Sunday, 14 October 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)


           “የሃሳብ ድህነት፣ የተፈጥሮን ምስጢር ያለመረዳት ነው”
                
     ሰውየው የትራፊክ መብራት አስቁሞት ሲጠባበቅ፣ ረሃብ ሊጥለው የደረሰ የሚመስል ሰው በመስኮቱ በኩል ተጠግቶ፤
“ጋሼ እርቦኛል” አለው፡፡
“የአርብ ቀን ዕድልህ ነው፣ ዕጣ ፈንታህ፤ በእግዜር ስራ ጣልቃ አልገባም” አለው፡፡
ሌላ ቡቱቷም መጣ፡፡
“ጋሼ፤ አሮጌ ልብስ ካለዎት ጣሉልኝ” አለው፡፡
“የአርባ ቀን ዕድልህ ነው፤ በእግዜር ስራ ጣልቃ አልገባም” በማለት መለሰው፤እንደ ፊተኛው፡፡
ወዲያው ደግሞ አንዲት ከሲታ መጥታ …
“ጋሼ፤ ታምሜ መድኃኒት መግዣ አጣሁ” አለችው። እንደ ሌሎቹ መልሶላት መስታወቱን ከፍ አደረገ፡፡ … አረንጓዴ በርቶ ከተንቀሳቀሰ በኋላ ግን ምክንያቱን ሳያውቀው ስለ ምስኪኖቹ ሰዎች ማሰብ ጀመረ፡፡ የዓይኖቻቸው ብርሃንና የድምፃቸው ቃና እየተመላለሰ ረበሸው፡፡ ካሁን ቀደም እንዲህ ሆኖ አያውቅም፡፡ … ለምን ይሆን?
***
ወዳጄ፡- ብትራብ የመንግስት ነጻ ምግብ፣ ብትታረዝ ሳልቫጅ ልታገኝ ትችላለህ፡፡ ማሰብ ከተቸገርክ ግን እንዴት ትኖራለህ? … ከሌሎች ሰዎች ሃሳብ እየለመንክ? … ታዲያ ከእንስሳት መሻልህ በምንድን ነው? … ‹ሰው› ሆኖ ከመኖር ፀጋ ያተረፍከውስ? … ሊቃውንቶች እንደሚሉት፤ ሃሳብ አቅም ነው፡፡ ትልልቅ አእምሮዎች ስለ ሃሳብ ይጨነቃሉ፡፡ (great minds discuss ideas እንደሚሉት)
በትክክል ስታስብ የሰውን ልጅ (ሰብአዊነትን)  ታግዛለህ፡፡ ለስልጣኔ ታዋጣለህ፡፡ በእጅህ የያዝከው ስልክ፣ ዓይኖችህ ላይ የሰካኸው መነፅር፣ የምትሰራበት ኮምፒውተር ወዘተ--በትክክል የሚያስቡ ሰዎች የሰጡህ ነው፡፡ የስልጣኔ ትሩፋት!! የሃሳብ ድህነት፣ ስልጣኔን ያቆሽሻል፤ የሰብአዊነት አረም ነው፡፡ የሃሳብ ድህነት፣ማፍቀርና መውደድ ያለመቻል ነው፡፡ የሃሳብ ድህነት፣ የጓደኝነትና የወዳጅነት መተሳሰብን ጥላሸት የሚቀባ ነው፡፡ የሃሳብ ድህነት፣ የተፈጥሮን ምስጢር ያለመረዳት ነው፡፡ የሃሳብ ድህነት፣ የዓለም ህዝቦችን ግንኙነት፣ አንድነትና ልዩነት በትክክል ያለመገንዘብ ነው፡፡ የሃሳብ ድህነት፣ የሳይንስ፣ የፍልስፍና፣ የጥበብ፣ የእምነትና የቴክኖሎጂ መካንነት ነው፡፡ የሃሳብ ድህነት፣ የሞራልና የግብረገብነት ጥቅምን አለማወቅ ነው፡፡ የሃሳብ ድህነት፣ የጦርነት፣ የተስፋፊነት፣ የጭቆና፣ የፀረ-ዴሞክራሲና ኢ-ፍትሃዊነት ምክንያት ነው፡፡ የሃሳብ ድህነት፣ ተፈጥሮን የመንከባከብ ተነሳሽነት ማጣት ነው፡፡ የሃሳብ ድህነት፣ ስቃይና መከራችንን እያጎላ፣ ተስፋችንን እያጨለመ፣ ህይወት እንድታጥር እያደረገ መኖርን ኪሳራ ያደርገዋል፡፡ የሃሳብ ድህነት፤ የሌሎችን በጎነትና መልካምነት እያደበዘዘ፣ ነውርና ክፋታቸውን ያጎላል፡፡ የሃሳብ ድህነት፤ አጉል እምነቶች፣ ወጎችና ልማዶችን ያሞካሻል፡፡ … የሀሳብ ድህነት፣ ተዘርዝረው ለማያልቁ ብዙ … ብዙ ሰው ሰራሽ ችግሮች ምንጭ ነው።
ወዳጄ፡- ህዝባችን መከራና ደስታ፣ ተስፋና እንግልት ተደባልቀው ያናውዙታል፡፡ አንዳንዶቻችን ጥሬ ነን፤ እንደ ልጅነታችን፡፡ አንዳንዶቻችን በዕውቀትና በልምድ በስለናል፡፡ አንዳንዶቻችን በዕድሜ ጫና እየተዳቆስን ምሬተኛ ሆነናል፡፡ መኖር ከአስደሳችነቱ አስጨናቂነቱ፣ ከውድነቱ ዕዳነቱ ከብዶ፣ የህዝባችን ትከሻ ጎብጧል። በዚህ ላይ ስለ ሰላም፣ ስለ መሰደድና መፈናቀል፣ ስለ አገር አንድነት፣ ስለ ፍትህና ዲሞክራሲ ስናስብ … ህይወት፤ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ሆኖብን እርፍ!!
ጥያቄው፡- ፖለቲከኞቻችን የብርሃን ጮራ እየፈነጠቁ፣ በስልጣኔ መንገድ እንድንጓዝ ምሳሌ ሆነው ይመሩናል? ከድህነት ተላቀን በፍቅርና በመተጋገዝ፣ አገራችንን የምናሳድግበትን ሃሳብና ስትራቴጂ ይነድፉልናል? በህዝባችን መሃከል የሚነሱትን ከዘርና ከጎሳ ጋር የተነካኩ ግጭቶችን ሸምግለው፣ ለዘመናት የተገነቡት የአብሮነት እሴቶች፣ አላፊ በሆነው የዘር ፖለቲካ እንዳይመረዝ (infected እንዳይሆን) በማከም፣ ሲቪል አስተዳደር (Civil state) እያደራጁልን ነው? … ወይስ አይደለም? የሚል ነው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በጥብቅ ካልታሰበባቸው፣ ቶማስ ሆብስ፤ “ሁሉም ከሁሉም ጋር እየተጋጨ ይኖራል … ያውም ሁልጊዜ!” (Outside of civil state, there is always a war of all against all) እንደሚለው ይሆንና እናዝናለን፡፡
ወዳጄ፡- አንድ ነገር ልብ በል፤ “ያልተበጠበጠ አይጠራም” ወይም “ያልተማሰለ አይዋሃድም” (Chemical unshaked, desentigrate) እንደሚባለው፤ ትርምሱ ጊዜውን የጠበቀ፣ የተሻለ ነገር የሚወልድ ከሆነ፣ ለበጎ ነው ብለን ልናስብ እንችል ይሆናል፡፡ እናቶቻችን፤ ሽሮ እንዴት እንደሚመቱ፣ በሶ እንዴት እንደሚበጠብጡ አይተናል፡፡ ሆን ተብሎ የለውጡን ሂደት ለማደናቀፍ የሚደረግ ግጭትና ብጥብጥ ግን የሃሳብ ድህነት ብቻ ሳይሆን ዕብደትም ነው፡፡ በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ ዓይነት!! ስለ ዕብደት ካነሳን ሰር አይዛክ ኒውተን፤ “I can calculate the motions of the heavenly bodies, but not the madness of people” በማለት ፅፏል፡፡
***
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- ሰውየው ሦስቱን ‹ችጋራሞች› ከሸኘም በኋላ ማሰቡን አላቆመም ብለናል፡፡ ዘመን በዘመን ላይ እየተደረበ፣ መንግስታት እየተቀያየሩ ሲመጡ፣ ሁሉም ነገር ተለዋወጠና ረሳቸው፡፡ እንኳን ስለ ሌሎች ስለ ራሱም ማሰብ አቃተው፡፡ ኑሮው ተቀይሮ ደኸየ፡፡ የበፊቱን እያስታወሰ ስለሚበሳጭ፣ ጠጪና ቤተሰቡን አዋኪ ሆነ፡፡ አንድ ቀን … ዘመን በሳቀለት ጊዜ፣ ዐዋቂ ነኝ ባይ በነበረበት ወቅት የሚያውቀው ወዳጅ፣ አገኘና ዕድሉን እያማረረ፣ ዕጣ ፈንታውን ሲራገም፤
“እግዜር ቢሮ ከፍቷል፣ ሄደህ ተወካዮቹን አነጋግር” በማለት ወዳጁ ነገረው፡፡ አድራሻውን አመላከተውናም ሄደ፡፡ ከተባለው ቦታ ደርሶ፣ ተራውን ጠብቆ ገባ፡፡ ፊት ለፊት የተቀመጡትን ሰዎች ሲመለከት ተሸበረ፡፡ የት እንደሚያውቃቸው ለማስታወስ እየጣረ ሳለ፣ ዓይኖቹ ግድግዳው ላይ በተለጠፈው ወረቀት ላይ አረፉ ፡፡ … “To be good means to be God” በሚል ርዕስ ስር የመስሪያ ቤቱ መርሆዎች ተዘርዝረዋል፡፡
አንደኛ - ዕድል፣ ዕጣ ፈንታ እያሉ፣ ያላኖሩትን ዕቃ ለሚፈልጉ፣ ያልዘሩትን ለማጨድ ለሚሞክሩ ቦታ የለም፡፡
ሁለተኛ፡- ስራብ ላላጎረሱኝ፣ ስጠማ ላላጠጡኝ፣ ስታመም ላልጠየቁኝ፣ ስታረዝ ላላበሱኝ፣ እንግዳ ሆኜ ስመጣ በፍቅር ላልተቀበሉኝ ቦታ የለም፡፡ ሦስተኛ፣ አራተኛ … እያለ ይቀጥላል፡፡ ሰውየው የመጀመሪያና ሁለተኛውን እንዳነበበ፣ ከፊት ለፊቱ የተቀመጡት እነማን እንደሆኑ አስታወሰ፡፡ ወዲያውም፤ “ና! ያንተ ቦታ እዚህ አይደለም” የሚለውን ድምፅ ሲሰማና እጆቹ ሲጎተቱ አንድ ሆነ፡፡
ወዳጄ፡- ነገህ ምን እንዳረገዘች አይታወቅምና፣ ዛሬን መጠቀም ብልህነት አይመስልህም?
“Be him a king, Be him a bishop … whoever is he, whatever his position is … can not tell what tommorrow has in store” … ሲል የጻፈው ማን እንደሆነ ታስታውሳለህ?
በነገራችን ላይ፣ “ነገን ዛሬ እንስራ!” የሚለው ማስታወቂያ ይመቸኛል፡፡
ሠላም!!  

Read 1258 times