Sunday, 07 October 2018 00:00

ተቃዋሚዎች ከኢህአዴግ ጉባኤ ምን ይጠብቃሉ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ሳምንት አራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች በየፊናቸው፣ የየራሳቸውን ጉባኤዎች ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን ከስያሜና የደንብ ማሻሻያዎች በተጨማሪ፣ አዳዲስ ወጣቶችን ወደ አመራር ደረጃ
በማምጣት፣ ከሌላው ጊዜ በተለየ ውጤት መጠናቀቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባለፉት ሦስት ቀናት ደግሞ አገሪቱን ለ28 ዓመታት የመራው ገዢ ፓርቲ፤ ለራሱም ሆነ ለአገሪቱ ወሳኝ መሆኑ
የተነገረለትን የኢህአዴግ 11ኛ ጉባኤ፣ “ሀገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል በሃዋሳ ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ የድርጅቱ ሊቀ መንበርና ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ
የጉባኤውን መከፈት ባበሰሩበት ንግግራቸው፤ “የአገራችንን መጻኢ ጊዜ የሚወስን ታሪካዊ ጉባኤ ነው” ብለው ነበር፡፡
ለመሆኑ ከኢህአዴግ ድርጅቶች ጉባኤ ምን አዲስ ውጤት ተገኘ? ከኢህአዴግ ጉባኤስ ምን ዓይነት ውጤት ይጠበቃል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ የተቃዋሚ
ፓርቲ አመራሮች አስተያየቶችን አሰባስቦ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

“ህዝቡን የሚመጥንአመራር ይፈጠራል የሚልእምነት አለኝ”
ዶ/ር ጫኔ ከበደ (የኢዴፓ ፕሬዚዳንት)

ኦህዴድ ስም ቀይሮ ኦዴፓ፣ ብአዴንም አዴፓ ብሏል፡፡ ህወሓት ደግሞ ባለበት ነው የቀጠለው፡፡ ለኔ በተለይ ብአዴን፤ ህዝቡ ጥያቄና ቅሬታ ሲያቀርብባቸው የነበሩ አመራሮችን ያወረደበት ሁኔታ አለ፡፡ ሌሎቹም በየራሳቸው ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ያስችለናል ያሉትን ለውጥ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ብዙዎቹ ከድርጅቶቹ የተወገዱት ሰዎች በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት በሰፊው የሚታሙ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር፣ ድርጅቶቹ ራሳቸውን ለማጥራትና በአዲስ አመራር ለመቅረብ፣ ቀላል የማይባል ርቀት መጓዛቸውን ማየት ይቻላል፡፡ የፓርቲ የስም ለውጥ ማድረጋቸውም፣ ከዚህ በፊት በሄዱበት መንገድ ላለመሄድ ፍላጎት እንዳላቸው ያመላክታል፡፡ ከዚህ በፊት ንቅናቄ፣ ድርጅት ነበር የሚባሉት፤ አሁን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ነን እያሉ ነው፡፡ ፓርቲ ለመባል ሲወስኑ፣ ህዝብን በስፋት ለማሳተፍ አቅደዋል ማለት ነው፡፡ በአንድ ፓርቲ ስር ለመጠቃለል ማቀዳቸውንም ያመለክታል፡፡
ሁሉም ድርጅቶች፤ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ለማሳተፍ ያስችለናል ያሉትን የደንብ ማሻሻያ አድርገዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ ለህዝቡ ቀናነታቸውን ለማሳየት እየሞከሩ ነው ያሉት፡፡ ይሄ በበጎ የሚታይ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን እየጋበዙ ነው፡፡ ይሄ ለመቀራረብ ያላቸውን ፍላጎት ያሳያል፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ፣ ወደፊት የፖለቲካ ምህዳሩ ሊሰፋ ይችላል የሚል ተስፋ እንድናሳድር ያደርገናል፡፡ ኢህአዴግ በጠቅላላ ጉባኤው፣ በተለይ ለዲሞክራሲ መጎልበት አጋዥ የሆኑ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን ያሳልፋል የሚል ግምት ነው ያለኝ፡፡ የኢህአዴግ ስብሰባ፤ የኢትዮጵያን ህዝብ የሚመጥን አመራር ተዋቅሮ ይወጣበታል የሚልም እምነት አለኝ፡፡ ለውጡ ቁርጠኛ አመራር ይፈልጋል፡፡ ከጉባኤው በኋላ ቁርጠኛ አመራር  ይፈጠራል የሚል እምነት አለኝ፡፡

---------------------------
“ከኢህአዴግ ጉባኤ ብዙአልጠብቅም”
አቶ የሸዋስ አሰፋ (የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር)

ከአራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ጉባኤ፣ የሁለቱ ማለትም፣ የኦዴፓ እና የአዴፓ ጉባኤ ነው የተለየ  ውጤት ያመጣው፡፡ ቀሪዎቹ ሁለቱ ግን ምንም ያደረጉት ለውጥ የለም፡፡ ብአዴን እና ኦህዴድ  ወደ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲነት ተለውጠዋል፡፡
ህወሓት እና ደኢህዴን በዚህ ደረጃ ቢለወጡ ነበር ኢህአዴግ፣ እንደ ኢህአዴግ ተለውጧል ሊባል የሚችለው፡፡ በኦህዴድ እና ብአዴን በኩል የተደረገው ለውጥ ጥሩ ጅምር ነው፡፡ ይህ ማለት ግን አሁን ባደረገው ጉባኤ ኢህአዴግ፣ የህዝቡን ጥያቄ መመለስ የሚያስችለው ቁመና ላይ ደርሷል ማለት አይደለም፡፡ የህዝብን ጥያቄ አሟልቶ ለመመለስ፣ የፖሊሲ ለውጥና ሁለንተናዊ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ኢህአዴግ ግን  ያንን አላደረገም፡፡
ድርጅቱ ጎታች ናቸው ያላቸውን አመራሮች እያራገፈ መምጣቱ፣ ለሀገር ጤንነት መልካም ነው። ነገር ግን አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚሉት ርዕዮተ-ዓለም ለሃገር አይበጅም፡፡ ሃገሪቱ የደረሰችበትንና የህዝቡን ጥያቄ የሚመጥን አይደለም፡፡ ይሄን ቢገመግሙና ማሻሻያ ቢያደርጉ ኖሮ፣ የለውጡ ጭላንጭል የበለጠ ይፈካ ነበር፡፡ የኢህአዴግ ጉባኤ፤ የአራቱ ድርጅቶች ጉባኤ ውጤት ከመሆኑ አንፃር ብዙ ለውጥ አልጠብቅም፡፡ ህወሓት “ገና 1980ዎቹ ላይ ነኝ፤ ተዉኝ” ብሏል፡፡ ደኢህዴንም የፖለቲካ አቋሙ አልጠራም፡፡ ስለዚህ ከኢህአዴግ ጉባኤ ብዙ አልጠብቅም፡፡

------------------------

“በህወሓት በኩል ምንምማሻሻያ አልተደረገም”
አቶ አምዶም ገ/ሥላሴ (የአረና ቃል አቀባ

 አራቱ ድርጅቶች ያደረጉት ጉባኤ የተራራቀ ውጤት የነበረው ነው፡፡ በተለይ የህወሓት እና የሌሎቹ በእጅጉ የተራራቀ ሆኖ ነው ያገኘሁት። ህወሓት በነበረበት ነው እየሄደ ያለው፡፡ ኦህዴድ በአንጻሩ የተማሩና ወጣቶችን ወደ ሥራ አስፈጻሚነት አምጥቷል፡፡ ስሙንም አድሷል፡፡ በህወሓት በኩል ግን ይሄ አልተደረገም፡፡ የተካሄደ ግምገማም የለም፡፡ ለአመራርነት ብቁ አይደሉም የተባሉ ሳይቀር የህወሓት መሪነትን እንደያዙ ነው። ኦህዴድ ግን ብዙ ተራማጅ እርምጃዎችን የወሰደ ይመስላል፡፡
ብአዴንም በሙከራ ደረጃ እንጂ እንደ ኦህዴድ አልሆነም፡፡ በርዕዮተ-ዓለምም ድርጅቶቹ የተለያዩ ይመስላል፡፡ ህወሓት አብዮታዊ ዲሞክራሲን ይዤ እቀጥላለሁ ብሏል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ እንፈትሸዋለን እያሉ ነው፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ኢህአዴግ ሊፈርስም ይችላል፡፡ አሊያም ህወሓት ከግንባሩ ሊወጣ የሚችልበት ዕድል አለ፡፡
አብዮታዊ ዲሞክራሲ ህገ-መንግስቱን የሚጻረር፣ አፋኝ  ርዕዮተ-ዓለም ነው፡፡ ይሄ ርዕዮተ-ዓለም በሃዋሳው የኢህአዴግ ጉባኤ ቢለወጥ መልካም ነው፡፡ ርዕዮተ-ዓለሙ ካልተለወጠ ግን ለውጡ በግለሰቦች ደረጃ እንጂ በአስተሳሰብ አይኖርም ማለት ነው፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሲለወጥ ነው የዲሞክራሲ ተቋማት ነጻ ሆነው ሊዋቀሩ የሚችሉት፡፡ ከዚህ አንጻር፣ ኢህአዴግ ይሄን ርዕዮተ-ዓለም መለወጥ አለበት ማለት ነው፡፡   

----------------------

“ለለውጡ የተቀመጠፍኖተ ካርታ የለም”
አቶ ሙላቱ ገመቹ (የኦፌኮ ም/ሊቀ መንበር)

የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ያደረጓቸው ጉባኤዎች፤ ስርአትና ሲስተምን የሚቀይር ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ለህዝብ ጥያቄ መልስ መስጠት የሚችለው የፖሊሲ፣ የአሰራር ለውጥ እንጂ የግለሰቦች ሽግሽግ ብቻ አይደለም፡፡ ሰዎች በነበረው የፓርቲ ሲስተም ላይ ቢቀያየሩ፣ እምብዛም ጉልህ ለውጥ ላያመጡ ይችላሉ። ምናልባት በግላቸው ቀናዎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን ሲስተሙ ካልተቀየረ፣ ወደዱም ጠሉም፣እነሱም  የሲስተሙ ተገዢዎች ናቸው፡፡ ኢህአዴግ በሰፊው ያሰበበት አይመስለኝም፡፡ ዝም ብሎ ለውጥ ለውጥ ይላል እንጂ ምን አይነት ለውጥ? በምን ጉዳይ ላይ ነው ለውጡ የሚያስፈልገው? በሚለው ዙሪያ እስካሁን በየጉባኤዎቹ የተቀመጠ ፍኖተ ካርታ የለም፡፡ ሀገሪቱን ወደ ዲሞክራሲ የሚያሻግር ግልፅ ፍኖተ ካርታ መቀመጥ አለበት፡፡
ኢህአዴግ ለውጡን ለማስቀጠልና ለውጡን ለመቀልበስ በተሰለፉ ሁለት ኃይሎች መሃል እንዳለ ነው ሁልጊዜ የሚናገረው፡፡ የጉባኤዎቹ ቅኝትም በዚህ የተሞላ ነው፡፡ ለውጡ ከተጀመረ ወዲህ  የዜጎች ግድያ፣ ማፈናቀል፣ ሙስና አልተወገዱም፡፡ ዛሬም ድርጅቱ በራሱ ጉዳይ ብቻ እንደተጠመደ ነው፡፡ ጥያቄዎች ዛሬም በእንጥልጥል ላይ ናቸው፡፡ ሰዎችን ያፈናቀሉ፣ ያስገደሉ ባለስልጣናት ወይም ግለሰቦች ተጠያቂ አልሆኑም፡፡ ሁለት ሚሊዮን ገደማ ዜጎች ሲፈናቀሉ፣ ኃላፊነት ወስዶ ህግ ፊት የቀረበ ወገን አላየንም፡፡ የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ለእነዚህ ጉዳዮች ትኩረት መንፈጉ፣ዛሬም ድርጅቱ፣ የህዝብን ጥያቄ በተግባራዊ ምላሽ ለመፍታት ብርቱ አለመሆኑን አመላክቷል፡፡ በራሱ የውስጥ ጉዳይ ብቻ መጠመዱ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ከሚታየው አለመረጋጋት አንፃር፣ ተገቢ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡

Read 4138 times