Sunday, 14 October 2018 00:00

የፀረ ሽብር ህግ “ያስፈልጋል አያስፈልግም?”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)


በጠቅላይ አቃቤ ህግ ሥር የተቋቋመው የፍትህ እና ህግ ማሻሻያ ም/ቤት ኮሚቴ ሰሞኑን በአዋጁ ላይ ያደረገውን ጥናት ውጤት ለውይይት አቅርቧል፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ተቋማትና የማህበረሰብ ኮሚቴዎች በፀረ ሽብር ህጉ ላይ የተወያዩ ሲሆን “የፀረ ሽብር ህግ ለኢትዮጵያ ያስፈልጋል አያስፈልግም” በሚለው ላይ ሰፊ ክርክርና ውይይት ተካሂዷል፡፡
አብዛኛው አስተያየት ሰጪ አገሪቱ ከምትገኝበት ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታ አንፃር፣ የፀረ ሽብር ህግ ያስፈልጋታል የሚለውን ሃሳብ ያንፀባረቀ ሲሆን ላለፉት 8 ዓመታት የተተገበረው የፀረ ሽብር ህግ ግን ለፖለቲካዊ ማጥቂያ ውሏል በሚል ክፉኛ ተተችቷል፡፡
የፍትህና የህግ ማሻሻያ ም/ቤት አባሉ፣ ጠበቃና የህግ አማካሪ አቶ አመሃ መኮንን ባቀረቡት ጥናት ላይም፤ በተለይ የተለየ አመለካከትና ሃሳብ ያላቸው፣ የያዙት ሃሳብ ለመንግስት ስጋት ነው ተብለው የሚገመቱ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች የነበረው የፀረ ሽብር ህግ እንደማጥቂያ መሳሪያ አገልግሏል ብሏል፡፡
በርካቶችም በዚህ ህግ ምክንያት ለሰብአዊ ጉስቁልና እና ጉዳት እንዲሁም ለህሊናዊና ሞራላዊ ጉዳት መዳረጋቸውን በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡
ለኢትዮጵያ “የፀረ ሽብር ህግ ያስፈልጋል አያስፈልግም” በሚለው ጉዳይ ላይ በተደረገው ውይይት እንደቀድሞ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ኢላማ የማያደርግ ነገር ግን ሀገሪቱን ከአለማቀፍና አካባቢያዊ የሽብር ስጋት የሚከላከል የፀረ ሽብር ህግ አስፈላጊ ነው የሚል ሃሳብ ተሰንዝሯል፡፡
በሌላ በኩል ጥቂት የማይባሉ ተሳታፊዎችም፤ በወንጀለኛ ህጉ የተቀመጡ የወንጀል መከላከል ህጎች ሽብርን ለመዋጋት በቂ ናቸው፤ ስለዚህ ተጨማሪ የፀረ ሽብር ህግ አያስፈልግም ሲሉ ሞግተዋል፡፡
የግራ ቀኙን ውይይትና የሃሳብ ክርክር ሲከታተሉ የነበሩት የኮሚቴው አባላትም የተንሸራሸሩትን ሃሳቦች በቀጣይ ለሚደረጉ ውይይቶችና ለአዲስ የፀረ ሽብር ህግ ማርቀቅ ሂደት በግብአትነት እንደሚጠቀሙበት ገልፀዋል፡፡  

Read 4958 times