Saturday, 20 October 2018 13:37

ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በአፍሪካ ህብረት ሃውልት ሊቆምላቸው ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

ለአፍሪካ ሃገራት ነፃነትና ለአፍሪካ ህብረት ምስረታ፣ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ካበረከቱት የአፍሪካ መሪዎች በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ፤ በአፍሪካ ህብረት ግቢ ውስጥ የመታሰቢያ ሃውልት ሊቆምላቸው መሆኑ ተገለጸ፡፡  
በቻይና መንግስት ሙሉ ወጪ ተገንብቶ ለአፍሪካ ህብረት የተበረከተው አዲስ ህንጻ በተመረቀበት ወቅት  የአፍሪካ አንድነትን ከመሰረቱት አፍሪካውያን መሪዎች መካከል የጋናው መሪ የመታሰቢያ ሃውልት ቢቆምም፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሃውልት ግን መዘንጋቱ ብዙዎችን ማሳዘኑ የሚታወስ ሲሆን ጉዳዩ በኢትዮጵያ መንግስት ደረጃ ተነስቶ ለውይይት የቀረበበት ጊዜ የለም፡፡
ለቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የመታሰቢያ ሃውልት በሚቆምበት ሁኔታ ላይ በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ተወካይ ከሆኑት አምባሳደር ወይንሸት ታደሰ ጋር ምክክር ማድረጉን የገለፀው ህብረቱ፤ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል አዎንታዊ ምላሽ መገኘቱን አስታውቋል፡፡ በህብረቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የንጉሱን ሃውልት የማቆም ስራም እስከ ቀጣዩ የፈረንጆች 2019 ዓ.ም መጀመሪያ ድረስ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡   
ለቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ የሚቆመው ይህ ሃውልት፤ንጉሡ ለአፍሪካ ሃገራት ነፃነትና ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ላበረከቱት ወደር የለሽ አስተዋፅኦ፣ እውቅና ለመስጠት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረት ምስረታ የጎላ አስተዋፅኦ ማድረጓ የሚታወቅ ሲሆን ላለፉት 50 ዓመታትም  የህብረቱ ቋሚ መቀመጫ በመሆን ለአፍሪካውያን አንድነት መጠናከር የማይናቅ ሚና ተጫውታለች።  
የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ 126ኛ ዓመት የልደት በዓል በተከበረበት ወቅት፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፣ ለንጉሱ የመታሰቢያ ሃውልት እንዲሰራ መንግስትንና የአፍሪካ ህብረትን የማግባባት ስራ እንደሚሰራ ተናግረው ነበር፡፡

Read 10698 times