Saturday, 13 October 2018 10:44

“የላሊበላ ቅርስ ጥገና በ3 ዓመት ውስጥ ይካሄዳል”

Written by  አቶ ገዛኸኝ አባተ (የባህልና ቱሪዝም ሚ/ር ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ)
Rate this item
(4 votes)

• ቅርሱ የዓለም ቅርስ ስለሆነ መንግስት እንደፈቀደ ማድረግ አይችልም
• 300 ሚሊዮን ብር በአንድ ጊዜ ይገኛል ማለት ይከብዳል
• ቤተ ክርስቲያን በራሷ መንገድ መንቀሳቀስ ትችላለች
            ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ላሊበላን  ለመታደግ ምን ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው?
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ካለፈው ዓመት ጀምሮ ችግሩን በባለሙያዎች የማስጠናት ስራዎች ተሰርተዋል። ይሄ ቅርስ የሚጠገንበትና ዘላቂ መፍትሄ የሚገኝበት ሁኔታ መፍጠር ይገባል የሚል አቅጣጫ ተቀምጦ ወደ ተግባር እየተገባ ነው፡፡ ጉዳቱን ለመከላከል የተሰራው መጠለያ፣ ሰው ሰራሽ በሆነ መንገድ ቢፈርስ፣ ቅርሱን ድጋሚ ልናገኘው ስለማንችል፣መጠለያውን የሰሩትን ሰዎች በማግኘት የሚነሳበትን ሁኔታና አግባብ በጥናት እንዲቀርብ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ቅርሱ የዓለም ቅርስ ስለሆነ መንግስት እንደፈቀደ ማድረግ አይችልም። ዩኔስኮ ማወቅ ስላለበት መጥተው ተመልክተዋል፡፡ መጠለያውን የሚያነሳው አካልም መጥቶ አይቷል፡፡ መጠለያውን ማንሳት ቀላል ነው፡፡ መጀመሪያ ቅርሱ መጠገን አለበት፡፡ አዲስ የጥገና ዘዴም ስለተገኘ ቅርሱን ጠግኖ መጠለያውን ማንሳት ይቻላል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰናል፡፡ ስለዚህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው ሁሉም ባለድርሻዎች ጋር፣ ቤተ ክርስቲያኗንና አስተዳደሩን ጨምሮ በጉዳዩ ላይ ውይይት አድርገናል፡፡ ለቅርስ ጥገና በአጠቃላይ ከ300 ሚሊዮን ያላነሰ ብር እንደሚያስፈልግ፣ ይሄንንም በ3 ዓመት ጊዜ ውስጥ በሂደት ለማከናወን ተነጋግረናል። በመጀመሪያ ጥገና መደረግ አለበት በሚለው ላይም ተነጋግረናል፡፡ ማንኛውም አካል፣ አለኝ የሚለውን ገንዘብ ይዞ መጥቶ ስራው እንዲሰራ ተስማምተናል፡፡
ጥያቄው ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ፣ በጀት ተበጅቶ፣ በአጭር ጊዜ ይሰራ የሚል ነው?
ነገሩ በመንግስት በጀት ብቻ ይሰራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ 300 ሚሊዮን ብር በአንድ ጊዜ ይገኛል ማለትም ይከብዳል፡፡
ቴሌቶን ቢዘጋጅ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ቢዘረጋ --- የሚል ሃሳብ ይቀርባል፡፡ ይሄን መንግስት አላጤነውም?
ይሄን በተመለከተም በወቅቱ ምክክር ተደርጓል፡፡ እንደውም እኛ ይሄን ያህል ብር አምጡ ብለን አናዝም፤ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኗ አለኝ የምትለውን አምጡ፤እኛ ግን አናዛችሁም ነው ያልናቸው፡፡ ደብዳቤ ፃፉልንና ምዕመኑን ብንጠይቅ ይሰጠናል ብለውን ነበር፤ አሁንም ይሄን ያህል ብር አምጡ ማለት አንችልም የሚል ምላሽ ነው የሰጠናቸው፡፡ ቤተ ክህነቱ በራሱ መንገድ ማሰባሰብ ይችላል፡፡ ባለቤትነቱ ለሁላችንም ነው፡፡ እናንተም የቻላችሁትን አሰባስቡና አምጡ ብለናቸዋል። ገንዘብ ማሰባሰቡን ደግሞ በራሳቸው መንገድ ማስኬድ ይችላሉ፤ ነገር ግን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር “ይሄን ያህል ገንዘብ አምጡ ወይም ይጠበቅባችኋል” ማለት አይችልም፡፡ ለምሳሌ፡- የአማራ ብሔራዊ ክልል ማንንም ሳይጠብቅ ለቅርስ ማስጠበቅና ጥገና የሚውል የባንክ አካውንት ከፍቷል፡፡ እንዲህ ማድረግ ይቻላል፡፡
ቤተ ክህነት ብቻ ሳትሆን አየር መንገድ፣ ሆቴሎች፣ የቱሪዝም ድርጅቶች ማዋጣት የለባቸውም? የእነሱ ድርሻስ ምን ድረስ ነው? እነዚህን አካላት የሚያስተባብር አንድ አካል ተፈጥሮ ለምን መዋጮው አይሰባሰብም?
ይሄ ሃሳብ ቀርቧል፤ ውይይቱም ተደርጎበታል፤ ነገር ግን መንግስት የራሱን በጀት ይዞ ስራውን ያስጀምራል፤ ሌላውን የማስገደድ አቅጣጫ አልተቀመጠም፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገንዘብ የማሰባሰብ ስልጣን የለውም፤ መንግስት በአንድ ጊዜ ማሰባሰብ ይፈፀም የሚለው ውይይት ተደርጎበት እስኪወሰን ድረስ ግን እጃችን ላይ ባለው ገንዘብ እንስራ ብለን ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው፡፡ በዚያው ልክ የህዝብ ገንዘብ ያለ አግባብ እንዳይሰበሰብም መንግስት ኃላፊነት አለበት፡፡ ላሊበላ ተጎድቷልና ገንዘብ አምጡ የሚሉ አግባብነት የሌላቸው እንቅስቃሴዎች መደረግ የለባቸውም፤ስለዚህ የህግ አግባብነት ያለው ተቋም ተቋቁሞ፣ በምን መንገድ ይሰራ በሚለው ላይ መንግስት አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡  
ቤተ ክርስቲያኒቱ በራሷ መንገድ ገንዘብ ማሰባሰብ ትችላለች ማለት ነው?
አዎ ከምዕመናን በተለያየ መንገድ ታሰባስብ የለም እንዴ? ከራሷም ወጪ ማድረግ ትችላለች፡፡ መንግስት ትልቁን ድርሻ እመድባለሁ ብሎ ተነስቷል። ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በራሷ መንገድ መንቀሳቀስ ትችላለች፡፡ የጋራ መዋጮው የተፈለገውን ሥራ ሊያሳካ  ይችላል፡፡ ባለሙያዎችም፤300 ሚሊዮን ብር በአንድ ጀምበር ተገኝቶ ስራው በአንድ ጀንበር የሚሰራ አይደለም፤ በሂደት ምዕራፎች ስላሉት በዚያ አግባብ ይሰራ ነው የሚሉት፡፡ በአንድ ጊዜ 300 ሚሊዮን ብር ይመደብ የሚለው ብዙም አያስኬድም፡፡ ቤተ ክህነት ግን ማንኛውንም ቤተ ክርስቲያን ለመስራት እንደምትሰበስበው ከምዕመናን ማሰባሰብ ትችላለች። የቤተ ክርስቲያኒቱ ህግና ስርአት የማይከለክል ከሆነ ትችላለች፡፡
መቼ ነው ጥገናው የሚጀመረው?
ዘንድሮ የተለያየ ሥራ ይሰራል፡፡ የተለያዩ የሙያ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ 20 ሚሊዮን ብር ተመድቧል፤ ስራውን ማስጀመር ይችላል፡፡ በሂደት ባለድርሻዎች የሚያመጡት ገንዘብ ደግሞ ታክሎበት ስራው ይሰራል፡፡
መንግስት ለቅርሱ ተገቢውን ትኩረት አልሰጠም የሚል ወቀሳ ይሰነዘራል---
እኔ ይሄን አልቀበለውም፡፡ የላሊበላ ጉዳይ የተጠናው ባለፈው ዓመት ነው፡፡ ጥናቱን ይፋ ያደረገውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ነው፡፡ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የእንቅስቃሴ አጀንዳ ቀምቶ መውቀሱ ብዙም አያስኬድም፡፡
እርግጥ ነው በሀገሪቱ ውስጥ የነበሩት አንዳንድ ሁኔታዎች፣ መንግስት ተረጋግቶ አቅጣጫ እንዳይሰጥበት አድርገዋል፡፡ ከለውጡ በኋላ ነው አሁን በአግባቡ ስራ መስራት የተጀመረው፡፡ አዳዲሶቹ ሚኒስትሮች ስራቸውን ሲጀምሩ፤ ቁጥር አንድ ስራችን፣ ላሊበላን መታደግ ነው ብለው ነው የጀመሩት፡፡ የመጀመሪያ ስራቸው ያደረጉትም የላሊበላን ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ስራው በሰፊው የሚሰራው። መንግስት ትኩረት ሰጥቶታል፤ አሁንም ይሰጠዋል። የዩኔስኮ ሰዎች መጥተው የተወያየነው ሐምሌ ወር ላይ ነው፡፡ ከእነሱ ጋር ገና ተመካክረን መጨረሳችን ነው፡፡ ትኩረት ያስፈልጋል፣ አደጋ ላይ ነው የሚለው ትክክል ነው፡፡ አደጋ ላይ መሆኑን አስጠንተን ይፋ ያደረግነውም እኛው ነን፡፡
በሦስት አመት ጊዜ ውስጥ ይጠገናል ነው ያሉት፡፡ ሦስት ዓመት የመቆየት እድል አለው?
ባለሙያዎቹ፤ መጠለያው እስከ 20 ዓመት መቆየት ይችላል ተብሎ የተሰራ ነው ብለውናል፡፡ በስህተት ለ5 ዓመት ታስቦ የተሰራ ነው ተብሎ ነበር፤ ይሄ ስህተት ነው። የመጠለያው ጉዳይ ጊዜ ይሰጣል፡፡ ይሄ በባለሙያዎቹ የተረጋገጠ ነው፡፡ ስለዚህ በሦስት ዓመት ውስጥ ቢሰራ ችግር የለውም፡፡ ገንዘቡ በአንድ ጊዜ ተገኝቶ ወደ ስራ ቢገባም፣ በሦስት ዓመት ውስጥ ቢሰራም ችግር የለውም፡፡ ጉዳዩ እንቅልፍ የሚነሳ እንደመሆኑ፣ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡  

Read 5596 times