Saturday, 06 October 2018 10:28

ፍጥነተ - ለውጥ!

Written by  ከቃል ኪዳን
Rate this item
(12 votes)

 ድንገት በአንዲት ደሴት ላይ ነቃሁ፡፡ እውነቱን ለመናገር፣ ልንቃ ወይስ ልተኛ እርግጠኛ አይደለሁም። የመንቃትና የመተኛት ልዩነት፤ በነጭና በሌላ ነጭ መሀል ያለ ዓይነት ልዩነት ሆኖ ነው የሚሰማኝ፡፡ ደሴቲቱ ቅልብጭ ያለችና ብዙ ኮተቶችን ያልያዘች ናት፡፡ ለጸሐይ መውጫና መጥለቂያ የሚያገለግሏት የምሥራቅና የምዕራብ አቅጣጫዎች ብቻ ነው ያሏት፡፡ አቅጣጫዎቹ እግራቸው ላይ፤ ጫፉ የማይታይ የሚያብረቀርቅ የውሃ ጫማ ተጫምተዋል፡፡ በየአፍታው  ባህሩን ከጫፍ እስከ ጫፍ፣ ሊጠበስ እንደሚዘጋጅ አሳ የሚሰነጥቁት፤ በየተወሰነ ርቀት የሚነሱት ሞገዶች፤ የዚያ ውብ ጫማ ማሠርያዎች ይመስላሉ፡፡ የምሥራቅና የምዕራብ ነፋሳትም ከነዚህ ሞገዶች ነው የሚነሱት፡፡
በደሴቲቱ ላይ የጓጎለና ተራራ የሚመስል ነገር አይታይም፡፡ ጸሐይ እንኳን ደሴቲቱ ፈልቅቃ በምሥራቅና በምዕራብ ሰማይ ላይ ከከመረቻቸው የጥጥ ባዘቶዎች ውስጥ ነው  እየወጣች  የምትጠልቀው፡፡ ከጥጡ ጸአዳነት የተነሳ ጸሐይቱ ጠልቃ እንኳን ብርሃኗ ፍንትው ብሎ ይታያል፡፡ ተኝታ እንኳን ነጸብራቋ ያንን አብረቅራቂ የውሃ ጫማ ያደምቀዋል፡፡ እንደው ልማድ ሆኖባት ወይ ደግሞ ሁለት ቤት ለምዳ እንጂ ጸሐይቱ ባትወጣም፣ ባትጠልቅም ልዩነት አልነበረውም፡፡
ድንገት ሰባት ሰዎች መጥተው ከፊቴ ቆሙ። ሰባቱም ልጅነት የሚነበብባቸው  ግን ሙሉ ሰው ተብለው ለመጠራት ብቁ የሆኑ ናቸው፡፡ ሰዎቹ እንደኔ ግራ መጋባት አይታይባቸውም፡፡ ነገር ግን እናውቀዋለን የሚሉትን ነገር በደንብ እንደማያውቁት ያስታውቅባቸዋል፡፡
‹‹የት ነው ያለሁት?›› ስፈራ ስቸር ጠየቅኋቸው፡፡
አንድ አይነት ቋንቋ እንደምንናገር እንኳን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ታዲያ አንድ ዓይነት ቋንቋ ባንናገር እንኳን በራሴ ቋንቋ ከመጠየቅ ውጪ ሌላ ምን አማራጭ አለኝ?
‹‹እዚህ ነው ያለነው፡፡›› አንደኛው በችኮላ መለሰ፡፡ ችኩል እንደሆነ ሁሉ ነገሩ ይናገራል፡፡
‹‹እዚህ የት ነው?›› ምናልባት የኔን ቋንቋ የሚናገረው እሱ ብቻ ከሆነ ብዬ መልሼ ጠየቅሁት፡፡
‹‹እዚህ - እዚህ ነዋ!›› በቁጣ መለሰልኝ፤ ሌላኛው፡፡ ቁጡ መሆኑን ሁሉ ነገሩ ይናገራል፡፡
ከዛም ወደተቀሩት ሰዎች ዞሮ፣ በሌባ ጣቱ ጆሮው  አጠገብ ጠቆመና፣ ጣቱን ከላይ ወደ ታች በማሽከርከር፣ እብድ ልሆን እንደምችል ግምቱን ነገራቸው፡፡ ሁሉም ግምቱን ይዘው፣ በመስማማት እራሳቸውን ነቀነቁ፡፡ የሰዎቹ ድምዳሜ ቅር የሚያሰኝና የሚያስከፋ ቢሆንም ከንግግር ቋንቋ ባለፈ፤ ከሰዎቹ ጋር ተመሳሳይ የምልክት ቋንቋም እንደምንጠቀም ስለተረዳሁ ብቸኝነቱ ትንሽ ቀለለልኝ፡፡
‹‹እዚህ ምንድነው የምትሠሩት?›› ችኩሉን ሰውዬ ጠየቅሁት፡፡
ከቁጡ መቼም ችኩሉ ሳይሻል አይቀርም፡፡ በርግጥ ሁለቱም ከዳኝነት ዙፋን ላይ ቢቀመጡ አንዱ በጥድፍያ፤ ሌላኛው በንዴት ሆነው  የግፍ ፍርድ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ቢሆንም ቁጡው ሰውዬ፣ እብድ ነው ብሎ ስሜን በማጥፋቱ ተናድጄበታለሁ፡፡
‹‹እየኖርን ነዋ!›› አለኝ፤ ቁጡው ሰውዬ በቁጣ፡፡
ከቁጣው በተጨማሪ ያልተጠየቀውን ጥያቄ በመመለሱ አናደደኝ፡፡ ሰውዬው ለምን እና በማን እንደሚቆጣ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ የሚቆጣው በኔ ከሆነ፣ የቁጣው  መንስኤ ‹ለምን ሁሉም ነገር ደርሶ አይገባህም› ማለት ስለሆነ ቁጣው አግባብ አይደለም። ሰውዬው እራሱ እብድ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ቅድም በምልክት እራሱን ይሆን እንዴ ‹እብድ ሳልሆን አልቀርም!› ሲላቸው የነበረው?
‹‹እየኖርን ነው ማለት ምን ማለት ነው?›› እብዱን አፈጠጥኩበት፡፡ ቁጣና እብደት ልዩነት አላቸው እንዴ?
‹‹መኖር ነዋ! መኖር አታውቅም?›› ችኩሉ ሰውዬ በችኮላ መለሰ፡፡ አንዳቸው ለአንዳቸው ጥብቅና መቆማቸው የሚገርም ነው፡፡
ወዲያው ችኩሉ ሰውዬ፤ ሁሉንም ሰበሰባቸውና ክብ ሠርተው የአእምሮ ጤንነቴን በተመለከተ ውይይት ማድረግ ያዙ፡፡ ቁጡው ሰውዬ ከቁጣው መለስ ብሎ፤ አሁንም ሌባ ጣቱን ከጆሮው በላይ ሰክቶ፣ እብድ ስለመሆኔ በዝግታ ያስረዳቸው ጀመር፡፡ ሁሉም በመስማማት እራሳቸውን መነቅነቅ ያዙ፡፡ ችኩሉ ሰውዬ በችኮላ እራሱን ነቅንቆ ቀድሟቸው ጨረሰ፡፡
ምክክራቸውን ሲጨርሱ፤ በተርታ ተሰልፈው መጥተው  ፊቴ ቆሙ፡፡ ሰባቱም ሰዎቹ ቅድም ይታይባቸው የነበረው ልጅነት ጠፍቶ በጉርምስና ተተክቷል፡፡ ፈጣኖችና ደፋሮች መስለዋል፡፡ ግድየለሽነትም ይታይባቸዋል፡፡
‹‹ቆይ እኔን ማነው እዚህ ያመጣኝ? እዚህ ለምን መጣሁ?›› ሁሉም እየተያዩ ተሳሳቁ፡፡
ችኩሉ ሰውዬ በጩኸት፤
‹‹እንዴት እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ ትጠይቃለህ? ማንም ወደዚህ ፈቅዶ የመጣ የለም፡፡ መጥተሀል፣ ትኖራለህ! አለቀ!››
‹‹ማለት!? እንዴት በማን ሥር እንደሆንኩና  የመጣሁበትን ጉዳይ ሳላውቅ ዝም ብዬ እኖራለሁ?››
የሚሉት ነገር አልዋጥ አለኝ፡፡
‹‹ይኸውልህ ወንድም--!›› አለኝ እስካሁን ዝም ብለው ከነበሩት መሀል፣ አንደኛው ወደኔ እየተጠጋ፡፡
ሳየው ሰውዬዉ እኔኑ እንደሚመስል ተሰማኝ፡፡ እኔ ምን እንደምመስል ግን መገመት አልችልም፡፡ ምናልባት ይሄን ሰውዬ ብመስል ነው፡፡
‹‹ወንድሜ ምን መሰለህ? ኧ……እኛ……እንዴት መሰለህ?......ኧ›› ነገሩን ለማፍታታት ትልቅ ፍላጎት እንዳለው ሁለመናው ቢናገርም፣ አንደበቱ ግን ቃላትን ፈጥሮና አሳክቶ ሊያወጣለት አልቻለም፡፡
‹‹ምን መሰለህ? የሰው ልጅ……ኧ……እኛ በዚህች......ኧ››  
ንግግሩን አቋርጦ ወደ ኋላ ተመለሰና ሌላኛዉ ሰውዬ እሱ ያቃተውን ሀሳብ እንዲያስረዳለት ጀርባውን ቸብ፣ ቸብ አድርጎ ወደፊት ገፋው፡፡ ሰውዬው የባሰ ሆነ፡፡ የቀሩት ሶስቱም በተከታታይ መጡና መናገርና ማስረዳት እያቃተቸው፣ ወደ ቦታቸው ተመለሱ፡፡ ከዛም ችኩልና ቁጡ የሆኑት ሁለቱ ተናጋሪዎች፣ ለተቀሩት ሀሳባቸውን እንደነሱ ሆነው እንዲናገሩላቸውና እንዲያስረዱላቸው ዕድሉን ሰጧቸው፡፡
‹‹‹ማን አመጣኝ› እና ‹ለምን መጣሁኝ?› የሚሉት ጥያቄዎች እዚህ መልስ የላቸውም፡፡ መልስ ቢኖራቸውም እንኳን መልሱ አይጠቅምህም፡፡›› አለኝ፤ ችኩሉ ሰውዬ በችኮላ፡፡
‹‹እዚህ እስካለህ ድረስ፤ እዚህ አርፈህ ኑር!›› አለኝ፤ ቁጡው ሰውዬ ከሱ ቀበል አድርጎ፡፡
ሰባቱም ሳላያቸው እንደመጡ፤ ሳላያቸው  ተመለሱ፡፡ ወቅቶች ባይፈራረቁም፤ ጊዜያት አለፉ፡፡ በምሥራቅና በምዕራብ ሰማይ ላይ ያሉት ደመናዎች፣ ለጸሐይቱ መሥረቂያና መጥለቂያ እንጂ የህይወትን ውሃ ለመስጠት አልተፈጠሩም - ልክ መሽኛ ብቻ እንደሆነ አባላዘር፡፡ በምሥራቅና በምዕራብ ዳርቻዎች ያሉት የውሃ አካላትም ዝናብ ባይኖርም አንዲት ጠብታ እንኳን አልጎደሉም፡፡ እኔም አልጠማኝም፡፡
አሁንም በደሴቲቱ ላይ እንዳለሁ ነኝ፡፡ ግን ደሴቲቱ፤ እውነት ደሴት ናት? ደሴትና ሴት ምን ዓይነት ዝምድና አላቸው? ደሴት መንታ ጸሐይ ያለበት የደረተ-ሴት አምሳያ ነው? ደሴቲቱ ለምን የሴት ደረት መሰለች? ለምን እንደ ልጃገረድ ጡት ሾለው፤ እንደ ሙሉ ሴት ጡት ግራና ቀኝ ዘንበል ብለው፤ እንደ ውሃ ጡት ማስያዣ፤ የውሃ ጫማ የተጫሙ፤ ከበላያቸዉ ባሉ የደመና ባዘቶዎች ውስጥ ጸሐይዋን የሚያስተኙ፤ ቀስቅሰው የሚያባሩ ምሥራቅና ምዕራብን በደረቷ መሰረተች?
ሰባቱ ሰዎች መጥተው ድንገት ከፊቴ ቆሙ። ወጣትነታቸው  እንደ አሮጌ ሸማ በላያቸው ላይ አልቋል - ዕድሜ ተጭኗቸዋል፡፡ ችኩል የነበረው ተረጋግቶ፤ ቁጡው  ሰክኗል፡፡ መናገር የማይችሉ የነበሩት አምስቱ፣ እርጅናቸውን ተገን አድርገው መካሪና አማካሪ ሆነዋል።
‹‹የት ነው ያለነው?›› አልኳቸው፤ እስካሁን ያልመለሱልኝን ጥያቄ በማንሳት፡፡ አወይ ትዕግስቴ! እስኪመጡ እየጠበቅኳቸው ነበር ማለት ነው?
ማንም መልሱን ለመመለስ የቸኮለ ወይም የደፈረ የለም፡፡ ችኩሉን ሰውዬ አየሁት፡፡ የመመለስ እንኳን ፍላጎት ፊቱ ላይ የለም፡፡ ቁጡውን ሰውዬ እየፈራሁ ተመለከትኩት፡፡ ዓይኖቹን ጨፍኖ፤ ጸሐይቱ  ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ስትንከባለል የምታወጣውን ሙዚቃዊ ድምጽ እየኮመኮመ ነው፡፡ ፊቱ ላይ ፈገግታ እረብቧል፡፡
‹‹የት ነው ያለነው? ለምንድነው እዚህ የመጣነው?›› አልኳቸው በቁጣ፡፡ ሁሉም ከየሀሳባቸው ተመልሰው በንቃት ውስጥ ሆኑ፡፡
‹‹እባካችሁ ንገሩኝ! የት ነው ያለሁት? ማን ወደዚህ አመጣኝ? ለምንድነው ወደዚህ የመጣሁት?››
‹‹ልብ ብለህ አድምጥ!›› አሉኝ፤ ሁሉም በአንድነትና በአንድ ድምጽ፡፡
ከአንድነታቸው የተነሳ ድምጻቸው ኃይልና አሳማኝነት ነበረው፡፡
ልብ ብዬ ሳስተውል፣ ስድስቱ ዓለም ላይ ብዙ ተከታይ ያላቸውን ሃይማኖቶች መለያ ልብሶችን ለብሰዋል፡፡ አንደኛው ‹እና ሌሎች› በሚል ልብስ ተከፍኗል፡፡
‹‹ወደዚህ ያመጣህ እሱ ነዉ! ሁላችንንም ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣን እሱ ነው! ከምንምነት ወደ እንትንነት ያመጣን እሱ ነዉ!››
‹‹እሱን ታውቁታላችሁ? እኔም እሱን እንደናንተ ባውቀው ደስ ይለኝ ነበር›› አልኳቸው፡፡
‹‹እንዴታ! በሚገባ እንጂ! አንተም ዳባ የመሰለ ጠጉርህንና የተንዠረገገ ጢምህን ብቻ በማየት ህልውናውን ልታረጋግጥና ልታውቀው ትችላለህ፡፡››
ለካ ፂሜና ጸጉሬ አድጓል፡፡
‹‹እሺ ወደዚህ ለምን አመጣን?››
‹‹ለዝግጅት!›› በአንድ ድምጽ መለሱ፡፡
‹‹የምን ዝግጅት?›› ግራ በመጋባት ጠየቅኋቸው፡፡
‹‹ለሽልማት! ለልጅነት ነዋ! መንግስቱን ለመውረስ!›› እየተሽቀዳደሙ መለሱ፡፡
 ሁሉም ደረታቸውን ነፉ፡፡ ድምጻቸው ኃይሉንና አሳማኝነቱን አጣ፡፡
‹‹ታዲያ እንዴት እየተዘጋጃችሁ ነው?››
ሁሉም ዝም አሉ፡፡ ደግሜ ጠየቅኋቸው፡፡ መልስ የሚሰጠኝ ጠፋ፡፡
‹‹እሺ ዝግጅቱ ምን ምንን ይጠይቃል? ምን ማድረግ አለባችሁ ነው የሚለው?›› ጥያቄውን ቀየርኩላቸው፡፡
‹‹በቅድስና መኖር!›› በአንድነት መለሱ፡፡
 ድምጻቸው ዳግም ኃይሉንና አሳማኝነቱን ተጎናጸፈ፡፡
‹‹ታዲያ ለምን በቅድስና አትኖሩም?›› በመገረም ጠየቅኋቸው፡፡
ድንገት ሁሉም ዓይኔ እያየ፣ ወደ ፈሪ ውሻነት ተቀየሩና፤
‹‹ዉዉ……ዉዉ……ዉዉ›› ሲሉ መለሱልኝ፡፡
‹‹ቆይ በዚህ ቀፋፊ ማንነታችሁ እርሱ ሳይጠየፍ ካፈቀራችሁ፣ ለምን እርስ በርስ መፋቀር አቃታችሁ?››
‹‹ዉዉ!……ዉዉ!……ዉዉ! መናፍቅ! ከሀዲ! ዉዉ!››
‹‹ቆይ ሁሉንም አጥግቦ፤ ከተበላለት በላይ የሚተርፈውን ማዕድ ለምን ብቻችሁን ለመብላት ትስገበገባላችሁ?››
‹‹ዉዉ!……ዉዉ!……ዉዉ! መናፍቅ! ከሀዲ! ዉዉ!››
‹‹ቆይ በእናንተ ቁጥር ያሉት ኃያላን አማልክቶቻችሁ፣ እንዴት አንድ ሰይጣን ማሸነፍ አቃታቸው? ወይስ እናንተ ኑሯችሁን በእሱ ላይ ጥገኛ ስላደረጋችሁ ለእናንተ ሲሉ አዝነውለት ነዉ? መቼም ከእነ እድፋችሁ ያፈቀሯችሁ፣ ለናንተ ሲሉ የማያደርጉት ነገር የለም!››
‹‹ዉዉ…ዉዉ…ከይሲ! መአተኛ! ዉዉ!...ዉዉ! ምኑን ጉድ ነው የሚያወራው?››
‹‹መቼም የሁላችሁም ሃይማኖት አትጠይቁ፣ አትመርምሩ አይልም አይደል? እንደውም በተቃራኒው ጠይቁ፣ መርምሩ ነው የሚለው አይደል? ግን ቆይ እውነት እንደሚባለው  አምላክ ግን አለ? ገነት እና ሲኦልስ ?››
‹‹ዉዉ!……ዉዉ!……ዉዉ! ኡ……ኡ……ኡ……ኡ……ኧረ! ኡኡኡኡ……ዉዉ!……ዉዉ!……ዉዉ!››
‹‹ባደባባይ ሁላችሁም ሃይማኖታችን መልስ አላት ትላላችሁ፡፡ ስትጠየቁ ግን መልስ አትሰጡም። ለምን? ስለገዛ ሃይማኖታችሁ በቂ እውቀት ስለሌላችሁ? አዋቂዎቹን ጋርዳችሁ ስለቆማችሁ? ወይስ ሃይማኖተኝነት ሌላ ስጋዊ ፍላጎታችሁን የምታሯሩጡበት መደበቂያችሁ ስለሆነ?››
‹‹ዉዉ!……ዉዉ!……ዉዉ! እንዴ አሁንስ በጣም በዛ! ዉዉ!...ዉዉ! አንለቅህም! ዉዉ!››
ከልጅነት በፍጥነተ-ዝግመት ወደ ፈሪ ውሻነት የተቀየሩት ሰባቱ ሰዎች ሊነክሱኝ ተንደረደሩ፡፡ ሹል ጥርሳቸውን ሳይ በቆምኩበት ተርበደበድኩኝ፡፡ እንደምንም ብዬ እንደ ዱካክ ተጫጭኖ፣ አስሮ ካቆመኝ ከባድ መንፈስ እራሴን አላቀቅሁ፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ሰውነቴን ተመለከትኩ፡፡ ቆዳዬ ለውሾቹ ሹል ጥርስ እንደማይበገር ሳውቅ ተረጋጋሁ፡፡


Read 3550 times