Saturday, 19 May 2012 10:31

የህፃናት ብዝበዛ ተባብሷል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

ስንቅነሽ ታመነ ተወልዳ ካደገችበት ደቡብ ጎንደር ንፋስ መውጫ ከመጣች ሁለት አመት ሊሞላት ጥቂት ቀናት ብቻ እንደቀራት ነገረችኝ፡፡ ፊቷ በድካም የመወየብ ምልክቶች ቢታዩበትም ጠይምና መልከ መልካም ነች የ14 አመቷ ስንቅነሽ፡፡ ያገኘኋት በአዲስ አበባ ሰፊ የቤቶች ግንባታ በሚካሄድበት ቦሌ ክፍለ ከተማ ሲ ኤም ሲ/ሰሚት የሚባለው አካባቢ ነው፡፡ በንፋስ መውጫ እስከ ሶስተኛ ክፍል ተምሬያለሁ ያለችኝ ሀገሪቱ፤ ከጎንደር ይዛት የመጣችው አክስቷ ወደ አረብ ሃገር ስትሄድ ለአባቷ ዘመዶች ሰጥታት እንደሄደች አጫወተችኝ፡፡ አክስቷም ሆነች አሁን የምትኖርባቸው ዘመዶቿ “የተሻለ ትምህርት ቤት እናስገባሻለን” ቢሏትም የትምህርት ቤት ደጃፍን ከረገጠች ድፍን ሁለት አመት ሊሆናት ነው፡፡ ስለ ትምህርት ስጠይቃት በርዕሱ መነሳት ደስተኛ እንዳልሆነች የሚሸሸኝ አይኗ ያሳብቃል፡፡

“ዘመዶችሽ ቤት ታዲያ ምን እየሰራሽ ነው?” ጠየቅኋት፡፡

“ምግብ እሰራለሁ፣ ቤት አፀዳለሁ…”

“ዘመዶችሽ ልጆች አሏቸው?”

“ሶስት ልጆች አላቸው፣ በእድሜ የኔ ታናሾች ናቸው፣ ሁሉም ይማራሉ” አከታትላ መለሰችልኝ፡፡

ሶስቱንም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የላኩት የስንቅነሽ ዘመዶች፤ ለእሷ የሰጧት “እድል” ለልጆቻቸው የምሳ እቃቸውን የማዘጋጀት ስራን ብቻ ነው፡፡ ይህ የስንቅነሽ ታሪክ ከሲኤምሲ እስከ አየር ጤና፣ ከሰሜን ማዘጋጃ እስከ ሳሪስ በርካታ የአዲስ አበባ ቤቶችን የሚያንኳኳ፤ የክልል ከተሞችንም የሚነካ እውነታ ነው፡፡

በኢትዮጵያ አሁንም በገጠር ያለው ድህነት ከከተማው የከፋ ነው፡፡ ከኢኮኖሚ ባለፈ ገጠር በማህበራዊ አገልግሎቶችም በከተማው የሚመራ መሆኑ ደግሞ በርካቶች ከተማን እንዲናፍቁ አስገድዷቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ማህበራዊ ትስስራቸው ጠንካራ በመሆኑ ልጅን ከተማ ያለ ቤተ-ዘመድ ጋር ልኮ ማስተማር የተለመደ ነው፡፡ ከተማ ያለ ዘመድም ልጅሽን/ልጅህን እንደራሳችን ልጅ አድርገን እናስተምራለን ማለቱ አይቀርም፡፡

የወላጅን አደራ ተቀብለው የሚያስተምሩ በርካቶች መኖራቸው እርግጥ ቢሆንም የዛሬው ጉዳያችን ግን በገጠር አልያም በአነስተኛ ከተሞች ያለ ቤተ-ዘመድን አቅም ማጣት ምክንያት አድርገው የልጆቻቸውን እኩዮች ጉልበት ስለሚበዘብዙት ነው፡፡

ወደ ትምህርት ቤት የሚወስዳቸውን አውቶብስ አንድ ሰአት ላይ ለሚይዙት ሶስት ታዳጊዎች ስንቅነሽ ማልዳ ቁርስ ማዘጋጀትና የምሳ እቃቸውን መቋጠር ይጠበቅባታል፡፡ ለቤቱ ጌቶች ምግብ ማዘጋጀት፣ ቤት ማፅዳት፣ ልብስ ማጠብ ደግሞ በተከታታይ የሚጠብቋት ተግባራት ናቸው፡፡ እናም እንደ ጋራ ፊቷ የተቆለለው ስራ ካላለቀ የሚደርስባትን የቁጣ ውርጅብኝ ሽሽት ያለ እረፍት ስትባትል ትውላለች፡፡ በለጋነቷ አምስት አባላት ያለውን ቤተሰብ፣ የእለት ተእለት ስራ የተሸከመችው ስንቅነሽ፤ የልጅነት ወዟ እየተመጠጠ መሆኑን እረፍት የራቀውና በስራ ብዛት የደቀቀው ሰውነቷ ይጠቁማል፡፡

የአሜሪካ አለምአቀፍ ተራድኦ ድርጅት USAID እና የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት unicef እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2007 ባደረጉት የጋራ ጥናት፤ በአመት 10,000 የሚደርሱ በገጠር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለቤት ሰራተኝነት ወደ መሃል አገር ያቀናሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ለአካለ መጠን ያልደረሱና እድሜያቸው 17 ዓመትን ያልዘለለ ታዳጊዎች ናቸው፡፡ በእርግጥ እንደ ስንቅነሽ ሁሉ ቤተ-ዘመድ ጋር ሆነው ለመማር ወደ ከተማ የሚያቀኑት ታዳጊ ሴቶች ጥቂት ባይሆኑም ለህፃናቱ የቤት ሰራተኛ መሆን የሚጠቀሱ ምክንያቶች በርካታ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሰረት፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ዜጎች ቁጥር እየቀነሰ 29 በመቶ አካባቢ ቢደርስም የቤተሰባቸውን ኑሮ ለመደጎም (እጅግ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ነጠላ ወላጆችን ለመደገፍ) ሴት ህፃናት በሰው ቤት ይቀጠራሉ፡፡

እንደ ስንቅነሽ በቤተ-ዘመድ አለሁ ባይነት ከሚመጡት በተጨማሪ ደግሞ በህገወጥ ደላሎች ተታልለው ወደ ስራው የሚገቡም አሉ፡፡

የUSAID እና unicef ጥናት እንደሚያመለክተው፤ በኢትዮጵያ 77,000 ቤተሰብ በህፃናት አስተዳዳሪነት የሚመራ ነው፡፡ በተለያየ አጋጣሚ በሚከሰት የወላጆች አልያም አሳዳጊ ማጣትና ግድየለሽነት ታዳጊዎች የቤተሰብ ሃላፊነትን ሲሸከሙ አብላጫዎቹ በሴት ህፃናት “እማወራዎች” ነው የሚመራው፡፡ እናም ህፃናቱ ትምህርታቸውን በማቋረጥ “ቀለል” ወዳለው የቤት ሰራተኝነት ይገባሉ፡፡

የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት unicef፤ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2003 ይፋ ያደረገው መረጃ በህገወጥ የህፃናት ዝውውር (child trafficking) በአለም አቀፍ ደረጃ ከ7 እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር ይንቀሳቀሳል፡፡

ስንቅነሽ በአንድ አመት እድሜ የምትበልጠው ታደለች አባተም ከሰሜን ወሎ ወልዲያ የመጣችው አዲስ አበባ እጇን ዘርግታ ትቀበልሻለች፣ በዛው ወደ አረብ ሃገር ሄደሽ እንደነ ዘቢባ (ከአካባቢው ወደ አረብ ሃገር ሄዳ እንደተሳካላት የሚነገርላት ታዳጊ) ገንዘብ ታገኛለሽ ባላት አቀባባይ ደላላ ነበር፡፡

በመንደሯ የምታውቃቸው ሁለት ታዳጊዎችን ጨምሮ ስምንት እኩዮቿን ያመጣቸው ሰው፤ አዲስ አበባ ላለ የስራ ጓደኛው አስረከባቸው፡፡ ታደለች አረብ ሃገር መሄድን ተስፋ ብታደርግም በአንድ አመት የአዲስ አበባ ቆይታዋ ሶስተኛ ቤት ለመቀየር የደላላ ደጅ እየጠናች ነው፡፡

“ቤተሰቦችሽ የት እንዳለሽ ያውቃሉ?” ስል ጠየቅኋት

“አባቴ እንኳን ሞቷል፡፡ እናቴ ግን አሁን ሰምታለች፡፡”

“ለምን ወደ አዲስ አበባ መጣሽ?” አስከተልኩ

“ሁለት ታናናሾች ስላሉኝ እናቴ በየሰዉ ቤት እየዞረች የምትሰራው ስለማይበቃን ነበር ወደ አዲስ አበባ ተደብቄ የመጣሁት፡፡ እንዳሰብኩት በቀላሉ ወደ አረብ ሃገር መሄድ አልቻልኩም፡፡ ብር ያስፈልግሻል ስላለኝ በሰው ቤት እየሰራሁ ነው”

“ማነው ያለሽ?”

“ደላላው”

የዘመዶቿ ቁጣ የእለት ቀለቧ እንደሆነ ያጫወተችኝ ስንቅነሽ፣ የእርሷ ታናናሾች የሆኑት የቤቱ ህፃናት የቤተሰቦቿን ድህነትና የከተማ ሰው አለመሆን እያነሱ እንደሚሰድቧት ስትነግረኝ እፍረት ፊቷ ላይ ይነበብ ነበር፡፡ በድካም የዛለ ለጋ ሰውነቷ ተልፈስፍሶ እቃ ከእጇ ቢወድቅ ዱላ እንደማይቀርላት ነግራኛለች፡፡ የ14 አመቷ ስንቅነሽ የህፃንነት ወዟ ብቻ አይደለም የተመጠጠው፤ ፊቷ ላይ የመደናገጥና የመበርገግ ስሜት ይታያል፡፡ በራስ መተማመኗስ? ስል ራሴን ጠየቅሁ፡፡

የUSAID እና የunicef ጥናት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2002 ዓ.ም፤ እንደ ልጃችን አድርገን እናስተምራለን ብለው ቤተ-ዘመድ አልያም የቅርብ ወዳጅ ልጆችን የሚያስኮበልሉ አሰሪዎች ቁጥር 262 ነበር፡፡ ይህ አሃዝ በ2007 በከፍተኛ ፍጥነት በመጨመር ወደ 2,520 ማደጉን የሁለቱ ተቋማት የጋራ ጥናት አመልክቷል፡፡

በቤት ሰራተኝነት የሚያገለግሉ ህፃናት ከሚደርስባቸው በደሎች የመጀመሪያውን ስፍራ የሚይዙት በቂ ምግብ፣ እረፍት፣ መጫወቻ ጊዜ አለማግኘት ነው፡፡ እነኚህ በደሎች ደግሞ በህፃናቱ አካላዊና አእምሮአዊ እድገት ላይ ጫና ያሳድራሉ፡፡ የዛሬ ብቻ ሳይሆን የነገ ተስፋቸውንም የሚወስነው እድገት ስለሚስተጓጎል የወደፊት ህይወታቸውንም እድል የሚያጨልም ይሆናል፡፡

ህፃናቱ የሚገጥማቸው ሁለተኛው ችግር የስነልቦና ቀውስ ነው፡፡ የስነልቦና ባለሙያዎች እንደሚስማሙት ከአእምሮአዊ ብስለት ጋር የማይጣጣም (የህፃናት አእምሮ ሊቋቋመው የማይችል) የቃል ዘለፋም ሆነ አካላዊ ቅጣት የሚያደርሰው የስነልቦና ቀውስ 17 አመት ያልሞላቸው ህፃናት የማያገግሙበት ህመም ውስጥ ሊጥላቸው ይችላል፡፡በሶስተኛነት የሚነሳው ጉዳይ፣ ህፃናቱ ለስራቸው ክፍያ አለማግኘታቸው ነው፡፡ ከወልዲያ መጥታ በአዲስ አበባ ሶስተኛ ቤት ለመቀየር ወደ ደላላ ጋ ያቀናችው የ15 አመቷ ታደለች፤ አሰሪዎቿ ደሞዝ የሚከፍሏት እነርሱ ደስ ባላቸው ሰአት እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ከበላሽ ከጠጣሽ ምን አነሰሽ? እንደሚሏት፤ አልያም ደሞዟን እንዳሻቸው ቆርጠው እንደሚሰጧት ነው የምትገልፀው፡፡

ሁለተኛውን ቤት የለቀቀችው ለሶስት ወር ሰርታ የአንድ ወር ከግማሽ ደሞዝ ብቻ ስለሰጧት እንደሆነም አጫውታኛለች፡፡

በስተመጨረሻ የሚቀመጠውና እጅግ የሚያስከፋው ቀውስ ወሲባዊ ጥቃት ነው፡፡ መሰለ ፈትካሴ የተባሉ አጥኝ ለሁለተኛ ዲግሪ ማሟያቸው ያደረጉት ጥናት፤ በአዲስ አበባ የካቲት 12 ሆስፒታል እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2002 ብቻ እድሜያቸው ከ15 ሳይዘል ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸው የተመዘገቡ ህፃናት ቁጥር 241 ነበር፡፡ አካላዊና አእምሮአዊ ህክምና የተደረገላቸው ህፃናቱ፣ በአብላጫው በሚኖሩበት አካባቢ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተረጋግጧል፡፡ በተለይ የቤት ሰራተኛ የሆኑ ህፃናት፤ የቤቱ እማወራዎች በማይኖሩበት ወቅት በጎረምሳ ልጆች፣ በቅርብ ቤተ-ዘመድ ከዚያም ሲያልፍ በቤቱ አባወራ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ጥናቶች አመላክተዋል፡፡

የኢፌድሪ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንደ unicef,USAID እና Save the Children ካሉ የተራድኦ ድርጅቶች ጋር በመሆን በማህበረሰቡ ውስጥ ንቅናቄ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን በተደጋጋሚ ይገልፃል፡፡ በተለይ ሴት ልጆችን ለማስተማርና ከስነ-ልቦናዊም ሆነ ከአካላዊ ጥቃት ለመታደግ የሚደረጉ ስራዎች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡

በተለይ በሴት ህፃናት ላይ ከፍተኛ ጫና ባለባቸው አካባቢዎች፣ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግና እንደ ትምህርትና ጤና የመሳሰሉ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ማስፋፋት ዋነኛው ተግባር ነው፡፡

ግን አሁንም በመላ ኢትዮጵያ በህፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃትና በደል በዋዛ የሚታለፍ አይደለም፡፡ በስንቅነሽ ህገ መንግስትም ሆነ ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው አለም አቀፍ ድንጋጌዎች የህግ ተጠያቂነትን ይዘው እንደሚመጡ ያለው ግንዛቤ እምብዛም ነው፡፡

 

 

 

 

Read 16095 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 12:44