Saturday, 13 October 2018 10:24

የአፄ ምኒልክ የክተት አዋጅ 123ኛ ዓመት ትላንት ተዘከረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  6ኛው ዙር የጉዞ አድዋ ተጓዦች ምዝገባ ትላንት ተጀምሯል

    ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ለሰራዊታቸው የክተት አዋጅ ያወጁበት 123ኛ አመት፣ ትላንት ምሽት በተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች የተዘከረ ሲሆን 6ኛው ዙር ጉዞ አድዋ ምዝገባም ተጀምሯል፡፡ አፄ ምኒልክ ፋሽስት ጣሊያንን ለመዋጋት ለሰራዊታቸው የክተት አዋጅ ያወጁትና ሁሉም ሰራዊት ከያለበት ተሰብስቦ ወደ አድዋ ጉዞ የጀመረው የዛሬ 123 ዓመት፣ ጥቅምት 2 ሲሆን  ይህንን ቀን ለመዘከርም ፕሮግራሙ ጥቅምት 2 መዘጋጀቱን፣ ከጉዞ አድዋ መስራቾች አንዱ የሆነው፣ የፊልም ባለሙያ ያሬድ ሹመቴ ተናግሯል፡፡
በምሽቱ ዝግጅት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፣ በክተት አዋጁ ዙሪያ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን ዜማ ነጋሪት የሙዚቃ ቡድን፣ የተለያዩ ሙዚቃዎችን ለታዳሚው አቅርቧል፡፡ በተጨማሪም፤ ግጥም፣ ፉከራ፣ ሽለላና የተለያዩ ስነ ፅሑፎች ቀርበዋል፡፡ “የሚኒሊክ ዜና መዋዕል” (ዘ ክሮኒክል ኦፍ ኢምፔሪያል ሚኒልክ ዘ ሰከንድ” አሳታሚ ፀሐይ አሳታሚ፣ በሁለት ዳጎስ ያሉ እትሞች፣ የአምስት የጉዞ አድዋ ተጓዦች ፊርማ ያረፈበትን መፅሐፍ ለዩኒቨርሲቲዎች በነፃ ማስረከቡንም ያሬድ ሹመቴ ጨምሮ ገልጿል፡፡
በትላንትናው ዕለት 6ኛው ዙር የጉዞ አድዋ ተጓዦች ምዝገባ የተጀመረ ሲሆን እስከ ህዳር ወር መጨረሻ ምዝገባው እንደሚቀጥልም ታውቋል፡፡


Read 2220 times