Saturday, 06 October 2018 11:16

የ2018 የኖቤል ተሸላሚዎች ይፋ እየተደረጉ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በስዊዘርላንዳዊው ሳይንቲስት አልፍሬድ ኖቤል መታሰቢያነት በተለያዩ ዘርፎች በየአመቱ ሽልማት የሚሰጠውና መቀመጫውን በስዊዘርላንድ ያደረገው የኖቤል የሽልማት ተቋም፣ የ2018  የኖቤል ተሸላሚዎችን ዝርዝር በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ ማድረግ ጀምሯል፡፡
ተቋሙ ባለፈው ሰኞ የአመቱን የኖቤል የህክምና ዘርፍ ተሸላሚዎች ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በካንሰር ህክምና ዘርፍ የላቀ ፈጠራ ያበረከቱት ጄምስ ፒ አሊሰንና ታሳኩ ሆንጆ የተባሉ የዘርፉ ዝነኛ ሳይንቲስቶች ሽልማቱን እንደተጋሩት ታውቋል፡፡
ማክሰኞ ዕለት ይፋ የተደረገው የፊዚክስ ዘርፍ የኖቤል ተሸላሚዎች መረጃ ደግሞ፣ በመስኩ አዲስና ፈር-ቀዳጅ የፈጠራ ውጤት ያበረከቱት አሜሪካዊቷ አርተር አሽኪን፣ ፈረንሳዊው ጄራርድ ሞሩ እና ካናዳዊቷ ዶና ስቲክላንድ በጋራ አሸናፊ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡
ካናዳዊቷ ዶና ስቲክላንድ፣ የኖቤል የፊዚክስ ሽልማትን ከ55 አመታት በኋላ ያገኙ የመጀመሪያዋ ሴት ሳይንቲስት ሲሆኑ፣ ሌላኛው የዘርፉ ተሸላሚ የ96 አመቱ አሜሪካዊ አርተር አሽኪን ደግሞ በኖቤል ሽልማት ታሪክ እጅግ ካረጁ በኋላ የተሸለሙ የመጀመሪያው የእድሜ ባለጸጋ ናቸው ተብሏል፡፡
 ተቋሙ ባለፈው ረቡዕ ከስቶክሆልም ይፋ ባደረገው መረጃ፣ አሜሪካዊቷ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ኤች አርኖልድ፣ ከሌላኛው የአገሯ ልጅ ጆርጅ ፒ ስሚዝና እንግሊዛዊው ግሪጎሪ ፒ ዊንተር፣ በጋራ በኬሚስትሪ ዘርፍ የአመቱ የኖቤል ተሸላሚ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
በካሊፎርኒያ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ የኬሚካል ምህንድስና መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ኤች አርኖልድ፣ በኖቤል ሽልማት ያለፉት 117 አመታት ታሪክ፣ በኬሚስትሪ ዘርፍ ተሸላሚ የሆኑ አምስተኛዋ ሴት መሆናቸው ተነግሯል፡፡
ብዙዎች በጉጉት ሲጠብቁት በነበረውና ትናንት ይፋ የተደረገው የዘንድሮው የኖቤል የሰላም ሽልማት ዘርፍ ውጤት ደግሞ፣  ጾታዊ ጥቃትን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀምን ለማሰቀረት ውጤታማ ስራ ያከናወኑት ኮንጓዊው ዴኒስ ሙክዌጌ እና በአሸባሪው ቡድን አይሲስ ለወሲብ ባርነት ተዳርጋ የነበረቺው ኢራቃዊቷ ናዲያ ሙራድ ተሸላሚ መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡
የዘንድሮው የኖቤል የኢኮኖሚ ዘርፍ ተሸላሚዎች ከነገ በስቲያ ይፋ እንደሚደረጉ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የኖቤል የሽልማት ተቋም ዘንድሮ በስነጽሁፍ ዘርፍ እንደማይሸልም አስታውቋል፡፡
የኖቤል የሽልማት ተቋም ከተመሰረተበት እ.ኤ.አ ከ1901 አንስቶ 585 ሽልማቶችን ለ896 ግለሰቦችና 27 ተቋማት የሰጠ ሲሆን፣ በተለያዩ ዘርፎች እስካሁን 49 ሴቶች መሸለማቸው ተነግሯል፡፡ በለጋ እድሜ የኖቤል ሽልማትን በመሸለም ቀዳሚነቱን ይዛ የምትገኘው በ2014 ላይ በ17 አመት ዕድሜዋ፣የኖቤል የሰላም ሽልማትን ያገኘቺው ማላላ ዩሱፋዚ ናት፡፡

Read 1398 times