Saturday, 06 October 2018 11:17

259 ሰዎች በሞባይል ‘ሰልፊ’ ለመነሳት ሲሞክሩ ሞተዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የመጀመሪያው ባለ 10ጂቢ ራም ሞባይል እየመጣ ነው

   የሞባይል ቴክኖሎጂ እየተራቀቀ መምጣቱን ተከትሎ፣ ፎቶ ለመነሳት ወደ ፎቶ ቤት መሄድ ታሪክ እየሆነ መጥቷል፤ ህጻን አዋቂው ሞባይሉን ወደ ራሱ ደግኖ፣ በሰኮንዶች እድሜ ውስጥ ጥርት ኩልል ያለ የራሱን ፎቶ ማንሳት ጀምሯል፡፡
ጥራት ያላቸው ካሜራዎች በተገጠሙላቸው ሞባይሎች ተጠቅመው፣ ራሳቸውን ፎቶ በማንሳት ወይም ሰልፊ ሱስ የተጠመዱ ሰዎችን ማየት የተለመደ አለማቀፋዊ ክስተት እንደሆነ የዘገበው ቢቢሲ፤ ችግሩ ግን የራሳቸውን  አስገራሚ ፎቶ ለማንሳት ከመጓጓት የተነሳ ለአደጋና ለሞት የሚጋለጡ የሰልፊ ሱሰኞች እየበዙ መምጣታቸውን አመልክቷል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ የተሰራን አንድ አለማቀፍ ጥናት ዋቢ አድርጎ ቢቢሲ ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፣ ባለፉት ስድስት አመታት ብቻ በአለማችን 259 ሰዎች በአደገኛ ሁኔታ ራሳቸውን ፎቶ ለማንሳት ሲሞክሩ ለሞት መዳረጋቸው የተረጋገጠ ሲሆን በዚህ ሰበብ መሞታቸው ሳይታወቅ የቀሩ እጅግ በርካቶች እንደሚኖሩም ይገመታል፡፡
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በሰልፊ ምክንያት ለሞት ከተዳረጉት መካከል 72.5 በመቶው ወንዶች እንደሆኑ የጠቆመው ዘገባው፤ አብዛኞቹ ከተራራና ከሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች ጫፍ፣ ባህር ውስጥና በፍጥነት በሚበርሩ ተሽከርካሪዎች ላይ ሆነው፣ እንዲሁም ከአደገኛ እንስሳት ጋር ፎቶ ለመነሳት ሲሞክሩ ለሞት የተዳረጉ መሆናቸውን  አመልክቷል፡፡ በአደገኛ ሁኔታ ሰልፊ ለመነሳት ከሚደረግ ሙከራ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የሞት አደጋዎች ከሚበዙባቸው የአለማችን አገራት መካከል ህንድ፣ ሩስያ፣ አሜሪካና ፓኪስታን እንደሚጠቀሱ የጠቆመው ዘገባው፣ በመሰል ሁኔታ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም ከአመት ወደ አመት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንም ገልጧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ቴና የተባለው የቻይና ታዋቂ የሞባይል ስልኮች አምራች ኩባንያ፣ ኦፖ ፋይንድ ኤክስ የተሰኘውንና በአለማችን የመጀመሪያውን ባለ 10ጂቢ ራም የሞባይል ስልክ አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ እየተዘጋጀ መሆኑን ዘ ቨርጅ የቴክኖሎጂ ድረገጽ ዘግቧል፡፡ በአለማችን የሞባይል ስልኮች ኢንዱስትሪ ውስጥ እስካሁን ድረስ ከፍተኛ ራም ወይም ውስጣዊ የመረጃ መያዝ አቅም ተብሎ ሲጠቀስ የነበረው 8 ጊጋ ባይት ራም እንደነበረ ያስታወሰው ዘገባው፤ ኦፖ ፋይድ ኤክስ የተባለው አዲሱ ሞባይል ግን ባለ ሁለት ዲጂት ጊጋ ባይት የመረጃ መያዝ አቅም ተጎናጽፎ በመምጣት በታሪክ የመጀመሪያው ሞባይል ይሆናል መባሉን ገልጧል፡፡
አዲሱ ሞባይል ከአንዳንድ መካከለኛ ዋጋ የሚያወጡ ላፕቶፖች የበለጠ መረጃ የመያዝ አቅምና ፍጥነት እንዳለውም ተነግሯል፡፡ ኦፖ ፋይድ ኤክስ ከዚህ በተጨማሪም ለአስራ አምስት ደቂቃዎች ያህል ብቻ ቻርጅ ተደርጎ ግማሽ ያህል ባትሪው የሚሞላ መሆኑና ካሜራዎቹም ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምስሎችና ቪዲዮዎች የመቅረጽ ብቃት ያላቸው መሆናቸው ሞባይሉን በገበያ ዘንድ ተመራጭ ያደርገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፣ ያም ሆኖ ግን ስልኩ ተመርቶ በገበያ ላይ የሚውልበትን ትክክለኛ ወቅት በተመለከተ በይፋ የተባለ ነገር አለመኖሩን ገልጧል፡፡

Read 1296 times