Saturday, 29 September 2018 14:36

ቢያገኝም ያበላል ቢያጣም ያዝናል ሆዱ

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሀሳብ አለን…ነገሮች መለዋወጣቸው ካልቀረ ለ‘አራድነት’ ደረጃ ይውጣልን። ተቸገርን እኮ! እኔ የምለው… አለ አይደል… የ‘አራድነት’ የሦስት ወር ስልጠና ምናምን ተጀመረ እንዴ! እንደዛ ከሆነ እውቅና የሌላቸው አሰልጣኞች በዝተዋል ማለት ነው (ቂ… ቂ… ቂ... እኔ የምለው… እነ እንትና… የዘንድሮው አራድነት እናንተን አይመለከትም።) አሀ… እንዴት ብሎ ደረጃ ይውጣ! በምን መለኪያ! አስር ብር በሚመስሉ የሎተሪ ትኬቶች ዶሮ ማነቂያን ያመሳችሁት እኮ ዘንድሮ ‘አራድነት’ ሳይሆን “ህገ ወጥ የምናምን ዝውውር” አይነት ነው። እናማ…ለእናንተ አራድነትማ እንዴት ብለን ደረጃ እናውጣ! አሁን ለምሳሌ… አለ አይደል… ጸጉሩን መሀል ለመሀል ከፍሎ “ኤልቪስ ካላላችሁኝ ወዮላችሁ!” የሚለውን ደረጃ ስንት ልንለው ነው! ባይሆን የዛኛው ዘመን ‘አራድነት’  በዓለም ታሪካዊ ቅርስነት እንዲመዘገብ ለዩኔስኮ ደብዳቤ የማናቀርብሳ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የዘንድሮውም ‘አራድነት’ መአት የሚያስቸግር ነገር አለው። ጠዋት አንድ ሰዓት ላይ ያደረገውን የጸሀይ መከላከያ መነጽር፤ ማታ ሦስት ሰዓት ላይ አጥልቆ ‘ዲምላይት’ ቡና ቤት የሚገባውን ሸላይ ምን ልንለው ነው! “የአንተ እንኳን በልዩ ሁኔታ የሚታይ ነው” ልንል ነው!
የምር ግን ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…በዚህ የ‘ስልጣኔ’ ዘመን በ‘ፈጣን አራድነት’ “ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ሁለተኛ” ያልተባልነው በተሸረበብን ዓለም አቀፍ ‘ሴራ’ ነው። (መቼም ‘የሴራ ንድፈ ሀሳብ’ን እንደኛ ‘በደንብ’ የሚጠቀምባት የለም ብለን ነው።
“ስሚ፣ እስካሁን ድረስ የት ነው ያመሸሽው?”
“ጓደኛዬ አሟት እሷ ቤት ሄጄ መሸብኝ”
ሄድኩባት ያለቻትን ጓደኛዋን ከአርባ አምስት ደቂቃ በፊት አውቶብስ ስትጋፋ ስላየናት የሰጠችው ምክንያት ውሸት ይሆናል፡፡ ‘ላይፍ’…አለ አይደል…‘ኢንተረስቲንግ’ ሆነ ማለት አይደለም! ‘ሰስፔንሱ’ን አስቡትማ!…
“ለቅሶ ቤት ነበርኩ” ምናምን አይነት ‘ሰበብ’ መስጠትም ይቻል ነበር፡፡ የምር ግን…  በቃለ ጉባኤ ምናምን ነገር አይስፈር እንጂ “ሰልስት አድራለሁ” እየተባለ፣ ‘ታሪካዊውን ቀዶ ጥገና’ ሳይንስ ሳይደርስበት በፊት ‘ስንት ነገር’ ላይመለስ ተበላሽቶ ቀርቷል!  
አሁን፣ መጀመሪያ ነገር “የት ነው ያመሸሽው?” ምናምን የሚል ‘አራድነቱን’… አለ አይደል… ‘አፕግሬድ’ ያላደረገ ነው። እንደዛ ቢልም… “አንተ ማነህና ነው የት ነበርሽ፣ የት አመሸሽ የምትለኝ!” ቢባል ነው፡፡ “ከወፈሩ ሰው አይፈሩ” የሚል ነገር ነበር አይደል! ዘንድሮ በ‘ተነፈሰ ሆድ’ም የምንወፍር አለን።
ስሙኝማ…የውፍረት ነገር ካነሳን አይቀር ብዙ ቀዳዳ ያለው ቀበቶ ያስፈልገናል፡፡ (‘ፍሌክሲብል’ እንደሚሉት አይነት ማለት ነው።) “ምናልባት እኮ ክብደት ልጨምር እችላለሁ” የሚል ስጋት ቀርቷላ! (ወይም ‘ከቀረብን’) ቀበቶው እንደ ጎል መረብ በርከት ያሉ ቀዳዳዎች ይኑሩት...በየሁለት ወሩ ምስማር ከመፈለግ ያድነናላ!
በነገራችን ላይ… “አንተ፤ ሙክት አክለህ የለም እንዴ!” ማለት አድናቆት ሊሆንም፣ ላይሆንም ይችላል። በአንድ በኩል… አለ አይደል… “ተመችቶሀል፣ ደልበሀል፣ ምን ተገኝቶ ነው?”  በሌላ በኩል “ወደ ላይ ጠጋ ብለህ ዝግ ዘጋህ ወይ?” ማለት ሊሆን ይችላል። 
እናላችሁ…ስለ አራድነት ስናወራ ቀደም ሲል… 
መገን የአራዳ ልጅ እነ ድንጋይ ኳሱ
ምን ጊዜ ተጩሆ ምን ጊዜ ደረሱ
የሚሏት ነገር ነበረች። መጯጯህ እንደ ልብ ነበራ! እሪ በከንቱ አካባቢ ወዳጆቻችን ‘ሜሞሪው’ እንዴት ነው! የምር እኮ ይባል የነበረው “እንግዲህ መሸላቸው መጯጯሀቸውን ጀመሩ” ሳይሆን… አለ አይደል… “ዛሬ ምነው ጸጥ እረጭ አለ! ባሻ ወልዴ ችሎት ሰላም አይደለም እንዴ!” አይነት ነገር ነው።
“እነ ድንጋይ ኳሱ” ብሎ ቸስ ማለት “ምን የሚሉት አራድነት ነው?” ለሚሉ መልስ ያላችሁ በቴልገራም ምናምን ላኩልንማ! የምር እኮ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ያኔ ‘ቦዲ ቢልደርነት’ ከዱባይ ከምናምን የሚመጣ ኪኒን ባልነበረበት ዘመን፣ ዝም ብሎ ጡንቻ ቢፈረጥም ምን ዋጋ አለው! ወሬው እኮ… “በቃ ይህ ልጅ ያለመደባደብ ሌላ ስራ የለውም!” አይነት ሳይሆን እናቶች እንኳን… “ብቻ እንዲህ ሽቅብ ብድግ አደረገውና መሬት ላይ ጧ ነው ያደረገው! አይ ጀግና!” አይነት ነበር የሚሉት። ተደብድቦ የመጣ ልጅ እኮ ከሰው በመጣላቱ ሳይሆን ተደብድቦ በመምጣቱ ከአባቱ  ተጨማሪ ጥፊና ኩርኩም ይገጥመው ነበር! እናማ… “እነ ድንጋይ ኳሱ…” መባል እንደ ዘንድሮው ‘ቪአይፒ’ ነገር ማለት ነው።
እኔ የምለው… “እነ ድንጋይ ኳሱ…” አራዶች፣ ያ የካውቦይ ፊልም ትዝ አይላችሁም… ‘ቴክሱ’ አንድ ሃምሳ ምናምን ‘ሬድ ኢንዲያን’ ሲፈጅ ያጨበጨብነው ማጨብጨብ!…ያኔ ደግነቱ ‘ጄኖሳይድ’ ምናምን የሚባል ነገር አልነበረማ! ኮሚኩ ነገር እኮ… አለ አይደል… ሽጉጥዬው የሚጎርሰው ስድስት ጥይት ብቻ ነው! እናላችሁ…‘ቴክሱ’ አንድም ጊዜ መልሶ ሳያጎርስ አስራ ሰባቱን ይረፈርፋል። አሀ…ቻርለስ ብሮንሰን ወይም ጃክ ፓላንስ ይቺን ካልቻሉማ፣ ወደ ሰማይ ተኩሰው ነገርዬዋ በፊት ለፊት ሳይሆን በጀርባ ዞራ ‘ሬድ ኢንዲያኑን’… አለ አይደል…‘ጠብ’ ካላደረገችማ…  (ቂ…ቂ…ቂ…) ምኑን ‘ቴክስ’ ሆኑ!
ስሙኛማ… እኛ የጎረቤቷ ሴትዮ ትዝ አይሏችሁም? እሳቸው ሴትዮ ግን በሆነ ባልሆነው ጭናችሁ ስር ገብተው የሚመለዝጓችሁ ለምን ነበር? አሀ…ካልጠፋ የአካል ክፍል እጃቸውን ለምን ጭናችሁ ውስጥ እንደሚወሽቁ እስከ ዛሬ ገብቷችኋል? የምር ግን ያን ጊዜ እንኳንም ተደብቀን  ‘አንተን’ የምናይበት ዩቲዩብ ምናምን አልነበር። ጉድ ይፈላ ነበራ! ድምዳሜ ላይ ይደረሳላ! “እትዬ እንትና ጭኔ ስር የመዘለጉኝ ሊቀጡኝ አስበው ሳይሆን ምልክት ሊሰጡኝ ነው” አይነት ውሳኔ ላይ ይደረሳላ… ኸረ እንኳንም ዩቲዩብ አልኖረ! ይሄኔ ሁለት መቶ ሚሊዮኗን ተጠግተን  ለኪሎ ቲማቲም ብር በማዳበሪያ እየሞላን እንሄድ ነበር።
ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ነው። አንዷ ልጅ ከረዳቱ ጋር ትጋጫለች። ጭቅጭቃቸው… “መልስ አልሰጠኸኝም፣” “ሰጥቼሻለሁ” ነበር። ልጅቱ የምትፈልግበት ስፍራ ደርሳ ስትወርድ ምን ብትል ጥሩ ነው… “በአንተ ቤት አራዳ መሆንህ ነው!”
በየቦታው ቀሽም ‘አራድነት’ ይገጥማችኋል። በቀደም የሆነ ቀን  ረፋድ ላይ ነው…አራት ኪሎ አካባቢ አንድ ትልቅ የአደጋ ጊዜ መኪና እየከነፈ ነበር። ታዲያ ከሹፌሩ ጀርባ የነበሩት ሰዎች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ዘፈን አይሉት ምን…ብቻ ይጮሁ ነበር…የሆነ ቀሽም ‘አራድነት!’ እነዛ ሰዎች በዛን ሰዓት ሥራ ላይ ነበሩ እኮ! ልክ ቢሮ ውስጥ እንዳሉ ሰዎች ነበሩ እኮ! ይህ ‘አራድነት!’ ምናምን ሳይሆን ስርአት አለማክበር ነው።
ስሙኝማ… “እኔ ኪስ ያለው ሱሪ አድርጌም አላውቅ፣ አልወድም” ሲል የነበረው ሰው “ዋሌቴን ሱሪ ኪሴ ውስጥ ረስቼው ስለመጣሁ መቶ ብር ታበድረኛለህ!” አይነት ቅሽምና ጥግ የደረሰ የ‘ቶክ ሾው’ አይነት አራድነት (ቂ…ቂ…ቂ…) ስታዩ የድሮ አራድነት ቅሪተ አካል ይፈለግልን ለማለት ምንም አይቀራችሁ፡፡
ከዚህ በፊት ያወራናት ነገር…ሲኒማ ቤት ነው፡፡ ውጪ ተመልካቾች ሲኒማ ቤት ሲገቡ ካፖርታቸውን ተቀብለው የሚያስቀመጡ አስተጋጆች አሉ። እናም ካፖርቱን ቀበል ሲያደርግ ፍራንክ ጣል ይደረግለታል፡፡ አንድ ጊዜ ልብ አንጠልጣይ የሚባል የወንጀል ነክ ፊልም ለማየት ባልና ሚስት ይገባሉ። ሚስት ካፖርቷን ለአስተናጋጁ ትሰጥና መንገዷን ትቀጥላለች፡፡ የተለመደው ‘ቲፕ’ ጉርሻ አልነበረም። አስተናጋጁም ተበሳጨ፤ ወደ ሴትየዋ ጠጋ አለና በጆሮዋ “ሴትየዋን የሚገድላት የቤቱ አገልጋይ ነው” አላትና አረፈው፡፡ ከዛ በኋላ ፊልሙን ማየት አያስፈልግም። አራዳ አስተናጋጅ እንዲህም ያደርጋል ማለት ነው!
ከአራዳ ልጅ ጋራ በአንድ አብረው ሲሄዱ
ቢያገኝም ያበላል ቢያጣም ያዝናል ሆዱ
ይቺኛዋ ‘አራድነት’ እንደገና ሪሳይክል ሳይደረግ ብትመለስልን አሪፍ ነው…  ግራ የተጋባነው መተዛዘን የሚሉት ነገር እየጠፋ ነውና!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4431 times