Saturday, 29 September 2018 14:22

ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የኤርትራውያን ስደተኞች ቁጥር ጨምሯል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

ላለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ዝግ ሆኖ የቆየው ድንበር መስከረም 1 ቀን 2011 ዓ.ም መከፈቱን ተከትሎ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከ15 ሺህ በላይ ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር አቋርጠው መግባታቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒሰትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያን ዘመን መለወጫ ምክንያት በማድረግ በቡሬና በዛላምበሳ ዝግ የነበረውን ድንበር ማስከፈታቸውን ተከትሎ፣ የሰዎች ዝውውር ከፍተኛ መሆኑን ተቋሙ አስታውቋል፡፡
አብዛኞቹ ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ያሉት ኤርትራውያን ኑሮአቸውን በኢትዮጵያ ለማድረግ መሆኑን የጠቆመው የተቋሙ ሪፖርት፤ ቀሪዎቹም በኢትዮጵያ የሚገኙ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ በማሰብ መምጣታቸውን አመልክቷል፡፡ ለንግድ የሚመላለሱ ኤርትራውያን ነጋዴዎች ቁጥርም ቀላል እንዳልሆነ ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
የሁለቱ ሃገራት ድንበር ከተከፈተ በኋላ ቀድሞ የኤርትራን መንግስት ጭቆና ሽሽት በድብቅ ይመጡ የነበሩ ኤርትራውያን አሁን በይፋ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት መጀመራቸውን የጠቆመው ተቋሙ፤ በየቀኑ 500 ያህል ስደተኞች ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ነው ብሏል፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤርትራውያን ጥገኝነት ፈላጊዎች ቁጥር ወደ 175 ሺህ ከፍ ማለቱን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
አብዛኞቹ ጥገኝነት ጠያቂዎች በሽሬ አካባቢ በሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ የጠቆመው የመንግሥታቱ ድርጅት፤ ከኤርትራ መንግሥት ጥቃት ሊደርስብን ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸውም አመልክቷል፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ለመጣው የስደተኞች ቁጥር ዓለም አቀፍ ለጋሾች የድጋፍ ርብርብ እንዲያደርጉም ተጠይቋል፡፡ 

Read 6955 times