Saturday, 06 October 2018 10:00

'አርቲስት'፣ አትሌት'፣ 'ታዋቂ ሰው' እና...የጋዜጣ 'ፊለር' ሚና!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሀሳብ አለን… ለአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የዓመት እረፍት ይሰጣቸው። እንዴ … መከራቸውን በሉ እኮ! ማይክራፎን የያዝን ሁሉ መጀመሪያ የሚታዩን ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች’ ብቻ ሆኗል። እና… አለ አይደል… የዓመት ፈቃድ ቢሰጣቸው ይሻላል፤ አለበለዚያ  ከድካም የተነሳ ‘ሲክ ሊቭ’ ሊጠይቁ ይችላሉ!
በጋዜጣ ሥራ ላይ አንዳንድ ጊዜ በቂ ጽሁፍ ሳይኖር ይቀርና መሙያ ጽሁፎች ከዚህም ከዚያም ተለቃቅመው ሊገቡ ይችላሉ… ‘ፊለር’ እንላቸዋለን። እናማ.. ቴሌቪዥን ላይ የ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ’ ነዋሪዎች ሚና፣… አለ አይደል… ሀሳብ የመስጠት ሳይሆን እንደ ጋዜጣ ‘ፊለር’ ሊመስል ምንም አልቀረውም፡፡ (በነገራችን ላይ አርቲስቶች አካባቢ… “እነሱ ማናቸውና ነው!” የሚሉ አይነት ነገሮች እንዳሉ እየሰማን ነው፡፡ ነገርየውማ... አለ አይደል…ብዙ ጊዜ የሚታዩት የተለመዱት ፊቶች ናቸው የሚባል ነገር ሳይኖር አይቀርም፡፡ የምንወዛገብበት ነገር ያነሰን ይመስል ሌሎችም ‘እየተጨመሩልን’ ነው መሰለኝ!)
እናላችሁ… ለምሳሌ፣ “የመብራት መቆራረጥ እንዳማረራቸው አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ” አይነት ‘ፊለር’ ቢቀነስልን ሸጋ ይመስለናል! ድፍን አገር በመብራት ጉዳይ “እሪ!” እያለ፣ ለ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች’ ብቻ መስጠት ቀሺም ነው፡፡
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ አርቲስቶች በቃ ፈረንጅ እንደሚለው ‘ባይ ዲፎልት’ ቪአይፒ ሆኑ እንዴ! ትንሽ ግራ ስለገባን ነው፡፡ ቁርጡን እንወቅና እኛም ጠባያችንን እናስተካክላለን፡፡  እናማ… ሁሉም ነገር ላይ “አርቲስቶች በተገኙበት--”፣ “አትሌቶች በተገኙበት…” ምናምን የሚል ነገር ልክ አለ አይደል …“ያለበት ሁኔታ ነው ያለው-” እንደሚለው ተደጋገመብንሳ!
እናማ… አርቲስቶቹ በተለይ በማህበራዊ አገልግሎት፣ ችግረኞችን በመርዳት፣ ለአስፈላጊ ማህበራዊና መሰል ጉዳዮች ገንዘብ በማሰባሰብ ምናምን ብዙ ነገር ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ ታዋቂነታቸውን ለራሳቸው ‘ፕሮሞሽን’ ሳይሆን ለማህበረሰቡ ጥቅም ሊያውሉት ይችላሉ፡፡ ይህ ማለት ግን… እንደ ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች’ ሁሉም ቦታ ብቅ እያሉ፣ የጋዜጣ ‘ፊለር’ አይነት መሆን የለባቸውም፡፡
እሺ ይሁን… ግን ዋናው ሙያውስ! የአርቲስትነቱ ሥራ ይረሳና ቪአይፒነቱ ቦታውን ይይዛል  ብለን ስለፈራን ነው! ደግሞ አሁን ለእንትን ኮንሰርት ሞቅ ያለውን ከከፈልን እኮ ሁላችንም ቪአይፒ  መሆን እንችላለና!
“እንደሚታወቀው” እንላለን ጋዜጠኞች፣ የከተማችን የንጽህና ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በህብረተሰቡ ዘንድ አጅግ ተወዳጅ የሆነችውን አርቲስት እከሊትን አነጋግረናል፡፡
“አርቲስት እከሊት፤ መጀመሪያ በዚህ ጉዳይ አስተያየትሽን ልትሰጪን ፈቃደኛ ስለሆንሽ አመሰግናለሁ፡፡”
“እኔም አመሰግናለሁ፡፡”
“አዲስ አበባ እንደሚታወቀው የአፍሪካ መዲና፣ የ… (አንዴ ቆይማ፣ “ሥራ ነው ጭቅጭቅ! ምንድነው አንድን ነገር መቶና ሺህ ጊዜ መደጋገም! ይህንን መጨረሱ ‘ጊዜ’ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት መፈጸም ይሆናል፡፡)
“በከተማው የጽዳት ሁኔታ ላይ አስተያየትሽን ብትሰጪን…”
“በእውነቱ እኔን ሁልጊዜ እንቅልፍ የሚነሳኝን ጉዳይ ነው ያነሳህልኝ፡፡” (አንቺ ደግሞ! ለእንቅልፉ መጥፋት ተጠያቂው የአዲስ አበባ የጽዳት ጉዳይ ሳይሆን በትኩስነቱ ከተማ የደረሰው የባህር ዳሩ ‘ደረቁ ቂማ’ ሊሆን ይችላል፡፡ ‘ሲሉ ስለምንሰማ’ ነው!) ከዛማ እነዚያው የተለመዱት ሺህ ሰዎች፣ ሺህ ጊዜ ያሏቸው ነገሮች ይደገማሉ፡፡
እግረ መንገድ አንዳንድ ጊዜ ሚዲያዎች ላያ የምናያቸው ግዴለሽነት የሚመስሉ ነገሮች በዚህ ዘመን የሚጠበቁ አይደሉም፡፡ ከ‘ስክሪን’ ስር በጽሁፍ የሚንደረደሩት ዜናዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት አንድ ጣቢያ ላይ ፕሬዚዳንቱ የሆነ ልኡካን ቡድን ማነጋገራቸውን እያወራ፣ ከስር የነበረው የጽሁፍ መግለጫ ግን ልኡካኑን ያነጋገሯቸው ‘ፕሬዚዳንት ተሾመ’ ይላል። ቀላል ቢመስልም ቀላል ስህተት አይደለም፡፡ የሰዋሰው፣ የቃላትና የስርዓተ ነጥብ ችግሩንማ መተው ይሻላል፡፡
እኔ የምለው… እግረ መንገድ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው… እኛ ዘንድ አንድ ከመለመድ አልፎ ‘ሱስ’ የሆነ የሚመስል ነገር አለ፡፡ ሁላችንም ከተሰጠን ሥራ ግማሹን እንኳን ሳንሠራ እንዲጨበጨብልን እንፈልጋለን። “የመልካም አስተዳደር ያለህ” እያልን ወንበር ይዞ እያስጮኸን ያለው ሁሉ ጭብጨባ ይፈልጋል፡፡ ከሥራ አስኪያጅ እስከ ጥበቃ ሠራተኛው ያለው ሁሉ ጭብጨባ ይፈልጋል። ‘ሲንግል’ ለቃቂውም ገና ብቅ ከማለቱ ጭብጨባ ይፈልጋል፡፡ ‘የእንትን ወረዳ ምናምን የስራ ሂደት ሀላፊ’ ቢሮ ገብቶ ስለወጣ ብቻ አጨብጭቡልኝ ይላል፡፡ (እንደ ቀለበት መንገድ የሚጥመለመሉ መሥሪያ ቤቶችና የሥራ ሀላፊነቶች መጠሪያ ስም ይጠርልንማ!) አሁንም በየአካባቢው ጭብጨባ ትንሽ የበዛ እየመሰለን ነው፡፡ ጉሮሯችንን በስምንት መለኪያ ‘ዳግም’ አርሰን “የሁዋይት ሀውስን ወንበር በግፍ ነው የተቀማሁት” ለማለት እንደምንሞክረው ጠመም ያለውን ቀና ለማድረግ እንኳን ሳንሞክር … “ለሜሲ እንደዛ እጃችሁ እንትን እስኪመስል ስታጨበጭቡ ለእኔስ!” አይነት ነገር ለማለት ይዳዳናል፡፡
በአንድ ወቅት አንድ በጣም ሀይለኛ አንበሳ ጫካ ውስጥ ይኖር ነበር፡፡ ይህ አንበሳ የትኛውንም እንስሳ ሲያገኝ ያለ ልዩነት ይበላ ጀመር፡፡ በጫካው ያሉት እንስሳት በሙሉ ተሰበሰቡና “ምን ይሻላል?” ብለው መከሩ፡፡ ከዚያም በየቀኑ ከእየአንዳንዱ ዘር አንድ እንስሳ ብቻ እንዲበላ ሀሳብ ሊያቀርቡለት ተስማሙ፡፡ አንበሳውም በሃሳባቸው ተስማማ። ይህ ነገር ቀጠለና የጥንቸሎች ተራ ደረሰ፡፡ ጥንቸሎችም ከመሀላቸው በእድሜ ገፋ ያለውን መረጡና እንዲሄድ ነገሩት፡፡ አዛውንቱ ጥንቸል በብልህነቱም የታወቀ ነበር፡፡
ጥንቸሉም በጣም ዝግ ብሎ መንገድ ጀመረ። አንበሳውም ጥንቸሉ ሲዘገይበት ትእግስቱ ሊሟጠጥ ዳር ደረሰ፡፡ በንዴት ያገኘውን እንስሳ ሁሉ ለመብላት ወስኖ ሊንቀሳቀስ ሲል ጥንቸሉ ደረሰ፡፡ ዘሎ ሊከመርበት ሲልም “አትቸኩል፣ የቆየሁበትን ምክንያት ልንገርህ” አለው፡፡
አንበሳውም ፈቀደለት… “እኔ ብቻ ሳልሆን በርከት ያሉ ጥንቸሎች ወደ አንተ እየመጡ ሳለ አንድ የተቆጣ አንበሳ መንገድ ላይ አገኘንና ሁሉንም ሲበላ እኔ ብቻ ተረፍኩ፡፡ አንበሳው የጫካው ንጉሥ እኔ ነኝ እያለ እየፎከረ ነው” ይለዋል፡፡
ይህኛው አንበሳ በጣም ይናደድና ወደ እሱ እንዲወስደው ይነግረዋል፡፡ ብልሁ ጥንቸልም ወደ አንድ ኩሬ ይዞት ሄደ፡፡ ኩሬው አጠገብ ሲደርስም “ይኸውልህ፣” አለው፡፡ አንበሳው፤ ኩሬው ውስጥ የተቆጣ አንበሳ ያያል፡፡ የራሱ ምስል ነጸብራቅ መሆኑን ሳያውቅ ዘሎ ገባና ሰመጠ፡፡ በብልሁም ጥንቸል ምክንያት ጫካው ውስጥ ያሉ እንስሳት ኑሯቸውን በሰላም ቀጠሉ ይባላል፡፡
እኛም እንደ ብልሁ ጥንቸል የሆኑ ብልሆች ያስፈልጉናል፡፡ በብልህነት መጥፋት ብዙ ጥፋቶች እየደረሱ ነውና!
በነገራችን ላይ… የወደቀ ግንድ ምሳር ይበዛበታል የሚለው የሚሠራው በእርግጥም በእኛ አገር ነው። ወድቋላ!  ተነስቶ “ምን ነበር አሁን ያልከው?” አይልማ! ‘የሞተ በሬ መደብደብ’ የሚሉት ነገር እኮ አርቀን እንዳናይ የሆነ የምናምን ግንብ እየሆነብን ነው፡፡ ደግሞ ይሄ የዛሬውን ለማጣጣል ትናንትን እየቆፈሩና እየፈረፈሩ “ጉዱን አያችሁ!” አይነት ማሳጣት ‘ቦተሊካ’ እኮ ዘመኑ አልፎበታል … ወይም ያለፈበት ይመስለናል፡፡ ከሀያ አምስት ዓመት በፊት ያደረገውን እያስታወሰ ሰው መሀል… “እድሜ ለእኔ በል፣ እግሬ ላይ ወድቀህ ያቺን ሁለት መቶ ሀምሳ ብር ባልሰጥህ ኖሮ፣ ይሄኔ መንደር ለመንደር ትዞር ነበር” አይነት ነገር ቀሺም ነው፡፡
እናማ…እንደ ጋዜጣ ‘ፊለር’ እያገለገሉ ያሉ የሚመስሉ ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች’ ወይ የዓመት ፈቃድ ይሰጣቸው ወይ ደግሞ ለሚያቃጥሉት ካሎሪ መተኪያ ወተት ምናምን ይዘጋጅላቸው! “ይሞታል እንዴ!” እንዲል ሰዉ! ደግሞማ… ‘አንዳንድ አርቲስቶች፣ አትሌቶች፣ ‘ታዋቂ ሰዎች’…ሚናቸው የጋዜጣ ‘ፊለር’ አይነት ይሁን፣ አይሁን ልብ ቢሉ አሪፍ ነው…‘እንገነባዋለን ያሉት ስም፣ ቡናና ድራፍት ላይ ‘ቅድመ ታሪክ’ እና ‘ድህረ ታሪክ’ ሊሆን ይችላልና!
ደህና ሰንብቱልኝማ!



Read 2313 times