Saturday, 20 October 2018 13:59

ንዴት ቤትንም፣ አገርንም አያቀናም!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(12 votes)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…በየቴሌቪዥን መስኮቱ በቃለ መጠይቅ ወቅት የተናደዱ የሚመሰሉ ሰዎች  እያየን ነው ልበል! “ኸረ ንዴት ለማንም አይበጅም» የሚለን ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡
ይቺን ስሙኝማ…አንድ ትንሽ ልጅ ነበር። ባህሪው በጣም አስቸጋሪና ሲበዛ ተናዳጅ ነው፡፡ ከእለታት አንድ ቀን አባቱ አንድ ከረጢት ሙሉ ሚስማር ሰጠው፡፡ እንዲህም አለው…
“በተናደድክ ቁጠር አንድ ሚስማር አጥሩ ላይ ምታ!”
በመጀመሪያው ቀን ልጁ 37 ምስማር አጥሩ ላይ መታ፡፡ በተከታዮቹ ሳምንታትም ቀስ በቀስ ንዴቱን እየተቆጣጠረ መሄድ ጀመረ፡፡ በዚሁም ልክ አጥሩ ላይ የሚመታቸው ሚስማሮች ቁጥርም እየቀነሰ ሄደ። በመጨረሻም ለአንዲትም ስከንድ ያልተናደደበት ቀን መጣ፡፡ ለአባቱም ነገረው…
“አባ፤ ዛሬ አንድም ጊዜ ሳልናደድ ዋልኩ፡፡”
አባቱም እንዲህ አለው…
“አሁን ደግሞ ንዴትህን ለተቆጣጠርክባት እያንዳንዷ ቀን፣ አንድ ሚስማር ከአጥሩ ላይ ንቀል!”
ቀኖቹ እየነጎዱ ሄዱ፡፡ አንድ ቀን ልጁ ለአባቱ እንዲህ አለው…
“አባ፤ ሁሉንም ሚስማሮች ነቅዬ ጨረስኩ፡፡”
አባቱም ካበረታታው በኋላ ልጁን ወደ አጥሩ ይዞት ሄደ፡፡ እንዲህም አለው…
“በጣም ጥሩ ነው ያደረግኸው፤ ግን አጥሩ ላይ ያሉትን ቀዳዳዎች ተመልከታቸው፡፡ አጥሩ መቼም ቢሆን የቀድሞ መልኩ አይኖረውም፡፡ አንተ በንዴት ነገሮችን በተናገርክ ቁጥር ልከ እንደዚሁ ጠባሳ ይተዋሉ። ስማኝ ልጄ፤ አንድ ሰው ሰውነት ውስጥ ስለት ከትተህ ልታወጣ ትችላለህ፡፡ የፈለገውን ያህል ይቅርታ ብትል ቁስሉ ምንም ጊዜም እዛ ይኖራል፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ ቆይቶ የሚቆጭህ ነገር ከመናገርህ በፊት ንዴትህን ተቆጣጠር፡፡”
ምናልባትም ይህ አባት ለልጁ የመከረው ምክር፣ በአሁኑ ወቅት ለብዙዎቻችን ሳያስፈልገን አይቀርም። ይሄ ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን’ም ይመለከታል።
“ተመልካቾቻችን፤ በከተማችን የተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚታየውን የመልካም አስተዳደር ችግር በሚመለከት አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሰጡትን አስተያየት እናስደምጣለን፡፡ ሆኖም ተመልካቾቻችን፤ ምናልባት ከሚቀርቡት አንዳንድ የአዲስ አባበ ነዋሪዎች መሀል ከዚህ በፊት በሌሎች መገናኛ ብዙሀን፣ በአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪነት የቀረቡ ከሆነ ስህተቱ የእኛ አለመሆኑን እንገልጻለን። በእኛ አሰራር፤ አንድ ግለሰብ በ‘አንዳንድ ነዋሪነት’ ከቀረበ፣ በተከታዩ ጊዜ የሆነ ነገር ካልደረበ፣ ከካሜራው ፊት ዘወር ማለት አለበት ብለን እናምናለን፡፡” አሪፍ አይደል!!
የምር ግን ከልምዶች መላቀቅ አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ የሚዲያ ሰዎቻችን አስቡትማ! አንድ አንድ፣ ሰባት ሰባት ምናምን አይነት ስልችት ያሉና ከሆነ የስታንድአፕ ኮሜዲ ‘ስክሪፕት’ የተወሰዱ የሚመስሉ ቃላትና ሀረጋት፣ ምትክ ይፈለግላቸውማ!  ቆጠራ ምን ያደርጋል! በቃ… “የከተማችንን ነዋሪዎች እናነጋግራለን፣” ቢባል ሰማይ አይደፋ! ካዝና ውስጥ ያለውን ገንዘባችንን ብቻ ሳይሆን መዝገብ ቃላት ውስጥ ያሉ ቃላቶቻችንም ላይ ወጪ ቁጠባ ይደረግልን!
“ጤና ይስጥልኝ የእኔ እመቤት…”
“ጤ…ጤና ይስጥልኝ…” (አኮሰታተሯ አንድ ባታሊዮን ጦር፣ ጠብመንጃውን ጥሎ እንዲሄድ ባያደርግ ነው!)
“በሚኖሩበት አካባቢ ስለሚታየው የመልካም አስተዳደር ችግር ልጠይቅዎት ፈልጌ ነው፡፡ በዚህ ላይ እሚነገሩን ካለ-.”
“መጀመሪያ የት አለና!”
“አልገባኝም፣ ምኑ የአኔ እመቤት?”
“መልካም አስተዳደር ቅብጥርስዮ የምትለው-- መጀመሪያ አስተዳደር የሚባል  ነገር የት አለና ነው!”
“ቢሆንም የእኔ እመቤት፣ አንደው አገልግሎት ፈልገው ሲሄዱ የገጠመዎት የመልካም አስተዳደር ችግር ካለ ቢነግሩን!”
“ስማ ጋዜጠኛው…” (‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዋ፣ ትን እስኪላት ትስቃለች፡፡) ”አልሰሜን ግባ በለው አሉ!”
“እመቤቴ፣ ይሄን ያህል ያሳቀዎት ምንድነው?”
“እንደው የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው… ድሮ ጋዜጠኛ የምንለው መንደር ውስጥ ወሬ የሚያቀባብለውን ነበር እኮ! ካልጠፋ ስም ጋዜጠኛ ይሏችኋል!”
“እመቤቴ ወደ ጉዳያችን ብንገባ…”
“ስማኝ፣ መጀመሪያ ነገር አስተዳደር የሚባል የት አለና ነው! ንገረኛ… ከአስር ወንበር ሰባቱ ባዶ እየሆነ ምን አስተዳደር አለና ነው! ምድረ ሴቷ፣ ምድረ ወንዷ ሁሉ ኮምፒዩተር ላይ ቁጭ ብላ ካርታ ስትጫወትና ፌስቡክ ስታይ እየዋለች ምን አስተዳደር ምናምን ትለኛለህ! ለነገሩ ብንለፈልፍ ምን ዋጋ አለው! የምታጠግቧቸው እናንተ አይደላችሁ …”
“ቢሆንም የእኔ እመቤት፣ ቢሆንም... ለምሳሌ የነዋሪነት መታወቂያ ለማውጣት ሲሄዱ ችግር ገጥሞዎት አያውቅም?”
“በቃ ችግራችን ሁሉ መታወቂያ ማውጣት ብቻ ነው የሚመስላችሁ! እኛ አንጀታችን በብስጭት ተቆራርጧል እናንተ ስለ ቁራጭ ወረቀት ነው የምታስቡት! የተከራየሁት የቀበሌ ቤት ዝናቡ በጣራ እየወረደ፣ ጎርፉ በምድር እየሰረሰረ አድሱልኝ ስል ሰሚ አጥቼ ሰባት ወር እያመላለሱኝ፣ መታወቂያ ትለኛለህ! መታወቂያ የሚኖረው እኮ መጀመሪያ እኔ ስኖር ነው፡፡
”የእኔ አመቤት ምን መሰለዎት…”
”የእኔ እመቤት፣ የእኔ እመቤት አትበለኝ! ለነገሩስ አናውቃችሁምና ነው! ሁላችሁም ያው ናችሁ። የምንለውን ቆራርጣችሁ ‘ወደቀ’ ያልነውን ‘ተነሳ’ እንዳልን አድርጋችሁ የምታቀርቡትን የማናውቅ መሰለህ!”
“እሱም ላይ እኮ መነጋገር ይቻላል፣ ከዚህ ቀደም እንደዛ ተደርጎ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን እንደሚያዩት ሰዉ የልቡን መናገር  የሚችልበት ጊዜ ላይ ነን፡፡”
“የልቡን! የልቡን ነው ያልከው? የልቡን ታናግሩታላችሁ እንዴ! ለነገሩ የእኛ ሰው ምን ልብ አለውና!”
“ከአርእስቱ እንዳንወጣ…”
“ይኸዋ! አየህ እኔ የልቤን ለተናገርኩት አንተን አላበህ…!”
እኔ የምለው... “በቴሌቪዥን የምትቀርብ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ ያድርግሀ!” የሚል ሚጢጢ እርግማን ነገር አለ እንዴ!
በነገራችን ላይ የሚዲያ ሰዎቻችንን የህዝብን እምነት ለማግኘት ብዙ ሥራ እንደሚጠብቃቸው ማወቁ አሪፍ ነው፡፡ አሁን አንዳንድ ቃለ መጠይቆችን ስናይ ከትናንቱ ቃና መውጣት የሚቸግረን አለን። ፒያኖው ስለተለወጠ ብቻ እኮ ሙዚቃው አያምርም፡፡ ዋናው ነገር ቅኝቱን ማስተካከሉ ነው፡፡ (ለማሳመር  ያህል እንጂ ‘ለመፈላሰፍ’ እንዳልሆነ ልብ ይባልልንማ! ለነገሩ ፈላስፋ ስለበዛ ፣እንሁን ብንልም መወሸቂያ እንኳን የምትሆን ክፍት ስፍራ አናገኝም።)
እግረ መንገድ…ይቺ ነገር ታክሲ ላይ ያየናት ነች…
መብራት እስኪመጣ እኔ ስጠብቃት
አራዳው መጣና በሻማ ወሰዳት
ለነገሩ በሻማ እንድትሄድ ማሳመን መቻሉ ራሱ ‘ችሎታ’ ነው፡፡ ነገርየው ግን ምን መሰላችሁ…የወሰደበት መንገድ፡፡ ‘አራዳ’ የተባለው በ‘ፌይር ፕሌይ’ ሳይሆን አሳብሮ ሄዶ ነዋ ያገኛት! እንደ ብዙ የከተማችን ሚኒባስ ታክሲዎች ባልተፈቀደለት መንገድ ተሹለክልኮ ሄዶ ነዋ የወሰዳት! ላለፉት በርካታ ዓመታት፣ እዚህ አገር አብዛኛው ነገራችን እንዲሁ ሆኗል…በቀጥታው መንገድ የሚሄደው መሀል መንገድ ላይ ‘አጨብጭቦ’ ሲቀር…በአቋራጭ የሄደው የአሸናፊነቱን ዋንጫ ሲያነሳ፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺን ስሙኝማ፣ ከጥቂት ቀናት በፊት የሆነ ነው። በተጨናነቀ ትራፊክ መሀል የነበርንበት ሚኒባስ ታክሲ አንዱን ሸላይ መኪና ሊገጨው አለና ተንሲያጦ ቆመ፡፡ ባለ ሸላዩዋ መኪና ሰውዬ አቁሞ ወረደና እዚህ መጥቀስ የሚከብዱ ብዙ አላስፈላጊ ነገሮች ተናገረ፡፡ መኪናዋ እኮ ምኗም አልተነካም! በጣም አስገራሚው ግን ጎረምሳው ባለታክሲ፣ የእኔ ቢጤውን እግር የሚያካክሉ እጆቹን አጣምሮ፣ ራሱን እየነቀነቀ ከማዳመጥ በቀር አንዲት ቃል አልተነፈሰም፡፡ ሰውየው ሲበቃው አስነስቶ ሄደ፡፡ ተሳፈሪው ሁሉ ባለታክሲውን ለትእግስቱ አመሰገነው። አንድ ጎልማሳ ተሳፈሪም፤ “መታገስህ ቢገባው ለእሱም ትምህርት ነው” አለው፡፡ ንዴት ቤትንም፣ አገርንም አያቀናም!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6495 times