Saturday, 06 October 2018 10:45

ስለ ግ ጥም…

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(1 Vote)

ግርጊያም ገጣሚያን
የሚገርሙኝ ገጣሚዎች አሉ…
የጨረሰበትን ጊዜ ለመመዝገብ የራሱን ሰዓት ይዞ ወደ ሩጫ ውድድር እንደሚገባ አትሌት፣ ሰዓት ይዘው መጻፍ የሚጀምሩ የሚመስሉ፡፡
“ከንጋቱ 11፡35 የተጻፈ”
“ቀትር 7፡15፡56 የገጠምኳት”
“ለምሳ ልወጣ 5 ደቂቃ ሲቀረኝ የከተብኩት”
ምናምን ምናምን----እያሉ ቅጥያ የጊዜ ማስታወሻ ከግጥማቸው ግርጌ ካላስቀመጡ የገጠሙ የማይመስላቸው፡፡
የእነዚህ ቢጤዎች ሌላም አመል አለባቸው፡፡
“ብሄራዊ ትያትር ዋርካው ውስጥ ቁጭ ብዬ፣ ያዘዝኩት ማኪያቶ እስኪደርስ የከተብኳት ስንኝ”…
“የቀላል የከተማ ባቡር ሃዲዱ መዘርጋት በጀመረበት ዕለት ውስጤን ፈንቅሎ የወጣውን ስሜት የገጠምኳት”…
“ሃዋሳ፣ የፍቅር ሃይቅ ዳር፣ ጀምበር ስታዘቀዝቅ” (ሃዋሳን በስም ብቻ የምታውቅ ገጣሚ ልትሆንም ትችላለች)…
“የሳሪስ ታክሲ ስጠብቅ፣ ከአንዲት የፓርኪንግ ሰራተኛ ሊያልቅ ትንሽ የቀረው ቀጭ ቀጭ እስክርቢቶ ተውሼ በቁሜ የከተብኳት”…
እንዲህ እና እንዲያ የሚሉ ‘ግርጌያም’ ገጣምያን!

“የዚህ ግጥም ደራሲ…”
የአራተኛ ክፍል ተማሪዎች ሆነን፣ በሙዚቃ ክፍለ ጊዜ ራሳችን ያዘጋጀናቸውን ግጥሞች እናቀርብ ነበር፡፡ የራሳችንን ግጥም ከማቅረባችን በፊት ታዲያ፣ ማን እንደገጠማት የማናውቃትን አንዲት የጋራችን የሆነች ግጥማዊ ሰላምታ እንደ መግቢያ እንጠቀማት ነበር፡፡
“በፈረስ አፍንጫ አይገባም ትንኝ
ሙዚቃ መምህር ጤና ይስጥልኝ!...”
ይህቺን መግቢያ አስከትለን፣ ሁላችንም ያዘጋጀነውን ግጥም እናቀርባለን፡፡
አንድ ዕለት…
ሙዚቃ አስተማሪያችን እትዬ ውብሃረግ እንደተለመደው፣ የክፍሉን ተማሪዎች ስም ተራ በተራ እየጠራች ያዘጋጀናቸውን ግጥሞች እንድናቀርብ ትጋብዘናለች፡፡
በመካከል ላይ፣ ብርሃኑ ገላዬ የተባለው የክፍል ጓደኛችን ተራው ደረሰና ስሙ ተጠራ፡፡ በፍጥነት ብድግ ብሎም ያዘጋጀውን ግጥም ማቅረብ ጀመረ፡፡
“በፈረስ አፍንጫ አይገባም ትንኝ
ሙዚቃ መምህር ጤና ይስጥልኝ!
በአህያም አፍንጫ አይገባም ትንኝ
እትዬ ውብሃረግ ጤና ይስጥልኝ!
በዝንብም አፍንጫ አይገባም ትንኝ
የክፍል ጓደኞች ጤና ይስጥልኝ!”
አለ ብሬ እንደተለመደው ከአንገቱ ሰበር ብሎ ለመምህርቷና ለክፍል ጓደኞቹ ሰላምታ እየሰጠ፡፡ እንደተለመደው ተጨበጨበለት፡፡ ጭብጨባው ጋብ ሲል፣ ዋናውን ግጥም ማቅረብ ጀመረ፡፡
“ከእኛ መንደር በታች ይሸጣል ፓፓዬ
የዚህ ግጥም ደራሲ ብርሃኑ ገላዬ!
አመሰግናለሁ!...”
ሁላችንም ደግመን አጨበጨብንለት እንጂ፣ “የየትኛው ግጥም ደራሲ?” ብለን አልጠየቅነውም…
“ከእናንተ መንደር በታች፣ አረቄ ነው እንጂ ፓፓዬ መሸጥ የተጀመረው ደግሞ ከመቼ ወዲህ ነው!?...” ብለንም አልሞገትነውም፡፡


የሆነ የግጥም ምሽት ላይ…
“እስካለህ በጤና፣ ተደሰት ተዝናና!” የሚል ርዕስ የሰጠውንና “ዛሬን ተደስተን እንኑር” የሚል መልዕክት ያዘለ ግጥሙን አዳራሹ ውስጥ ለተሰበሰበው ታዳሚ በማንበብ ላይ ያለው ወጣት ገጣሚ፣ የግጥሙ የመጨረሻዎቹ ሁለት ስንኞች ላይ ደርሷል፡፡
“…ስለዚህ የሰው ልጅ እስካለ በጤና
አግባብ ነው መሳቁ እንዲሁም መዝናና…” አለና፣ በድንጋጤ ክው ብሎ ማይኩን ከአፉ አራቀ… አንዲት ፊደል ተርፋበታለች፡፡ ምንም ማድረግ አልቻለም፡፡ ግጥም በጻፈበት ወረቀት አፉን ከተመልካቹ ከልሎ፣ ምላሱ ጫፍ ላይ የደረሰችዋን ትራፊ ፊደል ፊቱን ዘወር አድርጎ መሬት ላይ ተፋት፡፡
“ቱ!...”

ስንኝ ምንተፋ
የአምስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ…
የአማርኛ መምህራችን ጋሼ ዋለ፣ በፈለግነው ጉዳይ ዙሪያ ከአስሩ የሚታረም ግጥም ጽፈን እንድንመጣ አዘዙን፡፡ ሁላችንም የቻልነውን ያህል ለመግጠም ሞከርን፡፡ በየተራ እየወጣን ግጥሞቻችንን ለክፍሉ ተማሪና ለመምህሩ አቀረብን፡፡
ከሁሉም ተማሪ አሪፍ ግጥም እንደጻፈ በመምህሩ የተመሰከረለትና ከአስሩ አስር ያገኘው፣ ከጎኔ የሚቀመጠው አላዛር ነበር፡፡ እርግጥ የአላዛር ግጥም የክፍሉን ተማሪ በሙሉ ያስደመመች ነበረች፡፡ ለማስታወስ እሞክራለሁ…
“…ሺህ ፈረስ ከኋላው ሺህ ፈረስ ከፊቱ
ሺህ ብረት ከኋላው ሺህ ብረት ከፊቱ
እንደሚያጋጥመው ሲነግሩት አባቱ
እንቢ ብሎ ወጥቶ አምልጦ ከቤቱ
ይሄው ጉዱ ፈላ በዛበት ጭንቀቱ
ምክር የማይሰማው ይሄ የልጅ ከንቱ
ያ ጎረቤታችን ተስፋዬ ሙላቱ
እናንተም እንደሱ እንዳትንገላቱ
የአባት ምክር ስሙ ደመቀና ቱቱ!...”
አላዛር ግጥሙን አንብቦ ሲጨርስ፣ የአማርኛ መምህራችን ጋሽ ዘሪሁን እንዴት በአድናቆት ተውጠው እንዳቀፉት ዛሬም ድረስ አልረሳውም። “መቼም በህይወት ዘመኔ ብዙ ግጥም አንብቢያለሁ፣ እንዲች ያለ ሸጋ ግጥም አይቼ አላውቅም!... ይሄ ልጅ ነገ ተነገ ወዲያ እሳት የላሰ ገጣሚ ባይወጣው ምናለ በሉኝ!” አሉ ጋሽ ዋለ በአድናቆት ተውጠው። ምን ይሄ ብቻ!... በቀጣዩ ፔሬድ ወደ አምስተኛ ሲ ክፍል ሲሄዱም፣ አላዛርን አስከትለውት ነበር - ግጥሟን ለተማሪዎቹ እንዲያቀርብ፡፡
አላዛር ግጥሙን አቅርቦ እስኪመለስ፣ ላጲስ ፍለጋ ቦርሳውን ስከፍት፣ የሆነ ትልቅ ቢጫ መጽሃፍ አገኘሁ፡፡ ጎትቼ አውጥቼ ስገልጠው፣ አይኖቼ የሆነ ግጥም ላይ አረፉ፡፡
“…ሺህ ፈረስ ከኋላው ሺህ ፈረስ ከፊቱ
ሺህ ብረት ከኋላው ሺህ ብረት ከፊቱ
ይህን ሳታይ ሞተች ኮሶ ሻጭ እናቱ…”
በድንጋጤ መጽሃፉን ሳጥፈው፣ ሽፋኑ ላይ ሹርባ የተሰሩ ኮስታራ ሰውዬ ስዕል አየሁ፡፡
መጽሃፉ የተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ ስዕሉም የአጼ ቴዎድሮስ እንደሆነ ያወቅኩት ማትሪክ ልፈተን ሰሞን ነው፡፡ ጋሽ ዋለ ያን ዕለት እንደነገሩን በህይወት ዘመናቸው ብዙ ግጥም እንዳላነበቡ፣ አላዛርም እሳት የላሰ ገጣሚ እንደማይወጣው የተረዳሁትም ያን ሰሞን ነው፡፡


Read 886 times