Sunday, 07 October 2018 00:00

ለሕወሓቶች የረሱትን ልንገራቸው?

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(6 votes)

“ያለ ኢትዮጵያ ትግራይ፣ ያለ ትግራይ ኢትዮጵያ፣ እንዳይሆን እንዳይሆን”


''እውነትም በትግራይ ነገድ ልማትና ጉዳት ምን ቸገረኝ የሚል ንጉሥ ለራሱ ይጎዳል፡፡ ትግሬን የሚያህል ትልቅ ነገድ ቢጠፋ ለኢትዮጵያ ትልቅ ጉዳት ነው፤ ቢለማና ቢመቸው ግን ትልቅ ጥቅም፡፡ የኢትዮጵያ መሠረት ትግሬ ነው፡፡ ከቀሩትም የኢትዮጵያ ነገዶች ይልቅ የኢትዮጵያ መንግሥት እድሜ መለመን የሚገባው ለትግሬ ነው፡፡
“አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ”
(ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ)
የትግራይ ሕዝብ ብሔራዊ ትግል ጸረ አማራ ብሔራዊ ጭቆና፣ ጸረ ኢምፔሪያሊዝም እንዲሁም ጸረ ንዑስ ከበርቴያዊ ጠጋኝ ለውጥ ነው፡፡ ስለዚህም የአብዮታዊው ትግል አላማ ከባላባታዊ ሥርዓትና ከኢምፔሪያሊዝም ነጻ የሆነ የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ማቋቋም ይሆናል፡፡››
የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ድርጅት
መግለጫ 1968
ሕወሓት ይህን ስም መጠሪያው አድርጎ፣ ጸረ አማራ ብሔራዊ ጭቆና ያወጀው፣ መሬት ለአራሹ ታውጆ፣ በእድገት በኅብረት ዘማቾች አማካይነት ተግባራዊ ከሆነና ገበሬው የመሬት ባለቤትነቱን በእጁ ካስገባ ከወራት በኋላ መሆኑን ማስታወሱ ደግ ነው፡፡
ከሁሉም ከሁሉም በፊት ግን  አስቀድሜ ማሳወቅ የምፈልገው ሕወሓትን መንቀፍ፣ አብጠልጥሎ መተቸት ጠና ሲልም፣ ሞትህን ያቅርበው ማለት፤ ጨርሶ የትግራይን ሕዝብ መጥላትና ማጥላላት አለመሆኑን ነው፡፡ የት ተገኝተው?! ትናንት ለጦርነቱ፣ ዛሬ ለካድሬነትና ለሌሎችም ሥራዎች ልጆቻቸውን ለሕወሓት የሰጡ የትግራይ ወላጆች፣ ቢረዱት የምወደው፤ የድርጅቱ ባለቤቶች የፓርቲው አባሎች እንጂ እነሱና የእነሱ ልጆች አልፎም ሌላው የትግራይ ሕዝብ አለመሆኑን ነው፡፡
ወደ መግለጫው እንመለስ፤ ሕወሓት በዚህ መግለጫው መግቢያ ላይ፤ የአክሱም መንግሥት እስከወደቀበት ጊዜ ድረስ ትግራይ 'የአክሱም መንግሥት' እየተባለች ትጠራ እንደነበር ይገልፃል። ይህን የሕወሓት ስህተት አንድ ማለት ይቻላል፡፡ የዛሬይቱ አዲስ አበባ ከደጋ ሐቡር እስከ መተማ፣ ከጋምቤላ እስከ ዛላ አንበሳ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋና ከተማ እንደሆነች፣ መንግሥቱ የአዲስ አበባ መንግሥት እንደሚባለው ሁሉ  አክሱምም አሁን ከአለችው ብዙ እጥፍ ለምትሰፋው ኢትዮጵያ፤ ዋና ከተማ ስለነበረች የአክሱም መንግሥት መባል የሚለው አያስኬድም፡፡ በሌሎች አገሮች የሚሆነው እንዲህ በመሆኑ በኢትዮጵያ ሲሆን የሚለወጥ ነገር የለውም። በእኔ እምነት፤ የሕወሓት ስም ባለበት መቀጠል  ይህን ችግር ይዞ መጓዝ ይሆናል፡፡ ልክ እንደ ትናንቱ “የአክሱም መንግሥት የእኔ እንጂ የሌላው ኢትዮጵያዊ አይደለም” ማለትን ያመጣል፡፡
ሕወሓት በዚህ መግለጫው፤ የትግራይ ሕዝብ የሚለው በትግራይ ውስጥና ውጭ ያለውን ትግርኛ ተናጋሪ ሕዝብ በሙሉ ያጠቃልላል፡፡ እነሱ ደግሞ በአፋር አካባቢ ጠልጠል፣ አገው፣ ሳሆ፤ ኩናማ ወዘተ መሆናቸውን ይጠቁምና የትግራይ መሬት በደቡብ እስከ አልውኃ፣ በምዕራብ በኩል ደግሞ ወልቃይትንና ጸለምትን እንደሚያጠቃልል ያስረዳል፡፡
አንዳንድ ጊዜ እንዳለቀለት፣ ሌላ ጊዜ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንደሚፈታ ሕወሓት የሚናገርለት የወልቃይትና የጠለምት ጉዳይ፤ በሕወሓት አቋም የተያዘበት ደርግን አሸንፎ ሥልጣን ከመያዙ 15 አመት፣ ሕገ መንግሥቱ ከመጽደቁ 19 አመት በፊት ነው፡፡ ለሕወሓት የቋንጃ ቁስል ሆኖ ሰላም እየነሳው ያለው ይህ ችግር፤ ከስሙ ጋር እንደ ጆሮ ጌጥ ተንጠልጥሎ የሚኖር መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
‹‹ከአጼ ዮሐንስ ሞት በኋላ በዳግማዊ ምኒልክ አማካይነት ትግራይ በሸዋ ማዕከላዊ መንግሥት ግዛት ሥር ወደቀች፡፡ ከዚህ በኋላ ነው የአማራው የመሳፍንት ቡድን ተከታዮች የትግራይን ነጻነት ገፍፈው የሕዝቡን አንድነት ያናጉት፡፡ ግልጽና ስውር በሆነ ዘዴያቸው የትግራይን ሕዝብ በድንቁርና፣ በበሽታና በርሃብ አዘቅት እንዲሰምጥ ያደረጉት›› ይላል፤ ሕወሓት ቀደም ሲል በጠቀስኩት መግለጫው፡፡
ሕውሓት እራሱን ለእውነቱ ባዕድ አድርጎ፣ ማንሳትም ማስታወስም የማይፈልገው እውነት፤ በ1870 ደብረታቦር አካባቢ የነበሩት አፄ ዮሐንስ ሸዋ ገብተው “ንጉሠ ነገሥት” ነኝ ብለው ዘውድ የደፉትን ምኒልክን፣ ንጉሠ ነገሥትነቱን አንስተው፣ ምኒልክን ንጉሠ ሸዋ ብለው አንግሰው ተመለሱ፡፡ የአፄ ዮሐንስ ሸዋ መጥቶ ማስገበር ያልታየው ሕውሓት፤ የምኒልክ መቀሌ መግባት የሚያመው ድርጅት ነው፡፡ ይህ በሽታው ደግሞ ትልቋን ኢትዮጵያን ለመቀበል እንዳስቸገረው አለ፡፡ ገብረሕይወት ባይከዳኝ የሚመክሩት ግን “ያለ ኢትዮጵያ ትግራይ፣ ያለ ትግራይ ኢትዮጵያ … እንዳይሆን እንዳይሆን” መሆኑን ነው፡፡ ነፃ አውጭነቱ መቅረት ያለበት አብሮነቱን ግድ ስለሚያደርገው ነው።    
ከስምንት ዓመት በፊት በ“ነጋድራስ” ጋዜጣ ላይ አንድ ጥያቄ አንስቼ ነበር፡፡ ስለ ኢህአዴግና አባል ድርጅቶቹ፡፡ ኢሕአዴግ የተመሰረተው የደርግን መንግስት ለመጣል ነው፤ እሱ ከወደቀ ዘመን የለውም፤ ኢሕአዴግ ግንባር ሆኖ የሚቀጥለው ማንን ለመዋጋት ነው? ሕውሓትስ የትግራይ ነፃ አውጪ እየተባለ እስከ መቼ ይኖራል? የሚል ነበር ጥያቄው፡፡
ዛሬም ሕውሓት በነፃ አውጪነቱ ቀጥሏል፡፡ ኢሕአዴግም እንደዚያው፡፡ የሕውሓት በትግራይ ነፃ አውጪነት ለመቀጠሉ አዲስ ትርጉም እየተሰጠው ነው፡፡ በክልሉ ያለውና የተንሰራፋው ድህነትን ማስወገድ ጥያቄው ድህነት ያልተንሰራፋበት፣ ከድህነት ነፃ የወጣ አካባቢ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ወይ? ነው፡፡
ሰው መስተዋት የሰራው፤ የራሱን ዓይን በራሱ ማየት ስለማይችል ነው፡፡ ስለዚህም ነው ለሕውሓቶች መንገር የምንፈልገው፡፡

Read 1998 times