Saturday, 22 September 2018 14:59

ሐገርም እንደ ሰው ይታከማል

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

ኢትዮጵያ በቅርብ ዘመን ታሪኳ ሦስት መንግስታትን አይታለች - አፄያዊው አገዛዝ፤ ኮምኒስት ነኝ ባዩ ወታደራዊ ደርግ እና  ባለፉት ሦስት ዓመታት በህዝብ አመጽ ሲናጥ የከረመው ፌዴራላዊ ስርዓት፡፡ አሁን የምናየውን የዶ/ር ዐቢይ መንግስት አራተኛ መንግስት አድርጌ ባልመለከተውም፣ አብዮት በሚመስል ሂደት ውስጥ ማለፋችንን አምናለሁ፡፡ አብዮት አሮጌውን (ህገ መንግስት) በአዲስ ለመቀየር ወይም ለመሻሻል ወይም ለመፍጠር ይካሄዳል፡፡ ስለዚህ የአሁኑን ለማሻሻል የተደረገ አብዮት ማለት እንችላለን፡፡
በርግጥ የአሁኑን የለውጥ እንቅስቃሴ ከ‹‹አብዮት›› መቁጠር ሆነ የስርዓት ሽግግር አድርጎ ማየት ሊያስቸግር ይችላል፡፡ በአንድ መንግስት ውስጥ ሁለት ተቀናቃኝ ኃይሎች ሲፈጠሩ፤ ለመሸናነፍ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ግጭት የሚነሳበት ዕድል ይፈጠራል፡፡ ግጭቱም ደም አፋሳሽ የመሆን ሰፊ ዕድል ይኖረዋል። እናም አሁን በኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረው ልዩነት በዶ/ር ዐቢይ አመራር ባይያዝ ኖሮ፤ ደም መፋሰስ ሊፈጥር የሚችል ‹‹ሽግግር›› ይሆን ነበር፡፡ የዶ/ር ዐቢይ ‹‹የመደመር ፍልስፍና›› ሐገሪቱን ከ‹‹ሽግግር›› ደም መፋሰስ ታሪክ ጠብቋታል፡፡ የዶ/ር ዐቢይ ‹‹የመደመር ፍልስፍና›› ትልቁ ፋይዳም ይኸው ይመስለኛል፡፡ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ወደ ደርግ፤ ከደርግ ወደ ኢህአዴግ የተደረገው ሽግግር ደም ተሻግሮ የመጣ ነው፡፡ የዶ/ር ዐቢይ ሽግግር፤ በመደመር ድልድይ ተሻግሮ፤ በይቅርታ እና ምህረት ተሞሽሮ የተከናወነ ነው፡፡ ስለዚህ ከሁለቱ ሽግግሮች የተለየ ነው፡፡
‹‹ያለ ምንም ደም›› እያለ ይዘምር የነበረው ደርግ፤ የስርዓት ሽግግሩን ያወጀው፤ 60 የሚሆኑ የንጉሡን ከፍተኛ ባለስልጣናት በመረሸን ነበር፡፡ የደርግ ባለስልጣናት በአፄው ሹማምንት ላይ በወሰዱት ደመ-ቀዝቃዛ እርምጃ የታሪካቸውን መጋረጃ ገለጡ፡፡ ሽግግሩ በደም ተበከለ፡፡ ግን በዚህ አላበቃም፡፡ በነጭና በቀይ ሽብር የደም አበላ ወረደ፡፡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በጠራራ ፀሐይ ተገደሉ፡፡ የከተማ የትጥቅ ትግል የጀመሩት ወጣቶች፤ ነገሩ አዋጭ እንዳልሆነ ሲረዱ ሜዳ ወጡ፡፡
እንደ ኢህአፓ ያሉ የትጥቅ ትግልን አማራጭ አድርገው ሜዳ የገቡትም የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነታቸውን ከደርግ በተለየ  ሲፈቱ አናያቸውም። እንዲያውም የሚያመሳስል ፍርደ-ገምድል ባህርይ ይታይባቸው ነበር፡፡ ይህን በተመለከተ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ‹‹የነፃነት ጎህ ሲቀድ›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መፅሐፋቸው ያነሱትን አንድ ታሪክ መጥቀስ ይቻላል። ዶ/ር ብርሃኑ የሚከተለውን ይላሉ፤
‹‹ከኢህአፓ ሠራዊት ነፃ መሬት እንደ ደረስኩ … በሠራዊቱ የደህንነት አባላት (ጋንታ 44 ይባል ነበር) የሚታዘዝ እስር ቤት እንዳለው ሰማሁ፡፡ በዚህ እስር ቤት እስረኞች በሆኑ የሠራዊቱ አባሎች …  ላይ ሰቆቃ ይደርስ ነበር፡፡… የኢህአፓ ሠራዊት አመራሮች በአባላት ላይ ሰቆቃ ይፈፅማል ብለን ለማመን አቃተን። ... ከታሰርነው ሰዎች መሐል አንዱ…ሁለተኛ ዲግሪ ያለው ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው በተፈጠረው ሁኔታ በጣም ከተደናገጡትና ከተረበሹት ሰዎች ውስጥ አንዱ ነበር፡፡ … የፍርድ ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት ወንጀሉን በሚመለከት ሁለት ደብተር ሙሉ (ምንም በሌለ ወንጀል) ዘርዝሮ … ጽሑፉን ለከሳሻችን ይሰጣል፡፡ …. ከሌሊቱ 11 ሰዓት ገደማ አንድ የማጓራት ድምፅ ሰማሁ። በድንጋጤ ባንኜ ስመለከት ተንጠልጥሏል፡፡ … እግሩ በትንሹ መሬቱን እየነካው በቶሎ መሞት አልቻለም። እንደምንም ተደጋግፈን አወረድነው፡፡ … ይህ ሰው ራሱን ያዳነ መስሎት፤ ሁለት ደብተር ሙሉ በፃፈው በፍፁም እውነት ያልሆነ ነገር፤ ብዙ ሰው እንደ ወነጀለና ብዙ ንፁህ ሰዎች ሊጎዱ እንደሚችሉ … ሲያውቅ ከራሱ ጋር ተጣልቶ ከሚኖር ለመሞት መወሰኑን በዝርዝር አጫወተኝ፡፡ ….የሚያሳዝነው ሰውየው ይህንን አድርጎም አልተረፈም፡፡ … ድርጅቱ ከህወሓት ጋር ጦርነት ገጥሞ ወደ ኤርትራ ሲያፈግፈግ፤ የፍርድ ሂደቱ ሳይጠናቀቅ ‹ሞት ሊፈረድባቸው የሚችሉ› በሚል ለይተው ከተገደሉት ስምንት እስረኞች መሐል አንዱ ሆነ፡፡ …ከሠራዊቱ ጋር በማፈግፈግ ወደ ኤርትራ ስንሄድ የሌሎች ጓደኞቻችንን ሁኔታ ብንጠይቅ፣ እናንተን አይመለከታችሁም ተባልን፡፡ ወደ ኤርትራ ጉዞ በጀመርን በጥቂት ጊዜ ውስጥ ጠባቂዎቻችን ከነበሩ አንዳንድ ታጋዮች፣ ጥቂቶቹ የጓደኞቻችን ልብስ ለብሰው አየን፡፡ ቀሪዎቹን እስረኞች እንደ ገደሏቸው ተረዳን›› ይላል፡፡ ከመቶ ዓመታት በፊት (በዘመነ መሣፍንት) የነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት ዳግም በኤርትራና በትግራይ ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ለሰብዓዊ መብት መከበር ቁርጠኛ ሲሆኑ እና ሐገርን ከደም መፋሰስ የሚጠብቅ ምርጫ ሲያደርጉ አይታዩም። ስለዚህ ኢትዮጵያ ዛሬም ግዙፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈፀምባት ሐገር ሆነች፡፡ መንግስት ብቻ አይደለም። የተለያዩ ቡድኖችና ግለሰቦች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጽማሉ፡፡ ሰዎችን በደቦ ፍርድ ይሰቅላሉ፡፡ ይገድላሉ፡፡ የ60ዎቹ ቁስል ህመሙ ጨርሶ አልጠፋም። በተለይ በደርግ የዘር ማጥፋት ወንጀል ውዶቻቸውን ካጡ ሰዎች አንደበት ዛሬም ኃይሉ ጢም ያለ ሐዘን ይሰማል፡፡ ትዝታው አስርት ዓመታትን ተሻግሮ ልብን ይሰብራል፡፡ እንደ ሐገር ከባድ የህሊና ጠባሳ አስታቅፎን ሄዷል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እንባውን ውጦ ሰቀቀኑን ተሸክሞ ይኖራል፡፡ በዚህ ረገድ ኢህአዴግ የሚመሰገን ሥራ ሰርቷል፡፡ ያለ ፍርድ ብዙ ዜጎች የገደሉትን የደርግ ባለሥልጣናት፤ ከበቀል እርምጃ ተቆጥቦ በፍርድ አደባባይ አቁሟቸዋል፡፡ በመጨረሻም፤ አንዳንዶች በይቅርታ ከእስር መውጣት ችለዋል፡፡
አቶ መለስ ዜናዊ፤ በቀይ ሽብር ላይ ጥናት ካደረገው ቻርልስ ሻፈር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሲናገሩ፤ ‹‹ጦርነቱ በኢህአዴግ አሸናፊነት እንደሚደመደም በግልፅ መታየት ሲጀምር፣ የግንባሩ ከፍተኛ አመራሮች ውይይት አድርገው፣ ነገሩ ባማረ ሁኔታ ፍፃሜ ሊያገኝ የሚችለው በፍርድ አደባባይ እንደሆነ ሰፊ ክርክር ካደረግን በኋላ ውሳኔ አሳልፈን ነበር›› ብለዋል። ‹‹ኢህአዴግ የኢትዮጵያን የእርቅ ትውፊት በደንብ ያውቀዋል፡፡ ሆኖም በRestorative Justice ሰላም የማስፈን ስልትን በመተው፤ የደርግ ባለስልጣናት ጉዳይ በፍርድ አደባባይ እንዲያልቅ ወስኗል›› የሚለው ሻፈር፤ ኢህአዴግ ጉዳዩ በፍርድ እንዲታይ ውሳኔ ያደረገው፤ በሦስት መሠረታዊ ምክንያቶች መሆኑንም ይናገራል፡፡ የመጀመሪያው፤ የተፈፀመው የሰብአዊ መብት ጥሰት እና ከዘር ማጥፋት ጋር የተቆራኘ ፍጅት እጅግ አረመኒያዊ ተግባር በመሆኑ፤ ጉዳዩን ከፖለቲካ አድማስ እንዲወጣ ስላደረገው፤ ሁለተኛ፤ ለከት ያጣ እና ጨርሶ ተጠያቂነት የሚባል ነገር ያልጎበኘው፣ እንደ እብድ ሥራ ሊቆጠር የሚችል የኃይል አጠቃቀም የታየበት በመሆኑ፤ ትናንትን ከዛሬ የሚለየው መስመር በግልፅ እንዲሰመር ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ ሦስተኛ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ችግርን በፍርድ ሂደት እልባት የመስጠት የቆየ ታሪክ እና ልምድ ያለው ህዝብ በመሆኑ የፍርድ ቤት ውሳኔ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንደሚኖረው በማመን መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መናገራቸውን ሻፈር ይጠቅሳል፡፡
የቀይ ሽብር ወንጀል በኢትዮጵያ ህግ፣ በኢትዮጵያዊ ዳኞችና በኢትዮጵያዊ ዓቃቢያነ ህግ እንዲታይ መደረጉ ትልቅ ስኬት ቢሆንም፤ የአቅም፣ የገንዘብ፣ የልምድ ችግሮች ሂደቱን በማጓተት፣የፍትሕ ሂደቱን ጥራቱ አጓድሎታል፡፡ ‹‹ለመዋጥ ከሚችለው በላይ ለመጉረስ›› የሞከረውን የኢህአዴግ መንግስት እጄ ሰባራ አድርጎታል፡፡
ታዲያ ደርግ ከነባሩ የፖለቲካና የግጭት አፈታት ባህል በወጣ አካሄድ የፈጸመው ግፍ በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ያለመተማመን አስተሳሰብ አንግሷል። እንዲህ ዓይነቱን የሐገራችንን ሸክም የተረዱት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፤ ባለፉት 50 ዓመታት እንደ ህዝብ ከደረሰብን ከእንዲህ ያለ መከራ እንፈወስ ዘንድ የመረጡት ‹‹የሽግግር ፍትሕ›› - ፍቅር፣ ይቅርታ እና እርቅ ነው፡፡ ከዚህ መሰል የታሪክ ዳራ ወጥተን፤ መሠረታዊ መብቶች እና ነፃነቶች የተከበሩበት ፖለቲካዊ ስርዓት ለመፍጠር የምንችለው የሐገራችን ፖለቲካ ሰብአዊ መልክ እንዲይዝ በማድረግ መሆኑን ተረድተው፤ ‹‹እኔ ዶ/ር ብርሃኑን ገድዬ በስልጣን ለመቆየት፤ ዶ/ር ብርሃኑ እኔን ገድሎ ስልጣን ለመያዝ ማሰብ አይጠቅመንም›› በማለት፤ እንዲህ ዓይነት የፖለቲካ ባህል  ሊወገድ እንደሚገባ ደጋግመው ተናግረዋል፡፡
እንዲህ ያለ ግዙፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በግለሰቦች ጥረት የሚጠግግ ቁስል አይደለም፡፡ በጋራ ጥረት የሚታከም ቁስል እንጂ፡፡ እናም ‹‹የትም መቼም እንዳይደገም›› ስንል፤ የዚያን ስርዓት ችግሮች በመዘርዘርና የውግዘት ናዳ በማውረድ ሳይሆን፤ ያ ስርዓት እንደ ትቢያ የረገጠውን የህግ የበላይነት በማንሳት ተቋማዊና ህገ መንግስታዊ ስርዓት በማፅናት ነው፡፡
ከ1968 እስከ 1970 ባለው ጊዜ በተፈፀመው ‹‹ቀይ ሽብር›› ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን፣ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተገድለዋል፤ አለያም ቶርች ተደርገዋል። የህግ ሊቃውንት፤ ‹‹ለሰው ልጆች ታላቅ ሐሴትን የሚያጎናፅፍ፤ ታላቅ ምድራዊ ፀጋ ፍትሕ ነው›› ይላሉ፡፡ ከደርግ ወደ ኢህአዴግ በተደረገው ሽግግር ፍትህ ሲሰራ ማየት ለሐገራች ትልቅ ነገር ነው፡፡ ኢህአዴግ የሽግርር ሂደት ምዕራፉን የከፈተው፤ በዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ የቀረበባቸው የደርግ ባለስልጣናት፤ ሰብአዊ መብታቸው ተከብሮ ጉዳያቸው በፍርድ እንዲታይ በማድረግ ነበር፡፡   
የሽግግሩ መንግስት ዋነኛ አጀንዳ ያ የሰብዓዊ መበት ጥሰት፤ አንድ መልክ ይዞ እልባት እንዲያገኝ ማድረግ እና በደም ከተጨማለቀው የትናንት ታሪክ መውጣት፤ በተለያዩ የህብረተሰብ ቡድኖች መካከል እርቅ እንዲወርድ በማድረግ የአዲስ ተስፋ ምድር መፍጠር ነበር፡፡ ኢህአዴግ የደርግ ባለስልጣናትን ጉዳይ በፍርድ ቤት እንዲታይ ማድረጉ፤ ከትናንት ታሪክ የተለየ አካሄድ ለመከተል መወሰኑን የሚያመለክት ነበር፡፡ ሐገሪቱም ከኋላ ታሪኳ ጋር ለመታረቅ የምትችልበትን ዕድልም የፈጠረ ነበር፡፡ ኢህአዴግ በ960ዎቹ እና 70ዎቹ የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመመርመርና ወንጀለኞቹ በህግ የሚጠየቁበትን ሁኔታ በማመቻቸት ረገድ ያሳየው ቁርጠኝነትና የታየው የእስረኞች አያያዝ ሁኔታ፤ መጪውን ጊዜ ከትናንት የሚለይ አንድ ግልጽና ጉልህ መስመር ያሰመረ ነበር፡፡
በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠ/ሚ፤ ከኒው አፍሪካ መፅሔት ጋር (ሴፕቴምበር፣ 1994)፤ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ‹‹ለኢትዮጵያ ህዝብ ህግን የጣሱ፣ ሰብዓዊ መበትን የረገጡ ሰዎች፣ ራሳቸውን ከህግ በላይ አድርገው የተመለከቱ ሰዎች፤ በእርግጥ ከህግ በላይ እንዳልሆኑ አንድ ቀን ሂሳብ መወራረዱ እንደማይቀር፤ ዕዳ የሚከፈልበት፣ ሁሉም ሰው የእጁን የሚያገኝበት ጊዜ እንደሚመጣ በተጨባጭ ማሳየት በጣም አስፈላጊ ነው›› በማለት ተናግረው ነበር፡፡ ሆኖም የኢህአዴግ ከዛ በኋላ ያለው የታሪክ መዝገብ ከችግር የጸዳ እንዲሆን ለማድረግ አልቻለም፡፡ በቅርቡ በእስረኞች ላይ ምን ዓይነት ግፍ ይፈጸም እንደነበረ በመገናኛ ብዙሃን ከቀረቡ ዘገባዎች ተመልክተናል፡፡
ችግሩ ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፤ ክፉውን የኋላ ታሪክ እየነቀሱና እየጠቀሱ በህዝቦች መካከል አደገኛ የጥላቻ መንፈስ እንዲፈጠር የሚያደርግ ክፉ ሥራ ተሰርቷል፡፡ ከአንድነት ይልቅ ለልዩነት የሚገፋፋ አመለካከት ተጠናክሯል፡፡ አዳዲስ ቅራኔዎች ተፈጥዋል፡፡ ከፖለቲካ ባህል ድህነትና ከዴሞክራሲ ስርዓት ልምድ እጦት ጋር የተያያዙ ችግሮች በፖለቲካ መድረኩ ውጥረት እንግሰውበታል። ዴሞክራሲን ያልተለማመዱ እንደ እኛ ያሉ ሐገሮች ከአምባገነንነት ስርዓት ወደ ዴሞክራሲ ስርዓት ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት እጅግ ፈታኝ በመሆኑ፤ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ስርዓት ወጥተን ወደ ዴሞክራሲ ለመግባት ጉዞ ስናደርግ አርባ አራት ዓመታት ብናስቆጥርም ሥራው ገና ፈቀቅ አላለልንም፡፡
ስለዚህ በአዲስ የመደመር ፍልስፍና የፖለቲካ እና የታሪክ ሸክማችንን አውርደን፤ እስከ ዛሬ ሞክረን ስኬት ያላመጣልንን የአስተሳሰብ ጎዳና ትተን፤ ይቅርታ እና ፍቅርን መሪ ቃላችን አድርገን፤ ሕዝብን ወደ አንድ ሐሳብ የሚያመጣ የመደመር ርዕዮተ ዓለም ይዘን መጓዝ ጀምረናል፡፡ የሕዝብ ልብ በፍቅር ተሸንፎፏል። የኢትዮጵያ ምድርም በመጠኑ እፎይ ብላለች። ተስፋ እና ደስታን አግኝታለች፡፡ ይህን አዲስ አስተሳሰብ በደንብ ከተረዳነውና ከተገበርነው ለሐገር ልማት እጅ ለእጅ ተያይዘን መሰራት እንችላለን፡፡ መደመር ለሥልጣን መናቆርና ማናቆር ያለፈበት ፋሽን መሆኑን ያስረዳናል፡፡ በዚህም በምንም ዓይነት ሊታከም የማይችል የሐገር ቁስል ይታከማል፡፡

Read 1227 times