Saturday, 29 September 2018 14:30

“ኢህአፓ ለሀገሪቱ የፖለቲካ ሀሁን ያስተማረ ነው”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)


  • ለተጐዱ ቤተሰቦች በሙሉ በትውልዱ ስም ከፍተኛ ይቅርታ እንጠይቃለን
  • ለአንድ ቀን እንኳ በሃገር ውስጥ የምናደርገውን ትግል አላቆምንም
  • ትልቅ ህዝብን በጐሣ አጥር ውስጥ እየከተትን አሳንሰነዋል
  • ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ስንታገል ቆይተናል

    ለ46 አመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ የቆዩት የኢህአፓ አመራሮች ባለፈው ሳምንት ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል፡፡
ኢህአፓ እስከ ዛሬ ምን እንቅስቃሴ ሲያደርግ ነበር? አሁንስ ዓላማውና ግቡ ምንድን ነው? የሚመራበት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምስ ምንድን ነው? ስለ ዘር ፖለቲካ ምን ይላል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ሊቀመንበር አቶ በላይነህ ንጋቱን (መርሻ ዮሴፍን) በእነዚህና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-

    ኢህአፓ እስከ ዛሬ እንዴት ነበር የሚንቀሳቀሰው?
ብዙ ሰው ኢህአፓ በውጪ ብቻ የነበረ ድርጅት ይመስለዋል፡፡ ነገር ግን ድርጅታችን ላለፉት 46 ዓመታት፣ ለአንድ ቀን እንኳ በሃገር ውስጥ የሚያደርገውን ትግል አላቆመም፡፡ በህቡዕ የሚታገሉ አባላት በሃገር ውስጥ ነበሩን፡፡ በደርግ ስርአት ለ17 ዓመታት የትጥቅ ትግል ስናካሄድ ነበር፡፡ ስለዚህ ኢህአፓ በውጪ ብቻ አይደለም ሲታገል የነበረው። በውጪ ባለው መዋቅር ደግሞ በበርካታ ሀገራት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ በጐረቤት ሀገራት፤ በኬንያ ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ አውሮፓ፣ ካናዳና አሜሪካ መዋቅሮች አሉት፡፡ አሁንም በትግል ላይ ነው፡፡
ባለፉት 27 ዓመታት እንዴት ነው ስትታገሉ የቆያችሁት?
ህወሓት ደርግን አሸንፎ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ከኛ ጋር ለአንድ ዓመት ተኩል ተዋግቷል። ጐጃምና ጐንደር ላይ ከ1983 እስከ 1985  ተዋግቷል፡፡ ለህዝቡ አጥፍቻቸዋለሁ እያለ፣ ነገር ግን ከኛ ጋር መደበኛ ጦርነት ያካሂድ ነበር። ወያኔ ብቻውን አልነበረም፤የሻዕቢያና የሱዳን እገዛ ነበረው፡፡ በተለይ የሱዳን ጦር በመተከል በኩል ገብቶ፣ ከወያኔ ጋር ተጣምሮ ወግቶናል፡፡ ለአንድ ዓመት ተኩል ከተዋጋን በኋላም ተሸንፈን፣ አመራሮቻችን ተማርከውብናል፡፡ እስካሁን ድረስ ወያኔ ምርኮኞቹን የት እንዳደረሳቸው አናውቅም፡፡
የተማረኩትን አባላት ስማቸውን ሊጠቅሱልን ይችላሉ?
እነ ደብተራው፣ እነ ይስሃቅ ደብረፅዮን፣ እነ በላይ (አምባዬ)፣ እነ አሉላን ጨምሮ 40 ያህል የኢህአፓ ነባር አመራሮች ከተማረኩ በኋላ እስከ ዛሬ ደብዛቸውን አጥፍተዋቸዋል። የተወሰኑትን እንደገደሏቸው እንሰማለን፤ ነገር ግን አላረጋገጡልንም፡፡ ይሄም አሁን አንዱ ጥያቄያችን ነው፡፡ በወቅቱ የተረፍነው ሸሽተን ወደ ውጪ ወጣን፡፡ ከዚያ በኋላ በውጭ ሀገር መዋቅሩን አጠናክረን ትግላችንን ቀጠልን፤ በሃገር ውስጥም በተለይ በከተማ አካባቢ በህቡዕ ተደራጅተን፣ በተለይ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ እንደ ሚዛን ሆነን ስንታገል ቆይተናል፡፡
ኢህአፓ ወደ ሀገር ቤት ይገባል ሲባል፣ በርካቶች አለ እንዴ? የሚል ጥያቄን ነው ያነሱት፡፡ እናንተ ደግሞ ተጨባጭ ትግል ስናደርግ ቆይተናል እያላችሁ ነው----
እንደውም ሰው ኢህአፓ ጠፍቷል የሚል ድምዳሜ ላይ ባይደርስ ነበር የሚገርመኝ፡፡ ምክንያቱም 17 አመት ሙሉ ደርግ ሲያጠለሸን ነው የኖረው፡፡ ያልሰራነውን ሠሩ እያለ ሲያቆሽሸን፤ እንደሌለን እንዲቆጠር ስማችንን እንኳ ላለማንሳት ሲጠነቀቅ ነው የኖረው። ለምሣሌ ጐንደርና ጐጃም ኢህአፓ-ኢህአሠ ሲንቀሳቀስ፣ ኢህአፓ የሚለው ስም እንዳይጠራ፣ አንዲትን የኢህአፓ ኮሚሳር የነበረችን ሰው ስም ብቻ ነበር የሚጠቅሰው። ህወሓት-ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ደግሞ እንደሚታወቀው፣ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ሲሠራ የነበረ ድርጅት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን ያስቀደሙና በኢትዮጵያ ሃገራዊ ህልውና ያመኑ ድርጅቶችን ማፍረስ፣ መካድና ማጣልሸትን ስራዬ ብሎ ሲሰራ ነበር፡፡ በዚህ መንገድ ታዲያ ኢህአፓ እንዴት ይታወቅ። በተፃራሪው ታሪኩን የሚያበላሹ የሚያጠለሹ አካላት፣ መድረኩን ያዙና ህገ-ወጥ ተባለ፡፡ ኢህአፓ የለም የሚለው በግልጽ ሲነገር ነው የኖረው፡፡ የኛ ሁኔታ እንዲታወቅ አይፈለግም ነበር፡፡
ታዲያ እንዴት ነው እስከ ዛሬ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ስናደርግ ቆይተናል ማለት የምትችሉት?
ኢትዮጵያን የሚያፈርስ ሃይል ኢትዮጵያን መቆጣጠሩን ስናውቅ፣ በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምኑ ድርጅቶችን በውጪ በማሰባሰብ ኢዲሃቅ (የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ቅንጅት) የሚባል ድርጅት አቋቁመን ለመንቀሳቀስ ሞክረናል፡፡ በፊት እርስ በእርስ ይጋጩ የነበሩ ኢዲዩ መኢሶን፣ ኢህአፓ--- ሳይቀሩ የተሰባሰቡበት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የሚንቀሳቀስ ስብስብ አቋቁመን ነበር፡፡ በተጨማሪም አድማስ የሚባል ሬዲዮ አቋቁመን፣ ከዩክሬን ወደ ኢትዮጵያ ይደመጥ ነበር፡፡ ፕሬሶች በሰፊው በሚንቀሳቀሱበት ወቅትም በህቡዕ እየተገናኘን ሃሳቦቻችንን እንጽፍ እናጋራ ነበር፡፡ መረጃም እንሰጣቸው ነበር፡፡ ያኔ አምባገነንነቱ በመጠኑ ስለነበር በተለያየ ስም ቃለ ምልልስና በኢትዮጵያዊነት ላይ ያተኮሩ መጣጥፎችን ለጋዜጦች እንሰጥ ነበር፡፡ በሃገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶችንም በሃሳብ እንረዳ ነበር፡፡
ለምሳሌ እነማንን እንዳገዛችሁ ሊጠቅሱልን ይችላሉ?
ለምሣሌ የእነ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስን ድርጅቶች፣ የእነ ዶ/ር መረራ ጉዲና ድርጅቶችን እያገናኘን ህብረት የሚለውን ስብስብ እስከ መመስረት ተደርሶ ነበር። በኋላም መኢአድን፣ ኢዴፓንም በህብረቱ ውስጥ ለማካተት ሞክረናል፡፡ በኋላ እነሱ ቅንጅትን መሰረቱ። እኛ በዋናነት የህብረትና የአንድነት ፖለቲካ በህዝቡ ውስጥ ሠርፆ እንዲገባ በማድረግ፣ የህወሓት አፍራሽ አስተሳሰብ ሰፊ ቦታ እንዳይይዝ የቻልነውን ያህል ሠርተናል፡፡ በኛ በኩል ትልቅ ተግባር አከናውነናል የሚል እምነት ነው ያለን፡፡
ኢህአፓ ራሱ የተከፋፈለ ነው፤ በአሜሪካን ሃገር ሁለት ቦታ መከፈሉ ይታወቃል---
ኢህአፓ ውስጥ በእርግጥም ችግር ነበር፤ ተከፈለ ማለት ግን አይደለም፡፡ ትንሽ ፍንጣሪዎች ናቸው የወጡት፡፡ አብዛኛው ሃይል ከኛ ጋር ነው ያለው። አብዛኛው ሃይል ከኛ ጋር ስለሆነ ነው በድፍረት “ኢህአፓ እኛ ነን” ብለን ወደ ሀገር ቤት የገባነው፡፡
ግን መከፋፈሉ ለምን ተፈጠረ?
መከፋፈሉ የተፈጠረው በአሰራር አለመስማማት ነው፡፡ እኛ “ኢህአፓ ሃገር ውስጥ ህዝቡ መሃል ገብቶ መስራት አለበት” የሚል ሃሳብ ከ1997 በፊት አነሳን። ምክንያቱም አንድ ድርጅት ከህዝብ ውጪ ከሆነ እየከሰመነ ነው የሚሄደው፤ ሊጠፋም ይችላል። አብዛኛው የኢህአፓ ሃሣብ አራማጆችና አባላት በእድሜ የገፉ ናቸው፣ ወጣቶች ወደ ትግሉ መምጣት አለባቸው። ይሄን ለማድረግ ደግሞ ሃገር ውስጥ ህዝቡ መሃል በደንብ ገብቶ ትግል ማድረግ ያስፈልጋል። ይሄን ፖለቲካ የማይቀበሉ ሰዎች፣ የታሪክ ሂደት አልገባቸውም ማለት ነው ብለን ሞገትናቸው። ይሄ ሃሣብ ተደማጭነትና ተቀባይነት እያገኘ ሲመጣ፣ የተወሰኑት ደግሞ “ወደ ሃገር ውስጥ ከገባን፣ ወያኔዎች ያጠፉናል” በሚል ስጋት ውስጥ ገቡ። እኛ ደግሞ እየሞትን የምንታገል ነን በሚለው ፀናን፡፡ እንዳጋጣሚ ደግሞ ምርጫ 97 ላይ ትንሽ ከፈት ያለ ነገር ተፈጠረ። ሆኖም አልተስማማንም። እነሱ ስሙን (ኢህአፓ) እንደያዙ ትተንላቸው፣ “ኢህአፓ- ዲሞክራቲክ” ብለን ተለየን፡፡ በኋላ ደግሞ የተወሰኑት ወደኛ መጡ፡፡ እኛ “የእነ ዶ/ር ዐቢይ፣ አቶ ለማ፣ አቶ ገዱ፣ አቶ ደመቀና ሌሎች የኢህአዴግ የለውጥ ሃይሎች ህልም መሳካት አለበት፣ ሃሳባቸው ተቋማዊ እንዲሆን ልንደግፋቸው ይገባል፣ መጠናከር አለባቸው፤” በማለት በቅርቡ ባደረግነው ጉባኤ ወስነን ነው፣ ወደ ሀገር ቤት የመጣነው፡፡ ተከፍለው የቀሩት ጥቂቶች ግን ዛሬም የለውጡን ሁኔታ አልተገነዘቡም፤ የህዝቡን ፍላጐት አላዳመጡም፡፡ አልተለወጡም፡፡ እኛ ግን አሁንም ወዲህ ቢመጡ ወንድሞቻችን ናቸው፤ እንቀበላቸዋለን።
በሀገር ውስጥ ምን አይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ነው የምታደርጉት?
እንደሚታወቀው አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ፖለቲካ የዘር ፖለቲካ ነው፡፡ ይሄን መቀየር ያስፈልጋል፡፡ ፖለቲካችን በአስተሳሰብ፣ በርዕዮተ ዓለም፣ በአመለካከት ላይ የተመሠረት እንዲሆን የፖለቲካ ልምዳችንንና ባህላችንን ተጠቅመን ለማገዝ እንሞክራለን፡፡ አሁን ያለው የዘር፣ የስሜት ፖለቲካ ነው፡፡ ይሄ ፖለቲካ ደግሞ ወደ ኋላ የቀረ ፖለቲካ ነው፡፡ ፖለቲካችን፤ የፖለቲካ መልክ ያለው እንዲሆን እንሠራለን፡፡
ለኢትዮጵያ ምን ዓይነት ሥርዓት ነው የሚጠቅመው ትላላችሁ?
አሁን የምንከተለው የፌደራል ስርአት አይነት ጥቅሙ ምንድን ነው? ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ነው? አሁን ያለው የፌደራል ስርአት፣ ለአፍሪካስ ምን ትርጉም ይሰጣል? ይሄን ሁሉ በውይይት፣ በሃሳብ ፍጭት እንዲመረመር የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን፡፡ ፖለቲካችንን በውይይት ላይ የተመሠረተ የበለፀገ፣ የዘመነ ለማድረግ ነው የምንሰራው፡፡ ኢህአፓ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ ታሪክ፣ ፈር ቀዳጅ ነበር። አሁንም ራሱን ከዘመኑ ጋር አስማምቶ፣ በሀገራችን ውስጥ በሃሣብ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ እንዲካሄድ፣ የራሱን ድርሻ ይወጣል፡፡ በጠባብ ብሔርተኛ ኋላቀር ፖለቲካ የተበከለውን ወጣት በማስተማር፣ በአስተሳሰብና በርዕዮተ ዓለም ዙሪያ እንዲሰባሰብ ለማድረግ እቅድ አለን፡፡ በየመድረኮቹ ወጣት ምሁራንን እያሳተፍን፣ የጐሣና የመንደር ፖለቲካውን ለመለወጥ፣ በሰላማዊ መልኩ እንሠራለን፡፡ ይሄን ስናደርግ ኢትዮጵያዊነት በአዲስ መልክ፣ ህብረ ብሔራዊ በሆነ መልኩ ይለመልማል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ኢትዮጵያ እያደገች ስትመጣ፣ በባህልም በአስተሳሰብም የበለፀገ ህብረተሰብ እየተፈጠረ ይመጣል የሚል እምነት አለን። ከዚህ አንፃር፣ ዶ/ር ዐቢይ የጀመሩት ፖለቲካ፣ ለኢትዮጵያ ብሩህ ራዕይን የሰነቀ በመሆኑ፣ ሊደገፍ ይገባዋል ብለን ነው የመጣነው፡፡
ኢህአፓ አሁን የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ምንድን ነው?
ኢህአፓ ድሮ ማርክሲስት ሌኒንስት ነበር። አንዳንዶች ያጥላሉን እየመሠላቸው ኮሚኒስት ይሉን ነበር፡፡ እኛ ግን ማርክሲስት ሌኒንስት ነበርን። በኋላ ግን ርዕዮተ አለማችንን ወደ ሶሻል ዲሞክራት ቀይረናል፡፡ ይሄን ያደረግነውም በሁለተኛው የቋራው ጉባኤያችን ማለትም በ1976 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢህአፓ ርዕዮተ አለሙ ሶሻል ዲሞክራት ነው፡፡ የመድብለ ፓርቲ ስርአት ለኢትዮጵያ ያስፈልጋል የሚል አቋም ይዟል፡፡ ህዝባችን ማህበራዊ ፍትህ ያስፈልገዋል ብሎ ያምናል፡፡  
ወጣቶች በእናንተ ድርጅት ውስጥ ተሳትፎአቸው ምን ያህል ነው?
በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ይሄን የፈጠረው ደግሞ ህገ ወጥ ተብለን፣ ከሀገር ተገፍትረን በስደት ስለኖርን ነው፡፡ ውጪ ያለው ወጣት ደግሞ ኑሮውን ማመቻቸት ላይ ነው የሚያተኩረው፡፡ ሁለተኛ ነገር ባለፉት 37 ዓመታት የኛ ትውልድ ሲወገዝ፣ ሲጠላ ነው የኖረው። ወጣቱ ከዚህ አንፃር ቀርቦ ሳያየን፣ በሩቁ ነው የሚሸሸው፡፡ ሃሳባችንን ለማንበብ የሞከሩ ወጣቶች ካልሆኑ በስተቀር ሌሎች የጥላቻ ፕሮፓጋንዳው ሰለባ ሆነዋል፡፡ አሁን ነው ከወጣቶቹ ጋር ልንገናኝ የምንችልበትን እድል እያገኘን ያለነው፡፡ ስለዚህ አሁን ትኩረታችን ወጣቱ ላይ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ወጣቱ ለሀገሩ ያስባል፣ አዲስ ሃሳብ ካገኘም ይቀበላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክክር ያስፈልጋል፡፡
በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ለመወዳደር አቅዳችኋል?
እኛ አሁን ለምርጫ አንጣደፍም፡፡ ማንም የፖለቲካ ድርጅት አንዱ ተግባሩ፣ በምርጫ ፖለቲካ ስልጣን መያዝ ቢሆንም፣ እኛ ግን ከዚያ በፊት ስራ መስራት እንፈልጋለን፤ ለምርጫ አንጣደፍም። በተለይ ይሄ የተጀመረው ለውጥ እንዳይቀለበስ ጠንክረን እንሠራለን። አፍራሽ ሃይሉ ወደ ቦታው እንዳይመለስ ጠንክረን እንሠራለን፡፡ ይሄ ለውጥ ሃገርን የሚጠቅም ስለሆነ እንደግፈዋለን፡፡ በዚያው ልክ ለውጡን የበለጠ መሠረት ለማስያዝ መሠራት አለበት፡፡
“ኢህአፓ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከሠራው በላይ ያጠፋው ይበልጣል፣ የእርስ በእርስ ፍጅትን ጋብዟል” የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የእርስዎ አቋም ምንድን ነው?
ይሄ በጣም የተጋነነ፣ በውሸት የታጀበ ክስ ነው። ደርግ እንደዚህ ቢል ምንም አይሰማንም፡፡ ደርግ ያሰበን ጭምር የሚቀጣ አምባገነናዊ ስርአት ነበር። ኢህአፓ ያለማው ነው የሚበዛው፡፡  
ይሄን በምሣሌ ማስረዳት ይችላሉ---
ኢህአፓ ለሀገሪቱ የፖለቲካ ሀሁን ያስተማረ ነው። ከማንም በፊት መደራጀትን ያስተማረ፣ ህዝባዊ ድርጅት ማቋቋምን ያስተማረ፣ ስለ ብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ያነሣ፣ የሃይማኖት፣ የሴቶች፣ የመደብ እኩልነትን ጥያቄ ያነሣና በዚህ ላይም ህይወቱን እየገበረ ትግል ያደረገ ድርጅት ነው፡፡ መሬት ላራሹ ብሎ በተግባር የታገለ ድርጅት ነው። ግን ኢህአፓን የሚያጥላሉትና ትግሉን ለማኮሰስ የሚፈልጉ፣ ፊውዳላዊ ስርአቱን ለማስቀጠል የሚሹ ነበሩ፡፡ በዚህ መንግስት የህዝብ ነው የሚለውን ሃሳብ፣ ህዝቡ ውስጥ አስርጿል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከጭቆና ነፃ ለመውጣት የሚደረግን ትግል ያስተማረ ድርጅት ነው፡፡ ይሄን ሁሉ አስተዋጽኦ ያደረገ ድርጅት፣ ምንም አላበረከተም ማለት ነጭ ክህደት ነው። በእርግጥ በኋላ የመጣውን መስዋዕትነት፣ ደርግ ኢህአፓ ላይ በመለጠፉ፣ የተፈጠረ ውዥንብር አለ፡፡
ኢህአፓ በ”ነጭ ሽብር” ብዙ ሰዎችን ገድሏል፣ ትውልድን አስጨርሷል፤ በዚህም ተጠያቂ ሊሆን ይገባል የሚሉ ወገኖች አሉ---
አዎ ሰዎች ተገድለዋል፡፡ እኛን ሊያጠፋ የመጣን ሃይል ቅቤ አንቀባም፡፡ እርምጃችን ራስን የመከላከል ነበር፡፡ ራስን የመከላከያ ቡድን (defence squad) ነበር የሚባለው፡፡ ግን በዚህ ውስጥ ስህተት ተሠርቷል፡፡ ያልሆነ ሰው ጠላት ነው ተብሎ የሚፈረጅበት ሁኔታን ተከትሎ፣ የተወሰኑ በስህተት የተገደሉ ይኖራሉ። በዚያ ስህተት ለተጐዱ ቤተሰቦች በሙሉ ዛሬ ከፍተኛ ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ ግድያዎቹ ራስን በመከላከል ውስጥ የተፈፀሙ ናቸው፡፡ ለዚህም በትውልዱ ስም ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡
ግን በወቅቱ ቀድሞ ግድያን የጀመረው ኢህአፓ ነው ይባላል ---
ይሄ ውሸት ነው፡፡ ኢህአፓ አይደለም የጀመረው። ደርግ ነው፡፡ እንዲያውም መርካቶ አካባቢና ጅማ ላይ 25 የኢህአፓ አባላትን ስም ዝርዝር ይዘው ለመግደል ተዘጋጅተዋል የሚል መረጃ ደርሶን፣ ያንን እየተጠባበቅን እያለ ነው በየቦታው መግደል የጀመሩት፡፡ እኛ ስብስባችንን፣ የህትመት ማባዣ    ቦታዎቻችን ለመጠበቅ ስንል ነው፣ መከላከያ ስኳድ ያዘጋጀነው እንጂ ለማጥቃት አይደለም፡፡ እነሱ ከጀመሩ በኋላም ቢሆን “እባካችሁ አቁሙ” እያልናቸው ነበር፤ ነገር ግን ገፍተው ቀጠሉበት፡፡ በዚህም እኛ አንዳንዶቹን እንደተባለው ገድለናል፤ ይሄ አይካድም፡፡ በወቅቱ የነበረው አፈናና አማቂ ሁኔታ ነው ወደዚህ የገፋን። በዚህ መሃል ያለ ሃጢያታቸው ለተገደሉ ቤተሰቦች በሙሉ ልባዊ ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡
ለቀይ ሽብር ሰማዕታት ሃውልት ቆሞላቸዋል፤ በነጭ ሽብር  የተገደሉትስ የሰማዕታት ሃውልት አያስፈልጋቸውም?
እንግዲህ የመኢሶን እና የሌላ ታጋይ ድርጅት አባላት በዚህ መታሰቢያ ውስጥ ቢካተቱ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን የደርግ/ኢሠፓ አባላት ነፃ እርምጃ ሲወስዱ ነው የነበረው፡፡ ሠልፍ የሚያደርጉ ወጣቶችን በጥይት ፈጅተው፣ በየደጃፉ እየጣሉና ለጥይት ገንዘብ እያስከፈሉ----ግፍ የፈፀሙ ሰዎች፣ ዛሬ እንዴት ነው ስለ መብት የሚያወሩት? ስለ የትኛው ሰብአዊነት ነው የሚናገሩት? እነሱ ንስሃ መግባት አለባቸው፡፡ ወንጀላቸውን ለኢትዮጵያ ህዝብ ማመን ይገባቸዋል። በዚህ የጭካኔ ድርጊታቸው እኮ የሚፈራ ትውልድ ነው የፈጠሩት፡፡
እነሱም ግን ኢህአፓ ይብዛም ይነስ ይሄን ድርጊት ፈጽሟል ብለው ይወነጅላሉ---
የኛና የነሱ ፈጽሞ አይነፃፀርም፡፡ እኛ ባንዳዎችን፣ ገዳዮችን ነው የገደልነው፡፡ ደርጐችን ባገኘንበት ብንገድላቸው፣ ያን ጊዜ ደስታውን አንችለውም ነበር። እኛ ህዝባዊ የመብት ጥያቄ በማንሳታችን ነው የገደሉን። ስለዚህ የኛና የእነሱ ፈጽሞ አይነፃፀርም፡፡ እኛ የአፈናን ስርዓት ነው የታገልነው፡፡
ኢህአፓ ለኢትዮጵያ አንድነት እታገላለሁ፣ ኢትዮጵያዊነትን አስቀድማለሁ እያለ ነው፡፡ ይሄንን አሁን በሀገሪቱ ጎልቶ ከሚታየው የብሔር ፖለቲካ ጋር እንዴት ነው ለማስታረቅ ያሰባችሁት?
እኛ ከስረ መሠረቱ ብሔረሰቦች የእኩልነት መብት እንዲቀዳጁ ነው የታገልነው፡፡ የእኛ ትግል የእኩልነት ጉዳይ ነው፡፡ በስልጣን ላይ ያለው ሃይል ግን ይሄን የእኩልነት ጉዳይ ባልሆነ መንገድ ተርጉሞ አበላሸው፤ አበሻቅጦ አጨማለቀው፡፡ የጠብ፣ የጥላቻና የልዩነት ማስፋፊያ አደረገው፡፡ ይሄ ደግሞ ፖለቲካችንን ወደ ኋላ ነው የወሰደው። በሃሣብ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ቀርቶ የጐሣ ፖለቲካ ነው መድረኩን የተቆጣጠረው፡፡ ይሄ በእጅጉ ወደ ኋላ ቀርነት አስገብቶናል፡፡ ይሄን ስል ብሔረሰቦችን በመካድ ግን አይደለም። ብሔረሰቦች አሉ፤ ነገር ግን በመጀመሪያ ሰዎች ነን፣ ከዚያ ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ የጐሣን ፖለቲካ ይዞ፣ የዚህ ሃገር መፍትሔ ይሄ ብቻ ነው ማለት ስህተት ነው፡፡ ሲጀመር ህወሓት ነፃ አውጪ ድርጅት ነው፡፡ አንዱን ብሔረሰብ ነፃ ለማውጣት፣ ሌላውን ለማጥላላት የተነሣ ነው። ታዲያ ይሄ ድርጅት እንዴት ነው እኛ ለምንለው የብሔር እኩልነት ቆሜያለሁ ሊል የሚችለው፡፡ በተለይም የአማራውን ብሔረሰብ ነጥሎ ለማጥቃት የተነሳ ድርጅት ነው፡፡ ቀስ በቀስም የሱን ፖለቲካ ነው ሌላውም ላይ የጫነው፡፡ ይሄ በጣም ጐጂ ፖለቲካ ነው።
የብሄር/ጎሳ ፖለቲካ እንዲቀየር መፍትሄው ምንድን ነው ትላላችሁ?
በጣም ብዙ ዲሞክራሲያዊ የውይይት መድረኮች መፈጠር አለባቸው፡፡ ሴሚናሮች፣ ሲምፖዚየሞች እየተዘጋጁ ህዝቡ ራሱ በቀጥታ እየሳተፈ በጉዳዩ ላይ መምከር አለበት፡፡ በብሔረሰብና በክልል የሚያስብ ምሁር፣ ከዚህ አስተሳሰብ የሚወጣበትን መንገድ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ግን ጥሩ አይደለም፡፡ መለወጥ አለበት፡፡ ኢትዮጵያውያን እንደ ህዝብ ትልቅ ነን፡፡ እንደ ህዝብ የአፍሪካ ፈርጥ ነን፣ የነፃነት ቀንዲል ነን፡፡ ታዲያ እንዴት የመከፋፈል ምሣሌ ለመሆን እንጣደፋለን፡፡ እውነት ለመናገር በጣም ትልቅ የሆነን ህዝብ በጐሣ አጥር ውስጥ እየከተትን አሳንሰነዋል፡፡ አሁን ወደ ቀድሞ ትልቅነቱ እንመልሰው እያልን ነው ያለነው፡፡  
በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ላይ የተቀመጠውን የመገንጠል መብት በተመለከተ የኢህአፓ አቋም ምንድን ነው?
ህወሓት/ኢህአዴግ በህገ መንግስቱ ያስቀመጠው የመገንጠል መብት ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ይህ እንዲለወጥ ትልቅ ስራ መሰራት አለበት። ኢትዮጵያን የወረስነው ኢትዮጵያውያን በሙሉ ነን፡፡ አባቶቻችን አገሪቷን ሸንሽነው አይደለም ያወረሱን፡፡ እኛ ሙሉ ኢትዮጵያን ነው የወረስነው፡፡ ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት፡፡ የሁላችንም መብት ተከብሮ በእኩልነት ልንኖር ይገባል፡፡ የብሔር ፖለቲካ ትርፉ ግጭት ነው፡፡ ይሄንን አሁንም እያየነው ነው፡፡       

Read 2249 times