Saturday, 19 May 2012 10:33

አዲሱ አማራጭ ጦማር

Written by  ተስፋዬ ዓለማየሁ
Rate this item
(5 votes)

ንድ ለሰማንያ ሚሊዮን የሆነው ቴሌኮማችን ምስጋና ይግባውና በተጣበበ እና በተጨናነቀው የኔትወርክ አገልግሎቱ ስልኩንም ኢንትርኔቱንም ባለው አቅም ሊያዳርሰን እየሞከረ ነው፡፡ ከቴሌኮም አገልግሎቶች መሃከል የሞባይል ስልክ አገልግሎት እና ሌሎችም የመረጃ መረብ ወይም የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ከሰማንያ ሚሊዮን በላይ ለሚሆን የኢትዮጵያ ህዝብ በብቸኝነት የሚያቀርበው ብቸኛው የኢትዮጵያ ቴሌኮም ኮርፖሬሽን ነው፤ የምንብሰለሰልባቸውን የአገልግሎት ጥራት እና ቅልጥፍና ጉዳይ ለዛሬ አቆይተን ከነችግሮቹ ሾላ በድፍን እየሰጠን ስላለው መልካም እድል እና አጋጣሚ እያመሰገንን” አዲሱን ሚዲያ እንተዋወቀው፡፡ አዲሱ ሚዲያ በውስጡ ሁሉንም ስራ የምንፈታባቸውንና በዛው ልክ እንጀራ የመሰረትንባቸውንና የምንመሰረትባቸውን ዌብሳይቶችንና ማህበራዊ ድረ ገፆችን ያጠቃለለ ነው፡፡

ከኢትዮ ቴሌኮም የምናገኘው የኢንተርኔት አገልግሎት ፈርጀ ብዙ ጥቅም እየሰጠን ነው፡፡ ብዙውን የማህበራዊ ህይወታችንን ሃሳባዊ (ቨርቹዋል) እና ሰፊ እንዲሁም አለማቀፋዊ እያደረገው ነው፡፡ ይህን ያልኩበት ዋነኛ ምክንያት በየቀኑ በዙሪያዬ ከማየውና ከሚገጥመኝ በመነሳት ነው፡፡

የክፍል ጓደኞቼም ሆኑ የስራ ባልደረቦቼ እኔ አጠገባቸው ካለሁት የቅርብ ጓደኛቸው ይልቅ ቅድሚያ እና ትኩረት የሚሰጡት በተለያዩ የማህበረሰብ ድረ ገፆች ለተዋወቋቸው የርቀት ጓደኞቻቸው ነው፡፡ ፌስ ቡክ፣ ቱዊተር፣ ሊንክዲን፣ ሀይ ፋይቭ፣ ማይ ስፔስ፣ ጉግል ፕላስ እና ሌሎች እኔ የረሳኋቸው ከአዲሱ ሚዲያ የሚመደቡ እና በዋነኛነት የሃሳባዊው ማህበራዊ ህይወታችንን የመሰረትንባቸው፤ ወዳጅነት እና ዝምድናን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያፈራንባቸው የማህበረሰብ ድረ ገፆች ናቸው፡፡  ዩ ቲዩብ ፣ድሬ ቲ ዩብ እና መሰል ሳይቶች ደግሞ ዘና የምንልባቸው ሙዚቃዎችንና ፊልሞችን፣ እውቀት የምንገበይባቸው ዶክመንተሪና ትምህርታዊ ፊልሞችን እና ንግግሮች የምናገኝባቸው ሳይቶች ናቸው፡፡ ብሎግ ወይም ጦማር የሚል አማርኛ አቻ የተሰጠው ሌላኛው የአዲሱ ሚዲያ አይነት ደግሞ አስተሳሰባችንን፣ እምነታችንን፣ ስሜታችንን፣ ተሰጥኦዎቻችንን ሙያዊ እውቀታችንን ገጠመኞቻችን የምናሰፍርበት እና ለሌሎች የምናካፍልበት በአለም አቀፉ የመረጃ መረብ ላይ የምናዘጋጀው ሃሳባዊ (ቨርቹዋል) ግል ማስታወሻችን ነው፡፡.

ዋነኛ አጀንዳችን ብሎግ ወይም ጦማር ነው፡፡ ከዚህ በኋላም ጦማር የሚለውን ሀገርኛ አጠራር እየተጠቀምን እንዘልቃለን:: ማንኛውም ሰው እምነቱን፣ አስተሳሰቡን፣ በውስጡ የሚብላላ ወይም የሚላወስ ርዕሰ ጉዳይ ያለው እና በፅሁፍ ማካፈል የሚፈልግ ሁሉ የራሱን ጦማር ከፍቶ መፃፍ ወይም መጦመር ይችላል፡፡ አንድ ቀጠን ያለች ግዴታ ግን አለበት- ከሚኖረው ግዜ እና ጉልበት ትንሽ መሰዋት ይጠበቅበታል፡፡

ከዚያም በከፈተው የጦማር አውድ ስለሚሰማው ርዕሰ ጉዳይ በነፃነት መፃፍ ነው፡፡ ታዲያ ግን ጦማሪው በሚያነሳው ጉዳይ ላይ አድናቆት” ምርቃት፣ እርግማን፣ ማበረታቻዎችና የተለያዩ አስተያየቶች ይሰጡታል፡፡ በፀጋ ተቀብሎ ማስተናገድ አስፈላጊም ሲሆን ምላሽ መስጠት የአንድ ጦማሪ  ድርሻ ይሆናል፡፡ ጦማሪነት አስተያየትን በነፃነት አካፍሎ ከመቀበል ባሻገርም ወዳጅነት ለመመስረትም ያስችላል፡፡ እናም ከአዲሱ ዘመን ቴክኖሎጂ ትሩፋት ለሚዲያው እና ተግባቦት ዘርፍ ከተበረከቱት ገፀ በረከቶች አንዱ የሆነውን የአዲሱን ሚዲያ አንደኛውን አይነት በአጭሩ ከተዋወቅን ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት እና ከማውቃቸው ጥቂት ጦማርያን ጦማሮቻቸው ጋር ላስተዋውቃችሁ፡፡

ጦማሪያኑን እና ጦማሮቻቸውን ከማስተዋወቄ በፊት ጥቂት ጦማር ስለምን? በሚለው ሃሳብ ዙሪያ ቆይታ እናድርግ፡፡ ጦማሪ ለመሆን የተለያዩ ምክንያቶች በጦማሪያኑ ይሰጣሉ፤  የሁሉም ሃሳብ ግን ተመሳሳይ ነው፡፡ ከሀገርኛ ጦማሪያንም ሆነ ከውጭ ጦማሪያን ጦማር ለመጀመር በምክንያትነት ካነሷቸው ነጥቦች የተወሰኑትን ላካፍላችሁ፤ ከወንዛችን ስጀምር የእውቀት ጦማር ፀኃፊ፡- “እኔ የምፅፈው ለአእምሮዬ ነፃነት ነው፡፡ እንደማምነው ለጓደኞቼ ብዙ የማካፍላቸው አለኝ፡፡ ዓለምን ለመቀየር እቅድ የለኝም” ግን ትንሽ ክበብ እየሰራሁ ነው፡፡ ይህችን ክበብ መለወጥ ከቻልኩ የክበቧ መስፋፋት መቼም አይቆምም፡፡” ብሏል የጦማሪነቱን ምክንያት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የዚሁ ጦማር ፀሃፊ ኢትዮጵያ ውስጥ መጦመር የሚያስፈልግባቸው አስር ምክንያቶች ብሎ በጦማሩ የዘረዘራቸውን ነጥቦች እንደሚከተለው ጠቅለል አድርጌ አስቀምጫቸዋለሁ፡- ለነፃ እና ጠንካራ እይታ፣ የአመለካከት ልዩነት ለማስተናገድ፣ የዌብ ሳይቶች እና የጦማሮች ቁጥር ውስን መሆኑ፣ ያለንን ሃሳብ ምርት እና አገልግሎት ለገበያ ለማቅረብ ፣ ጠንካራ የኦን ላይን ማህበረሰብ ለመፍጠር እና ዘና ለማለት ሲል ሃሳቡን ቋጭቷል፡፡ ሙሉ ፅሁፉን ለማግኘት እና በጦማሪው የተፃፉትን ሌሎች ፅሁፎቹን ለማንበብ በሚከተለውን አድራሻ ይፈልጉት- http://eweket.wordpress.com

ጎርደን ማርሲ የተባለ የውጭ ጦማሪም የሚከተሉትን እንደ ጦማሪነት ለምክንያት እና የጦማርን ጠቀሜታ እንዲህ ይገልፀዋል ፡- “አንድ አመት ከፃፍኩም በኋላ ጦማር ለሁሉም ግንኙነት የከፈተውን በር ሳስበው አሁንም ይደንቀኛል፤ ጦማር ሁሉንም ሰው በሚገባ አስተሳስሯል፡፡ ሰዎችን ከአስተሳሰቦቻቸው ጋር ማገናኘት አስችሏል፣ ሃሳባቸውን መጋራትና መተባበርን እንዲሁም የእርስ በርስ ግንኙነታቸውንም አፋጥኗል፡፡” እንግዲህ የጦማርን ጥቅም ከጦማሪዎቹ አስነብቤያችኋለሁ፡፡ በመቀጠል የማውቃቸውን ጥቂት ኢትዮጵያዊ ጦማሮች እና ጦማሪዎቻቸውን አስተዋውቃችኋለሁ፡፡ የጦማሪዎቹን ፅሁፍ ስታነቡ ግን አንድ ነገር በድጋሚ ልጋባዛችሁ እወዳለሁ፤ የራሳችሁን ጦማር መክፈት፡፡

የሚከተሉትን የጦማር አድራሻዎች የወሰድኳቸው ጦማሪ እንዳልካቸው ኃይለሚካኤል ኢትዮጵያዊ ጦማሮችን እና ጦማሪዎችን ለማስተዋወቅ በጦማሩ ካሰፈረው ጽሁፍ ነው፡፡ እንዳልካቸው ኃይለሚካኤል በጦማሩ የሚፅፋቸውን ቁም ነገሮች እንድትጋሩት እና አስተያየቶቻችሁን ጀባ እንድትሉት በሚከተለው የጦማር አድራሻው እመራችኋለሁ http://endalk.wordpress.com፡፡

በሃይማኖት፣ በትምህርት፣ በፍልስፍና፣ በስነ ፅሁፍ፣ በህግ፣ በፖለቲካ እና በማህበራዊ ሕይወት ዙሪያ የራሳቸውን ግንዛቤ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ላይ የሚፅፉ ጦማሪዎችን በሚከተለው አድራሻቸው ጎብኟቸው፡፡ ማበረታቻ ምርቃት ወይም ማስተካከያ እርምት አስተያየቶቻችሁን ፅሁፎቻቸውን አንብባችሁ ስትጨርሱ” ከፅሁፎቻቸው ስር በተዘጋጀው ቦታ አስፈሩላቸው፡፡

http://mesfinwoldemariam.wordpress.com

http://abelawinet.blogspot.com

http://afroaddis.wordpress.com

http://arefe.wordpress.com/

http://afterride.wordpress.com

http://www.debirhan.com

http://www.danielkibret.com

http://fasiledes.posterous.com

http://sukersays.com/

http://antigaye.wordpress.com

http://zeelittletes.wordpress.com

http://freemanpoets.wordpress.com

http://meetmatewos.wordpress.com

በማብቂያዬም፤ በህትመቱም ሆነ በብሮድካስቱ ዘርፍ ላላችሁ ሚዲያዎቻችን በሙሉ ለአንባቢዎቼ የጋበዝኩትን ተመሳሳይ የጦማር ክፈቱ ግብዣዬን ለእናንተም ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡ ምክንያቴም፡- በህትመት ሚዲያው ለተሰማራችሁት የወረቀት መወደድ እና የገፅ ውስንነት የተነሳ የሚደርሷችሁን አስተያየቶች ለማስተናገድ የሚፈጠርባችሁን ጫና ሙሉ በሙሉ የሚቀርፍ መፍትሄ መስሎ ስለታየኝ” ከመደበኛ ዌብ ሳይታችሁ ጋር የተያያዘ ተጨማሪ ጦማር ቢኖራችሁ የተለያዩ አስተያየቶችን በሰፊው ለማስተናገድ አማራጭ  ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ በብሮድካስቱ ዘርፍም ላላችሁት በአየር ሰዓት ጥበት እና እጥረት ምክንያት ለሚኖርባችሁ ውስንነት አስተያየቶችን ለማስተናገጃ አዋጭ እና አማራጭ መፍትሄ ይመስለኛል፡፡

 

 

 

Read 5175 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 10:37