Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 19 May 2012 10:23

አክራሪነትን ለመመከት፤ “ጨዋነት” በቂ አይደለም

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ፍቱኑ መድሃኒት፤ የሳይንስና የነፃነት አስተሳሰብ ነው

ነፃነትን ለሚሸረሽር መንግስት፤ አክራሪነት ፈተና ይሆንበታል

በሃይማኖት ዙሪያ የሚታየው የአገራችን መንፈስ፤ በሚያስገርም ፍጥነት ጠረኑና ቀለሙ እየተቀየረ መጥቷል - ባለፉት አምስት አመታት። የሃይማኖት ነገር እንግዳ እስኪሆንብን ድረስ፤ አይናችንና አፍንጫችን ስር፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለዋወጠ ያስደነግጠናል። ይሄ ሁሉ ሲሆን፤ አስተማማኝ መፍትሄ ጎልቶ አለመውጣቱ ነው በጣም አሳሳቢው ነገር።

በእርግጥ፤ ስብሰባዎች በየጊዜው ይካሄዳሉ፤ መግለጫዎች ይወጣሉ። የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች በየቦታው የጋራ ምክር ቤት ሲያቋቁሙና ሲነጋገሩ ይታያል። ነገር ግን፤ የሚያጠግብ መፍትሄ ሲያቀርቡ አልሰማሁም። በርካታ የሃይማኖት መፃህፍትን እየጠቀሱ፤ አክራሪነትን መንቀፍ እንደሚችሉ አልጠራጠርም። ነገር ግን፤ አክራሪዎችም ከየሃይማኖታቸው መፃህፍት ውስጥ ብዙ ጥቅሶችንና መከራከሪያዎችን መደርደር አያቅታቸውም። የሃይማኖት ክርክር መቼ እልባት አግኝቶ ያውቃል!

በሳይንስ ጥያቄዎች ላይ የሚፈጠር ክርክር፤ የጊዜ ጉዳይ እንጂ እልባት ላይ መድረሱ አይቀርም - የትኛውንም መከራከሪያ የምንዳኘው በተጨባጭ መረጃ ነውና። የሃይማነቶት ጥያቄ ግን፤ ዞሮ ዞሮ የእምነት ጉዳይ ነው። እናም በጥቅሶች ብዛት የሃይማኖት ክርክርን ወደ እልባት ማድረስ አይቻልም። በተለያዩ አገራት ውስጥ፤ በርካታ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች አክራሪነትን ለመመከት የሚቸገሩት በዚሁ ምክንያት ነው። በአገራችን እያየን ያለውም፣ ያንኑን ተመሳሳይ ፈተና ይመስለኛል - ቁልጭ ያለ መፍትሄ ያልተገኘለት ፈተና።

ብዙ ዜጎች፤ ይህንን ፈተና፤ በስጋትና በዝምታ አልያም በጨዋነትና በቁጥብነት ከመመልከት በስተቀር፤ አደገኛውን አዝማሚያ ለመከላከል የሚያስችል ሃሳብ ወይም ዘዴ አልያዙም። እየሞከሩ አይደለም ማለቴ አይደለም። የተለመዱ አባባሎችንና ንግግሮችን፤ ከሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና ከብዙ ዜጎች አንደበት ነጋ ጠባ እየሰማን አይደል?

በእርግጥ፤ “የሃይማኖት መከባበር ባህላችንኮ ለመላው አለም አርአያ ነው”፤ “አብሮ የመኖር ረዥም ታሪክ አለን” ... እና ሌሎች ተመሳሳይ አባባሎች፤ ምሳሌያዊ ትረካዎችና ገጠመኞች በተደጋጋሚ መወሳታቸው መጥፎ አይደለም። ቁጥብነትንና ጨዋነትን የሚያንፀባርቁ ናቸው። እውነትም፤ አገራችን ውስጥ በስፋት የሚታየው የጨዋነትና የቁጥብነት ልማድ፤ ሶሻሊዝምን፣ ዘረኝነትንና የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካን ለተወሰነ ጊዜ ለማለዘብ እንደሚያግዘን ሁሉ፤ የአክራሪነትን ግስጋሴ ለማዘግየትም ይረዳል።

ነገር ግን፤ ብዙዎቹ ዜጎች እንደዋነኛ መከታ የያዙት ይሄው የጨዋነት ልምድ፣ ብቻውን የሚያዛልቅ መፍትሄ አይደለም። የጨዋነት ልምድ፤ የደርግን ሶሻሊዝም ለማስቀረት እንዳልጠቀመን ሁሉ፤ ዘረኝነትንም ሆነ አክራሪነትን ለረዥም ጊዜ ሊገታልን አይችልም። እንዲያውም ቀስ በቀስ፤ በጠላትነት የሚያስፈርጅ እየሆነ ይመጣል። ጨዋ ለመሆን የሚሞክር ሰው ፤ “አድሃሪ፤ መሃል ሰፋሪ” ተብሎ በሶሻሊስቶቹ አፉ እንደሚዘጋ አይተናልል። ወይም “ፀረህዝብ፤ አድርባይ፤ በማንነቱ የማይኮራ” ተብሎ በዘረኞች ይወገዛል - አንገቱን እንዲደፋ። ወይም፤ “ከሃዲ፤ ፀረሃይማኖት፤ አረመኔ፤ እምነት የለሽ” ተብሎ በአክራሪዎች ይኮነናል - ወድቆ እንዲሰግድላቸው። የጨዋነት ልምድ አስተማማኝ መከላከያ ስላልሆነም ነው፤ በየጊዜው የአክራሪነት አዝማሚያ እየጎላ ሲመጣ የምናየው።

ነፃነትን ያጥላላ በአክራሪነት ይፈተናል

ብዙዎቹ ዜጎችና የሃይማኖት ተቋማት፤ አክራሪነትን መመከት ቀላል ባይሆንላቸው እንኳ፤ መንግስትስ አክራሪነትን ለመግታት ሁነኛ መፍትሄ አለው? በክስ፣ በስብሰባ፣ በስልጠና ወይም በሌላ መንገድ የሚያከናውናቸው ሙከራዎች መኖራቸው አይካድም። መንግስት፤ ከሃላፊነቱ ጋር የሚጣጣምና ድንበሩን ያልዘለለ ሁነኛ መፍትሄ ይዟል የሚያሰኝ ማረጋገጫ ግን፤ አላየሁም። በእርግጥ፤ “የሃይማኖት እኩልነት፤ የሃይማኖት ነፃነት፤ ህገመንግስት” በሚሉ ቃላት ዙሪያ የባለስልጣናት ንግግሮችን ሰምተናል። ነገር ግን፤ እነዚህ ቃላትና ሃሳቦች መሰረታዊ መፍትሄ አይደሉም። እስካሁን አክራሪነት ሲቀንስ አላየንማ። ሌላ አንድ ነጥብ እንጨምር።

“ሃይማኖት በመንግስት ላይ ጣልቃ አይገባም፤ መንግስትም በሃይማኖት ላይ ጣልቃ አይገባም” የሚለውን መርህ ተመልከቱ። ከሞላ ጎደል ትክክለኛ ሃሳብ (መርህ) ነው። ነገር ግን፤ “ለምንድነው ጣልቃ የማይገባው?” ለሚለው ጥያቄ የተሟላ ምላሽ መስጠትና ትክክለኛነቱን በፅኑ መሰረት ማረጋገጥ ካልቻልን፤ የያዝነው መርህ ያን ያህልም አያስኬደንም። ለምን?

አዎ፤ የእያንዳንዱን ግለሰብ ነፃነት ለማስከበርና የሰዎችን ግንኙነት ለመዳኘት የሚቋቋም መንግስት፤ በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመስርቶ መስራት ይኖርበታል። ስለዚህ፤ “እምነት” (faith) ላይ የተመሰረተ ሃይማኖት፤ የመንግስት ስራዎች ላይ ድርሻ ሊኖረው አይገባም። ተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሰረተ ምክንያታዊ ትንታኔን (ሎጂክን) ከመከተል ይልቅ፤ የሃይማኖት መፃህፍትን እያጣቀሰ የሚዳኝ መንግስት መኖር የለበትም።

በዚያው መጠን፤ የመንግስት ስራ፤ “የግለሰቦችን ነፃነት ለማስከበር የሰዎችን ግንኙነት መዳኘት” እንጂ፤ በግለሰብ ህይወት ውስጥ ጣልቃ እየገባ አድራጊ ፈጣሪ መሆን አይደለም። ማንም ሰው፤ በጉልበት የሌሎችን ሰዎች ንብረት ለመንጠቅ ወይም ሃሳብና እምነታቸውን ለመቆጣጠር እስካልሞከረ ድረስ፤ በራሱ የግል ንብርትና እምነት ላይ ብቸኛው ወሳኝ መሆን ይገባዋል። ስለዚህ፤ መንግስት በግለሰቦች ንብረትም ሆነ ሃይማኖት ውስጥ፤ በአጠቃላይ በግል ህይወት ውስጥ ጣልቃ የመግባት ስልጣን መያዝ የለበትም።

እውነትም እንዲህ መሰረት አስይዘን ስንተነትነው፤ “መንግስትና ሃይማኖት መነጣጠል አለባቸው” የሚለው መርህ ትክክለኛ ነው። “መንግስትና ቢዝነስ መነጣጠል አለባቸው” ከሚለው መርህ ጋርም ይመሳሰላሉ። ለምን ቢባል፤ “የግለሰብ ነፃነት መከበር አለበት” ከሚለው መሰረታዊ ሃሳብ የሚመነጩ መርሆች ናቸው። በዚህ መንገድ፤ መርሆቹን ከነፅኑ መሰረታቸው ስንይዛቸው፤ የሃሳብ ጥንካሬና የተግባር ውጤታማነት ይኖረናል። በተቃራኒው፤ ስረመሰረታቸውን ከናድነውና፤ በተናጠል አንዱን መርህ ጥለን ሌላኛውን ብቻ በማንጠልጠል ለመጓዝ ከሞከርን፤ መርሆቹ ይልፈሰፈሳሉ።

እስቲ አስቡት፤ በአንድ በኩል “መንግስት፣ የግለሰቦች ሃይማኖት ላይ ጣልቃ አይገባም” እየተባለ ይነገራል። በሌላ በኩል ግን “ድህነትን ለመዋጋትና ለህዝብ ጥቅም” በሚል ሰበብ፤ መንግስት በግለሰቦች ምርትና ንብረት ላይ ጣልቃ እየገባ አዛዥ ናዛዥ ሲሆን ታያላችሁ። አሳዛኙ ነገር፤ ብዙዎቹ ምሁራን፤ ብዙዎቹ ፓርቲዎች፤ ብዙዎቹ ዜጎች፤ ይህንን የኢኮኖሚ ጣልቃ ገብነት ይደግፋሉ - በሃሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ጭምር።

ያለፉት አምስት አመታት፤ የቢዝነስና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የመንግስት ድርሻና ቁጥጥር እየተስፋፋ መምጣቱኮ ሌላ ትርጉም የለውም። በግለሰቦች ስራ፣ ምርትና ንብረት ላይ የመንግስትን ጣልቃ ገብነት ለማስፋፋት የተደረገ ዘመቻ ነው። ከዘመቻው ጋር፤ “የግለሰብ ነፃነት” የተሰኘውን መሰረታዊ ሃሳብ፤ “የኒዮሊበራል አስተሳሰብ ነው” እየተባለ ሲንቋሸሽ ከርሟል። መዘዙ በዚህ አያቆምም።

በተመሳሳይ መንገድ፤ “ፅድቅን ለማስፋፋት፣ የህዝብን ስነምግባርና እምነት ለማጎልበት” በሚል ሰበብ፤ “መንግስት በሃይማኖት መመራት አለበት፤ መንግስትም በሃይማኖት ላይ ጣልቃ መግባት ይኖርበታል” የሚል የሃይማኖት አክራሪ ይመጣል። “መንግስትና ሃይማኖት የሚነጣጠሉበት ምክንያት የለም” የሚል የአክራሪ ሙግት ሲበረታ፤ መንግስት ምን አይነት ምላሽ ሊኖረው ይችላል? “የግለሰብ ነፃነትን ለማስከበር” በማለት ከመሰረታዊ ሃሳብ ተነስተው እንዳይከራከሩ፤ “የግለሰብ ነፃነትን” ሲሸረሽሩና ሲያንቋሽሹ ቆይተዋል።

ለነገሩ፤ ለወትሮውም በአገራችን ገና ጅምር ለጋ የነበረው የግለሰብ ነፃነት፤ ባለፉት አመታት እንዲዳከም የተደረገው በኢኮኖሚው መስክ ብቻ አይደለም። የፓርቲዎች እንቅስቃሴ ደብዝዟል። የምሁራን ትንታኔና ትችት ድምፁ እየጠፋ መጥቷል። ነፃ ፕሬስ እንዲዳከም ተደርጓል። የዜጎች ሃሳቦችና አስተያየቶች ከአደባባይ ጠፍተዋል - ከ97 ዓ.ም በፊት እንደ”ኖርማል” እየተለመደ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ፤ ባለፉት አምስት አመታት ብርቅ ሆኗል። እነዚህ ሁሉ... ዋና ስረ መሰረታቸው፤ የግለሰብ ነፃነት ነው - በየመስኩ ሲሸረሸርና ሲንቋሸሽ የከረመ መሰረታዊ ሃሳብ።

መዘዙን አሁን እያየነው ነው። ከግለሰብ ነፃነት ውጭ፤ የሃይማኖት አክራሪነትን ለመከላከልና ለመግታት የሚያስችል አስተማማኝ መንገድ የለም። እስካሁን፤ በመንግስት ጥረት የተገኘው ውጤት፤ ተስፋ ሰጪ ለመሆን ያልቻለውም በዚህ ምክንያት ይመስለኛል። በዊኪሊክስ ከተሰራጩት ሚስጥራዊ ሰነዶች መካከል፤ አንዳንዶቹ ይህንን እውነታ የሚጠቁሙ ናቸው። ገዢውን ፓርቲ የሚደግፉና የሚተቹ አስር ምሁራን፣ በተለያዩ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የሰጡትን አስተያየት በአምስት ሰነዶች ተዘርዝሮ ቀርቧል።

ምሁራኑ በበርካታ ጉዳዮች ላይ መንግስትን በመደገፍ ወይም በመተቸት የተለያየ አስተያየት ቢሰጡም፤ በአንድ ጉዳይ ላይ ግን ሁሉም ይስማማሉ። የሃይማኖት አክራሪነት፤ አገሪቱን ለአደጋ የሚዳርግ ከባድ ፈተና እየሆነ መምጣቱን የገለፁት ምሁራን፤ መንግስት አደገኛውን አዝማሚያ ለመመከት ውጤታማ ስራ አከናውኗል ብለው እንደማያምኑ ጠቅሰዋል። የዚህ ፓለቲካዊ ችግር መፍትሄ፤ ባለፉት አመታት የተፈፀመውን ስህተት ማረም ይመስለኛል። የግለሰብ ነፃነትን ከሌሎች የፖለቲካ መርሆች ሁሉ በማስቀደም ከፍተኛ ክብር ሊኖረው እንደሚገባ መገንዘብ ያስፈልጋል ማለቴ ነው።

መፍትሄው ግን ይህ ብቻ አይደለም። ምናልባት፤ “አክራሪነት” የተሰኘውን ቃል፤ በደንብ መመርመር ሳይኖርብን አይቀርም። እንዲሁ ስለተለመደና ስለተደጋገመ ቃሉን እንጠቀማለን እንጂ፤ ትርጉሙ በግልፅ ንጥር ብሎ ሲተነተን አላጋጠመኝም። እስቲ እንጀምረው። ምንድነው አክራሪነት? አንዳች ሃሳብን ወይም እምነትን አጥብቆ መያዝ ነው አክራሪነት?

 

ጭፍንነት፤ አክራሪነት፤ አሸባሪነት

“2 እና 2 ሲደመሩ አራት ይሆናሉ” ብሎ የሚያስብ ሰው፤ ሁል ጊዜ በዚሁ ሃሳብ ቢፀና፤ “አክራሪ” ብለን እናወግዘዋለን? በሃሳብ መፅናት የሚያስወግዝ ከሆነ፤ “አክራሪ” የሚለው ቃል ትርጉም ያጣል። አለበለዚያኮ፤ ጠላትነታችን ከእውቀትና ከሃሳብ፤ ከሳይንስና ከሎጂክ ጋር፤ በአጠቃላይ ከሰው ተፈጥሮና ከአእምሮ ጋር ይሆናል።

እንግዲህ፤ ሰውዬው በሃሳቡ የፀናው፤ በዘፈቀደ አይደለም። የሁለትና የሁለት ድምር አራት እንደሆነ፤ ደጋግሞ በመፈተሽ  በተጨባጭ ማስረጃ (በሳይንሳዊ ዘዴ፤ በሎጂክ) አረጋግጧል። ስህተት መሆኑን የሚጠቁም አንድም ተጨባጭ ማስረጃ ወይም መረጃ አልቀረበም። ታዲያ፤ በሃሳቡ መፅናት አይገባውም?

ላለመፅናት የሚፈልግ ሰው ይኖራል። አንዳንዴ ሃሳቡን ያለዝባል - “ምን ይታወቃል! ድምራቸው አራት ላይሆን ይችላል” በማለት። ወይም ደግሞ፤ “ድምራቸው እንደ አገሩ ተጨባጭ ሁኔታና እንደ ህዝቡ ባህል ሊለያይ ይችላል” በማለት ይናገራል - አክራሪ ላለመባል። እንዲህ አይነቱ ፍጡር፤ እንደ ሉሲና አርዲ በሚሊዮን አመታት ሰው ለመሆን ይችል እንደሆነ እንጂ፤ ገና እንደ ሰው የሚያስቆጥር የአእምሮ ብቃት የለውም ማለት ነው። አልያም፤ እንደ በቀቀን ከሰው የሰማውን ሁሉ ከመስተጋባት የዘለለ አንጎል የለውም። ሰው እስከሆነ ድረስ ግን፤ በማስረጃ ያረጋገጠውን እውነት ፈፅሞ ሳይክድ፤ ሁሌም በሃሳቡ መፅናት ይኖርበታል። አክራሪነት፤ በትክክለኛ ሃሳብ መፅናት ማለት አይደለም።

እዚህ ላይ፤ “የሁለትና የሁለት ድምር፤ አምስት ነው” የሚል ሃሳብ ይዞ የሚፀና ሰውስ? ምኑ ይገርማል! አዋቂ ሆኖ የሚወለድና ሳይሳሳት የሚኖር ሰው የለም። የማወቅ ፈቃደኝነት ይኑረው እንጂ፤ ቢሳሳት ችግር የለውም። ለጊዜው፤ ትክክለኛ ሃሳብ የያዘ መስሎት በሃሳቡ ፀንቷል። ነገ ከነገወዲያ፤ በተጨባጭ ማስረጃ ስህተቱን ሲመለከትና እውነታውን ሲገነዘብ ሃሳቡን ያስተካክላል። አክራሪነት፤ የተሳሳተ ሃሳብ ይዞ መፅናት ማለት አይደለም።

ስህተቱን ለማስተካከል የማይፈቅድ ሰው ቢኖርስ? ተጨባጭ ማስረጃ፤ ሳይንሳዊ ዘዴ፤ ሎጂክ ... ከአጠገቡ እንዲደርሱ የማይፈቅድ፤ ጭራሽ የሚጠላ ቢሆንስ? የተሳሳተ ሃሳብ እንደያዘ፤ “በቃ፤ እምነቴ ነው፤ እምነቴ ነው” ብሎ ቢፀናስ? ይሄማ፣ “ፅናት ሳይሆን ድርቅና ነው” እንል ይሆናል። ግን ከድርቅና ይብሳል። ጭፍንነት (Irrationality) ነው።

ለማየት ካለመቻል የሚመጣ ችግር ሳይሆን፤ ለማየት ካለመፈለግ የሚመነጭ ስለሆነ፤ በፈቃደኝነት የራስን አይን እንደማጥፋት ሊቆጠር ይችላል - አእምሮን ሽባ የሚያደርግ ጭፍንነት። ይሄ መጥፎ ነው። እንዲያውም “የመጥፎዎች ሁሉ እናት” ብንለው አይበዛበትም - የሃጥያቶች ሁሉ ስር፤ ጭፍንነት ነውና። ቢሆንም ግን፤ ጭፍንነት በቀጥታ አክራሪነት ይሆናል ማለት አይደለም። የአክራሪነት መነሻ ጭፍንነት ነው። ግን፤ ወደ አክራሪነት ደረጃ የማይደርስ ጭፍንነትም አለ። ልዩነታቸውን እንፈትሸው። በሳይንሳዊ ዘዴ የተረጋገጡትን እውነቶች ክዶ፤ የጥንቆላ፣ የምትሃት፣ የቡዳ እና የመሳሰሉ ተረቶችን እንደ እምነት መያዝ ጭፍንነት ነው - እምነቱ በግሉ እስከተያዘ ድረስ አክራሪነት አይደለም። ወንድምና እህት ሳይቀሩ፤ በሃሳብ፣ በባህርይና በዝንባሌ እንደሚለያዩ በግልፅ የሚታይ እውነት ሆኖ ሳለ፤ ሰዎችን በብሄር ብሄረሰብ ተወላጅነት ለማቧደንና ለመፈረጅ መሞከር... ጭፍንነት ነው። ዘረኝነትን ወደ መስበክ እስካልተሸጋገረ ድረስ፤ “አክራሪ” አይባልም።

እያንዳንዱ ሰው የግል አእምሮ እንዳለው በግልፅ እየታወቀ፤ የሰዎች አስተሳሰብ በሃብት መጠናቸው እንደሚወሰን ማመን፤ ጭፍንነትን መምረጥ ነው። የእያንዳንዱ ሰው ብቃትና ታታሪነት እንደየሰዉ ምርጫ የሚለያይ ሆኖ ሳለ፤ ሁሉም ሰው እኩል ሃብት እንዲኖረው በመመኘት በሶሻሊዝም ቲዎሪ ማመን፤ ጭፍንነት ነው። ተራራውንና ሸለቆውን፤ አፈሩንና ወንዙን ሳልነካ፤ አካባቢዬን በሙሉ እንደድሮው ለመጠበቅ መስዋእት መክፈል ያስፈልጋል የሚል የአካባቢ ጥበቃ እምነትም ጭፍንነት ነው - የሰው ህይወት የሚሻሻለው አካባቢውን በመለወጥ እንደሆነ በግልፅ ይታያልና። “የአእምሮ ህመምተኞች ጋኔን ይዟቸዋል” ወይም “ሴቶች አደባባይ መውጣት የለባቸውም” የሚል የሃይማኖት እምነት ጭፍንነት ነው።

ጭፍንነት፤ እንዴት አክራሪነት ይሆናል የሚለውን ጥያቄ ገና በግልፅ አልመለስነው - በመጠኑ ብንነካካውም።  አክራሪነት በጥቅሉ ሲታይ፤ ከበርካታ የጭፍንነት አይነቶች መካከል አንዱ ነው ማለት ይቻላል። “አፈሩንና ዛፉን ሳልነካ፤ እንደእንሰሳ ዋሻ ውስጥ መኖር አለብኝ” የሚል ሰው ጭፍን ነው። ከዚህ አልፎ፤ “ሰዎች ሁሉ እንደኔ ዋሻ ውስጥ መኖር ይገባቸዋል” እያለ የሚሰብክ ወይም የሃይል ማመንጫ ግድቦችን እየተቃወመ ቅስቀሳ የሚያካሂድ ከሆነ ፤ “አክራሪ” እንለዋለን - አክራሪ ጭፍንነት የተጠናወተው።

ሳይንሳዊ ህክምና አልፈልግም ከሚል ጭፍንነት ተነስቶ፤ “የሳይንሳዊ ህክም ለማናችሁም አይበጅም” ብሎ መስበክም አክራሪ ጭፍንነት ነው። በሰው ንብረት የመቋመጥ ጭፍንነት ላይ፤ እንደ ሶሻሊስቶች ቅናትንና ምቀኝነትን የሚያውጅ ሰው፤ አክራሪ ጭፍንነት ተጠናውቶታል። “ኢትዮጵያ ትቅደም” በሚል የፋሺዝም መፈክር ወይም በብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ ከማመን አልፎ መስበክንም ከጨመረበት፤ በአክራሪ ጭፍንነት ውስጥ ተዘፍቋል። “በቃ፤ እምነቴ ነው፤ እምነቴ ነው” ከሚል ጭፍንነት ተሻግሮ፤ ጭፍንነቱን የሚሰብክና የኔን እምነት ተከተሉ የሚል ሰውም፤ አክራሪ ጭፍንነት ውስጥ ገብቷል።

በአጭሩ፤ ለራስ በግል ጨለማን መምረጥ ጭፍንነት ነው፤ ሌሎችም ወደ ጨለማው እንዲገቡ መቀስቀስና መወትወት ደግሞ አክራሪ ጭፍንነት ይሆናል። ሁለቱም ደረጃቸው ቢለያይም፤ ሊነቀፉና ልንርቃቸው የሚገቡ መጥፎ ነገሮች ናቸው። ራስን ከጭፍንነት ማራቅ ያስፈልጋል - ሳይንሳዊ አስተሳሰብን በመምረጥ። የጭፍንነት ሰበካዎችን (አክራሪነትን) መንቀፍ ይገባናል - ለሳይንሳዊ አስተሳሰብ በፅናት በመቆም። የመጀመሪያው ቁም ነገር ይሄ ነው።

እንዲያም ሆኖ፤ ጭፍንነትና አክራሪ፤ ሁሌም ወንጀል ይሆናሉ ማለት አይደለም። ሶሻሊዝምን መስበክ ወይም ሳይንስን መብጠልጠል፤ ክፉ ተግባር ቢሆንም ወንጀል አይደለም - መብት ነው። የራስን ቤት አለማፅዳት ወይም የራስን የንግድ መደብር እስከ ረፋዱ አራት ሰአት ድረስ አለመክፈት፤ በዘፈቀደ ያለጥንቃቄ ወሲብ ለመፈፀም መፍቀድ ወይም ጠንቋይ ቤት መመላለስ... ልንርቃቸው የሚገቡ የጭፍንነት ድርጊቶች ቢሆኑም፤ ወንጀል አይደሉም። ዝርክርክነትንና ስንፍናን፤ ወይም መንዘላዘልንና ጥንቆላን መስበክም፤ ልንነቅፋቸው የሚገቡ የአክራሪነት ድርጊቶች ቢሆኑም፤ ወንጀል አይደሉም። ጭፍንነትና በአክራሪነት ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ ታክሎበት “በግድ እኔ የምሰብካችሁን ተከተሉ” ማለት ሲመጣ ግን፤  የጭፍንነት ቅስቀሳው ወደ ጡንቻና  ወደ ሃይል ጥቃት ተሸጋግሮ “በግድ እኔ የማዝዛችሁን አድርጉ” ማለት ሲጀመር ግን፤ ነገርዬው ያፈጠጠ ያገጠጠ የወንጀል ድርጊት ይሆናል። አምባገነንነትና አሸባሪነት እንዲህ ከጭፍንነት የሚመነጩ፤ ከአክራሪነት የሚወለዱ የወንጀል ድርጊቶች ናቸው - የግለሰብ ነፃነትን የሚጥሱ ክፉ የወንጀል ድርጊቶች።ምን ለማለት ነው የፈለግኩት? አምባገነንነትንና አሸባሪነትን ለመከላከል፤ በቅድሚያ አክራሪነትን የመንቀፍ ብቃት ሊኖረን ይገባል። አክራሪነትን እንደ ፅድቅ እያየን፤ አምባገነንነትንና አሸባሪነትን መከላከል አንችልም። አክራሪነትን ለመንቀፍ ደግሞ፤ በቅድሚያ ከስረ መሰረቱ ጭፍንነትን በመራቅ ሳይንሳዊ አስተሳሰብን መምረጥ ይኖርብናል። ጭፍንነትን ታቅፈን እያጨበጨብንለት፤ አክራሪነትን መመከት አንችልም። እናም፤ አሁን በብዙ ዜጎችና ምሁራን፤ በብዙ ፖለቲከኞችና ተቋማት ላይ እንደምናየው፤ አክራሪነትን መመከትና አሸባሪነትን መከላከል፤ ከባድ ፈተና እየሆነብን ወደ መጥፎ አደጋ እናመራለን።

 

 

Read 3980 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 10:26