Saturday, 29 September 2018 14:36

ለተሳከረው የአገራችን ትምህርት መፍትሄው፣... “ከእውቀት የራቀ ትምህርት” ነው?

Written by  ዮሃስ ሰ
Rate this item
(3 votes)

• በ3 ዓመት ጥናት የመጣው የትምህርት ሚኒስቴር “ፍኖተካርታ”፣... አስገራሚ “አዳዲስ ግኝቶች” እና “የመፍትሄ ሃሳቦች”!
  • “ከእውቀት የራቀ ትምህርት”? ይሄማ፣ እውቀትን የማጣጣል ነባር የውድቀት መንስኤ ነው - የሙያና የማወቅ ክህሎትን
   የሚያጠፋ)
  • “ፊደልን ማሳወቅ” የሚያጥላላ የተሳከረ ሃሳብ፣ የማንበብ ክህሎትን የሚፈጥር ሳይሆን ይብሱኑን የሚያጠፋ ነው።
  • የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያ ተብለው ከተዘረዘሩት 9 ነጥቦች መካከል፣ አንዳቸውም አዲስ ሃሳብ አይደሉም።
  • 7ቱ ነጥቦች፣... ሁለት ነባር ሃሳቦችን እንደ አዲስና እንደ ልዩ ሃሳብ በድግግሞሽ የሚዘረዝሩ ነጥቦች ናቸው።
  • አምስቴ በድግግሞሽ የቀረበውና ዋነኛው ሃሳብ፣ አዲስ አይደለም። ለዓመታት ሲሰበክና ሲተገበር የቆየ ሃሳብ ነው።
  • የማሻሻያ ሃሳብ ተብሎ መቅረቡስ? ለዓመታት የተተገበረ ዋነኛው የውድቀት መንስኤ ነው እንደ መፍትሄ የቀረበው።

     ከሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል፣ ግማሽ ያህሉ (ማለትም 50%)፣ አንዲት አጭር ዓረፍተነገር አንብበው ለመገንዘብ የሚያስችል እውቀት የላቸውም።
ሩብ (25%) ያህሉ ደግሞ፣ አንዲትም ቃል ማንበብ አይችሉም። አዎ፣ አሳዛኝ ውድቀት ነው። ግን፣ በእጣፈንታ ሰበብ የወረደ ክፉ መዓት፣ ባልታወቀ ፍጡር የተወረወረ እርግማን አይደለም። ያው፣... ትምህርትን ማበላሸት፣... መዘዝ አለው። “ከእውቀት የራቀ የማወቅ ክህሎትን እናስተምራለን” በሚል የተሳከረ አስተሳሰብ የተቃኘ ትምህርት፣... ከውድቀት ውጭ ሌላ ውጤት ሊኖረው አይችልም።
ማንበብ የማይችሉ ተማሪዎች እየበዙ መምጣታቸው፣... የተዓምርና የትንግርት ጉዳይ አይደለም። ዱብዳ ሳይሆን፣ “እውቀትን ሳይሆን የማወቅ ችሎታን እናስተምራለን” በሚለው የተሳከረ አስተሳሰብ አማካኝነት ተፀንሶ በበርካታ ዓመታት ተግባር አማካኝነት እየገዘፈ የመጣ ውድቀት ነው - የአገራችን የትምህርት ቀውስ።
“ፊደል ማወቅን የሚያጥላላ የንባብ ትምህርት”፣... “ፊደልን ከማሳወቅ የፀዳ፣ የንባብ ክህሎት”... በሚሉ ፈሊጦች ነው፣ ብዙ ተማሪዎች ለዘመናዊ መሃይምነት እየተዳረጉ የሚገኙት። ልጆች፣ ፊደል እንዳይማሩና እንዳያውቁ ማድረግ.... እንደ ጀግንነት መቆጠሩ ነው ችግሩ። ልጆች፣ ትምህርት ሲጀምሩ፣... በዘፈቀደና በደመነፍስ፣... ቃላትንና ዓረፍተነገሮችን በማንበብ እንዲጀምሩ የሚመኝ ሥርዓተ ትምህርት ነው፣ የአሳዛኙ ውድቀት መንስኤ።
ይሄንን የመቀየር ሃሳብ አልቀረበም - ፍኖተካርታ ተብሎ በሚታወቀው የትምህርት ሚኒስቴር ሰነድ።
ውድቀትን የሚያስወግድ የመፍትሄ ሃሳብ ለማቅረብ ይቅርና... ችግርን በትንሹ የሚያቃልል የመፍትሄ ሃሳብ እንኳ በሰነዱ ውስጥ የለም። በተቃራኒው፣ ውድቀትን በሚያባብሱና በተሳከሩ ሃሳቦች የታጨቀ ሰነድ ነው፣ እንደ ፍቱን መድሃኒት፣ እንደ ሁነኛ መፍትሄ የቀረበው። (ፍኖተካርታ” በሚል ስያሜ የሚታወቀውን የትምህርት ሚኒስቴር ሰነድ ለማዘጋጀት፣ ጥናት የተጀመረው ከሦስት ዓመት በፊት በ2007 ዓ.ም እንደሆነ ተጠቅሷል። “የትምህርትና ሥልጠና ችግሮቻችን እና የመፍትሔ አቅጣጫዎች” በሚል ርዕስ በ84 ገፅ የቀረበ ሰነድ ነው)።

“እውቀት በዛ” - የትምህርት ሚኒስቴር ጭንቀት!
በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ዙሪያ ዋነኛ የሥርዓተ-ትምህርት ችግር ተደርጎ፣ በትምህርት ሚኒስቴር ሰነድ ውስጥ የተጠቀሰው ዋና ችግር ምንድነው?
ሥርዓተ ትምህርቱ... “ሥነ-ውበትን  በሚገባ  ያላካተተ፣  በንድፈ-ሃሳብ  የታጨቀ፣  የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት የጐላ የባህሪ ለውጥ ያላመጣ፣ ለብዝሃነት የሰጠው ቦታ አናሳ መሆን፣ ለሙያ ትምህርቶችና ለፈጠራ ቦታ የሰጠ አይደለም” ይላል ሰነዱ (ገፅ 24)።
እንግዲህ ይሄው ነው፣ እንደ ዋነኛ የሥርዓተ ትምህርት ችግር፣ እንደ አዲስ ትልቅ “ግኝት” ተደርጎ በትምህርት ሚኒስቴር ሰነድ ውስጥ የቀረበው።
“ሥነ-ውበት” ነው ያነሰብን? ይሄ፣ በጣም አሳፋሪ ቀልድ ይመስላል። ሥነ-ውበት ትምህርት ማነሱ ነው ዋናው ችግር?
ኧረ ወደ ሂሊናችን እንመለስ። እንዴ.... እዚህችው አገራችን ውስጥ ነው፣ እንዲህ የሚቀለደው?
ከሦስተኛና ከአራተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል ሩብ ያህሉ፣... “2 ሲባዛ በ4” ስንት እንደሆነ እንደማያውቁ በግላጭ በሚታይባት አገር? ማንበብ የማይችሉና ፊደል ለይተው የማያውቁ ተማሪዎች እየበዙ በመጡባት አገር? መፃፍ... ለብዙ ልጆች የማይደፈር ትንግርት እየሆነባቸው? ያለ ንባብና ያለ ፅሁፍ፣... ያለ መደመርና ማባዛት ደግሞ፣... ሌላው ትምህርት ሁሉ፣ ትርፉ መደናቆር ብቻ እንደሆነ እየታወቀ...   
በየዓመቱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ልጆችን እየመዘገቡ የሚቀበሉ የአገሪቱ የመንግስት ትምህርት ቤቶች፣... ከሦስት አመታት በኋላና ከቢሊዮን ብሮች ወጪ በኋላ የሚያቀርቡልን ውጤት ምንድነው?
ከሁለት ሚሊዮን ተማሪዎች መካከል፣ ሩብ ያህሉ በትምህርት መቀጠል የማይችሉ፣ ሩብ ያህሉ ደግሞ አንዲት ቃል እንኳ ማንበብ የማይችሉ ተማሪዎችን የሚያሳቅፍ የትምህርት ቀውስ ውስጥ የተዘፈቀ አገር ላይ ሆነን ነው እንዲህ የሚቀለደው? ከ50% በላይ የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች፣... ዓረፍተነገር አንብበው መገንዘብ የማይችሉ መሆናቸው እየታየ?
ለትምህርት ሚኒስቴር አጥኚዎች የሚታያቸው የሥርዓተ ትምህርት ችግር ግን፣ “ሥነ-ውበት በሚገባ ያላካተተ...” መሆኑ ነው? “ትምህርቱ በንድፈ-ሃሳብና በእውቀት የታጨቀ ነው” የሚል እውቀትን የሚያጣጥል ዘመቻ? በትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት፣ “ብዝሃነት” የሚል ጭፍን ስብከት ከዳር እስከ መሃል ተስፋፍቶ በተንሰራፋባት አገር ውስጥ፣... በዚህም እየተቃወሰችና እየተፍረከረች ወደለየለት የትርምስ እንጦሮጦስ ለመውረድ አፋፍ ላይ የበደረሰች አገር ውስጥ፣... የአገሪቱ ትምህርት ዋና ችግር፣ “ለብዝሃነት የሰጠው ቦታ አናሳ መሆኑ” ነው ይለናል? ጭፍንነትና ዘረኝነትን የሚያስፋፋ “ብዝሃነት” የሚለውን ነባር ጭፍን ስብከት ለመድገም ነው የሚፈለገው? ከዚያም በላይ ነው... ለመድገም ብቻ ሳይሆን እያገዘፈ እያጋጋለ ለማባባስም ጭምር ነው።
“የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት የጐላ የባህሪ ለውጥ ያላመጣ” ነው ሲልስ ምን ማለቱ ነው? በጭፍን፣ “ብዝሃነት” እያለ የሚሰብክ ነባሩ የሥነ ዜጋና የሥነ ምግባር ትምህርት እንዲቀየር አስቦ ነው? አይደለም። ለዚያም ነው፣ 84 ገፅ በቀረበው ሰነድ ውስጥ፣ አንድም ቦታ ላይ የማሻሻያ ሃሳብ ያላቀረበው። ዋና ችግር እንደሆነ የሚልፅ ሰነድ፣ የሥነ ምግባር ትምህርት ይዘትና አቀራረብ እንዴት ቢለወጥ እንደሚሻል፣... ቅጥ የያዘ የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያ ሃሳብ ባያቀርብ እንኳ፣ ቢያንስ ቢያንስ አንዲት ብጣሽ የመፍትሄ ሃሳብ፣... ለወጉ ያህል መጥቀስ አልነበረበትም? አላደረገውም - (ነባሩን ከማባባስ በስተቀር ማለቴ ነው)።
በገፅ 66-67 የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያ ተብለው የቀረቡትን 9 ነጥቦች መመልከት ትችላላችሁ። ለነገሩ፣ ነጥቦቹ በደንብ ሲታዩ፣ አብዛኞቹ እርባና የሌላቸው ላለፉት 25 ዓመታት እልፍ ጊዜ ሲነገሩ የቆዩ አባባሎች ናቸው። ለምሳሌ፣ በ1994 ዓ.ም የትምህርት ፖሊሲ አተገባበር በሚል ርዕስ በትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀ ሰነድ፣ አገራዊ አግባብነት እና አለማቀፋዊ ተወዳዳሪነት በማለት ይናገራል። አሁን እንደ አዲስ ግኝት የማሻሻያ ሃሳብ ተብሎ የቀረበውን 5ኛ ነጥብ ደግሞ አንብቡ።
“በሁሉም ደረጃዎች/እርከኖች፣ አገራዊ አግባብ ያለው በአለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ ሥርአተ ትምህርት መቅረጽ” ይላል። በቃ? አዎ ይሄው ነው - ቃል በቃል። (“በአለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ” የሚለው የሰዋሰው ጉድለትም ጭምር ማለቴ ነው)። ከዚያስ?
ይሄው ነባር ሃሳብ፣ ከሁለት ሦስት ቃላት ለውጥ በስተቀር፣ እንደገና 8ኛ የማሻሻያ ሃሳብ ተብሎ ቀርቧል።...
“በሁሉም ደረጃዎች አገራዊ ተዛማጅነት ያላቸው እና አለም አቀፋዊነት ተወዳዳሪነትን የሚያረጋግጥ ሥርአተ ትምህርት በሁሉም ደረጃዎች መቅረጽ” 8ኛው የማሻሻያ ሃሳብ።
(ይሄም ቃል በቃል ነው ያሰፈርኩት - ከነስህተቶቹ። “በሁሉም ደረጃዎች”... በሚል ጀምሮ፣ “በሁሉም ደረጃዎች መቅረጽ” የሚል መሆኑ ብቻ አይደለም።... ሌሎቹ የሰዋሰው ስህተቶችም ጭምር ማለቴ ነው።)
የትምህርትን ጥራት ለማሻሻል ተብሎ በቀረበ ሰነድ ውስጥ፣ የዚህን ያህል የመዝረክረክ ስህተትና ድግግሞሽ መፈጠሩ አሳፋሪ ቢሆንም፣... የሚረባ ሃሳብ ለማቅረብ አለመሆኑም ይበልጥ ያሳዝናል (ለዓመታት የተነገረ ነባርና ድፍን አባባልን፣ እንደ አዲስ የማሻሻያ ሃሳብ ለማቅረብ)።
ዋነኛው የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያ ሃሳብ፣ 4ኛ ነጥብ ሆኖ የሰፈረው አባባል ነው - ይሄኛውም ነጥብ ግን አዲስ የመፍትሄ ሃሳብ አይደለም። አዲስ ሳይሆን ለዓመታት ሲሰበክና ሲተገበር የነበረ አባባል ነው፤... ትክክለኛ የመፍትሄ ሃሳብ ሳይሆን፣ ትምህርትንና እውቀትን ለዓመታት ሲሸረሸር የቆየ የተሳከረ ውድቀት ሃሳብ ነው።
“የሥርዓተ ትምህርቱ ዋነኛ ችግር፣ በእውቀት ላይ ያተኮረ መሆኑ ነው” የሚለውን የተሳከረ ሃሳብ፣ እንዳለፉት ዓመታት የሙጢኝ ይዞ ለመቀጠል ማቀድ፣... እንዴት የመፍትሄ ሃሳብ ይሆናል? እውቀት ላይ ከማተኮር ይልቅ፣... የትምህርት ትኩረት ወደ ክህሎት እንዲቀየር ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ነው ማሻሻያ ተብሎ የቀረበው ሃሳብ። ሌሎቹ የማሻሻያ ሃሳቦችም ተመሳሳይ ሃሳብ የያዙ ናቸው - “እውቀት ሳይሆን ክህሎት፣ እውቀት ሳይሆን የሙያ ክህሎት...” የሚል ሃሳብ፣ በተለያዩ አምስት ነጥቦች እንደ አዲስ እየተደጋገመ የማንበብ ያህል ነው።
እንግዲህ አስቡት። ባለፉት 15 ዓመታ ሲሰበክና ሲተገበር የቆየውን አባባል፣ እንደ አዲስ እና እንደ ዋነኛ የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያ ሃሳብ ሆኖ ነው የቀረበው። ነገር ግን፣ “ክህሎት” ላይ ማተኮር ማለት፣... ምን ማለት እንደሆነ ለመግለፅ፣ ሰነዱ አንድም ቦታ ላይ ቅንጣት ሙከራ አያደርግም። እንደተለመደው፣ በሚያምታታ መንገድ ሁለት መልእክቶችን ለማስለተላለፍ የሚያገለግል አባባል እንደሆነ ጠፍቷቸው ነው? ሁለቱም መልእክቶች ደግሞ፣ እውቀትን የማጣጣልና የማጥላላት መልእክቶች መሆናቸውስ?
በአንድ በኩል፣ “ቲዎሪና ፕራክቲስ” የተሰኘውን ፈሊጥ በመከተል፣ “እውቀትን ማስጨበጥ ሳይሆን ሙያን ማስተማር፣... የሙያ ክህሎትን ማስያዝ ነው የትምህርት ዓላማ”... የሚል መልእክት    ያስተላልፋሉ። (ያለ እውቀት የህክምና ሙያ፣ ያለ እውቀት የምህንድስናም ሆነ የአናፂነት ሙያ የሚኖር ይመስል?)።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ እውቀትና የማወቅ ችሎታ እርስበርስ ተቃራኒ ጠላቶች የሆኑ ይመስል፣ አንዱ ያለሌላው የሚኖር ይመስል፣... “የትምህርት አላማ፣ እውቀትን ለማስጨበጥ ሳይሆን፣ የማወቅ ክህሎትን ለማስያዝ ያለመ መሆን አለበት” የሚል መልእክት ያስተላልፋሉ - እውቀትን የሚያጣጥል። ለምሳሌ ያህል፣ “ፊደልን ሳናሳውቅ፣ የማንበብ ክህሎትን እናስተምራለን” በሚል ፈሊጥ፣ ማንበብ የማይችሉ ተማሪዎችን ማበራከት እንደማለት ነው። እውቀትን የሚያጣጥል ፈሊጥ፣ “የትምህርት አላማ፣ የማንበብ እውቀትንም ሆነ ክህሎትን ማሳጣት ነው” ከሚል ትርጉምና በተግባርም አሁን ከምናየውን የትምህርት ቀውስ ውጭ ሌላ ትርጉምና ውጤት የለውም።

Read 5852 times