Monday, 08 October 2018 00:00

የአዲስ አበባ አስተዳደር ተግዳሮቶች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አዲስ አበባ፤ አዲስ አስተዳደር ካገኘች ሁለት ወር አስቆጠረች፡፡ በፌደራል ደረጃ እየተካሄደ ከሚገኙት ለውጦች አንፃር በከተማችን አዲስ ለውጦችን ብንጠብቅ አይፈረድብንም፡፡ ለዛሬ ብዕሬን ያነሳሁት፣ አዲሱ አስተዳደር በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸውን ተግባራት ለመገምገም ሳይሆን የኛን የከተማዋን ዜጐች ምኞት፣ተስፋና ሥጋት በመግለጽ፣ አዲሱ አስተዳደሩ ትኩረት ሊያተኩርባቸው ይገባል የምላቸውን አንዳንድ ሃሳቦች ለመሰንዘር ነው፡፡
1ኛ) አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመንና ቀልጣፋ ማድረግ፤
አገልግሎት ሲባል በጣም በርካታ ጉዳዮች እንደ ጤና፣ ትምህርት፣ ትራንስፖርት፣ ግብር አሰባሰብ ያሉትን እጅግ ሰፊና ውስብስብ ጉዳዮች የሚያካትት ነው፤ በየራሳቸዉ ርዕስ ሆነው፣ ብዙ ሊፃፍባቸው የሚችሉም ናቸው፡፡ የዛሬው ትኩረቴ በተመረጡ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶች ላይ ነው፡፡ ከአካባቢ ውበትና ፅዳት ስንነሳ፣ አዲስ አበባን የፌደራል መንግስት መቀመጫ፣ የኢትዮጵያ ተምሳሌት ፣የአፍሪካ መዲና ወዘተ…እያልን  እናሞካሻታለን፡፡ እውነታው  ግን አዲስ አበባ በማንኛውም መመዘኛ፣ ሊጠቀሱ ከሚችሉ የአፍሪካ ከተሞች ባነሰ ደረጃ ላይ መገኘቷ ነው። ለስብሰባ ወይም እግር ጥሎት አዲስ አበባ የተገኘን የውጪ ዜጋ - አውሮፓዊ ወይም አሜሪካዊ፣ አይደለም አፍሪካዊ፣ አንድ ተጨማሪ ቀን ለማቆየት የሚያበቃ ሰው ሰራሽ ሆነ ተፈጥሮአዊ መስህብ አላደራጀችም፡፡ አዲስ አበባ አሁንም ድረስ ሰዎችና እንስሳት አብረው የሚኖሩባት ትልቅ መንደር ነች የሚሏት አሉ፡፡ እውነት ነዉ፣  በአዲስ አበባ አውራ ጎዳናዎችና አደባባዮች የቀንድ ከብቶች፣ አህዮች፣ በጎችና ባለቤት አልባ ውሾች ሲተረማመሱ መመልከት በጣም የተለመደ ነዉ፡፡ ይህ ሁኔታ የከተማዋን የገፅታ ግንባታ  ጥላሸት የሚቀባ ብቻ ሳይሆን የትራፊክ ፍሰቱን በእጅጉ የሚያስተጓጉል፣ የከተማዋን የፅዳት ሁኔታ የሚያበላሽ እንዲሁም መንገዶችንና ያሉትን ጥቂት አረንጓዴ ቦታዎች የሚያጎሳቁሉ መሆኑን መረዳት አዳጋች አይደለም።
እውን ይህን ይህን ሁኔታ መለወጥ የማይቻል ሆኖ ነው ወይስ በተለመደው ቸልተኝነታችን ተላምደው ነዉ? ዛሬ ዛሬ የገጠሩ ሕዝባችን እንኳን ቤት ሲሰራ የሰዎችንና የእንስሳቱን ለይቶ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች አያስፈልጉንም  እያልኩ አይደለም፤ ወይም በከብት እርባታና ንግድ ኑሯቸዉን የሚገፉ ዜጎች መኖራቸው ተዘንግቶኝም አይደለም፡፡ እያልኩ ያለሁት ለምን በተሻለ መንገድ አናካሂደውም ነዉ? አዲሱ የከተማው አስተዳደር  ይህንን ሁኔታ ለመለወጥ ተግቶ መስራት ይኖርበታል  ብዬ አስባለሁ፡፡  አዲስ አበባ የዘመናዊነት መስታወት እንጂ የእንስሳት መራኮቻ መሆኗ ማብቃት አለበት፡፡
የማዘጋጃ ቤት አገልግሎትን ከማዘመንና ቀልጣፋ ከማድረግ ጋር ተያይዞ መጠቀስ የሚገባቸው ሌሎች በርካታ ጉዳዮችም አሉ። በተለይ የስራ ቅልጥፍናን ከመፍጠርና ተጠያቂነትን ከማስፈን አኳያ፣ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው፣ ለአገልግሎቶች ዝቅተኛውን ደረጃ መወሰንና ተግባራዊ የማድረግ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ የህዝብ ማመላለሻ አገልግሎቶች ላይ የተሰማሩ ሁሉ ሊያሟሏቸዉ የሚገቡ መሰረታዊ ደረጃዎች ተለይተው ሊነገሯቸው ይገባል፡፡ ብዙዎች የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ላይ የተሰማሩ ተሽከርካሪዎች፤ ንፅህናቸው በእጅጉ የተጓደለ፣ የተጎሳቆሉና ጥገና ስለማይደረግላቸው፣ በሚያወጡት ጭስ፣ የከተማዋን የአየር ብክለት በማባባስ ላይ ናቸው። አብዛኛዎቹ የከተማዋ ህንፃዎች፤ አካል ጉዳቶችን ታሳቢ አለማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን የአደጋ ጊዜ መውጫ የሌላቸው ናቸው።
የህንፃው ተጠቃሚዎች እንኳ መኪኖቻቸውን የሚያቆሙበት ቦታ ስለማያዘጋጁም፣ መንገዶች ሁሉ ወደ መኪና ማቆሚያነት እየተቀየሩ ናቸዉ። የከተማ  መንገዶች  አሰራርና አስተዳደርም እንደዚሁ የተዘበራረቀና ለተጠቃሚዎች የማይመች ናቸው። እኛ ደሃ አገር ነን፤ እየሰራን እያፈረስን ልንቀጥል አንችልም፡፡ ሐብታችንን መቆጠብና በጥንቃቄ  መጠቀም አለብን፤ ይህ ደግሞ በዘመቻ ሳይሆን አቅዶ መስራትን የግድ ይላል፡፡ ከተማዋ የአጭር የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ሊኖራት ይገባል፡፡
የውሃ አቅርቦት ሌላዉ የአገልግሎት አይነት ነው:: በአለም ዙሪያ ያሉ በርካታ ከተሞች ለመጠጥና ለሌላ ስራ (ለፋብሪካ፣ ለማጠቢያ፣ ለአትክልት) የሚውለውን ውሃ ለይተው ያቀርባሉ:: ይህም ብቻ ሣይሆን የአንድን ግለሰብ (ቤተሰብ) ዝቅተኛውንና ከፍተኛውን የፍጆታ መጠን ይወስናሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉት የውሃ ሃብትን በአግባቡ አለመጠቀምና ስርጭቱንም ፍትሃዊ ለማድረግ ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ እንደምናውቀው፣ 24 ሰዓት ያልተቋረጠ ውሃ የሚያገኙ አካባቢዎች አሉ፤ በተቃራኒው  አንድ ወርና ከዚያም በላይ ለሆነ ጊዜ፣ እጅግ መሰረታዊ የሆነው የውሃ አቅርቦት የሚነፈጋቸው አካባቢዎችም  አሉ፡፡ ይህ በአጭር ጊዜ ባይሆን በመካከለኛ ጊዜ እንዲሻሻል መስተዳደሩ ተግቶ ሊሰራ ይገባዋል፤ በሌላ በሌላው ብንለያይ በውሃማ ሊሆን አይገባም፡፡
2ኛ) የአካባቢ ፅዳትና ውበትን ማሻሻል፤
የአዲስ አበባ የጽዳት ጉድለት ብዙ ተነግሮለታል። ለችግሩ መባባስ መስተዳደሩም ነዋሪውም አስተዋፅኦ አደርገዋል፡፡ ከተማና ከተሜነት የራሳቸው የሆነ መለያ ባህሪያት አሏቸው። እንደ ድፍረት እንዳይቆጠርብን እንጂ፣ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ ከተሜነት ይጎድለዋል፡፡ አዲስ አበባ እኮ ሥልጡን ነን ባዮች (ዘመናዊ መኪና የሚያሽከረክሩት ሳይቀር)፣ የበሉትን የሙዝና ብርቱካን ልጣጭ እንዲሁም  የተገለገሉበትን ዕቃ በየጎዳናው የሚጥሉ፤ ዘመናዊ  መኖሪያ ቤት ውስጥ እየኖሩ የራሳቸውን ቆሻሻ ከግቢያቸው አስወጥተው መንገድ ላይ የሚደፉ፣ ይባስ  ብሎም በየመንገዱና አጥር ስር  የሚፀዳዱ ሰዎች--የሞሉባት ከተማ ነች፡፡ ታዲያ እኛ  አዲስ አበቤዎች፣ ከተሜነት አይጎድለንም ትላላችሁ? በዓመት በዓል ሰሞን የሚታየውን በየመንገዱ የተዝረከረከ የእርድ ተረፈ ምርት ለተመለከተ፣ ለከተማው መቆሸሽና መጎሳቆል ዋናው ተጠያቂ፣ ነዋሪው መሆኑን አይጠራጠርም፡፡ እንዲያም ሆኖ የከተማው አስተዳደር፣ ተግባሩን በትክክል እየተወጣ ነው ማለት አይደለም፡፡ የህዝብ መጸዳጃ ቦታዎች፣ ሕዝብ በሚበዛባቸውና አማካይ በሆኑ ቦታዎች፣ በበቂ መጠን መገኘት ሲኖርባቸው፣ በፍለጋ እንኳን የማይገኙ ናቸው። ጥቂቶቹም አገልግሎት ከሚሰጡበት የሚዘጉበት ጊዜ ይበልጣል፡፡ የትራፊክ ፍሰት በሚበዛባቸው አካባቢዎች፣ ቀላልና ደረቅ ቆሻሻ የሚጠራቀሙባቸው ቅርጫቶች (በአንዳንድ ድርጅቶች ተነሳሽነት የተቀመጡት ቅርጫቶች፣ በወሮበሎችና ራስ ወዳዶች እየተነቀሉ መወሰዳቸው ወይም አገልግሎት እንዳይሰጡ መደረጋቸው እንደተጠበቀ ሆኖ)፣ በአግባቡ ተደራጅተው አይገኙም፡፡
የሕንፃና የመንገድ ግንባታ፣ አስገዳጅ ደረጃዎች እንዳሉ ሲነገር እንሰማለን፡፡ ግን ምን ያህል ተፈፃሚ ሆነዋል? ያልተተገበረ ደንብና መመሪያ ሳይኖር  አይቀርም፡፡ ከቶ ስለ ምን የምንናገረውን ፈፅመን ለመገኘት እንቸገራለን?  መጀመር እንጂ መጨረስ ዳገት እንደሆነብን ሊቀር  ነው ማለት ነው?  መስተዳደሩ፣ እነዚህን ሕፀፆች ከማስወገድ ባለፈ፣ የከተሜነት ባህልና እሴቶች እንዲስፋፉ ከመገናኛ ብዙሃንና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት፣ የተጠናከረ የትምህርት ፕሮግራም ቀርፆ ሊተገብር ይገባዋል። በቀጣይ ግን አስገዳጅ ደንብና መመሪያዎችን ማውጣትና ተግባራዊ ማድረግ አለበት፡፡ አካባቢን የማስዋብና አረንጓዴ የማድረግ ስራ ሌላው ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነዉ፡፡ አሁን ያለው የከተማ መስፋፋት ምጣኔ፣ በዚህ ከቀጠለ ከተማዋ ሩቅ በማይባል ጊዜ፣ ለከፋ የአየር ብክለት እንደምትጋለጥና የሙቀት መጠኑም በእጅጉ እንደሚጨምር አንዳንድ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በአንዳንድ ክፍለ ከተሞች፣ እዚህም እዚያም የተወሰኑ ጥረቶች ቢደገረጉም ያልተደራጁ፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁና ቀጣይነት የሌላቸው ናቸዉ። በነገራችን ላይ እንደ  አንድ ግብር ከፋይና ሃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ፣ በጣም ከሚያስቆጩኝ ነገሮች አንዱ፣ ምን እየሰሩ እንደሆነ እንኳ በውል የማይታወቁ የመንግስት ተቋማትን ለማስቀጠል የሚወጣው ገንዘብ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት የመንግስት ተቋማት፣ በርካታ ሲሆኑ የደንብ ማስከበር አገልግሎትና የውበትና መናፈሻ ኤጀንሲ በምሳሌነት  ሊጠቀሱ ይችላሉ። የባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንን፣ ከዚሁ ጎራ ልትመድቧቸዉ ትችላላችሁ። እባካችሁ፤ በየወሩ ስለምትሰበስቡት ደሞዛችሁ ስትሉ ሥራችሁን በአግባቡ ስሩ፡፡
3ኛ) በመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማረጋገጥ፤
ለአዲስ አበባ መንገዶች መጎሳቆል፣ ለከተማዋ ውበት ማጣትና ለነዋሪዎች መጉላላት ዋነኛ ተጠያቂ ማን ነዉ? ብትሉኝ፣ ከሶስቱ ድርጅቶች ማለትም፡- ከመብራት ኃይል፣ ቴሌኮሚኒኬሽንና ውሃና ፍሳሽ አልወርድም። እርግጥ ነው የእነዚህ ድርጅቶች አገልግሎት በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡ ያለ እነርሱ ከተማንና ዘመናዊ አኗኗርን መመኘት አይታሰብም፡፡ ግን አንዱ የገነባውን ሌላው እያፈረሰ የሚቀጥለው እስከ መቼ ነው? ስለ ምን እነዚህ ድርጅቶች አቅደውና ተቀናጅተው መስራት አቃታቸው? እውነት ይህን ያህል ሀብታም ነን ማለት ነዉ? ለጥገና ወይም ለማስፋፋት መንገድ መቁረጥ ግድ ሊሆን ይችላል፤ ግን የፈረሰውን ወደነበረበት መመለስ ለምን አይቻልም? ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ያለበትስ ማነው? ይህ መስተዳደር ለዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሄ መፈለግ አለበት ብዬ አምናለሁ፤ እየሰሩ ማፍረስ መቆም አለበት፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ መታየት ያለበት የመንገዶች አገልግሎት ጉዳይ ነዉ። ለእግረኛ ወይም ለመኪና የተዘጋጁ መንገዶች ከታሰቡላቸው አላማ ዉጪ ለጎዳና ላይ ንግድ፣ ለግንባታ እቃዎች ማከማቻ፣ ለካፌ፣ ለወርክሾፕ አገልግሎት ሲውሉ ማየት የተለመደ ነወ፡፡ ይህን ጉዳይ ማንሳት አንዳንዶች እንደሚያስቡት ምቀኝነት አይደለም፡፡ ሰዎች ሰርተው ኑሮአቸውን ማሻሻላቸው፣ አለፍ ሲልም በግብር መልክ ለአገር አስተዋጽኦ ማድረጋቸዉ የሚበረታታ ጉዳይ ሆኖ፤ ሲሰሩም ሆነ ሲያተርፉ የሌሎችን ምቾትና ደህንነት በመጋፋት፣ የከተማውን ገፅታ በማበላሸት፤ ሱቅ ከፍተው፣ ሰራተኛ ቀጥረው፣ ቤት ተከራይተው በሚሰሩት ኪሣራ መሆን የለበትም፡፡ ደንብ አስከባሪው  ተቋም ሊሠራ የሚገባው ትልቅ ተግባር ይህ ነበር። አዲሱ ከንቲባ እየሰሩ ያልሆኑ ተቋማትን መፈተሽ ሳይኖርባቸዉ አይቀርም፤ ተጠያቂነት የሚባል ነገር የለማ - በሁለቱም ወገን።
4ኛ) ከተማዋን ከማናቸውም የድምጽ ብክለት በህግ መከላከል፤
ኢትዮጵያ የእምነት አገር ነች፤ በየምክንያቱ ወደ እምነት ተቋማት የሚተመውን ሕዝብ ብዛት ለተመለከተ፣”በእውነት ኢትዮጵያዊያን ሃይማኖተኞች ናቸው” ያሰኛል፡፡ የፈጣሪ መንፈስ የቀረበዉ ሆኖ ከመገኘት የላቀ ነገር የለምና፣ ይህ በጣም ጥሩ ነገር ነዉ። ስንቶቻችን የእምነቶቹን ትዕዛዝ በአግባቡ እየፈፀምን ነው? ስንቶቻችንስ የምንለውን ሆነን ተገኝተናል?--- ለጊዜው  ጥያቄዎቹ ይቆየንና ወደ ርዕሰ ጉዳያችን እንመለስ፡፡
ከተማችንን የሚያሳስበው ሌላው ዋና ጉዳይ የድምፅ ብክለት ነዉ፡፡ ሁሉም ቤተ-እምነቶች ማለት ይቻላል፣ ፉክክር በሚመስል ሁኔታ፣ ከተማዋን በድምፅ ማጉሊያ ሲቀውጧት ይዉላሉ፣ ያድራሉ፡፡ የዉጪ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ፣ እንደ ማሳሰቢያ የሚነገራቸው (ወይም ከተመለሱ በኋላ፣ እንደ አሉታዊ ትውስታ የሚነሱት) ከትራፊክ አደጋና ከልመና መስፋፋት ቀጥሎ ከቤተ- እምነቶች የሚወጣው አዋኪ ድምፅ ነው፡፡ የዚህ መጣጥፍ አዘጋጅ  አማኝ ነው፤ ግን እውነቱን ለመናገር ይህ ገደብ ያለፈ ከእምነት ተቋማት የሚነሳ የድምፅ ብክለት መቆም አለበት ከሚሉት ወገን ነው፡፡
የድምፅ ብክለት ጉዳይ ከተነሣ፣ በአስፈሪ ሁኔታ እየተስፋፋ ያለዉ ደግሞ ከጭፈራ (መሽታ) ቤቶችና ከጋራዦች የሚወጣው ድምፅ ነዉ። ዓላማው ቢለያይም ሁሉም የራሱን ፍላጎት ለማራመድ በትጋት እየሰራ ነዉ፡፡ በዚህ መሃል እየተጎዳ ያለዉ የከተማው ነዋሪና የከተማዉ ገፅታ በመሆናቸው መስተዳድሩ ከተቋማቱ ጋር ሊመክርበት ይገባል፡፡ እንደ  አንድ ዘመናዊ  ከተማ፤  አስገዳጅ የድምፅ ብክለት ደረጃ ወጥቶ፣ ሁሉም ህብረተሰብ እንዲያዉቀው ብቻ ሳይሆን የማስፈጸሚያ ስርዓት ሊዘረጋ ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ አዲሱ መስተዳደር፤ ድክመቶችንና ዉስንነቶችን መሸፋፈኑን ትቶ፣ ሥኬቶችን ብቻ በማጋነን ከመኩራራት ወጥቶ፣ ከህዝቡ ጋር በመተባበር፣ ለዘላቂና ሁለንተናዊ ለዉጥ ተግቶ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ በመንግስት ላይ ጣት መቀሰር ቀላል ነዉ፡፡ እኛ የከተማ ነዋሪዎችም በያገባኛልና በኃላፊነት መንፈስ፣በግልና በጋራ የሚጠበቅብንን ሃላፊነት መወጣት ይኖርብናል። ይህ እንዲሆን መንግስት (መስተዳደሩ) ነዋሪዎች፣ በተናጠልና በተደራጀ መልክ የሚደርጉትን ተሳትፎ ለማሳለጥ የሚያስችል፣ የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ ሊቀርፅ ይገባል፡፡ በዚህም ሳያበቃ፣ መሰረታዊ በሆኑ ከተማ አቀፍ ጉዳዮች፣ ከነዋሪዎቹ ጋር የጋራ መግባባት ለመፍጠር መስራት አለበት። በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ሲኖር፣ ለጋራ ዓላማ መሥራት ይከተላል፡፡
ከአዘጋጁ፡-   (ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡)




Read 1989 times