Sunday, 14 October 2018 00:00

የያሬድ ጥበቡ “ወጥቼ አልወጣሁም” በወፍ በረር

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

(የመጨረሻ  ክፍል)
የ”ወጥቼ አልወጣሁም” ደራሲ ያሬድ ጥበቡ፤ የኢህአዴግ አንጋፋ ባለሥልጣናት የነበሩት አቶ በረከት ስምኦንንና አቶ አዲሱ ለገሰን የትግል አጋሬ ናቸው ይላቸዋል፤ ይሳሳላቸዋል፡፡ ሌላ ቦታ ደግሞ ያዝንባቸዋል፤ ይቆዝምባቸዋል፡፡ ይህንን የሚያደርገውም በየጊዜው በቆሙበት የትግል ቦታ ጥንካሬና በተንሸራተቱባቸው የድክመት ሰርጦች መሰረት ነው፡፡ በየቱም ግለሰብና ቡድን፣ በየቱም አቋም ጥንካሬና ድክመት፣ አንድን ቦታ ይዞ፣ የሙጢኝ ባለማለት ፍትሃዊነትን ያሳየናል፡፡ ለምሳሌ፡- ገፅ 142 ላይ እንዲህ ይለናል፡- “አቶ አዲሱ ለገሰና አቶ በረከት ስምዖን በብዙ የፈተና ስጋቶች አብረውኝ የቆሙ፣ የወያኔን ጠባብ ብሔርተኝነትና ተስፋፊነት አብረውኝ የተዋጉ የማደንቃቸው ጓዶቼ ነበሩ፡፡---”
እኒህ ሁለት  ጓዶቹ፣ ቀን ጠብቀው ሀሳባቸውን ያሳመሩ ሲመስለው፣ በተለይ ህወሓት ለሁለት የተሰነጠቀ ጊዜ እንዲህ ሲል  አድንቋቸዋል፡-
“--ሁላችንም ቃልኪዳናችንን ጠብቀን፣ በየተሰለፍንበት መስክ፣ የወያኔን ጠባብ ብሄርተኝነት መክተናል፡፡ ድካማችንም ከንቱ አልቀረም፡፡ ወያኔም ከራሱ ተሰንጥቋል፡፡--”
ይህ እንግዲህ ሕወሓት ሲሰነጠቅ፣ በስንጥቁ መሃል በታየው ተስፋ፣ ደራሲው ያወረደው ሀሳብ ነው፡፡ የድርጅቱ ራስ የሆነው አስኳል ከተሰነጠቀ፣ በእህት ድርጅቶች መካከል ያለው የበላይነት ይሻሻልና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመስረት የተዘጉ ደጆች ወለል ብለው ይከፈታሉ የሚል የናፍቆት ዜማም ይመስላል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ስለእነ አቶ በረከት ስምኦን ስጋት እንዳላቸውና በዚያኛው ወገን እንዳይደፈጠጡ ያስጠነቅቃል፡፡ ምናልባትም ከቀድሞው በተሻለ ሁኔታ በጥንቃቄ ካልተጓዙ አደጋ ሊገጥማቸው እንደሚችልም በምጥ ድምፀት ያሳስባል፡፡ እንዲያውም በአቶ በረከት ስምዖን ላይ “ወያኔ በተንኮል አስተባብሯል” የሚል ፍርሃት ያንዘፈዘፈው ይመስላል። ይህንንም፤ “ሰሞኑን ወያኔዎች በምክር ቤቱ ውስጥ በአቶ በረከት ላይ ለማስተባበር የቻሉት ተቃውሞ ፍንጭ የሚሰጥ ይመስለኛል፡፡” በማለት ገልጾታል፡፡
በደራሲው ገለፃ፤ አቶ በረከት “ደፋር፣ ፀረ ጠባብነት” አቋም የሚያቀነቅኑ ታጋይ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአንዳንዶች ዘንድ የአማራውን ህዝብ ትግል የጋረዱ ጥላ ተደርገውም ይቆጠራሉ። ለዚህም ይመስላል አንዱ መኮንን በደም ፍላት፤ “በረከት ያንተን ግንባር በጥይት የሚመታ ጀግና ይጥፋ!” ብሎ በመናገሩ፣ ታጠቅ ጦር ሰፈር ለመታሰር የበቃው፡፡ ይህንንም እዚያው መጽሐፉ ላይ ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡  
ደራሲው  እነዚህን ጓዶቹን አምርሮ የሚወቅስበትም አጋጣሚ  አለ፡-  
“--የትግራይን ጠባብ ብሔርተኝነት ከአናቱ በመሰንጠቅ የሞሸርኳቸው ጓዶቼ፣ ቀኝ ኋላ ዞረው እዚያው ብሔርተኝነት ጉያ ገብተው የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም፣ የሕዝብ ፍጅት ውስጥ የገቡበትንና እየጨመረ የሄደ ፍጅታቸውን ሳስብ ነው አምርሬ ያለቀስኩት፡፡--”
ያሬድ ጥበቡ፤ እነዚህንና ሌሎች መሰል ሚዛናዊ ሀሳቦችን በመጽሐፉ አስፍሯል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከወጣትነት ዕድሜው ጀምሮ አምርሮ የተቃወመውንና ለትጥቅ ትግል በረሃ ገብቶ የተንከራተተበትን ደርግ እንኳ በጎ ጎን እንዳለው ከመግለጽ ወደ ኋላ አላለም፡፡ ለምሳሌ፡- ዶ/ር እሸቱ ጮሌና ዶ/ር ታዬ ሀገር ጥለው ሲሄዱ፣ ልዑካን ልኮ በማግባባት፣ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን በአዎንታዊነት ይጠቅሰዋል፡፡   
“ዶ/ር እሸቱ ጮሌና የህክምና ባለሞያ የነበሩት ዶ/ር ታዬ፤ አገር ጥለው በተሰደዱበት ወቅት ደርግ በአፋጣኝ መልዕክተኛ በመላክ ወደ አገራቸው እንዲመለሱና ያለ ፍርሃት በነፃነት እንዲኖሩ ሊያግባባቸው መቻሉ፣ በቀጣዮቹ ዓመታት በእሸቱ የተማሩ የኢኮኖሚክስ ምሩቃንና በዶ/ር ታዬ የታከሙ ሕሙማን፣ መቻቻልና ይቅር ባይነት ለሚሰጡት ጥቅም  ቋሚ ምስክሮች ናቸው፡፡--” (ገፅ 163)
የ“ወጥቼ አልወጣሁም” ደራሲ፣ አንዳንድ ቦታ ፈሪ የሚያስመስሉት ሀሳቦች ቢያንጸባርቅም፣ እኔም ሆንኩ ሚዛናዊነትን የሚያደንቁ ሰዎች ሁሉ ግን መፈራረጅንና መገዳደልን ለመቀነስ የሚተጋ ፖለቲከኛ መሆኑን እንድንረዳ አድርጎናል ብዬ አስባለሁ፡፡ እንደ ትንቢት ከተናገራቸው ጉዳዮች መካከል የተወሰኑት ግባቸውን የመቱለት ይመስላል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ  አየር ላይ ባክነው ቀርተውበታል፡፡ ለምሳሌ አቶ መለስ ስልጣን በያዙ በአሥር ዓመታቸው የሚወድቁ መስሎት፣ ደራሲው ብዙ ብሏል፡፡ ምክንያቱን መደርደር መንዛዛት ስለሚሆንብኝ አላሰፍረውም እንጂ የአዲስ አበባን ህዝብ፣ ሻዕቢያን፣ የመንግስት ፖሊሲን ወዘተ--- በመዘርዘር፣ የመለስ አገዛዝ ማብቂያው  መድረሱን ተንብዮ ነበር፡፡ ግን አልያዘለትም፡፡
ደራሲው ገርነትም ይታይበታል፡፡ ከሞላ ጎደል ባህርያቸውን ያጤነ ቢመስለንም፣ አቶ መለስን፣ ወደ ኋላ ተመልሶ  ድንገት “ዲሞክራት ይሁኑ!” በማለት እንደ ቤተሰብ ሊመክር ይፈልጋል፡፡ በዚህም ራሱ ደራሲው ትምክህት፣ ጠባብነት----እያለ  የገለጸውን የሟቹን ጠ/ሚኒስትር ሰብዕና አፍርሶት ቁጭ ይላል።
በእምነት ያለመፅናትና የፈራ ተባ ድምፀት ያነበብኩበት መጣጥፍም አለ፡፡ በገፅ 74 “የኢሕአዴግ ጣምራ ባህርያት ወዴት” የሚለው የተወሰነ ክፍል፣ አንዳች የስሜት መላላት ወይም ስጋት ያለው ይመስላል። በመሆኑም የደራሲው ፈርጣማ እውነትና ጣፋጭ ፍሰት ብዙም አይታይበትም፡፡
በተረፈ መጽሐፉ ከጥቂት የአርትኦት ችግሮች በስተቀር፣ ለዛ ባለው ቋንቋ የተፃፈና ማራኪ ፍሰት ያለው፣ የአካባቢ ገለፃዎቹ ሳይቀር ማራኪ ሆነው የቀረቡበት ነው፡፡ አልፎ አልፎ ከመጣጥፍነት ወደ መጽሐፍነት ሲመለሱ ሊቀየሩ የሚገባቸው አንዳንድ ዓ.ነገሮች አምልጠው የወጡበት ሁኔታ ግን አለ፡፡ ለምሳሌ፡- ገፅ 110 ላይ፤ “የኢሕአዴግ ጉባኤ በያዝነው ክረምት ወራት ውስጥ እንደሚካሄድ…” ይላል፡፡ ይህ ሀረግ ወደ መጽሐፍ ሲመለስ መስተካከል ነበረበት፤ ምክንያቱም እኛ የምናነብበው በዚያ ክረምት አይደለም፡፡ ጉባኤው የተካሄደበት ወቅት በሃላፊ ጊዜ መገለፅ ነበረበት፡፡        
መጽሐፉ በጥሩ አጻጻፍ፣ በለዛ የፈሰሰና ስሜትን ሰቅዞ የመያዝ አቅም ያለው ነው፡፡ ደራሲው በታሪኩ ሁነቶች ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆኑ፣ የማናውቃቸውን ሀቆች መዝዞ በማውጣት፣ በርካታ እውነቶችን ያስቃኘናል፡፡ በተለይ ላለፉት አርባና ሀምሳ ዓመታት አደባባይ ያላያቸውን ሀቆች ገልጦ በማሳየት ያስደምመናል፡፡ ለእኔ ሚዛናዊነቱና ለሰለጠነ  ፖለቲካ ያለው ቁርጠኝነትም በእጅጉ የሚያስደንቅ ነው፡፡  


Read 945 times