Saturday, 13 October 2018 09:17

የፖለቲካ ድርጅቶች ምዝገባ አዋጅን ለማሻሻል ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ ያስፈልጋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

      የምርጫ ህጉን በተመለከተ የማሻሻያ ሃሳቦችን ያቀረበው ከፓርቲዎች የተውጣጣው የምርጫ ጉዳዮች ማሻሻያ ሃሳቦች አቅራቢ ኮሚቴ፤ የፖለቲካ ድርጅቶች ምዝገባ አዋጅን ለማሻሻል ህገ
መንግስታዊ ማሻሻያ ያስፈልጋል አለ፡፡ ኮሚቴው በፖለቲካ ድርጅቶች ምዝገባ አዋጅ እና በፓርቲዎች የስነ ምግባር አዋጅ ላይ ሲያካሂድ የነበረውን ማሻሻያ አጠናቆ ለፓርቲዎች ውይይት ዝግጁ ማድረጉን የኮሚቴው ፀሐፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ በቅርቡ ወደ ሀገር ውስጥ የተመለሱ የፖለቲካ ድርጅቶች አብዛኛው አመራሮቻቸው ከዜግነት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ምዝገባ ማከናወን እንዳልቻሉ ባለፈው ሳምንት ለአዲስ አድማስ መግለፃቸው የሚታወስ ሲሆን የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ማሻሻያ ሀሳብ አቅራቢ ኮሚቴውም፤ በጉዳዩ ላይ ውይይት ማድረጉ ተገልጿል፡፡
በጉዳዩ ላይ ለውይይት የሚቀርቡ የተለያዩ አማራጮች መቅረባቸውን የጠቆሙት አቶ ዋሲሁን፤ ኢትዮጵያዊ ባልሆኑ ግለሰቦች የተቋቋሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዴት ይስተናገዱ የሚለው
ራሱን ችሎ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው በጥናት ታግዞ በቀረበው የማሻሻያ ሃሳብ መመላከቱን አስረድተዋል፡፡ በቀጣይ ለፖለቲካ ድርጅቶች ውይይት በሚቀርበው የፓርቲዎች የስነ ምግባር አዋጅ ላይም ከዚህ ቀደም የፓርቲዎችን ነፃነት የሚገድቡ የተለያዩ አንቀፆች መሻሻላቸውን እንዲሁም በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የመምረጥ መብታቸውን እንዲጠቀሙ የሚያደርግ ሃሳብም መቅረቡን አቶ ዋሲሁን ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡

Read 2574 times