Saturday, 20 October 2018 13:20

ህገ-ወጥነትና ኢ-ስነምግባራዊነት የተጫናቸው የ”ሰንሴሽን ኮንዶም” ማስታወቂያዎች

Written by  ሰብለ አሰፋ (ጠበቃና የህግ አማካሪ)
Rate this item
(6 votes)

ማስታወቂያ ወይም ማስተዋወቅ “ad vertere” ከሚለው የላቲን ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም፤ አእምሮን ወደ አንድ ምርት መሳብ/ሀሳብን ወደዚህ ምርት መቀየር ማለት ነው፡፡ ይህ የአንድን ሰው አእምሮአዊ አስተሳሰብና እምነት ወደ አንድ ምርት፣ አገልግሎት፣ ሀሳብ ለመሳብ ፤ ለማቅረብ ያለመ የማስተዋወቅ ድርጊት በዋናነት ሁለት ሂደቶችን ያካትታል፡፡ እነኚህም አንድ ሰው፤ ስለዚህ ነገር የሚያውቅበትን መንገድ መፍጠርና ስለዚህ ምርትም ሰውየውን ማሳመንን ነው፡፡ ይህ  በአቅራቢና በተጠቃሚ መካከል ያለ ትልቅ ሀይል ያለው የመገናኛ መንገድ፣ ተጠቃሚዎች ስለ አንድ ምርት አገልግሎትና የጥራት ደረጃ የሚኖራቸውን አመለካከት በእጅጉ የሚወስን በመሆኑም፣ ማስታወቂያዎች፣ ስነ-ምግባራዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ ካልተሰሩ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላሉ፡፡
ከአገልግሎቱ ባህሪ አንጻር የተለያዩ አምራቾች ለገበያ የሚያቀርቧቸውን ኮንዶም አይነቶች ተጠቃሚ ለመጨመር የሚጠቀሙበት የማስታወቂያ ይዘትና አቀራረብ፣ ያልተፈለገ ባህሪን የሚያበረታታና በዚህም ማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል በመቻሉ፣ ኮንዶምን የማስተዋወቅ አግባብነት በአለምአቀፍ ደረጃ አጠያያቂና አነጋጋሪ ነው፡፡ በአለምአቀፍ ደረጃ የኮንዶም ማስታወቂያዎች፣ በአድማጭ ተመልካቹ ላይ ሊያስከትሉ ስለሚችሉት ውጤት አንድ አጠቃላይ ግንዛቤ አለ፡፡ ይህም በወሲብ አማካኝነት የሚተላለፉ በሽታዎች በተለይ ስለ ኤችአይቪ/ኤድስ እና ስለ መከላከያ መንገዶቻቸው በቂ መረጃና ግንዛቤ በሌለበት ማህበረሰብ ውስጥ ኮንዶምን ለማስተዋወቅ የሚሰራጩ ማስታወቂያዎች፣ከጥቅማቸው ጉዳታቸው የሚያመዝን መሆኑ  ነው፡፡ ከዚህ አንጻር መንግስታት የኮንዶም ማስታወቂያዎች ይዘት፣ አቀራረብና ስርጭት ላይ ቁጥጥር ያደርጋሉ፡፡
ይሁን እንጂ የኮንዶም ማስታወቂያዎች ሊያስከትሉት የሚችሉትን አሉታዊ ውጤት ለማስቀረት ሀገራት መውሰድ ያለባቸው ትክክለኛ እርምጃ ምንድን ነው የሚለው አነጋጋሪ ነው፡፡ ቁጥጥሩ ማስታወቂያዎቹን ሙሉ ለሙሉ እንዳይተላለፉ ማገድን መጨመር አለበት? ወይስ የይዘትና አቀራረብ እንዲሁም የሚተላለፉበትን ሰአት ብቻ መቆጣጠር? በተለይ በአንዳንድ ሀገራት ከሚታየው ሰፊ የበሽታው ስርጭት እንዲሁም  ስለ ኮንዶም ካለ ሰፊ የግንዛቤ እጥረት አንጻር፣ የኮንዶም ማስታወቂያን ሙሉ ለሙሉ ማገድ ለማህበረሰቡ የሚጠቅም ትክክለኛ እርምጃ ይሆናል፤ የሚሉት አከራካሪ ነጥቦች ናቸው፡፡
የኮንዶም ማስታወቂያዎች ሙሉ ለሙሉ ባልተከለከሉባቸው ሀገራት፣ ከምርቱ ባህሪና አገልግሎት አኳያ ሊያስከትሉ የሚችሉትን አሉታዊ ውጤት መቀነስ፣ መከላከልን በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲሰሩ ለማስቻል ማስታወቂያዎቹ ሊመዘኑበት የሚገባ የሞራል/ግብረ ገባዊ መርሆዎች በአለም አቀፍ ደረጃ ዳብሯል፡፡ የእነኚህ መርሆዎች በአንድ ማስታወቂያ ይዘት ወይም አቀራረብ አለመከበር ሊያስከትል የሚችለው ህጋዊ ውጤትም በየሀገራቱ ህግ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
በአለምአቀፍ ደረጃ  የማስታወቂያዎችን  ይዘትና አቀራረብ አግባብነት ከሚለኩ መርሆዎች ዋነኞቹ የሚከተሉት ናቸው፡-
1. እውነተኝነት- አንድ ማስታወቂያ የሚያስተላልፈው መልእክት፣ ስለሚያስተዋውቀው ነገር ትክክለኛ ባህሪና የጥራት ደረጃን የሚያመላክት መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ደንብ ጋር በተያያዘ  Puffery ወይም ስለ አንድ ምርት የተጋነነ መረጃ መስጠት ተቀባይነት የላቸውም በተባሉ በርካታ ማስታወቂያዎች የሚስተዋል ዋነኛ ችግር ነው፡፡
ባህል፣ ልማድና ወግን ያገናዘቡ/ያከበሩ መሆን፡- የአንድ ማስታወቂያ ይዘትም ሆነ አቀራረብ  የሚሰራጭበትን ሀገር ባህል፣ ልማድና ወግ ያገናዘበ መሆን አለበት፡፡ ይህም በዋናነት ተጠቃሚውን ወደ አልተፈለገና ማህበረሰባዊ ተቀባይነት ወደ ሌለው ባህሪና ድርጊት የማምራት አሉታዊ ውጤት እንዳይኖረው የሚያስችል ነው፡፡
የሰውን ልጅ ሰብአዊ ክብር ማንነት የማይነኩ መሆን አለባቸው፡- በዚህ ስነ ምግባራዊ ደንብ ስር ለዚህ ጽሁፍ አግባብ ያለው እና በአለምአቀፍ ደረጃ የተወገዘው ሴቶችን በተወሰነ፣ ባነሰ ሚና፣ በተወሰኑ ድርጊቶች ገድቦ የማቅረብ ተግባር ነው። /Stereotyping of women/ ይህ የማስታወቂያ ይዘትና አቀራረብ፣ ለምሳሌ ሴቶች በማህበረሰቡ ዘንድ ሊኖራቸው ስለሚገባው ሚና እና ሊሰጣቸው ስለሚገባ ቦታ አሉታዊ መልእክትን ለአድማጭ ተመልካች የሚያስተላልፍና በማህበረሰቡ ውስጥ ሊኖር የሚገባን ፍትሐዊና ጾታን መሰረት ያደረገ፣ አድልዎ የሌለበት የሰዎች ግንኙነት እንዳይኖር ከፍ ያለ ሚና  ሊጫወት በመቻሉ  በአለም አቀፍ ደረጃ የተወገዘ ነው፡፡
መሰል ማስታወቂያዎች ሴቶችን አስመልክቶ የሚያስተላልፉት መልእክት፤ትክክለኛነት የጎደለውና ሴቶችን በተሳሳተና አንድ ወጥ በሆነ መገለጫ የሚያስቀምጥ ነው፡፡ ይህም ጾታቸው ሴት የሆኑና በመላው አለም፣ በአንድ ሀገር፣ በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሁሉ፣ ሴት በመሆናቸው ብቻ በዝንባሌ፣ በትምህርት፣ በኑሮ፣ በስራ ደረጃ፣ በአመለካከት ወዘተ-- ተመሳሳይ እንደሆኑ አድርጎ ያለ አግባብ የማስቀመጥ አካሄድ ነው፡፡ ሴቶች በጾታ ቢመሳሰሉም፣ አንዳቸውን ከአንዳቸው ለመለየት የሚያስችሉ በርካታ መገለጫዎች ያሏቸው በመሆኑ፣ አንድና ወጥ የሆነ የሴት ሚና፣ ደረጃና ማንነት አለመኖሩን ማህበረሰቡ እንዳይገነዘብ የሚያደርግ የተሳሳተ መረጃን መስጠት፣ የማስታወቂያዎች ኢ-ስነምግባራዊነት መገለጫ ተደርገው ከተፈረጁት አንዱ ነው፡፡
ሀገራት ባላቸው የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭት መጠንና ማህበረሰቡ ስለ መከላከያ መንገዶቹ ካለው ግንዛቤ አንጻር የሚለያዩ በመሆኑ፣ ሀገራት ኮንዶምን ለማስተዋወቅ በሚለቀቁ ማስታወቂያዎች ላይ፣ ከላይ የተዘረዘሩትን መሰረታዊ የማስታወቂያ ሞራላዊ መመዘኛዎች መሰረት በማድረግ፣ የተለያዩ እርምጃዎችን  እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ እንደ ፓኪስታን ያሉ ሀገራት ኮንዶምን ለማስተዋወቅ የሚሰሩ ማስታወቂያዎችን በቴሊቪዥንና ራዲዮ ጣቢያዎች ማሰራጨትን ሙሉ ለሙሉ ከልክለዋል፡፡ ሌሎች ሀገራት ለምሳሌ ህንድ የኮንዶም ማስታወቂያዎቹ ከጠዋቱ 12 ሰአት እስከ ምሽቱ 4 ሰአት እንዳይተላለፉ በማገድ፣ ይዘታቸው በስፋት ማህበረሰቡ በእነኚህ ሚዲያዎች የሚለቀቁ ፕሮግራሞችና ማስታወቂያዎችን ሊያይ በሚችልባቸው ሰአታት እንዳይሰራጩ ማድረግ ችለዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ እዚሁ አህጉራችን አፍሪካ ያሉትን ሀገራት ለምሳሌ ኬንያና ናይጄሪያን ስንመለከት፤ የኮንዶም ማስታወቂያን ይዘትና አቀራረብ በቅርበት የሚከታተል ኮሚሽን ያቋቋሙ ሲሆን በዚህም ለሀዝብ መሰራጨታቸው ከመረጃ ሰጪነታቸው ጉዳታቸው ያመዝናል የሚባሉ እና አድማጭ ተመልካቹም ቅሬታ የሚያቀርብባቸውን ማስታወቂያዎች፣ ሰፊ ስርጭት ከማግኘታቸው በፊት የማስቆም አካሄድን ይከተላሉ። በተጨማሪም ናይጄሪያ፣ የማስታወቂያ ህጓን በማሻሻል፣ማንኛውም የኮንዶም ማስታወቂያ ሊኖረው ስለሚገባ ይዘት የደነገገች ሲሆን ይህ በአስገዳጅነት መካተት ያለበት መልእክት፡-
‹ የኮንዶም የመከላከል ውጤታማነት 100  ፐርሰንት አይደለም፡፡ ለመከላከል ዋነኛ ተመራጭ መንገዶች መታቀብ፣ ከአንድ ፍቅረኛ ጋር ታማኝ ሆኖ ለረዥም ጊዜ መዝለቅ ነው፡፡› የሚል ነው፡፡
ይህ የናይጄሪያ ህግ፤ የኮንዶም ማስታወቂያዎች በትምህርት ቤት፣አምልኮ ስፍራ መዝናኛ ቦታ ወዘተ-- አካባቢ ለህዝብ እይታ መቅረብ፣ መለቀቅ እንደሌለባቸውም ይደነግጋል፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ ከላይ የተጠቀሱትን አለምአቀፋዊ ማስታወቂያን የተመለከቱ ስነምግባራዊ መርሆዎች መነሻ በማድረግ፣ አንድ ማስታወቂያ ሊያሟላው ስለሚገባ ስነምግባራዊና ህጋዊ መስፈርቶች ዝርዝር ነጥቦችን የያዘ የማስታወቂያ አዋጅ ቁጥር 759 በ2004 ዓ.ም  ወጥቷል፡፡ በዚህ አዋጅ መሰረት፤ የተለያዩ መስፈርቶች የተቀመጡ ሲሆን በዋናነት ማስታወቂያዎቹ  በሚኖራቸው ይዘትና በአቀራረባቸው፣ ማናቸውንም ህጎችንና የማህበረሰቡን ስነምግባር፣ የማህበረሰቡን እሴትና ባህል መጻረር የለባቸውም፡፡ ስለሚያስተዋውቁት ምርት የሚያስተላልፉት መረጃም፣ ትክክለኛ መረጃ የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡ /አንቀጸ 6/
በተጨማሪም አዋጁ በአንቀጽ 7፣ አንድ የማስታወቂያ ይዘት ወይም አቀራረብ፣ መልካም ስነምግባርን ወይም ህግን የሚጻረር ነው የሚል ድምዳሜ ላይ የሚያደርሱ ዝርዝር መመዘኛዎችን ያስቀመጠ ሲሆን አንድ ማስታወቂያ በይዘቱም ሆነ በአቀራረቡ ጾታን አስመልክቶ፣ የሰው ልጅን ሰብእና፣ ነጻነት፣ እኩልነት የሚጻረር ምስል፣ አነጋገር ንጽጽር ከያዘ፣ ለመልካም ጸባይ ተቃራኒ የሆነ መልእክት፣ ምስል ወይም አቀራረብን ካካተተ unlawful or immoral advertisement ተደርጎ ይወሰዳል ብሎ በግልጽ አስቀምጧል፡፡
በሀገራችን በተደጋጋሚ የሚተላለፉ የሰንሴሽን ኮንዶም ማስታወቂያዎችን ይዘትና አቀራረብ፣ ከላይ ከተጠቀሱት ህግና ስነምግባራዊ መርሆዎች አንጻር መፈተሽ፣ የዚህ አጭር ጽሁፍ ዋነኛ አላማ ሲሆን ለአንባቢው ግልጽ ለማድረግ፣ 3 የኮንዶም ማስታወቂያዎች ይዘትና አቀራረብ በማሳያነት የሚዳሰሱ ይሆናል፡፡
የማስታወቂያዎቹ ይዘት-
ማስታወቂያ 1፡- አንዲት ሞዴል የፋሽን ትርኢት እያቀረበች ሳለ፣ በቁንጅናዋ የተሳበ ወንድ ትእይንቱን ከሌሎች በርካታ ሰዎች ጋር ተሰብስቦ እየተከታተለ መሆኑን ሁሉ ዘንግቶ፣ ለዚህች ሞዴል ረዥም ጭብጨባ ያሰማል፡፡ ይህን አይነት የአድናቆት ስሜት  ወንዱ ለሞዴሏ ውበት ከተሰማው የሚከተለው ተፈጥሮአዊ ውጤት (Natural and automatic consequence) ወንዱን ከዚህች ሞዴል ጋር  ወሲብ ለመፈጸም የሚዳርግ እንደሆነ ተደርጎ እንዲወሰድ በሚያስችል መልኩ፣ ይህን ትእይንት/የወንዱን በውበቷ ተማርኮ ስሜታዊ መሆንን ተከትሎ፣ ማስታወቂያው ለጥንቃቄው ኮንዶም እንዲጠቀም ወንዱን ይመክራል፡፡
ማስታወቂያ 2፡- በአንድ ካፌ ውስጥ በቡድን እየተዝናኑ ከነበሩ ወንዶች አንዱ፣ አንገቱን ቀና ሲያደርግ፣ ብቻዋን ካፌ ውስጥ የተቀመጠች ቆንጆ ወጣት ያያል ፤ ከኪሱ ኮንዶም አውጥቶ፣ ስልክ ቁጥሩን ጽፎበት በአስተናጋጅ አማካኝነትሊልክላት ሲሞክር፣ ከካፌው መውጣቷን ያስተውላል፤ ይህን ተከትሎ ሌላኛው ደኛው ለአስተናጋጇ ተመሳሳይ ፍላጎት ያድርበትና፣ ኮንዶም ላይ ስልክ ቁጥሩን ጽፎ ሲሰጣት፣ በድርጊቱ ተስማምታ ስትቀበል ይታያል፡፡
ማስታወቂያ 3፡- በአሁን ሰአት በቴሌቪዥን ጣቢያዎቻችን በየደቂቃው እየተላለፈ ያለው ማስታወቂያ አጭር መልእክቱ፤ ሴቷ ጥልፍ ጠልፋ አሳምራ የሰጠችውን ነጠላ፣ አሳምሮ ቋጨው አይነት መልእክት አለው፡፡ እንግዲህ እኔ እንደገባኝ የማስታወቂያው መልእክት፤ ከሴቷ ጋር ወሲብ  እንዲፈጽም ከእሷ ያገኘውን ፈቃደኝነት ተከትሎ፣ ይህንን በሰንሴሽን ኮንዶም በመፈጸም ድርጊቱን የተሻለ አደረገው ነው፡፡
የእነኚህን ማስታወቂያዎች ይዘትና አቀራረብ እንዲሁም በሀገራችን የቴሌቪዥን ማሰራጫዎች የሚተላለፉ የተለያዩ ማስታወቂያዎች፣በዋናነት የኮንዶም ማስታወቂያዎች ይዘትን አስመልክቶ፣ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ምን ያህል ማስታወቂያዎቹ፣ ኢ-ስነምግባራዊ መሆናቸውን አስረጂ ነው፡፡
ከባልነትና ከአባትነት ሚና ውጪ በበርካታ ሙያዊ ሚናዎች ከሚወከሉት ወንዶች አንጻር የሴቶች ሚና ምን ያህል እናትነትና የቤት እመቤትነት ሆኖ፣ በማስታወቂያዎቹ ቀርቧል?
በማስታወቂያዎቹ የሴቶች ልጆች አስተዳደግን አስመልክቶ ያላቸው ሚና የመንከባከብ ስለመሆኑ ወንዶች ለአስተዳደግ አስፈላጊ የሆኑ ወተትና መሰል ነገሮችን በገንዘብ ሀይል የሚቀርቡ፣ በዚህም ሴቶቹ የራሳቸው የኢኮኖሚ አቅም የሌላቸውና በባል ላይ ሙሉ ለሙሉ ጥገኛ ተደርገዋል?
የጥሩ ሴት መለኪያና መገለጫ ውጫዊ ውበት እንደሆነ፣ ውጫዊ ውበት ማለት በአለምአቀፍ ሚዲያ የሚለቀቅን የሞዴሎች ምስል የሚመስል ቅጥነት፣ አለባበስ ሜካፕ የያዘ እና ወጣትነት ብቻ ስለመሆኑ በማስታወቂያዎቹ ተደጋግሞ ይተላለፋል?
በተለይ የኮንዶም ማስታወቂያዎቹ ምን ያህል ሴቶቹን የወንድን የወሲብ ፍላጎት በእሱ ፍላጎትና ምርጫ ብቻ ሊያሟሉ የሚገባቸው፣ ከማን ጋር እና መቼ ወሲብ መፈጸም እንዳለባቸው ወዘተ የመወሰን አቅም እንደሌላቸውና የወንዱን ሙሉ ውሳኔ ተከትለው በተጠሩበት የሚሄዱ፣ ኮንዶም መጠቀም አለመጠቀም ለወንዱ የተተወ ጉዳይ እንደሆነ በማስመሰል  ያቀርባሉ?
በሀገራችን በየጊዜው በቴሌቪዥንና ሬዲዮ የሚለቀቁ የሰንሴሽን ኮንዶም ማስታወቂያዎች፣ ይዘትና አቀራረብ፣ ከኢትዮጵያ የማስታወቂያ ህግና አለምአቀፋዊ የማስታወቂያ መርሆዎች አንጻር ስንመለከት፤ እነኚህ የኮንዶም ማስታወቂያዎች እያስተላለፉ ያለው መልእክት፣ አንድ ወንድ የአንዲትን ሴት ውጫዊ ውበት ከወደደ፣ በቀጥታ ከእሷ ጋር የወሲብ ግንኙነት እንደሚኖረው ነው፡፡ ይህም ልቅ ወሲብን የሚያበረታታና ሰዎች ስሜታዊ ሆነው ከማን ጋር እና መቼ ወሲብ መፈጸም እንዳለባቸው ሳያስቡ ፤ በሁኔታዎች ብቻ ተገፋፍተው እንዲወስኑ የሚገፋፋ ነው፡፡ ስለዚህም ከማህበረሰቡ ወግና ልማድ ጋር ይጋጫል፡፡ የህብረተሰብ ጤና ፖሊሲና ህግጋትንም የሚቃረን ነው፡፡
ኤችአይቪን ከመከላከል አንጻር የወንድ ኮንዶም ያለው ውጤታማነት 85 በመቶ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፤ ኮንዶምን ተጠቅመው ወሲብ ከፈጸሙ 100 ሰዎች 15ቱ በበሽታው ሊያዙ ይችላሉ፡፡ ከዚህም በላይ ኮንዶም የራሱ የአጠቃቀም ህግጋት ያሉትና ወጥነት ባለው መንገድ ሁልጊዜ መጠቀምን የግድ የሚል፣ ይህ ካልተተገበረ፣ የመከላከል አቅሙ ከ85 በመቶ በታችም ዝቅ የሚል ስለሆነ፣ በወሲብ ምክንያት የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል ከኮንዶም በፊት የሚመከሩት መታቀብና ከአንድ ታማኝ ወዳጅ ጋር ረዥም ጊዜ በታማኝነት መቆየት ናቸው፡፡ የመከላከያ መንገዶቹ በቅደም ተከተል A B C  ሆነው የተቀመጡ ሲሆኑ ከመከላከል ውጤታማነት አንጻር ቢቻል መጠቀም ያለብን በ A እና B ያሉትን ነው፡፤. A-abstinence, B- be faithful and  C- use condom::
ስለዚህ ኮንዶም በመከላከል ረገድ በ3ኛ ደረጃ የሚመጣ ነው፡፡ የኮንዶም ማስታወቂያዎቹ ግን ወሲብ መፈጸም፣ ውብ ሴትን ማየትን ብቻ የሚጠይቅ አድርገው አቅልለው ማቅረባቸው ሳያንስ በመከላከል ረገድ ከኮንዶም በፊት የሚመረጡት መታቀብና ታማኝነት መሆናቸውን አይገልጹም፡፡
በሌላ አነጋገር፤ መታቀብና ታማኝነት የሚሉትን ቀዳሚ የመከላከያ ዘዴዎች ተመልካቹ እንዳይረዳቸው፣ በቂ መረጃ በማስታወቂያዎቹ አለመተላለፉ፣ ስለ ኮንዶም የመከላከል አቅም ተጠቃሚው ላይ የተዛባ አመለካከት የሚፈጥር፤ ለኮንዶም ከፍተኛ ግምት መስጠትን የሚያነሳሳ  ነው፡፡ በዚህ መልኩ፣ አንድን ምርት፣ የሌለውን ጠቀሜታ እንዳለው አድርጎ ማስተዋወቅ፤ ስለ ምርቱ በሚተላለፍ መልእክት ውስጥ አብሮ መገለጽ ያለባቸውን መረጃዎች ባለመስጠት፣ እንደተገለጸው ጥቅሙ አንደኛ ደረጃ መሆኑን ለህዝቡ ማስተላለፍ፣ ስለ ምርቱ ሀሰተኛና የተጋነነ መረጃ መስጠት በመሆኑ፣ በሀገራችን ህግ በግልጽ የተከለከለ፣ ህገወጥ፣ የማስታወቂያ መሰረታዊ የስነምግባር መርሆዎች የጣሰ ተግባር ነው፡፡
ኮንዶም የመከላከል አቅሙ በአጠቃቀም ህጎቹ የሚወሰን መሆኑን በመልእክቶቻቸው አለማካተታቸው፣ ኮንዶምን ወጥነት ባለው መልኩ መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ አለመግለጻቸው፣ ለተመልካቹ ስለ ኮንዶም የተጋነነ የመከላከል አቅም መረጃ እየሰጡ መሆኑን የሚያስረዳ ሲሆን በዚህም ከመረጃ ሰጪነታቸው ይልቅ አብረው ማስተላለፍ ሲኖርባቸው፣ ባላካተቷቸው ወሳኝ መልእክቶችና በሚያስተላልፉት ልቅ ወሲብን የማበረታታት አዝማሚያ፣ ለማህበረሰቡ ያላቸው ፋይዳ፣ ከመረጃ ሰጪነት ይልቅ ሀሰተኛ መረጃን በመልቀቅ ከፍተኛ ጉዳትን ማድረስ ነው፡፡
ማስታወቂያዎቹ፣ አቀራረባቸው፣ መልእክታቸውን ለወንዱ የሚያስተላልፉና ታሪኩ የሚነገርበት መንገድ /Storytelling/ ከወንድ አንጻር ሲሆን፣ የሚተዋወቀው የወንድ ኮንዶም መሆኑ፣ ተራኪው ወንድ መሆኑና የካሜራው አቅጣጫ /Perspective angel/ ከወንዱ አንጻር መሆናቸው በአንድነት ሲታይ፣ እነኚህ የኮንዶም ማስታወቂያዎች የሚያስተላልፉት መልእክት፣ ዋነኛ ባለጉዳይ፣ ወንድ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ይህ መልእክት የሚተላለፍበት አግባብ ደግሞ በሴቷ መሳብን፣ ከተሳበ በኋላም ወሲብ ለመፈጸም መወሰንን፣ ድርጊቱን በኮንዶም መፈጸምን ሁሉ የወንዱ ብቸኛ ውሳኔ አድርጎ የሚያቀርብ ነው፡፡ ሴቷ በዚህ ሂደት አንድም ሀሳብና ፈቃድ ስትሰጥ አይታይም፡፡
በሁሉም የሰንሴሽን ኮንዶም ማስታወቂያዎች እንደሚገለጽልን ከሆነ፤ ከተቃራኒ ጾታ ጋር በሚኖር ግንኙነት /ወሲብን / ጨምሮ፣ የሴቷ ሚና፣ በውጫዊ ውበቷ የፈለጋትን ወንድ ተከትሎ መሄድ ብቻ ነው፡፡ ከእነኚህ ማስታወቂያዎች በመነሳት፣ አንድ ተመልካች ሊገነዘበው የሚችለው፣ ሴቶች ከወንዶች ጋር ባላቸው የተቃራኒ ጾታ ግንኙነት፣ ምንም አይነት የመወሰን ነጻነት፣ ችሎታና አቅም የሌላቸው እንደሆኑ፣ ከወንዶች ያነሱ ፍጡራን መሆናቸውን ነው፡፡ ስነ-ተዋልዶንና ወሲብን አስመልክቶ፣ ጤናን ብሎም አደገኛና አጋላጭ ከሆነ ተግባር ለመጠበቅ የሴቶቹ ሚና ወሳኝ እንዳልሆነና ሁሉነገር በወንዱ ውሳኔ ስር ያለ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ ሁሉም ሴቶች፤ ወንዱ ከእነሱ ጋር ወሲብ እንደሚፈጽም መወሰኑ ብቻ ወሲብ ለመፈጸም እንደሚያስገድዳቸውና ሊያስቀሩት እንደማይችሉት፣ የመምረጥ፣ በአካላቸው ላይ የመወሰን አቅም እንደሌላቸው ምስኪን ተመልካቾች ተደርገው ተቀምጠዋል፡፡ ጾታን መሰረት አድርጎ፣ ሴቶችን እንደ ሰው የመወሰን ነጻነት፣ አቅም የሌላቸው ተደርገው እንዲወሰዱ መልእክት የሚያስተላልፉ ማስታወቂያዎች፣ ህገ ወጥ ስለመሆናቸው ከላይ በተጠቀሰው አዋጅ በግልጽ ተድንግጓል፡፡
በሁሉም የኮንዶም ማስታወቂያዎች ላይ ሴቶቹ እጅግ ቀጭን፣ በውበት ያማሩ፣ ውጫዊ ውበት ላይ የሚያተኩሩ፣ የሚሰሩት ስራም እንደ ካፌ አስተናጋጅ አይነት አድርጎ የቀረበበት ነው፡፡ በእነኚህና በሀገራችን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚተላለፉ በርካታ ማስታወቂያዎች ውስጥ የተካተቱ ሴቶች በውጫዊ ውበታቸው ብቻ የሚገለጹ፣ ማህበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነት እንዲኖራቸው፣ የተሻለ ተደማጭነት እንዲያገኙ የሚያስገድድ ከውበት ውጪ የሆነ ችሎታ እንደሌላቸው፣ ፍላጎታቸውና ዝንባሌአቸውም የቤት ውስጥ እመቤትነትና ቤተሰብን መንከባከብ ብቻ ተደርጎ፤ ወጣት ሴቶች ተክለ ሰውነታቸውን በሜካፕ በማሳመርና ቀጭን በመሆን፣ ወንድን ለመሳብ፣ ቀንና ሌሊት የሚሰሩ አድርጎ ማቅረብ፣ የሴትን ውበት ከወጣትነት ብሎም ከውጫዊ ገጽታ አንጻር ጋር ብቻ ያቆራኙም ናቸው፡፡
እነኚህ ማስታወቂያዎች፣ ወጥነትና ተመሳሳይነት ባለው መልኩ፣የማህበረሰቡን እሴትና የሴቶችን ሰብአዊ ክብርና መብት የሚጻረሩ በሆኑበት፣ እንደተፈለገ በየደቂቃው በየቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሲተላለፉ መመልከት፣ የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹንም የኤዲቶሪያል ፖሊሲ ደካማነት የሚያሳይ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን፣ እነኚህ ማስታወቂያዎች ከተመልካቹ በርካታ ቅሬታ እየቀረበባቸው ዝምታን መምረጡም እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ የኤችአይቪ ቫይረስ ስርጭት እንደገና በስፋት እየተስተዋለ በሚታይበት ሀገር፤ እነኚህ ማስታወቂያዎች በሚያስተላልፉት ልቅ ወሲብን የሚያበረታታና ኮንዶምን አስተማማኝ የመከላከያ መንገድ አድርጎ የማቅረብ የተሳሳተ አካሄድ እንዲቆም አለማድረግ፣ ለዜጎች ጤና እና ደህንነት፣ ሀላፊነት የጎደለው ቸልተኝነት እንደማሳየት የሚቆጠርም በመሆኑ፣ አፋጣኝ መፍትሄ የሚሻ  ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሁፉ የጸሃፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ መሆኑን ልንገለጽ እንወዳለን፡፡


Read 1565 times