Saturday, 20 October 2018 13:38

የጠ/ሚኒስትሩ ለሴቶች ትኩረት የሰጠ ሹመት አለማቀፍ አድናቆት አትርፏል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

 የካቢኔያቸውን እኩሌታ በሴቶች በማዋቀር፣ በሴቶች የለውጥ ኃይልነት እምነት ያሳደሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ የፆታ እኩልነትን በሚያረጋግጠው አዲስ የሴቶች ሹመታቸው አለማቀፍ ተቋማት አድናቆት የተቸራቸው ሲሆን ብዙዎቹ የዓለም መገናኛ ብዙኃንም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ዘግበውታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሴቶችን ለከፍተኛው የፖለቲካ ስልጣን በማብቃት ረገድ ከአፍሪካ ሃገራት መሪዎች ቀዳሚነቱን በመያዝ ፈርቀዳጅነታቸውን አስመስክረዋል ተብሏል፡፡ የመከላከያ ሚኒስትር እና በስሩ የደህንነትና የፀጥታ ኃይሎችን የያዘውን የሰላም ሚኒስትር በሴቶች እንዲመሩ ማድረጋቸውን በአድናቆት የዘገበው አሶሴትድ ፕሬስ፤ ይህም መሰረታዊ ለውጥ በማምጣት፣ ሀገሪቱን በአፍሪካ ጠቃሚና ስትራቴጂያዊ ሃገር ለማድረግ ያግዛታል ብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህን መሰረታዊ ለውጦች በራሳቸው ቀና አድርጓቸዋል ፖለቲካዊ ውሳኔ ማምጣታቸውን ዘገባው ጠቁሞ ይህ የለውጥ እርምጃቸውና አቅጣጫቸው በአመራር ዘመናቸው ተወዳጅነትና ታዋቂነትን ካተረፉት የደቡብ አፍሪካው ኔልሰን ማንዴላ፣ የአሜሪካው ባራክ ኦባማ እና የሩሲያው ሚኻኤል ጎርቫቾቭ ጋር እንዲመሳሰሉና እንዲነፃፀሩ አድርጓቸዋል ብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሴቶችን ወደ ፖለቲካ ስልጣን በማምጣት ሩዋንዳ እና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚዎቹ ሲሆኑ ሩዋንዳ ከፓርላማ አባሏ ከ60 በመቶ በላይ ሴቶች ሲሆኑ ኢትዮጵያ ዋናው የመንግስት አስፈፃሚ አካል የሚኒስትሮች ምክር ቤት 50 በመቶ ሴቶች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ 50 በመቶ የካቢኔ አባላት ሴቶች የሆኑበት ሌላ የአፍሪካ ሃገር የለም፡፡
ለሴቶች ትልቅ የፖለቲካ ስልጣን በመስጠት, ከአፍሪካ ሃገራት ትልቅ አድናቆት የሚቸራት ሩዋንዳ፤ ሴቶችን በዚህ መጠን ለማሳተፍ የተገደደችው እ.ኤ.አ በ1994 በሀገሪቱ ለአንድ መቶ ቀናት የቆየውና ዘርን መሰረት ያደረገው ጭፍጨፋ (Genocide) አንድ ሚሊዮን ገደማ (አብዛኛው ወንዶች) በመቅጠፉ ነው፡፡  በሩዋንዳ ከተከሰተው የዘር ፍጅት ከተረፉት ዜጎች ከ60 እስከ 70 በመቶ ሴቶች ሲሆኑ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፤ ሃገሪቱ ያላትን የሴቶች አቅም በመጠቀም፣ ሴቶችን በልዩ ትኩረት በማስተማር፣ ለፖለቲካ ስልጣን ማብቃታቸው በአድናቆት ይጠቀስላቸዋል፡፡
ሴቶችን በልዩ ትኩረት ከማስተማር ባሻገር እ.ኤ.አ በ2003 ከሀገሪቱ የፓርላማ ወንበር 30 በመቶው ለሴቶች በኮታ እንዲሰጥ አዋጅ ወጥቷል፡፡ ይህ አዋጅ ቢወጣም ሃገሪቱ ያላት የሴቶች አቅም ከወንዶች የሚልቅ በመሆኑ፣ ፓርላማው በዚያው አመት ከ48 በመቶ በላይ በሴቶች የተያዘ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ የሴቶች ድርሻ ከ60 በመቶ በላይ ነው፡፡
ሴቶችን ለፖለቲካ ስልጣን በማብቃት ከአፍሪካ ሃገራት ተጠቃሽ የሆነችው ሩዋንዳ፤ የካቢኔ አባላት የሴቶች ድርሻ ግን 48 በመቶ ነው ተብሏል፡፡
ሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በፈጠረው አስገዳጅ ሁኔታ ሴቶች በፖለቲካ ስልጣን የላቀ ድርሻ ያገኙ ሲሆን በኢትዮጵያ የሴቶች የፖለቲካ ድርሻ ላቅ ለማለቱ ግን የራሳቸው የሴቶቹ ትግልና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ጉልህ ሚና እንዳለው ተንታኞች ይገልፃሉ፡፡
ከዓለም ሃገራት በፖለቲካ ተሳትፎ ረገድ የሴቶችን እኩልነት በማረጋገጥ አይስላንድ፣ ፊንላንድ፣ ኖርዌይ፣ ስዊድንና ሩዋንዳ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ፣ በዲሞክራሲና በሰብአዊ መብት አጠባበቅ የዓለም ሞዴል መሆኗ የሚነገርላት አሜሪካ፤ በ45ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
በአሜሪካ ሴቶች በፓርላማ ያላቸው ድርሻ 19.3 በመቶ ብቻ ሲሆን ይህን ቁጥር አሳድጋ አፍሪካዊቷ ሩዋንዳ ላይ ለመድረስ አሁን ባለው የሀገሪቱ የፖለቲካ አካሄድ፣ 500 አመታት ይፈጅባታል ተብሏል፡፡
የዶ/ር ዐቢይ መንግስት የሴቶች ሹመት የይስሙላ ሳይሆን ልባዊ መሆኑን የሚመሰክሩት የፖለቲካ ተንታኞች በተለይ ሁለቱን ቁልፍ ሹመቶች ይጠቅሳሉ - የመከላከያ ሚኒስትር እና አዲስ የተዋቀረው ሰላም ሚኒስትር የኢኮኖሚና ሰብአዊ መብት ጥያቄዎችን ይዞ ላለፉት 3 ዓመታት መንግስትን ሲቃወም ለነበረው ህዝብ ግን ዋናው ነገር ሴቶች መሾማቸው ሳይሆን የሚያመጡት ውጤት ነው፡፡   

Read 8032 times