Sunday, 07 October 2018 00:00

ለቤኒሻንጉል ተፈናቃዮች መንገድ በመዘጋቱ እርዳታ ማቅረብ አልተቻለም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

· “ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመ ነው”    
· ግጭቱ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ተሰግቷል እየተፈፀመ ነው”

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተደራጁ ታጣቂዎች በሰነዘሩት ጥቃት ከ60 በላይ ዜጎች መገደላቸውን ተከትሎ፣ በተከሰተ ግጭት በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞና አማራ ተወላጆች የተፈናቀሉ  ሲሆን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ፤ በክልሉ ከፍተኛ መፈናቀልና የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመ መሆኑን ጠቁሞ፤ መንግስት አፋጣኝ እርምጃ ካልወሰደ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡ በአካባቢው ግጭቱና የሰብአዊ መብት ጥሰቱ መቀጠሉንም ኮሚሽኑ አስታውቋል። በሌላ በኩል፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንገድ በመቆረጡና በታጣቂዎች በመዘጋጋቱ ምክንያት ተፈናቅለው ለሚገኙ ከ82 ሺህ በላይ ዜጎች ተገቢውን ሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ አለመቻሉን የክልሉ መንግስት ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያሱ እና ሊጃንፎ በተባሉት የክልሉ ሁለት ወረዳዎች፣ አንፃራዊ መረጋጋት በመስፈኑ የተወሰኑ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ መሆኑን የተናገሩት የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ዘላለም ያደታ፤ በአንፃሩ አጋሎሜቲ በተባለው ወረዳ ትንኮሳዎችና ግጭቶች አሁንም አልፎ አልፎ እየተከሰቱ ነው ብለዋል፡፡
መረጋጋት ባለባቸው አካባቢዎች የበለጠ የማረጋጋት ስራ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዘላለም፤ የመንገዶች መዘጋጋት ግን ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ ከፍተኛ እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ “መንገድ ሙሉ ለሙሉ በተለይ ከአሶሳ ወደ ከማሹ የሚወስደው ተቆርጧል” ያሉት ኃላፊው “ለፀጥታ አካላት የእለት ራሽን እየታደለ ያለው በሄሊኮፕተር ነው” ብለዋል፡፡
ይሄን ችግር ለመፍታት መንግስት ከፍተኛ እርብርብ እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዘላለም፤ በቤኒሻንጉል ክልል ውስጥ ተፈናቅለው የሰብአዊ እርዳታ የሚፈልጉት ከ28 ሺ 600 በላይ ናቸው ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ ከክልሉ ተፈናቅለው በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ከ100 ሺ በላይ መሆናቸውን የገለፀው የአደጋ ስጋት
አመራር ኮሚሽን፤ ለተጎጂዎች ከ15 ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እርዳታ ወደ አካባቢው መላኩን አስታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዋናነት የማረጋጋት ስራ ለመስራት ጥረት እየተደረገ
መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፤ ዘላለም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ተጠርጣሪዎችን ለህግ የማቅረብና ስራ አለመጀመሩን ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ የኦነግን አርማ የያዙ ታጣቂዎች ፈፀሙት በተባለው ጥቃት ከ60 በላይ ዜጎች መገደላቸውን ተከትሎ በተነሳ ግጭት ከቤኒሻንጉል የተለያዩ አካባቢዎች የኦሮሞ፣ የአማራና ሌሎች

ብሔረሰብ ተወላጆች መፈናቀላቸው ታውቋል፡፡

Read 6523 times