Saturday, 29 September 2018 14:40

የአፍሪካ የፋሽን ሳምንት 2018 ዐውደ ርዕይ ሰኞ በሚሌኒየም አዳራሽ ይከፈታል

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

  ጅምላ ሻጮች፣ ቸርቻሪዎች፣ ቡቲኮችና የመስተንግዶ ሰጪ ተቋማት የሚሳተፉበት “4ኛው የሶርሲንግና ፋሽን ሳምንት 2018 - ኢትዮጵያ ዐውደ ርዕይ” ለአራት ቀናት ከመስከረም 21-24/2011 በሚሌኒየም አዳራሽ ይካሄዳል፡፡
በዚህ ዐውደ ርዕይ በጥጥ፣ በጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ በቆዳ ውጤቶች፣ በቴክኖሎጂ አቅርቦትና በቤት ውስጥ ማስዋብ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን፤ ከ250 የሚበልጡ ዓለም አቀፍ አምራቾችና ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ተቋማት ምርቶቻቸውንና ፈጠራዎቻቸውን ከመላው ዓለም ለተውጣጡ ነጋዴዎችና ገበያ አፈላላጊዎች እንደሚያቀርቡ አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡
በዐውደ ርዕዩ ላይ የግብፅ፣ የኢትዮጵያ፣ የቻይናና የፓኪስታን ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን፤ በአፍሪካ ሶርሲንግ ፋሽን ሳምንት 2018 ከምሥራቅ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን ከመላዋ አፍሪካ አኅጉር ለሚመጡ አምራቾች ምቹ መድረክ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በዚህ ዐውደ ርዕይ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ12 የሚበልጡ የደቡብ አፍሪካ የቆዳ ውጤት አምራቾች የሙያ ክህሎቶቻቸውንና ምርቶቻቸውን ለታዋቂ ዓለም አቀፍ የፋሽን ሸማቾች ያቀርባሉ ተብሏል፡፡
በልዩነት በሚካሄደው የWalk For Business ፕሮጀክት ከደቡባዊ፣ ምዕራባዊና ምሥራቃዊ አፍሪካ የተመረጡ ከ25 የሚበልጡ የላቁ ዲዛይነሮችን ከዓለም አቀፍ ሸማቾችና የፋሽን ብራንድ አቅራቢዎች ጋር ለቀጣይ ትብብር የሚያንደረድሩ ግንኙነትና ትስስሮች እንደሚፈጠር ለማወቅ ተችሏል፡፡
የአፍሪካ የሶርሲንግና ፋሽን ሳምንት ብቸኛው የአኅጉሪቱ የቴክኖሎጂና የንግድ ትርዒት ሲሆን፤ ለአልባሳትና ጨርቃጨርቅ ለማቅለሚያና ለፊኒሺንግ ሥራዎች የሚያገለግሉ ኬሚካሎችን ለማምረትና ለማቀነባበር የሚረዱ ማሽኖች እንዲሁም የጨርቃጨርቅ አልባሳት፣ የቆዳ ውጤቶች፣ ካልሲዎች፣ የቤት ውስጥ ማስዋቢያዎች፣ አዳዲስ ዲዛይነሮችና የጨርቃጨርቅ ቴክኖሎጂ ይቀርባሉ ተብሏል፡፡
የምርት ዘላቂነትና የትራንስፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በሚሉ መሪ ቃሎች የሚታወቀው ዐውደ-ርዕይ፤ በአፍሪካ ነፃ ንግድ ላይ በሞሪሸስ፣ በማዳጋስካር፣ በኬንያና በኢትዮጵያ ባሉት የኢንቨስትመንት ዕድሎች ላይ የፓናል ውይይት የሚካሄድ ሲሆን፤ የየሀገራቱ መንግሥታትም በሀገሮቻቸው ስላለው ወቅታዊ ሁኔታና ስለሚሰጡት ድጋፍ መረጃ እንደሚሰጡ ታውቋል፡፡
የአፍሪካ የሶርሲንግ ፋሽን ሳምንት በሜሴ ፍራንክፈርት ኤግዚቢሽን፣ በጂ ኤም ቢ ኤች፣ በኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ ልማት ኢንስቲትዩትና በኢትዮጵያ ጨርቅና አልባሳት አምራቾች ማኅበር በጥምረት የሚዘጋጅ ሲሆን፤ አስተባባሪዎቹ በጀርመንና ኬንያ የሚገኙ የንግድና የንግድ ትርዒት አዘጋጅ ድርጅቶች መሆናቸው ታውቋል።  

Read 1742 times