Sunday, 07 October 2018 00:00

“ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ”

Written by 
Rate this item
(11 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ከባድ የአገር ወረራ ሊካሄድ መሆኑ ይሰማና፣ ሰው ስጋት በስጋት ይሆናል፡፡ ዙሪያ ገባው ህዝብ መነጋገሪያው ይሄ ጉዳይ ይሆናል፡፡
ከሽማግሌዎቹ አንዱ፤
“በሰሜን በኩል እንሂድና ወደ ታች ወደ ምሥራቅ እንውረድ”
ሁለተኛው፤
“የለም የለም፤ ከምዕራብ ወደ ደቡብ ብንከባቸው ነው የሚያዋጣን”
ሶስተኛው፤
“ኧረ ኧረረ እረረ … ያማ በጭራሽ አይታሰብም፤ መሆን ያለበት ከደቡብ እንነሳና--- ዳር ዳሩን፣ አጥር ላጥር ተጉዘን ወደ ማህል መግባት ነው፡፡ ዋናው ያካሄድ ዘዴ ማበጀት ነው፡፡”
አራተኛው፤
“ሰሜንንም፣ ደቡብንም ምሥራቅንም፣ ምዕራብንም አካለላችሁ፡፡ ጠላት ግን የት ጋ እንደሆነ እንኳ አላነሳችሁም” አሉ፡፡
ሁሉም ግራ ተጋቡና ዝም አሉ፡፡
አንደኛው፤
“ችግራችን ይሄው ነው፡፡ ጦርነቱ የት ጋ እንደሆነ እንኳን ሳናውቅ ዘመቻ እንጀምራለን! ሳንደራጅ መሳሪያ እንወለውላለን፤ ሳናስብ እናውቃለን፡፡ ሳናውቅ ማሰብ እናቆማለን። ማሰብን እንገድፋለን፡፡ ያንን ብናውቅ፣ አገርን እየበደልን መሆኑን ተገንዝበን በጭራሽ አይፀፅተንም፡፡”
ሁለተኛው፤
“አሁን ወራሪ እየመጣብን ነው፡፡ ምን እናድርግ ብንባባል አይሻልም?”
ሦስተኛው፤
“ወራሪያችንማ ነገ ራሱ ነው፡፡ ቀኑ ነው፡፡”
በዚሁ ስብሰባው ተጠናቀቀና ወደ ምርጫ ሄዱ፡፡ የሰዎች ስሞች ተጠቁሞ፣ አንድ የጎበዝ አለቃና አስራ ሶስት ጎበዛዝት ተመረጡ፡፡
ጦርነቱ ተጀመረ፡፡ ተፋፋመ፡፡ ከግራም ከቀኝም ብዙ ሰው ወደቀ፡፡ በቀጠሉት ቀናትም ጦርነቶች ተካሄዱና በጠላት አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ የጎበዝ አለቃውም ወደ ቀዬው ተመለሰ።
የመንደሩ ሰው የጦርነቱን ውጤት ለማወቅ ልቡ ተንጠልጥሎ ነበርና፤
“የጦርነቱ መጨረሻ ምን ሆነ?” ሲል ጠየቀው፡፡
የጎበዝ አለቃውም፤
“አይ፤ እንደፈራነው አይደለም፡፡ እኔ በሰላም ተመልሻለሁ” አለ፡፡
*   *   *
ጉዟችን ዛሬም ረጂም ነው፡፡ አውሎ ነፋሱ ረግቦ፣ አቧራው መሬት ሲወርድ፣ መጠያየቅ መጀመሩ አይቀሬ ነው፡፡
“ቀጣይ ጉዟችን ወዴት ነው?”
“የራሳችን ጥያቄ አለን ወይስ መሪዎች እንደ መሩን መነዳት ነው?”
“ስለ ፖለቲካው ብዙ አወራን፡፡ የኢኮኖሚው የታመቀ መገለጫ ነውና ፖለቲካ፤ ኢኮኖሚው ምን ይዋጠው ሳንል ወዴት እንደርሳለን?”
“ሁሉን ነገር መንግሥት ላይ ላክከን አንችለውም፡፡ የተቃዋሚዎች ድርሻ ምንድን ነው? የሲቪል ተቋማትስ? የህዝብስ? የየአንዳንዱ ዜጋስ? ሁሉም የየድርሻውን እንዴት ይውሰድ?”
ሌሎችም ጥያቄዎች አሉ፡፡ እንጠይቃቸው፡፡ እንጠያየቅባቸው፡፡ እንጠየቅባቸው። ሁሉንም ነገር “ዓለም አላፊ ነው፡፡ መልክ ረጋፊ ነው፤ ፎቶግራፍ ቀሪ ነው” ብለን አንዘልቀውም፡፡ ከልብ እናስብ፡፡ እራሳችንን የምንወደውን ያህል አገራችንን እንውደድ፡፡ ድህነትን ለመዋጋት ወደ ጦርነቱ እንግባ!
ብዙ ግብረ-ገብነት፤ ከመሰላቸትና ውሎ አድሮም ከመናናቅ አያልፍም፡፡ መሪ ከተናቀና ተመሪ ከናጠጠ፣ ተከታይ አደጋ አይቀሬ ነው፡፡ ለማንም የማይበጅ ሥርዓተ - አልበኝነትን አውርሶን የሚሄድ፣ አልሮ ሂያጅ ግርግር ብቻ ነው የሚተርፈን፡፡ አመፅም አይደለም። ሥር ነቀል አብዮትም አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ክለሳም (ሪቪዥኒዝምም) አይደለም፡፡ እዚህ ውስጥ ስለ ሪፎርም ማሰብ፣ ስለ ሊብራሊዝም ማሰብ ዘበት ይሆናል፡፡ “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” የሚለው ተረት ፣ ቤት የሚመታው እዚህ ጋ ነው፡፡ ይሄን መቼም እናስብ። “ትንሽ ሥጋ እንደ መርፌ ትወጋ”ንም ልብ እንበል!
ለአገርና ለህዝብ ወደሚበጀው  በሰላም ያሸጋግረን!!

Read 8192 times