” ብለው ነው ታይትል የሰጡኝ፡፡ ይህንን ሳይ ዋው ነው ያልኩት፡፡ “ሲድ ፋውንዴሽን” የሚባል ትልቅ ፋውንዴሽን ነው ግብዣውን ያቀረበልኝ፡፡ ይህን ግብዣ የሚመጥን ምን ልስራ ስል የመጣልኝ ሀሳብ፣ እዛ ከሚገኝ አንድ ታዋቂና ትልቅ ዝና ያለው ዘፋኝ ጋር መስራት ነበር፤ ከዚህ አርቲስት ጋር ለመስራት ሀሳብ ሳቀርብላቸው ወደዱት፡፡ አሁን የእኛን ባህላዊ ሙዚቃ በአማርኛ፣ እሱ በሂብሩ ቋንቋ ለማቅረብ ዝግጅት ላይ ነን፡፡ ሙዚቃው በአለም ላይ የሚለቀቅ ነው የሚሆነው፡፡ ሌላው አሁን በተጀመረው የኢትዮ- ኤርትራ እርቅና ዳግም  ግንኙነት ላይ የሚያጠነጥን ዘፈን ከአንዲት ታዋቂ ኤርትራዊት ዘፋኝ ጋር ለመስራት በዝግጅት ላይ ነኝ፡፡ ሌሎችም ስራዎች ይቀጥላሉ፡፡ እኔ ሳድግ በጉርብትናም ከኤርትራዊያን ጓደኞቼ ጋር ነውና፣ ስራው የአሁኑን ዳግም ግንኙነትና ወንድማማችነት የሚያጎላ ይሆናል፡፡
በመጨረሻ ምን ትያለሽ …?
እንግዲህ ቀድሞ የሚመጣው የዲሴምበሩ የቴልአቪቭ ኤክስፖ በመሆኑ ለሁለቱም አገራት ኢንቨስተሮች ጥሩ አጋጣሚ ነውና እድሉን ተጠቀሙ፣ ተሳተፉ የሚል ግብዣ አቀርባለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡ በቅርቡ ከአድናቂዎቼ ጋር ስለምገናኝ፣ በሰላም ያገናኘን እላለሁ፡፡

Read 2115 times