Saturday, 06 October 2018 11:06

ንግድ ባንክ ለኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች የቤት መሥሪያ ወይም መግዣ ብድር አዘጋጀ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(5 votes)

 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውጭ አገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የቤት መስሪያ ወይም መግዣ የብድር አገልግሎት ሊሰጥ ነው፡፡
ማንኛውም ዕድሜው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነ ዲያስፖራ የብድር ጥያቄ ማቅረብ የሚችል ሲሆን፣ ጥያቄውን ሲያቀርብ መሟላት የሚገባቸው የመመዘኛ ስምምነቶች እንዳሉ አስታውቋል፡፡
መመዘኛዎቹም፣ የመኖሪያ ወይም የሥራ ፈቃድ፣ አመልካቹ ኢትዮጵያዊ ከሆነ የታደሰ ፓስፖርት፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆነ የውጭ ዜጋ ከሆነ የታደሰ መታወቂያና የትውልደ ኢትዮጵያውያን መታወቂያ (ብጫ ካርድ)፣ ሁለት የቅርብ ጊዜ የፓስፖርት መጠን ያለው ፎቶግራፍ፣ የጋብቻ የምስክር ወረቀት ወይም ያላገባ መሆኑን የሚገልጽ ሰነድ (ማስረጃ)፣ ብድሩ የተጠየቀው በወኪል አማካይነት ከሆነ የወኪሉ የታደሰ መታወቂያና ኮፒ እና ሁለት ፓስፖርት መጠን ያለው የቅርብ ጊዜ ፎቶግራፍና የውክልና ማስረጃ፣ እንዳስፈላጊነቱ ጠቅላላ ዓመታዊ የደመወዝ መጠንና የተጣራ ገቢን የሚገልጽ ከቀጣሪው የተሰጠ የቅጥር ደብዳቤ፣ እንደአግባብነቱ የቅጥር ውል ኮፒ፣ ከውጪ ሀገር ባንክ ቢያንስ የአንድ ዓመት የሂሳብ መግለጫ፣ አመልካቹ በንግድ ሥራ የሚተዳደር ከሆነ፤ ቢያንስ የሦስት ተከታታይ ዓመታት የሂሳብ ዝርዝር መግለጫ፣ የታደሰ የንግድ ፈቃድና የንግድ ምዝገባ የምስክር ወረቀትና የግብር ክፍያ ምስክር ወረቀት ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
አመልካቹ የመኖሪያ ቤት መሥሪያውን ወይም መግዣውን ቢያንስ 20 በመቶ በውጭ ምንዛሬ ማስገባት አለበት፡፡ ባንኩ የሚሰራውን ወይም የሚገዛውን ቤት እስከ 80 በመቶ ወጪ ያበድራል። ብድሩ በባንኩ ተቀባይነት ባላቸው የውጭ ገንዘቦች (የአሜሪካን ዶላር፣ የእንግሊዝ ፓውንድ ወይም በዩሮ) መክፈል አለበት፡፡
አመልካቹ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ወይም በሚኖርበት ሀገር በሚገኝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአካል በመቅረብ ወይም በሕጋዊ ወኪሉ አማካይነት የቁጠባ ሂሳብ በመክፈት የብድር መዋጮውን መቆጠብ ይችላል፡፡ አመልካቹ የሚፈለግበትን መዋጮ እንዳሟላ የብድር ጥያቄውን ለማንኛውም የባንከሉ የኮንስዩመርና የቤቶች ብድር ማዕከላት ወይም ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ የዲስትሪክት ቢሮዎች ማቅረብ ይችላል፡፡  
የብድር አገልግሎቱ ለመኖሪያ ቤት መሥሪያ/መግዣ የሚውል ነው፣ የብድሩ መክፈያ ጊዜው ከ20 ዓመት ሊበልጥ አይችልም፣ የብድር መዋጮው የሚሰራውን ወይም የሚገዛውን ቤት የመሀንዲስ ግምት ቢያንስ 20 በመቶ ይሆናል፣ የወለድ ምጣኔ ቢያንስ በዓመት 8.5 በመቶ ነው፣ ዳያስፖራው ያለበትን ቀሪ እዳ ያለተጨማሪ ክፍያ በፈለገበት ጊዜ አጠናቆ መክፈል ይችላል።

Read 5577 times