Saturday, 22 September 2018 15:10

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

“ኢ-ፍትሐዊነት በመሳሪያ ከተገዛ ትልቅ ጥፋት ያስከትላል”
              

    በጨዋታ መሃል “አንድ ጐረምሳ ከሞት ተነሳ” አሉ… ሃምሳ ዓመታት ካንቀላፋበት፤ ድንገት ብንን ብሎ!! “Wonders never end” እንዲሉ፡፡ ሊያልፍ ከት፤ ኦክዊላ ሸሚዝ፤ ነጭ፡፡ ራንግለር ሱሪና ጀምስ ቦንድ ጫማ አድርጓል፡፡ ከተማ ሲገባ እሱ የሚያውቀው ከተማ የለም፡፡ ታክሲዎቹ የሚወዷቸውን የቦታ ስሞች ሲሰማ ነው ተወልዶ ያደገበት አካባቢ መሆኑን የተረዳው፡፡ ቀስ እያለ ሲራመድ፣ ከአንድ ፎቅ ስር፣  በረንዳ ላይ ፣ ጀበናና ስኒ ከበው ሰዎች ቡና ይጠጣሉ፡፡
ቡና ከምትቀዳዋ ሴት ጀርባ “ኑ ቡና ጠጡ” የሚል ፅሁፍ አለ፡፡ ጐራ ብሎ ተቀመጠ፡፡ ተቀዳለትና ጠጣ፡፡ አመስግኖ ሊሄድ ሲል “ሂሳብ” ተባለ፡፡ “ይከፈላል እንዴ?” በማለት ገረመው፡፡ እንግዳ መሆኑ ስለሚያስታውቅ “ችግር የለም ከፈለግህም ደግሞ…” አሉት፡፡  “እኔ  መች አወቅሁ… ከሌላ ዓለም ገና መምጣቴ ነው” ሲላቸው፣ ህመምተኛ ነው ብለው አዘኑለት፡፡ ሰፈሩ ውስጥ አንድ ሰው እንኳን የሚያውቀው አልተገኘም፡፡ ወደ ወረዳው ጽ/ቤት ወስደውት መዛግብት ቢመረምሩም ምንም ፍንጭ የለም፡፡ በአጭር ጊዜ ተዋውቀው አብሮት ከነበረው ወጣት ጋር በመንገድ ሲዘዋወሩ “የደም አንተነትህን የሚገልፅ የሆነ ነገር ፈልግ” አለው፡፡ ምንም እንደሌለው ለማሳየት፣ ኪሶቹን ሲበረብር፣ በወረቀትና በላስቲክ የተሸፈነ ነገር አገኘ፡፡ በዚያው ቅፅበት “ወይኔ! … ጉድ ሆንኩ!” ብሎ ተንቀጠቀጠ፡፡ …. ለምን ይሆን?
***
ወዳጄ፡- እኛ ስናድግ ጥብቆዎቻችን ይጠባሉ። በልካችን የተሰፋ ልብስ እንፈልጋለን፡፡ ልብሱን በኛ ልክ እንጂ እኛን በልብሱ ልክ ማስተካከል አይቻልም። የልጅነታችንን ጥብቆ በስተርጅና “ልኬ ነው” ብሎ ለመልበስ መታገል፤ “አላደግሁም፣ ህፃን ነኝ” እንደማለት ነው፡፡ ትልቅ ሆኖ ትንሽ ማሰብ!!...
ከአርባና ሃምሳ አመት በፊት የተቀዳን የፖለቲካ ፕሮግራም ሳይሻሻል ተግባራዊ አደርጋለሁ ብሎ ማሰብ፣ የልጅነት ጥብቆዬን በስተርጅና ካላጠለኩት” ከማለት አይሻልም፡፡
ወዳጄ፡- አንድ ነገር ልብ በል፡፡ እድሜአችን ሲጨምር፣ የአካላችን መጠን አድጋል፡፡ የአስተሳሰባችን ከፍታ የሚጨምረው ግን አዕምሯችን ሲያድግ ነው። የሶስት ዓመትና የአስር ዓመት ጤነኛ ህፃናት ዕኩል አይሮጡም፣ የሚያዩት ርቀትም እኩል አይደለም፡፡ ወንበር ላይ የተንጠለጠለና ሜዳ ላይ የቆመ ሰውም እንደዚሁ፡፡ ፎቅ ላይ የወጣውን ደግሞ አስበው፡፡ ማሰብና ማስተዋል ላይ ግን ህጉ ይቀየራል፡፡ ከቦታውና ከዕድሜህ ይበልጥ ብስለትህ፣ ፍላጐትህና ዝንባሌህ እይታህን ይወስናል፡፡ የሁዋለኛው
“Your attitude determines your altitude” እንደሚሉት ሲሆን የመጀመሪያው ደግሞ “Your altitude determines your attitude” እንደሚባለው ነው፡፡ ከፍታህ አስተሳሰብህን፣ አስተሳሰብህ ከፍታህን ሊያወጣና ሊያወርድ ይችላል ማለት ነው፡፡
ወደኛ ጉዳይ ስንመጣ፡- የመለወጣችንና የማደጋችን ምልክት ሊሆን የሚችለው የአቅማችን መጠን ከሰለጠኑ ህዝቦች ጋር መራመድ ስንሞክር ነው፡፡ ፊታችንን አዙረን ወደ ኋላ ከተመለስንና ኢ-ፍትሃዊ ከሆንን፤ እርስ በራሳችን ከተናከስን፣ ገና ከእንስሳነት ባህሪ አልተላቀቅንም፡፡
“ኢ-ፍትሃዊነት በመሳሪያ ከተገዛ ትልቅ ጥፋት ያስከትላል፡፡ ሰው ደግሞ አንድን አጋጣሚ ለራሱ ጥቅም የሚያውልበት ተፈጥሯዊ ንቃት አለው፡፡ ቅድስናውን ሲገሥ፣ በአጉል ምኞትና ፍላጐት ይሰክራል፡፡ ያኔ ያገኘውን የሚዘነጥል ጨካኝ አውሬ ይሆናል (… for injustice is more dangerous when armed, and man is equipped at birth with the weapon of intelligence,… which he may use for the vilest ends. Wherefore if he has not virtue he is the most on holy savage of animals, full of glttony and lust” በማለት የሚያስጠነቅቀን አርስቶትል ነው፡፡
ወዳጄ፡- የሰው ልጅ በእንስሳነቱ ጊዜ ያለፈበትን አረመ ኔያዊነት በዚህ ዘመን ሲደግመው ያሳዝናል። አገራችን ምንም እንኳ ስር የሰደዱ እምነቶችና ሃይማኖቶች ያሏት ብትሆንም፤ ይቅር መባባል የህዝቦቿ ባህልና ወግ ቢሆንም፣ ባለፉት ቀናት ራሻቸውን መከላከለ በማይችሉ ፤ሰላማዊ ዜጐች ላይ የተፈፀመውን አይነት ጥቃት መሸከም ግን አትችልም። ጫንቃዋን ይሰብራል፡፡ …. ከትዕግስት በላይ ነውና! ዓለም እንደ አንድ መንደር በጠበበችበት በዚህ ዘመን፤ ከዘርና ከጐሳ፤ ከብሄርና ብሄረሰብ ጋር አነካክቶ ህዝቦች እርስ በርሳቸው እንዲጋጩ በማድረግ፣ የሚገኝ የፖለቲካ “ብልጠት” ትርፍ ሳይሆን ኪሳራ ነው፡፡ ….
ወዳጄ፡- አዲስ አበባ ትልቅ ከተማ ናት፡፡ በመሃሏም ሆነ በአካባቢዋ የሚፈፀሙ የተደራጁ ወንጀሎችን ማክሸፍ ካልቻለች፣ የዜጐችን መብትና ሰላም ማስከበር ከተሳናት ወሮበሎችን ህግ ፊት ማቅረብና ማስቀጣት ካዳገታት የመንግሥት ሚና ምንድን ነው?....

በዳር አገር በተደረጉ ውንብድናዎች የተጐዱና የተፈናቀሉ ወገኖች ቁስል ሳይጠግግ፣ አይናችን ስር የሚፈፀሙ ኢ-ሰብዓዊ ወንጀሎች እዚህ ደረጃ ከደረሱ፣ መንግሥት ዜጐችን  ሊጠብቃቸው ካልቻለ… ራሳቸውን በራሳቸው እንዲጠብቁ መፍቀድ አለበት፡፡ ብልጭ ያለችው የዴሞክራሲ ጀንበር ተመልሳ እንድትጠልቅ፣ በእጅ አዙር መተባበር፣ አገራችንን የበለጠ ችግር ውስጥ ይዘፍቃታል፡፡
ወዳጄ፡- ለውጥ የእድገት ሂደት ነው፡፡ የማይለወጥ ምንም የለም፡፡ አልለወጥም ብሎ ማሰብ፤ የሰው ተፈጥሮ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ሳይንስ የህብረተሰብ እድገትና ጥቅምን ማበልፀጊያ፤ የስልጣኔ መስኮት መክፈቻ፣ የጨዋነት፣ የግብረገብነት፣ የእውቀትና የሚዛናዊነት ማበልፀጊያ ሃሳብ እንጂ ጐታች፣ አደንቋሪ፣ ኢ-ሰብዓዊ መሳሪያ ሆኖ የጨቋኞችን ጥቅም ማስከበር የለበትም፡፡ ማንም ከህግ በላይ አይደለም….

እናም…. ”ባለህበት የቆምከው ወዳጄ፤ ሁሉም ነገር አላፊና ተለዋጭ መሆኑን ከዘነጋህ፣ በነበርክበት ሞተሃልና ብትነሳ ይሻልሃል፡፡ … በጨዋታችን መሃል እንደተነሳው ልጅ!!
                           ***
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፤ ልጁ ኪሱን ሲበረብር፣ በወረቀትና በላስቲክ  የተሸፈነ ነገር አወጣ ብለን ነበር፡፡ ወዲያውም፤ “ጉድ ሆንኩ!” ብሎ መጮሁን አውርተናል፡፡ በዚህን ጊዜ ጓደኛው፤ “አይዞህ!... ምንም አላየም” በማለት አረጋጋው፡፡ ትንፋሹ ተመልሶ ብቻቸውን ሲሆኑ፡-

“ነገሯ “የምትሸጥ ናት ወይስ ራስህ ትጠቀምባታለህ?” በማለት ጠየቀው፡፡ … የሚያነቃቃ ዕፅ ምናምን መስሎታል፡፡
“የቷ ነገር?”
“አሁን ያወጣሃት፣ ያስደነገጠችህ?!”
“ኧረ አይደለም! መፅሃፍ እኮ ናት” አለውና ሲያሳየው፤ “ኮምኒስት ማኒፌስቶ” ትላለች፡፡ …. ያኔ እሷን የያዘ ይታሰራል፡፡ ጓደኛው ከት ከት ብሎ ስቆ፤ “አሁን አመንኩህ ሞተህ ነበር” አለው፡፡
                                              ሰላም!!

Read 1210 times