Monday, 08 October 2018 00:00

ባንኮክ በ20.5 ሚ. ቱሪስቶች የአለማችንን ከተሞች ትመራለች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   ዱባይ ከቱሪስቶች 29.7 ቢ. ዶላር በማግኘት ቀዳሚ ከተማ ናት


    ለሁለት ተከታታይ አመታት በብዛት በመጎብኘት ከአለማችን ከተሞች ቀዳሚነቱን ይዛ የቀጠለቺው የታይላንድ ርዕሰ መዲና ባንኮክ፣ ዘንድሮም በ20.5 ሚሊዮን አለማቀፍ ቱሪስቶች በመጎብኘት፣ የአንደኛነት ስፍራዋን ማስጠበቋ ተነግሯል፡፡
ማስተርካርድ የተባለው ተቋም ሰሞኑን ያወጣውን የአለማችን የአመቱ ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ ከተሞች ሪፖርትን ጠቅሶ ፎርብስ እንደዘገበው፣ ባንኮክ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2017 ብቻ በ20.5 ሚሊዮን አለማቀፍ ቱሪስቶች የተጎበኘች ሲሆን ይህ የጎብኝዎቿ ቁጥር በተገባደደው የፈረንጆች አመት 2018 መጨረሻ በ9.06 በመቶ  እድገት ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በመላው አለም የሚገኙ 162 ከተሞችን የአመቱ አለማቀፍ የንግድና የቱሪዝም ጎብኝዎች ፍሰት መሰረት አድርጎ ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት፣ ከባንኮክ ቀጥሎ ያለውን የሁለተኛነት ደረጃ የያዘቺው የእንግሊዟ ርዕሰ መዲና ለንደን ስትሆን ከተማዋ በአመቱ በ19.83 ሚሊዮን ሰዎች ተጎብኝታለች፡፡
የፈረንሳይ መዲና ፓሪስ በ17.44 ሚሊዮን አለማቀፍ ጎብኝዎች የሶስተኛነት ደረጃን ስትይዝ፣ ዱባይ በ15.79 ሚሊዮን ጎብኝዎች በአራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ሲንጋፖር በ13.91 ሚሊዮን፣ ኒው ዮርክ በ13.13 ሚሊዮን፣ ኳላላምፑር በ12.58 ሚሊዮን፣ ቶኪዮ በ11.93 ሚሊዮን፣ ኢስታምቡል በ10.7 ሚሊዮን፣ ሴኡል በ9.54 ሚሊዮን ሰዎች በመጎብኘት እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአምስተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውን ዘገባው አስታውቋል፡፡
በፈረንጆች አመት 2017 ከአለማቀፍ ቱሪስቶች ብዙ ገቢ በማግኘት ከአለማችን ከተሞች ቀዳሚነቱን የያዘቺው ዱባይ መሆኗን የጠቆመው ዘገባው፣ ከተማዋ በአመቱ በድምሩ 29.7 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን አመልክቷል፡፡ ከአለማቀፍ ቱሪስቶች ብዙ ገቢ በማግኘት ሁለተኛ ደረጃን የያዘቺው የሳኡዲ አረቢያዋ መካ በአመቱ በድምሩ 18.45 ቢሊዮን ዶላር ያገኘች ሲሆን  ለንደን 17.45 ቢሊዮን ዶላር፣ ሲንጋፖር 17.02 ቢሊዮን ዶላር፣ ባንኮክ በ16.36 ቢሊዮን ዶላር በቅደም ተከተላቸው እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም ዘገባው ገልጧል፡፡

Read 4868 times