Monday, 08 October 2018 00:00

“መሬት የተወሰደባቸው ተቋማት ለማልማት ሀሳቡም ያላቸው አይመስሉም”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ከመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር፣ ከ1997
ዓ.ም ጀምሮ በሊዝ ህግ መሰረት መሬት በውል ወስደው፣ ላለፉት 13 ዓመታት ምንም ልማት
ሳይጀምሩ መሬቱን አጥረው ያስቀመጡና መጠነኛ ግንባታ ጀምረው ያልጨረሱ የ143 ተቋማትን
ውል በማቋረጥ 154 ቦታዎችን ወደ መሬት ባንክ አስገብቷል፡፡ተቋማቱ የወሰዱትን መሬት ለበርካታ ዓመታት
ሳያለሙ የቆዩት በምን ምክንያት ይሆን? በራሳቸው ቸልተኝነት ወይስ በቢሮክራሲ ችግር? መንግስትስ
ይሄን ያህል ጊዜ እርምጃ ሳይወስድ ለምን ታግሶ ጠበቃቸው? መሬቱ በዘመቻ ከመነጠቁ በፊት ወደ ልማት እንዲገቡ ተገቢው ክትትልና ግፊት ተደርጓል? ውል ተቋርጦ የተወሰዱት መሬቶች እጣ ፈንታ ምንድን ነው? --- በሚሉትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ከሆኑት አቶ ተስፋዬ ጥላሁን ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ሰሞኑን በወሰደው እርምጃ፤ መሬት በሊዝ ወስደው ያላለሙትን ተቋማት ውል በምን መልኩ አቋርጦ ቦታዎቹን እንደወሰደ ቢያብራሩልን?
በአሁን ወቅት ውል አቋርጠን መሬት የወሰድነው፣ በህጋዊ መንገድ በሊዝ ህጉ መሰረት፣ መሬት በእጃቸው ካስገቡ በኋላ ህጉ በሚፈቅደው የጊዜ ገደብ ውስጥ የሚገባውን ልማት ባለመስራታቸው ነው። ባለሀብቶች፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የተለያዩ የዲፕሎማቲክ ተቋማት የወሰዷቸውን መሬቶች ውል አፍርሰን ወደ መሬት ባንክ አስገብተናል፡፡ በ721/2004 የሊዝ ውልና ይህንን ለማስፈፀም በወጣው ደንብ መሰረት ውል ገብተው፣ መሬቱን ለተለያየ አገልግሎት ከወሰዱ በኋላ ምንም ነገር ሳያለሙ፣ መሬቶቹን አጥረው፣ ለረጅም ጊዜ ያቆዩ ተቋማት ናቸው የተወሰደባቸው፡፡  
እስኪ መሬት ከተወሰደባቸው ተቋማት ውስጥ ጥቂቶቹን ይጥቀሱልን?
እኛ እንግዲህ እርምጃውን የወሰድንባቸውን ተቋማት በጥቅል ነው እየገለጽን ያለነው፡፡ እርምጃዎቹን እየወሰድን ስንሄድ ነው ግለሰቦቹን ማወቅ የምንችለው። አሁን በተለያየ ዘርፍ ነው ያስቀመጥናቸው፡፡ የግል ባለሀብቶች አሉ፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ የሚድሮክ ኩባንያዎችና የዲፕሎማቲክ ተቋማት አሉ። እነዚህ የሊዝ ውል ያሰሩ 143 ድርጅቶች ናቸው፡፡ ሚድሮክ እንደሚታወቀው፣ በውስጡ ብዙ ድርጅቶች አሉት፡፡ ምንም እንኳን ሚድሮክ በግል ባለሀብቶች ስር የሚመደብ ቢሆንም ስሙን ነጥለን የጠራነው በከተማችንም ሆነ በአገራችን ትልቁ አልሚያችን በመሆኑ ነው፡፡
እስካሁን ውል ተቋርጦ መሬት የተቀሙት ከየዘርፉ ምን ያህል ናቸው?
ለተለያየ ልማት ቦታ ወስደው ያላለሙ 19 የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል። የግል ባለሀብቶቹ 95 ሲሆኑ ዲፕሎማቲክ ተቋማት ያልናቸው የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ለመኖሪያና ለኤምባሲ ግንባታ፣ “አፍሪካ መንደር” በሚል ቦታ ወስደው ያላለሙና በውሉ መሰረት ያልተገበሩ በመሆኑ ውላቸው ተቋርጧል፡፡ መንግስት በተለይ የውጭ ግንኙነትን ለማጠናከር፣ አገራቱም የአገራችን ወዳጆች ከሆኑት መካከል በመሆናቸው እንዲሁም አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና መሆኗ ከግምት ውስጥ ገብቶ ነበር ቦታ የተሰጣቸው፡፡ መንግስት ሃላፊነቱ ቦታውን መስጠት ነው፡፡ እነሱ ባሰሩት ውል መሰረት፣ በተፈቀደው የጊዜ ገደብ ወደ ልማቱ አልገቡም፡፡ ስለዚህ  በነሱም ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡
ተቋማቱ ውል ሲያስሩ ወደ ልማት የሚገቡበትና ልማቱን የሚያጠናቅቁበት የጊዜ ገደብ  በደንቡ ውስጥ የተጠቀሰ ይመስለኛል፡፡ እስኪ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ይስጡኝ?
ትክክል ነው የተቀመጠ የጊዜ ገደብ አለ፡፡ የልማት መጀመሪያውና ማጠናቀቂያው እንደየልማቱ አይነትና መጠን የተለያየና የልማቱን አይነት ግምት ውስጥ ያስገባ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ መጠነኛ ግንባታ የሚሠራ ድርጅት የጊዜ ገደብና አንድ ትላልቅ ግንባታዎችን የሚያካሂድ ድርጅት የጊዜ ገደብ የተለያየ ነው። ይህንን የሊዝ ህጉም ይህን ለማስፈፀም የወጣውም ደንብ በማያሻማ መልኩ አስቀምጦታል፡፡ ዝቅተኛ መካከለኛና ትላልቅ ግንባታዎች በሚል ከነጠባያቸውና ከነሙሉ ግምታቸው ያስቀመጠው ደንብ አለ፡፡ ለምን አይነት ግንባታ ምን ያህል ጊዜ የሚለው ግልጽ ነው። ተቋማቱም ውል ሲያስሩ በዚህ ደንብ መሰረት ነው፡፡
አማካይ የሆነ ማለትም ቢያንስ “በዚህ ጊዜ ጀምሮ በዚህ ጊዜ ማጠናቀቅ ይገባል” በሚል የተቀመጠ  የጊዜ ገደብ ካለ ይንገሩኝ----
እንግዲህ ወደ ግንባታ ለመግባት ያለን ትልቁ የጊዜ ገደብ ሁለት ዓመት ሲሆን፤ የመጨረሻ የማጠናቀቂያ ገደቡ አምስት ዓመት ነው፡፡ እኛ ውል አቋርጠን መሬት የተረከብናቸው ደግሞ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 13 ዓመታት ምንም ሳይሰሩ ባዶ ቦታ ይዘው የነበሩትን ተቋማት ነው፡፡ ጥቂቶቹ መሰረት ጥለውባቸዋል። አንዳንዶቹ ዝም ብለው ኮለን አቁመው እየገነቡ ያሉ ለመምሰል የሞከሩ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ጉዳዩን ስናየው እነዚህ ተቋማት ለማልማት ሀሳቡም ያላቸው አይመስሉም፡፡
ተቋማቱ ወደ ግንባታ ላለመግባታቸው ምክንያታቸው ምን እንደነበር ለማጣራት ሞክራችኋል? ለምሳሌ ቢሮክራሲያዊ አሰራሮች፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ሌሎች ችግሮችን በመጥቀስ እንቅፋት እንደሆነባቸው የሚገልፁና የሚያማርሩ ወገኖች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንጻር እርስዎ ምን ይላሉ?
እኛ አሁን ውል ያቋረጥንባቸው ድርጅቶች እንኳን ችግር ሊገጥማቸው እነሱም ችግር ፈቺዎች ናቸው። በአገር ደረጃ የሚታወቁ ባለሀብቶች፣ ትልልቅ የመንግስት ድርጅቶች ናቸው፡፡ አገሪቱም እምነት ጥላባቸው ያለሙልኛል ብላ ትልልቅ ቦታዎች የሰጠቻቸው ድርጅቶች ናቸው፡፡ አገሪቱ ስታግዛቸው የነበረችና ቢሮክራሲውም አጠገባቸው ሊደርስባቸው የማይችሉም ናቸው፡፡ ቢሮክራሲ እንዳልደረሰባቸው የምታውቂው፣ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ልማት ሳይገቡ አጥረው ሲቀመጡ የተናገራቸው ሰው የለም፡፡ ተፅዕኖ ቢኖር ኖሮ እስከ ዛሬም አጥረው ባልተቀመጡም ነበር፡፡ ትልልቅ ቦታዎችም ያለ ልማትና ያለ ጥቅም ይህን ያህል ጊዜ አይቀመጡም ነበር፡፡ አገሪቱም ከተማዋም በነዚህ ድርጅቶችና ድርጅቶቹን በሚመሩት ወገኖች ላይ ተስፋ ነበራቸው፡፡ ስለዚህም ነው በቻሉ ሰዓት ይሰራሉ በሚል ግምት በትዕግስት ሲጠብቋቸው የቆዩት፡፡  
እርግጥ ነው የተለያዩ ቢሮክራሲዎችና የአፈፃፀም ክፍተቶች በተለያዩ አካባቢዎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ድርጅቶች መሬቱን ወስደዋል፡፡ መሬቱን ለመውሰድ ቢጉላሉና ቢቸገሩ ነበር ቢሮክራሲው አስቸገራቸው የሚባለው፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የግንባታ እቃዎች ውድነትና ተያያዥ ችግሮች በአገር ደረጃ እንደ ችግር የተነሱት ከሁለት ዓመት ወዲህ ነው፡፡ ግዴለም ሶስት ዓመትም እንበለው፡፡ አምስት አመትም ይሁን። እነዚህ ተቋማት ግን መሬት ከወሰዱ ከ13 ዓመታት በላይ ተቆጥሯል፡፡ 15 እና ከዚያ በላይ የሆናቸውም አሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች አሁን እየሰጠናቸው ያሉ አዳዲስ አልሚዎች፤  ከ2006፣ ከ2007 እና 2008 ዓ.ም ወዲህ የወሰዱት ቢያነሱ ተቀባይነት ይኖራቸዋል። የእነዚህኞቹ ግን የማልማት ፍላጐት ማጣት እንጂ ሌላ ገለፃ አያስፈልገውም፡፡ መሃል ፒያሳ ታጥሮ ያለው መሬት ስንት ዘመኑ ነው? ሜክሲኮ ቦሌና ሌሎች ቦታዎች ታጥሮ የቆየ መሬት እንዳለ ግልጽ ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት የውጭ ምንዛሪውን እጥረት መቋቋም ይችላሉ፡፡ በደንብ ይቋቋሙታል፡፡ ብዙ ኢኮኖሚው እነሱ ዘንድ ነው ያለው፡፡ የሚታወቁ ትልልቅ የመንግስት ተቋማት ናቸው፡፡ ባለሀብቶቹም ይታወቃሉ፡፡ የአፍሪካ አገራቱም ቢሆኑ ትልልቅ አገራት ናቸው፡፡ የተጠቀሱት ችግሮች ከማልማት ያግዷቸዋል የሚል እምነት የለንም።
ተቋማቱ ራሳቸው ለምን ሳያለሙ እንደቆዩ ተጠይቀው የሰጡት ምክንያት የለም?
ተቋማቱ በተለያየ ጊዜ ሲጠኑ የነበሩ ናቸው፡፡ መቼም የማያለማ ሰው ምክንያት የለውም ማለት አይቻልም፡፡ እኛ የምንፈልገው ከምክንያቱ ዘለው እንዲያለሙልን ነው፡፡ ይሄ ማለት ምክንያት አናስተናግድም ማለት ነው፡፡ እኛ የምናስተናግደው ህጋችንን ነው፡፡ ከእኛ ጋር ውል ባሰሩበትና ህጉና ደንቡ በሚያዝዘው መሰረት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ነው የምንፈልገው፡፡
አሳማኝ የሆነ ምክንያትና እክል ቢገጥማቸውስ? እነሱን የሚያስተናግድ ህግ የለም?
በደንብ አለ፡፡ ህጉ ለእነሱም እድል ሰጥቷል፡፡ የሚፈቀዱ ምክንያቶች በሊዝ ህጉ ላይ ተቀምጠዋል። ለምሳሌ አንድ አልሚ ታስሮ እስር ቤት ካለ፣ ትክክለኛ ህመም ገጥሞትና የአልጋ ቁራኛ ሆኖ ልማቱን  የሚያንቀሳቅስለት ከሌለ፣ ይህም በትክክለኛ ማስረጃ ሲደገፍና መሰል እክሎች ሲገጥሙ፣ መንግስት እነዚህን ምክንያቶች እንደሚቀበል በሊዝ ህጉ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ምንም ምክንያት ቢቀርብ ቢሮው አይቀበልም፡፡
በሚድሮክ ስር የተያዙት ቦታዎች የተወሰዱት የኩባንያው ባለቤት ሼህ መሐመድ አሊ አላሙዲን በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ነው፡፡ ታዲያ ህጉ እንዴት አላስተናገዳቸውም?
ህጉ ባለሀብቱን በሁለት መንገድ አያስተናግዳቸውም፡፡ አንደኛ ባለሀብቱ የታሰሩት ከወራት በፊት ነው፡፡ ከቦታዎቹ አንዱ ከ20 ዓመት በላይ ሳይለማ ቆይቷል፡፡ የሸራተን ማስፋፊያውም ረጅም ጊዜው ነው፡፡ ስለዚህ ለቦታዎቹ አለመልማት የባለሀብቱ መታሰር ምክንያት አይሆንም፡፡ ሁለተኛ የልማት ቦታዎቹ በባለሃብቱ ሥም የተያዙ አይደሉም። በሚድሮክ ስር ነው ያሉት፡፡ ሚድሮክ 11 ቦታዎችን የወሰደ ድርጅት ነው፡፡ እንደ ድርጅትነቱ ደግሞ የራሱ ስራ አስኪያጅ፣ ፋይናንስና ሌሎች አደረጃጀቶች አሉት። ስለዚህ ከባለሀብቱ ጋር የሚያገናኝ ነገር ስለሌላቸው ህጉ አያስተናግዳቸውም፡፡
እንደተባለው ተቋማቱ ልማቱን ማጠናቀቅ ከሚገባቸው ከእጥፍ በላይ አመታትን ወደ ልማት ሳይገቡ ቆይተዋል፡፡ የእርስዎ  ቢሮ እነዚህ ተቋማት ወደ ልማት እንዲገቡና ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያደረገው ግፊትና የሰጠው ማስጠንቀቂያ ነበር? ለምንስ እስከ ዛሬ እርምጃ ሳይወስድ ቆየ?
ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልሽ፣ እነዚህ ለተቋማቱ የተሰጡ ቦታዎች ጉዳይ ከእኛ መስሪያ ቤትም አቅም በላይ ናቸው፡፡ በህዝብ ህሊና ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ አይደለም መስሪያ ቤት ህዝቡ ወጥቶ ሲቃወምባቸው የነበሩ ናቸው፡፡ መሬት በየቦታው ታጥሮ የሌባ መናኸሪያ ሆነ፣ እኛም በሌባ ማጅራታችንን እየመታን አደጋ ተጋርጦብናል---እያለ ህዝቡ ሲማረርባቸው የነበሩ ግልጽ ቦታዎች ናቸው፡፡ ሁለተኛ እኛ የሊዝ ክትትል ቡድን አለን፡፡ በቢሮ ብቻ ሳይሆን በክፍለ ከተማም ደረጃ ይህንን ጉዳይ ብቻ የሚከታተሉ ቡድኖች አሉ፡፡ እነዚህ ቡድኖች በየጊዜው ሁኔታዎችን እየተከታተሉ ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ ከተቋማቱም ጋር ይገናኛሉ፡፡ ከዚያም ባለፈ በከንቲባና በካቢኔ ደረጃ አልሚዎቹ ግንባታ የሚጀምሩበትን ጊዜ ይጠየቃሉ። ብዙ ጊዜም ውል ይቋረጣል፡፡ ባለሀብቶቹና ተቋማቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከመሆናቸው የተነሳ ቦታው ይመለስላቸዋል፡፡ መንግስት ልማቱን ይሰሩልኛል ብሎ ከመጓጓቱ የተነሳም ቦታዎቹን ይመልስላቸው ነበር። እነዚህ ሰዎች ከቢሯችንም ጋር ግንኙነት አላቸው፡፡ ለብዙ ጊዜ ህጉ ተፈፃሚ ሳይደረግባቸው በምክር ነበር የቆዩት፡፡ ተመክረው ተመክረው ወደ ስራ ስላልገቡና እንደማይገቡም እርግጠኛ ሲኮን ውሉን ለማቋረጥ ተገድደናል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ይህን ባያደርግ፣ ቢሮውንም በህግ ያስጠይቀዋል፡፡
ውል ያቋረጣችሁባቸው ቦታዎች አንዳንዶቹ ግንባታ ተጀምሮባቸዋል፡፡ ለምሳሌ መሀል ፒያሳ የሚገኘው የሚድሮክ ፕሮጀክትን ብንወስድ መሰረት ከመጣል በላይ ነው፡፡ የሸራተን ማስፋፊያም  ቢሆን ከሊዝ ክፍያ በተጨማሪ ለአካባቢው ነዋሪዎች ምትክ ቦታ ካሳ ለመክፈል ከ87 ሚ. ብር በላይ ማውጣቱን በመግለጽ የፕሮጀክቱ ሃላፊዎች ቅሬታ ያነሳሉ፡፡ ግንባታ ተጀምሮ የባለሀብቱ ገንዘብ የፈሰሰባቸውን ቦታዎች በምን መልኩ ነው የምታስተናግዱት? የተቀሙትን ቦታዎችስ ምን ልታደርጓቸው አስባችኋል?
ሳይለሙ ቆይተው በተመለሱ ቦታዎች ላይ መንግስት የራሱ እቅድ አለው፡፡ እነዚህን ጉዳዮች የሚያስፈጽምበት ማለት ነው፡፡ ሁለተኛ የሊዝ ህጉ ራሱ ያስቀመጠው የነዛ አልሚዎች መብትም አለ፡፡ ያ ቦታ ሲተላለፍ እንዴት ነው የሚሆነው? እዚያ ቦታ ላይ የጀመረው ግንባታ ምን ይደረጋል? ለሚለው በህግ የተቀመጠ አሰራር አለ፡፡ ተቋማቱ  ቦታው ላይ የጀመሩት ግንባታ እስካሁን ያለባቸውን እዳ የማይመልስም ይሆናል፡፡ ገና ከኪሳቸውም ገንዘብ ሊፈለግ ይችላል፡፡ በህግ የተቀመጡ ቅጣቶችና ክፍያዎችም ይኖራሉ፡፡ በሌላ በኩል፤ አልሚዎቹ ቦታውን ለመያዝና ግንባታ የጀመሩ ለማስመሰል ዝም ብለው ጠፍጥፈው ያስቀመጡት ነገር ካለ፣ ብዙም ቦታ አንሰጠውም፡፡ ለምን ብትይ፣ አንድ ድርጅት ይህን ሁሉ ዓመት በውል መሰረት ሳያለማ አጥሮ መቆየቱ የልማቱ ጐታች ነው የሚያሰኘው፡፡ ነገር ግን ቦታዎቹ ላይ የተጀመሩት ግንባታዎች እየታዩ ህጉ በሚፈቅድላቸው መብትና ግዴታ ይስተናገዳሉ፡፡ ለምሳሌ ግንባታቸው ከ30 በመቶ በታች ከሆኑ ይወሰዳሉ፡፡ የተወሰዱት ደግሞ በጨረታ ይሸጣሉ ይላል፡፡ በጨረታ የሚሸጡና መንግስት ራሱ ቦታውን የሚያለማ ከሆነ፣ የራሱን ማካካሻ ሊያካሂድ ይችላል፡፡ ብቻ ተቋሙም  ይህን ያህል ቦታና ጊዜ ወስዶ ግዴታውን ባለመወጣቱ፣ ብዙ ጥፋት ስላለበት፣ ያ ጉዳይ ብዙም አያሳስበንም፡፡
ባለሀብቶቹና ተቋማቱ በጊዜ ገደቡ ባለማልማታቸው የተነሳ አገሪቱ የደረሰባት ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ተጠንቶ ይሆን?
ይሄ እኮ እንደውም ትልቅ ጥናት የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም፡፡ አገሪቱ ምን አጣች የሚለው፣ በፖለቲካውም ብዙ ነገር አጥታለች፡፡ ከህብረተሰቡም ጋር በተለይ ከተማዋ ተቃርናለች፡፡ ማህበራዊ ህይወቱም ተመሳቅሎ፣ በእድሩ በሁሉም ነገር አንድ ላይ የነበረው ተፈናቅሎ የተለያየ ቦታ ላይ ሰፍሯል፡፡ ህዝቡ ከኖረበት ልጆቹን ካሳደገበት የተፈናቀለው እኮ ልማቱ ይፋጠናል፣ አገር ትቀየራለች፣ አገሬ ስትቀየር እኔም በዚያ መሀል እጠቀማለሁ ብሎ አምኖ ነው፡፡ እርግጥ ሳያምንበትም የተፈናቀለ አለ፡፡ ያ ልማት ሳይሰራ ማህበረሰቡም ከኖረበት ርቆ ሄዶ ሲታይ፣ የሚያመጣውን ወይም የፈጠረውን ቅሬታና ቁጣ ማየት ነው፡፡ እርግጥ በፊትም በህዝቡ በኩል ቅሬታ እንደሚመጣ ይታወቃል፡፡ ግን ሁለቱን ነገሮች በማመዛዘን ይሄ ባለሀብት ቦታውን ቢያለማው ኢትዮጵያ ትቀየራለች፣ ልጆቿም ይቀየራሉ የሚለውን በማስቀደም ነው፡፡ ካልለማ ግን ማንም አይቀየርም፣ ስለዚህ በፖለቲካውም በማህበራዊ ህይወትም በኢኮኖሚውም ችግር ተፈጥሯል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የከተማዋ ዲዛይን ላይም ችግር አድርሰዋል። ከተማዋ ሊኖራት የሚገባውን ውበት እንዳታገኝ አድርገዋል። በዓለም መድረክ እንዳትታይ ተፅዕኖ ፈጥረዋል፡፡ ከቱሪዝምና ከገጽታ ግንባታ አንፃር ጉዳት ደርሷል፡፡ አንድ ቱሪስት አንድን አገር ሊያይና ሊጐበኝ የሚችለው አንድም ከመሰረተ ልማት አኳያ ነው፡፡ አረብ አገራትን ተመልከቺ፡፡ አገሮቻቸው የሚጐበኙት በግንባታቸው ነው፡፡ የእኛ ግንባታ ደግሞ አጥር ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ ይህን ያደረጉት እነዚህ ድርጅቶችና ባለሀብቶች ናቸው። ይሄ ሁሉ ጉዳት በግልጽ የሚታይ በመሆኑ ጥናት ያስፈልገዋል ብዬ አላምንም፡፡
አሁን እርምጃ የተወሰደው በህጋዊ መንገድ መሬት በያዙት ላይ ነው፤ ነገር ግን በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ በርካታ ቦታዎች እንዳሉ ይነገራል፡፡ በተጨማሪም በከተማዋ መሬት ላይ የተገነቡ ወደ 70 ያህል ባለቤት አልባ ህንፃዎች ተገኝተዋል ተብሏል፡፡ እስኪ ስለነዚህ ጉዳዮች ያብራሩልኝ---?
እስካሁን እርምጃ የወሰድነው በህጋዊ መንገድ ተይዘው ባልለሙ ቦታዎች ላይ ነው፡፡ በህገ ወጥ መንገድ  የተያዙት ቦታዎች ላይ ራሱን ችሎ የመሬት ኦዲት በቀጣይ ይካሄዳል፡፡ ህንፃዎቹን በተመለከተ ላነሳሺው በከተማው ያሉ በርካታ ህገ-ወጥ ነገሮችን ለማውጣት እየሰራ ያለው በአንድ ዘርፍ ብቻ አይደለም፡፡ በተለያዩ ሴክተሮች የተለያየ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ እኔ አሁን የምገልጽልሽ፣ የመሬት ጉዳዮች ላይ ብቻ ነው። ሌሎቹ ከቤቶች ኤጀንሲ፣ ከፋይናንስ ጋር በተገናኘ የሚሰራ አለ፡፡ ከተለያዩ ንብረቶች እንዲሁም ከግንባታ ጋር የተያያዙም በዛው ዘርፍ እየተሰሩ ነው፡፡ ነገር ግን ባለቤት አልባ የሚለው አባባል፣ በህጋዊ መንገድ ወስዶ መሀል ከተማ ላይ አጥሮ ሳያለማ ካቆየው፣ ባለቤት አለው ማለት ነው እንዴ? በአጠቃላይ ህገ ወጥ ሥራ ባለቤት አልባ ነው፡፡ ከህንፃዎቹ ጋር በተያያዘ እነዚህ ከህግና ከፋይል ጋር የሚገናኙና እንደ ቢሮም ባለቤት ያላቸው ናቸው፡፡ አሁን ተነስተን ይሄን ያህል ህንፃ ቦሌ ወይም ሌላ አካባቢ ባለቤት የለውም የማለት አቅሙም አይኖረንም ማለት ነው፡፡
Read 3592 times