Saturday, 29 September 2018 14:37

ሬጌ ሮቢክስ ስፖርትም ዳንስም!

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)


   ጃማይካዊቷ ዜላ ጌይል አፍሪካ ግሪፍትዝ በኢትዮጵያ መኖር ከጀመረች ከ8 ዓመታት በላይ ሆኗታል፡፡ በእንግሊዝ ሳውዝሃምፐተን ከሚገኘው ዩኒቨርስቲ ኦፍ ዊንቸስተር በዳንስ ሙያ ማሰትሬት ዲግሪዋን ያገኘች ሲሆን በዳንስ አሰልጣኝነት እና አስተማሪነት በሳንፎርድ ኢንተርናሽናል ስኩል፤ በላዮንሃርት፡ በማያ እና በአንድነት አካዳሚዎች ስታገለግል ቆይታለች፡፡ ባለፈው ሳምንት  ከክሁል ሆሊስቲክ ዴቨሎፕመንት ማዕከል ጋር በመተባበር  ‹‹ኢነር ዚል ሬጌ ሮቢክስ›› የተባለውን ልዩ ስልጠና አዲስ አበባ ውስጥ መስጠት ጀምራለች፡፡
ስልጠናው የአካል ብቃት፤ የኤሮቢክስ እንቅስቃሴዎችን ከልዩ የሬጌ ዳንሶች ጋር በማዋሃድ የሚሰራበር የሬጌ ሮቢክስ ነው፡፡ ባለፈው ሰሞን ደምበል አካባቢ በሚገኘው ሬቲና ህንፃ 9ኛ ፎቅ ላይ የሬጌ ሮቢክስ ስልጠናው ሲጀመር፤ ዲፕሎማቶች፤ መሃንዲሶች፤ የዮጋ፤ የአፍሮቢት እና የአፍሮ ሬጌ ዳንስ አሰልጣኞችና..ሌሎችም ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡
በተለያዩ የአዲስ አበባ ስፍራዎች በየሳምንቱ እሁድ በሚቀጥለው ልዩ ስልጠናው የመጀመርያ ቀን ተሳትፎዬ እንደታዘብኩት ‹‹ሬጌ ሮቢክስ›› በጣም የሚያዝናና፤ ሙሉ ሰውነትን የሚያፍታታ፤ አዕምሮን የሚያነቃ እና ቀልጣፋ የሚያደርግ አዝናኝ ስፖርትና ዳንስ መሆኑን ነው፡፡  የዳንስ አሰልጣኟ  ዜላ ጌይል አፍሪካ ግሪፍትዝ   ‹‹ ሬጌ ሮቢክስ›› በመላው ኢትዮጵያ ለማስፋፋት በአዲስ ዓመት መነሳቷን  በማስመልከት ከስፖርት አድማስ ጋር ይህን ልዩ ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡

     ከጃማይካ ወደ እንግሊዝ ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ
ዜላ ጌይል አፍሪካ ግሪፍትዝ ትውልዷ በጃማይካ ነው። ወላጆቿ  በጃማይካ የሬጌ ሙዚቃ ኢንዱስትሪ በተለያዩ ሙያዎች በማገልገል ልዩ ከበሬታን ያተረፉ ናቸው፡፡ አባቷ በ1970ዎቹ በጃማይካ የሙዚቃ ኢንዱስትሪና በሬጌ  ዙርያ በመፃፍ የታወቁ ፈርቀዳጅ ጋዜጠኛ ሲሆኑ፤ በተለይ በጃማይካ እና ራስተፈርያኖች ኦፊሴላዊ ቋንቋ ‹‹ፓቶዋ›› በመፃፍ ታሪክ የሰሩ ናቸው። እናቷ ደግሞ የማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽን ባለሙያ ነበሩ፡፡ በጃማይካ በሚገኘውና የቦብ ማርሌይ በሆነው ታፍ ጎንግ ስቱድዮ ከ1978 ጀምሮ ለአምስት ዓመታት የሰሩ እና በተወሰኑ የቦብ ማርሌይ አልበሞች ህትመት እና ፕሮሞሽን ላይ ሰርተዋል፡፡ በሬጌው ዓለም ከሚታወቁ ፈርቀዳጅ ቤተሰቦቿ ዜላ የተወለደችው ቦብ ማርሌይ ከዚህ ዓለም እንደተለየ ነበር፡፡ መላው ቤተሰቧ ከሬጌ ሙዚቃ ጋር ባለው ትስስር ገና ከልጅነቷ ጀምሮ ከሙዚቃው ጋር በፍቅር አድጋበታለች፡፡ በተለይ ግን እናቷ በጃማይካ የሬጌ ሙዚቃ መስራታቸው፤ በሬጌ ባህልና የዳንስ ስልቶች ልዩ  ትኩረት ስለነበራቸው ዜላ ታዳጊ ሆና የዳንስ ፍቅር እንዲኖራት አስተዋፅኦ ነበረው። በኪንግስተን ከተማ በሚዘጋጁ የተለያዩ የሙዚቃ ዝግጅቶች እና ልዩ ልዩ ፌስቲቫሎች ላይ  ዜላ ደግሞ ከእናቷ ዱካ ስር አትጠፋም ነበር፡፡ በየትያትር ቤቱ እና በየሙዚቃ ፌስቲቫሉ ላይ ሁሌም የሚማርካት ዳንሶቹ እንደነበሩ ታስታውሳለች፡፡ ስለዚህም ገና ህፃን ልጅ ሆና ጨዋታዋ እና ጉጉቷ ለዳንስ ነበር፡፡ አባቷ እና እናቷ ይህን ተረድተው ገና 5 ዓመት እንደሞላት ፕሮፌሽናል የዳንስ ማስተማርያ ተቋም አስመዘገቧት። ስምንት ዓመቷን ስትደፍን ዜላ የተለያየ ውዝዋዜ የምትችል ምርጥ ዳንሰኛ ሆናለች፡፡ በቤተሰቧ ውስጥ በተለያዩ ድግሶች፤ የመዝናኛ ጉዞዎች እና ፓርቲዎች ገና ታዳጊ ብትሆንም ሁሉንም አድማቂ ኮከብ እንደነበረች  ለስፖርት አድማስ ስትናገር፤ ዳንስ በማይጠገብ ሁኔታ እንደምትጫወት፤ የምታውቃቸውን ዳንሶች ለእኩያ ዘመዶቿን ታለማምድ እንደነበርና በዚህ ባህርያዋም ጓደኞቿ፤ ቤተሰቦቿ ሌሎች የሚያውቋት ሁሉ ይወዷት እና ያደንቋት እንደነበር በማስታወስ ነው፡፡
ዜላ እና መላው ቤተሰቧ ከጃማይካ በመውጣት ቀጣይ ኑራቸውን ያደረጉት በእንግሊዝ ከተማ ለንደን ነበር፡፡ ወላጆቿ ይህን ውሳኔ ያሳለፉት የቤተሰባቸውን ኑሮ ለማሻሻል እና በተለይ ደግሞ ዜላ የዳንስ ሙያዋን በከፍተኛ ደረጃ ተምራ እንዲሳካላት በማሰባቸው ነበር። ስለዚህም በእንግሊዝ ቆይታቸው በሳውዝሃምፐተን ከሚገኘው ዩኒቨርስቲ ኦፍ ዊንቸስተር በዳንስ ሙያ ማስትሬት ዲግሪዋን እንድታገኝና ለተወሰኑ ዓመታትም በዳንስ አሰልጣኝነትና አስተማሪነት የምትሰራበትን እድል ፈጥረውላታል፡፡
ሬጌ ሮቢክስ መቼ እና እንዴት ተፈጠረ…
ጃማይካዊቷ ዜላ ጌይል አፍሪካ ግሪፍትስ ‹‹ሬጌ ሮቢክስ››  ብላ በሰየመችው ልዩ የዳንስና ኤሮቢክስ እንቅስቃሴ ለመስራት የተነሳሳችው ከ15 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ‹‹ሬጌ ሮቢክስ›› በሬጌ ሙዚቃ አጃቢነት ልዩ የሬጌ ዳንስ ችሎታ ኃይልና ፈጠራን ከአካል ብቃትና ከኤሮቢክስ እንቅስቃሴዎች ጋር ያጣመረ ነው፡፡ ዜላ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀችው ‹‹ሬጌ ሮቢክስ›› ላይ በሙሉ አቅም መስራት የጀመረችው በ2012 እኤአ ላይ ከስድስት ዓመታት በፊት ነው፡፡ ከጃማይካ ወደ እንግሊዝ ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ ከገባች በኋላ፡፡ ከስምንት ዓመት በፊት በ2010 እኤአ ላይ ነዋሪነቷን ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ስታደርግ ለሁለት ዓመታት  በአዲስ አበባ በሚገኙ የአካል ብቃት ማሰልጠኛ ጂሞች በአሰልጣኝነት እየሰራች ነበር፡፡ የሬጌ ሮቢክስ በወቅቱ እንደዝንባሌ የምትሰራውን ሬጌ ሮቢክስ በምታሳድግበት ሁኔታ ላይ ማሰቧ ግን አልቀረም። በአካል ብቃት አሰልጣኝነቷና በዳንስ ባለሙያነቷ ከሚያውቋት ኢትዮጵያውያን  መካከል ብዙዎቹ ሴት ሆና በዚያ መስክ መሰማራቷ ያስደንቃቸው ነበር። አንዳንዶች ደግሞ በተለይ ከጃማይካ መምጣቷን ምክንያት አድርገው በየጊዜው የሬጌ ዳንስ እና ሌሎች የውዝዋዜ ስልቶችን እንድታለማምዳቸው ይጠይቋታል፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ በየጂሞቹ የሚሰሩ የአካል ብቃትና የኤሮቢክስ እንቅስቃሴዎች በፈጣንና በኤሌክትሮኒክስ ሙዚቃ ብቻ የታጀቡ መሆናቸው አስተውላለች፡፡  ምናልባትም ፈጣን ሙዚቃዎች ካሎሪ በፍጥነት ለማቃጠል ያግዛሉ፤ ወይንም በኤሮቢክስ እንቅስቃሴ ላይ ከውስጥ ከፍ ያለ ሃይል ለማመንጨት ፈጣን ሙዚቃዎች በመለመዳቸው ይሆናል፡፡ ስለሆነም ከላይ የተጠቀሱትን ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ያስገባችው ዜላ ጌል አፍሪካ ግሪፍትዝ በራሷ መንገድ አዲስ ነገር ለመፍጠር ትነሳሳለች። ሬጌ ሮቢክስን ስትፈጥረው በኤሮብኪስ ዙርያ ያሉትን ሁኔታዎች በሚቃረኑ አዳዲስ ሙከራዎች ነው። በመጀመርያ የሬጌ ሮቢክስ ልዩ የስልጠና መርሃ ግብሮችን ለመፍጠር የአካል ብቃት እና የኤሮቢክስ እንቅስቃሴዎችን ከሬጌ የዳንስ ስልቶች ጋር አዋሃደች። በለስላሳ የሬጌ ሙዚቃዎች ታጅቦ የሚጀመሩና በፈጣን ሬጌ ሙዚቃ የሚያልቁ መርሃ ግብሮች ናቸው፡፡ ሬጌ ሮቢክስ የሬጌ ሙዚቃና ዳንስ፤ የአካል ብቃት እና የኤሮቢክስ እንቅስቃሴዎችን ያዋሃደ ሆኖም ተፈጠረ። ‹‹ሬጌ ሮቢክስ ሙሉ ሙሉ አዲስ ፈጠራ ነው፡፡ ልዩ የሚያደርገውም ሙሉ ተክለሰውነትን ቀልጣፋ እና ጠንካራ የሚያደርግ ስለሆነ ነው፡፡ ሬጌ ሮቢክስ ለሁሉም የሰውነት ክፍሎች የሚሆን እንቅስቃሴ ነው። በሁሉም የሰውነት ክፍሎች ያሉትን ጡንቻዎች ያንቀሳቅሳል፤ ያነቃቃል፡፡ ራሱን የቻለ የዳንስ ስልት እንጅ ከየትኛውም የሬጌ ወይንም የዳንስ ሆል ስልት ጋር የሚመሳሰል አይደለም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሬጌ ሙዚቃ አዲስ አቅጣጫ ባህልም የፈጠርኩበት ነው።›› በማለት ለስፖርት አድማስ ያብራራችው ዜላ ጌል አፍሪካ ግሪፍትዝ  ሬጌ ሮቢክስ፤ ከአዕምሮና ሃሳብ ጋር እንቅስቃሴዎችን የሚያቀናጅና የሚያዋህድ፤ ጠንካራ መንፈስ ያለው ስብዕናን የሚሰጥ እንዲሁም በአግባቡ የተደራጀ የሰውነት አቋም እና አኳኋንን የሚያጎናፅፍ ነው ትላለች፡፡
በሬጌ ሮቢክስ የሬጌ ሙዚቃ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡  እንደ አካል ብቃትእና የኤሮቢክስ እንቅስቃሴ የሚደረጉት ዳንሶች በሬጌ የሙዚቃ ቅንብር መዝናናትን፤ የሬጌ ሙዚቃ ስንኞች ያዘሏቸውን መልዕክቶች እየሰሙ መነቃቃትን እንዲሁም መላ ሰውነትን  ዜማዊ ሂደት ባላቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ መቆየትን የሚፈጥር ነው፡፡ ስለዚህም ከላይ በተዘረዘሩት የሬጌ ሮቢክስ ባህርያትና ዓላማዎች ላይ በማተኮር በኢትዮጵያ ኑሯዋን የቀጠለችው ዜላ፤ ሬጌ ሮቢክስን ከእለት ከእለት ጉዳዮቿ ዋናው አድርጋው ቆይታለች፡፡ በአካል ብቃት አሰልጣኝነት እንዲሁም በተለያዩ አካዳሚዎች ታዳጊዎችን ዳንስ በማስተማር ያገኛቸውን ልምዶች መነሻዋ አድርጋለች፡፡ ከዚያ ውጭ  በቂ ግዜ ሰጥታ ሰፊ ልምምድና ጥናት በማድረግ በሬጌ ሮቢክስ ራሷን አበቃች። ከዚያ በኋላ በመላው ኢትዮጵያ፤ አፍሪካ፤ ካረቢያንና …ይህን ፈጠራዋን ለማስፋፋት በቂ ምክንያቶች ነበሯት፡፡ ሬጌ ሮቢክስ በሬጌ ሙዚቃ ዓለም አቀፍ የእድገት ሂደት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት አምናበታለች፡፡ በአሜሪካ እና በእንግሊዝ በተመሳሳይ የሬጌ ሮቢክስ በመፍጠር የተደረጉ ሙከራዎችንም መገምገም ነበረባት፡፡ በሁለቱም አገራት የተለመደው ሬጌ ሮቢክስ  ከወገብ በታች ያሉ የሰውነት ክፍሎችን በሚያንቀሳቅስ ሁኔታ የተወሰነ ስለነበር ሙሉ የሰውነት ክፍሎችን የሚያንቀሳቅሰው የእሷ ሬጌ ሮቢክስ እንደሚለይ አረጋገጠች፡፡  ስለዚህም ዜላ ፈጠራዋን ‹‹ ኢነር ዚል ሬጌ ሮቢክስ›› በሚል ስያሜ እንዲለይ አድርጋ ጀመረችው፡፡  በአካል ብቃት ስልጠና እና በኤሮቢክስ ዙርያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ሁኔታ በስፋት መመርመሯ እንደ ብራንድ የምትመካበት ደረጃ አድርሷታል፡፡ በአጠቃላይ ሬጌ ሮቢክስን በይፋ ማስተማርና ማሰልጠንን በአዲስ አበባ ከመጀመሯ በፊት ቢያንስ ለሶስት ዓመታት ተዘጋጅታ ነው፡፡
ስፖርት፤ ዳንስ ወይንስ ሁለቱም…
ሬጌ ሮቢክስ  ለተሟላ የሰውነት ጥንካሬ፤ የአካል ብቃትና ቅልጥፍና በሚኖረው አስተዋፅኦ ከስፖርት ጋር ይቀራረባል። በተጨማሪም  እንደ ዮጋ በሁለገብ እንቅስቃሴ ሙሉ ሰውነትን የሚያሰራ እና አዕምሮን የሚያተጋም ነው፡፡ በተለይ በፈታኝ የአካል ብቃት  እና ከፍተኛ ትኩረት እና ትጋት በሚጠይቁ የኤሮቢክስ እንቅስቃሴዎች ለመስራት ለተቸገሩ ደግሞ አማራጭ ስፖርት ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፤ ኤሮቢክስና ዳንስን አዋህዶ የሚከናወን በመሆኑም ሬጌ ሮቢክስን የሚያዝናና ስፖርት አድርጎታል- ዜላ ጌል አፍሪካ ለስፖርት አድማስ እንደምታስረዳው፡፡ በሬጌ ሮቢክስ ላይ የሚተገበሩ እንቅስቃሴዎች ከባህላዊው የኤሮቢክስ የተወሰኑት ተውሰደው ወደ ዳንስ ስቴፖች ከተቀየሩ በኋላ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ሬጌ ሮቢክስ ላይ ከባድና የአካል ብቃት እና የኤሮቢክስ እንቅስቃሴ ለመስራት የማይችሉ እና ፍላጎት ለሌላቸው፤ ለጤናማ ተክለሰውነት እና ስብዕና አዝናኝ እንቅስቃሴዎችን ብቻ ለሚፈልጉ ልዩ አማራጭ ስፖርት ይሆናል፡፡
ሬጌ ሮቢክስ የአካል ብቃት እና የኤሮቢክስ እንቅስቃሴን ማካተቱ እና በሬጌ ሙዚቃ በመታጀቡ ከስፖርት ይልቅ አዝናኝ ዳንስ ወደ መሆኑ አያዘነብልም ወይ በሚል ከስፖርት አድማስ ጥያቄ የቀረበላት የዳንስ አሰልጣኝ እና አስተማሪ ዜላ ጌል ስትመልስ‹‹ ሬጌ ሮቢክስ ስፖርትም መዝናኛም ነው፡፡ ስፖርትና ዳንስ አንድ ሆነውበታል፡፡ ዳንስ፤ ኤሮቢክስ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማጣመሩ ልዩ ባህርይው ነው። ሬጌ ሮቢክስን ከማስተምራቸውና ከማሰለጥናቸው መካከል ፕሮፌሽናል ዳንሰኞች እንዲሁም ፕሮፌሽናል አትሌቶች እና ስፖርተኞች ይገኙበታል፡፡›› ብላለች። በተጨማሪም በስዊዘርላንድ ከቴኳንዶ ስፖርተኞች ጋር የሰራችበት ልምድ ለስፖርቱ የቀረበ መሆኑን እንዳረጋገጠላት ገልፃለች፡፡
ሬጌ ሮቢክስን ከ8 ዓመት ጀምሮ ለታዳጊዎች፤ ለወጣቶች እና ለአዋቂዎች በሁለቱም ፆታዎች እንደምታሰለጥን ለስፖርት አድማስ የምትገልፀው ዜላ፤ ፕሮፌሽናል አትሌቶች በተለይ ከውድድር በፊት ለሚያደርጉት የአዕምሮ ዝግጅት፤ በልምምድ የሚፈጠርባቸውን ጫና ለማቅለል እንዲሁም አዕምሮዋቸውንና የሰውነት ክፍሎቻቸውን በማቀናጀት ውጤታማ የሚሆኑበትን እድል የሚያሰፋ መሆኑን ትጠቁማለች፡፡ የሬጌ ሮቢክስ እንቅስቃሴ በየእለቱ ለአንድ ሰዓት የሚከናወን ሲሆን ሰልጣኞች በእንቅስቃሴው ሙሉ ብቃት እንዲኖራቸው ከ1 ወር በላይ መሰልጠንና ልምምድ ማድረግ እንደሚኖርባቸውም ትመክራለች፡፡
የሬጌ ሮቢክስ ሙዚቃዎች
ዜላ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀችው ሬጌ ሮቢክስን የፈጠረችበት ዋንኛ አላማ የጃማይካ እና የካረቢያን ሬጌ ሙዚቃዎች፤ ባህሎችና፤ የዳንስ አይነቶች ለማስተዋወቅ እና በተለየ ደረጃ ለማሳደግ ነው፡፡ ዜላ ሬጌ ሮቢክስን በኢትዮጵያ ውስጥ በመፍጠር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት ስትነሳ የትውልድ አገሯን ከማስተዋወቅም በላይ፤ በአካል ብቃት ማሰልጠኛ እና በኤሮቢክስ ስፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ አዋህዶ አዲስ የስልጠና እና የልምምድ መስክ ለማካሄድ እና በቢዝነስ ደረጃም ለመንቀሳቀስ እንደሚቻል አምናበት ነው፡፡
‹‹ሬጌ ሮቢክስ የጃማይካን ሬጌ ሙዚቃና ባህል ለማስተዋወቅ የምሰራው ቢሆንም በኢትዮጵያ ኑሮዬ የጀመርኩትና በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስፋፋበት ደረጃ ላይ የደረስኩበት መሆኑ በጣም ያኮራኛል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ አስታዋውቄው መስራት ከጀመርኩ በኋላ በአካል ብቃት እና በኤሮቢክስ ስልጠና ውስጥ ለማያልፉ የህብረተሰብ ክፍሎች አማራጭ መፍጠሬም ያስደስተኛል፡፡ ምንም እንኳን አሁን በሬጌ ሮቢክስ ላይ የምጠቀማቸው የሬጌ ሙዚቃዎች ከጃማይካ የተወሰዱ ቢሆንም ወደፊት በአማርኛ የተሰሩ የሬጌ ሙዚቃዎችን በመጠቀም ለማሰራት ማቀዴም ለኢትዮጵያ ያለውን አስተዋፅኦ ያመለክታል፡፡›› በማለት በሙያዋ ለኢትዮጵያ እያበረከተችው ያለውን አስተዋፅኦ አስገንዝባለች፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ ሬጌ ሮቢክስን በምስራቅ አፍሪካ ለማስፋፋትም ጥረት ማድረጓን እንዲሁም በቅርብ ዓመታት ወደ ኬንያ እና ታንዛኒያ በመሄድ የሰራችባቸውን ልምዶች እና በሁለቱ አገራት የሚገኙ የሬጌ ሙዚቀኞች እና ዘፈኖቻቸውን ለመጠቀም እንደሞከረችም  ጠቅሳለች፡፡
ሬጌ ሮቢክስ ስሙ እንደሚያመለክተው በተለይ የጃማይካ ኦርጅናል የሬጌ ሙዚቃዎችን እንደማጀቢያ በመጠቀም ይሰራበታል፡፡ ዜላ ስራዋን ለማስተዋወቅ በምትጠቀምባቸው የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በዚህ በኩል እንደተሳካላት የሚያረጋግጡ መረጃዎች አሉ፡፡ ታዋቂዎቹ ጃማይካዊ ሲዝላ ካሌንጂ ፤ አንቶኒ ቢ እና ሌሎችም  በአዲስ አበባ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ልዩ የሬጌ አብዮት በማድነቅ መስክረውላታል።  በሌላ በኩል እውቅ የረጌ ሙዚቀኞች ከጃማይካ ለሬጌ ሮቢክስ በተለይ ልዩ የማጀቢያ ሙዚቃዎች የሰሩላት ሲሆን ከእነሱም መካከል ዮቲ ራስ፤ ጃህ ዋዋ፤ ፕሪንስ ካዚያህ፤ አሊያህ ኑንስ… ይጠቀሳሉ። የሬጌ ሙዚቀኞች የሬጌ ሮቢክስ ሙዚቃዎች በዜማ ስልታቸውእና ምታቸው የሚስቡ፤ በስንኞቻቸው ይዘት ሞራል የሚሰጡ፣ የሚያበረታቱ እና የሚያነቃቁ ናቸው፡፡ በየዘፈኖቹ በሚረዱትና እና በሚናገሩት ቋንቋ የሚሰሟቸው DO NOT GIVE  UP, Keep going, you can do it,…. አይነት ስንኞችና ሃረጎች የሬጌ ሮቢክስ ሰዎች እንቅስቃሴያቸውን በትጋት እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል። ልዩ ተመስጥኦዎችን ይፈጥርላቸዋል፡፡ የመንፈስ ጥንካሬ ይሰጣቸዋል፡፡
የሬጌ ሮቢክስ ልምዶችና ተመክሮዎች
ዜላ ጌል አፍሪካ ግሪፍትዝ፤ በዳንስ አሰልጣኝነት እና አስተማሪነት በሳንፎርድ ኢንተርናሽናል ስኩል፤ በላዮንሃርት፡ በማያ እና በአንድነት አካዳሚዎች ስታገለግል ቆይታለች። በሬጌ ሮቢክስ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰራችባቸው ልምዶች ደግሞ በተለይ የሚጠቀሱት ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር የሰራችባቸው ናቸው።  ባለፉት ሁለት አመታት በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫ እና በአውሮፓ ህብረት በሚደገፈው የህፃናት ሩጫ ላይ ከውድድሮቹ በፊት የዜላ ሬጌ ሮቢክስ እንቅስቃሴዎች ማሟሟቂያዎች ነበሩ፡፡ ባለፈው ዓመት በላንጋኖ ተካሂዶ በነበረው ‹‹ዘ ግሬት ኢትዮጵያን ሳውንድ ሲስተም ፌስቲቫል›› ላይም ሬጌ ሮቢክስ መቅረቡም ይታወሳል፡፡
ሬጌ ሮቢክስ ወደፊት
ዜላ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀችው ሬጌ ሮቢክስን በተለያዩ ሁኔታዎች ለማሳደግ ከፍተኛ ፍላጎት አላት። በመጀመርያ ደረጃ  በቴሌቭዥን የጠዋት ፕሮግራም ይዛ በመቅረብ ሬጌ ሮቢክስን ለማሰልጠን እንደምትፈልግ ስትናገር ይህን ማሳካት ከቻለች ሰልጣኞቿን በማብዛት በላቀ ደረጃ የምትሰራበትን ሁኔታ እንደሚያጠናክረው ተስፋ አድርጋ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሚዘጋጁ የሬጌ ሙዚቃ ኮንሰርቶች እና ሌሎች ተያያዥ ዝግጅቶች እና ፌስቲቫሎች ሬጌ ሮቢክስን መክፈቻ እና መጋረጃ መግለጫ በማድረግ የማሟሟቅ ድባብ መፍጠር እንደሚቻልም ጠቁማለች። በመጨረሻ ሌላኛውን ትልቅ ዓለማዋን አስመልክቶ ለስፖርት አድማስ ዜላ ስትናገር ‹‹በኢትዮጵያ፤ በአፍሪካ እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሬጌ ሮቢክስ ማዕከሎችን መክፈትም እፈልጋለሁ፡፡ በተለይ ግን ቅድሚያ ትኩረት የምሰጠው ሬጌ ሮቢክስ በመላው ዓለም ወጥ በሆነ የልምምድ መርሃ ግብር እና የማሰልጠኛ መመርያ ሊሰራ የሚችልበትን መዋቅር መዘርጋት ነው። በአካል ብቃት እና በኤሮቢክስ አሰልጣኝነት የሚሰሩ ባለሙያዎች ልዩ ስልጠና አግኝተው በሬጌ ኤሮቢክስ ኢንስትራክተርነት እንዲሰሩ የሰርተፍኬት እና የብቃት ማረጋገጫ ለመስጠት እየሰራሁ ነው፡፡

Read 1496 times