Saturday, 22 September 2018 14:57

የተፈናቀሉ ተጎጂዎች በደላቸውን ይናገራሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 ባለፈው ሳምንት በቡራዩና አካባቢው በተፈፀመ ጥቃት ከ50 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን በአዲስ አበባ ኮልፌና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች ከ12 ሺህ በላይ ወገኖች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው በተለያዩ አካባቢዎች መጠለላቸው ታውቋል፡፡ ከተፈናቃዮቹ መካከል 4ሺህ ያህሉ በጉለሌ ክፍለ ከተማ በሸጐሌ፣ በሽሮ ሜዳና በአዲሱ ገበያ ወጣት ማዕከላት የተጠለሉ ሲሆን፤ በመድሃኒዓለም መሰናዶ ት/ቤት ብቻ 2ሺህ ያህል ተፈናቃዮች ተጠልለው አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ በጉለሌ ክ/ከተማ የወረዳ ዘጠኝ ዋና አስተዳደሪ አቶ እምሩ ሽፈራውና የጉለሌ ክ/ከተማ ወጣቶች ፌደሬሽን ሰብሳቢ አቶ ስንታየሁ ሰርጋዊ ተናግረዋል፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት የትምህርት መጀመሪያ ጊዜ እንደመሆኑ ት/ቤቱ የሚፈለግ ቢሆንም፤ ምን እናድርግ በሚለው ላይ ከወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን፣ የምግብ አቅርቦትን በተመለከተ ወረዳው ከክ/ከተማው ጋር በመተባበር ከፍተኛ በጀት መድቦ በጨረታ ያሸነፉ አራት ምግብ አቅራቢ ማኅበራት ምግብ እንዲያቀርቡ በማድረግ፣ ደረጃውን የጠበቀ ምግብ እያቀረቡ መሆናቸውን ኃላፊዎቹ ገልፀው፤ ተጐጂዎች ሕክምና እንዲያገኙ በት/ቤቱ ውስጥ በተቋቋመው ጊዜያዊ ክሊኒክ በጥሩ ሁኔታ አገልግሎት እያገኙ ነው ተብሏል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ተፈናቃዮች ከተጠለሉበት በአንዱ ማለትም በመድሃኒዓለም መሰናዶ ት/ቤት ተገኝታ፣ የጥቃት ተጎጂዎችን አነጋግራ፣ የጥቂቶቹን አሳዛኝ ታሪክ፣ እንዲህ አጠናቅራዋለች፡፡ እነሆ፡-
          
                   “እንደ እባብ ተቀጥቅጬ ሽባ ሆኛለሁ”
                      ከዝሩ ከልሌ

     ከ20 ዓመታት በላይ የኖርኩት ቡራዩ ድሬ ሶሎሊያ ከማሪያም ሰፈር አለፍ ብሎ ነው፡፡  ለበርካታ ዓመታት በሰላም እየሰራሁ ነበር ያሳለፍኩት፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ይበልጥ በሰላም የምኖርበትና ይበልጥ ኑሮዬን የማሻሽልበት ዓመት እንደሚሆን እገምት ነበር፡፡ ጥቃቱ በደረሰብኝ ዕለት ሸማ መስራት ላይ ተሰማርቼ ነበር። መጡ ብዙ ሆነው፡፡ “እዚህ ምን ትሰራለህ? ብሔርህ ምንድነው?” ሲሉኝ፣ ዶርዜ ነኝ አልኳቸው፡፡ መታወቂያ ሲጠይቁኝ፣ አለኝ ግን ቤቴ ነው ያለው አልኳቸው፡፡ “ሂድና አምጣ” ሲሉኝ፣ እሺ ብዬ ስሄድ፣ 30 ይሆናሉ፣ ተከትለውኝ ቤት ገቡ፡፡
በዚያ አካባቢ የሚኖሩ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም አይቻቸው አላውቅም፡፡ ቄሮ ይሁኑ አይሁኑም አላውቅም፡፡ ከሌላ ቦታ ተሳፍረው ነው የመጡት። መታወቂያዬን ላሳይ ስገባ ተከትለው ገብተው ቀጠቀጡኝ፡፡ ጮህኩኝ፣ ሰው ሁሉ ወጣ፤ ተሰበሰበ፡፡ በወቅቱ ማንንም ከማንም መለየት አይቻልም፡፡ በቢላዋ ተመልከቺ፣ እግሬን ቆራርጠው፣ በዱላ አድቅቀው፣ ራሴን ስስት ነው፣ ሞቷል ብለው ጥለውኝ የሄዱት (ለቅሶ…) ራሴን ስቼ ከቆየሁ ከሁለት ሰዓት በኋላ ከባድ ዝናብ ዘንቦ ቅዝቃዜው አነቃኝ፡፡ ራሴን ሳውቅ አንድ ቦታ አልተረፍኩም፤ ስብርብሬ ወጥቷል፡፡ “በእግዚአብሔር አድኑን” ብለን ለጐረቤት ብንጮህ፣ ”የእናንተ ጦስ ለእኛም ይተርፋል” ብለው ጨከኑብን፡፡ ፖሊስ እያየ እየሰማ፣ ዝም ብሎ አሳልፎ ሰጠን፡፡ አይናችን እያየ፣ ሰው አንገቱን አንጀቱን በቢላና በቆንጨራ ሲቆረጥ--- በጣም አዝነናል፡፡ ዶርዜም ብንሆን ኢትዮጵያዊያን ነን፡፡ ወገን ነን፡፡ በቀጣይ ህይወታችን እንዴት ነው የሚገፋው፣ ተመልከቺኝ እግሬም እጄም ከጥቅም ውጭ ሆኗል፡፡ ከልጅነት እስከ እውቀት ያፈራነው ንብረት የለም፡፡ ወደፊት ተስፋ የለንም፡፡ መንግስት በአደባባይ እንደ በግ የታረደውን ህዝብ ደም፣ እንዴት ነው የሚመልሰው? (ለቅሶ…) በተረፈ እዚህ ያመጣንን መከላከያና የአዲስ አበባን ህዝብ በጣም አመሰግናለሁ። እዚህ እየታከምን ምግብም፣ የምንጠጣውም፣ ልብስም እየቀረበልን ነው፡፡ ህዝቡን አሁንም ፈጣሪ ብድሩን ይክፈለው እንጂ እኛማ ወድቀን ቀርተን ነበር፡፡ ለአጥቂዎቻችንም ልብ ይስጣቸው! ከማለት ውጭ በቀል የምናስብ አይደለንም፡፡


-----------------


                ዶርዜ ጥበብ የሚያለብስ ጥበበኛ እንጂ ሀቅ የሚጋፋ አይደለም”
                  ወ/ሮ አየለች ምልክ

   የአቶ መንግስቱ ኦሼ ባለቤት ነኝ፡፡ እኛ ጋ ድብደባና ዘረፋ የተጀመረው ሀሙስ ከመስከረም 3 ቀን ጀምሮ ነው፡፡ “ዶርዜ አውጡ አጋልጡ” እየተባለ ነበር፡፡ “በቃ ሂዱ፤ ዶርዜ የለም” ተብለው ሄደው ነበር፡፡ ተመልሰው መጥተው፣ ቤትና አጥር ሲቀጠቅጡ ውለው ሲበቃቸው ሄዱ፡፡
እኛ ሸሽተን ባለንበት ቤታችን ዝብርቅርቅ አድርገው፣ እቃችንን ንብረታችንን አውጥተው ደጅ ጭቃ ላይ ጥለው ሄዱ፡፡ አርብም ተመልሰን እቤት አደርን፡፡ ቅዳሜ በጠዋት መጡ፡፡ ህፃን፣ አዋቂ፣ አሮጊት፣ ሽማግሌ ሁሉም ዱላ ይዟል፤ እቤቴ ገብተው ከላይ እስከ ታች ሰውነቴ አልቀራቸውም፣ ቅጥቅጥ አደረጉኝ፡፡ ባለቤቴንም ጐትተው አውጥተው እንደምትመለከቺው፣ ስብርብር አድርገው ሞተ ብለው፣ ጥለውት ሄዱ፡፡
ባለቤቴ ደም አስክሮት ብድግ ብሎ ሊሮጥ ሲል፣ ተመልሰው እንዳይሆን አድርገውት ሄዱ፡፡ እኔም ከላይ እስከ ታች ሰውነቴ ደቅቆ አለሁ፡፡ ከዚያ ፌደራል ፖሊሶች መጥተው ነው ነፍሳችን የተረፈው፡፡ ሐሙስና አርብ ለአካባቢው ፖሊስ አመልክተን የመጣልን የለም። እንደሚመስለኝ ፖሊሶቹ አጥቂዎቹን ይፈሯቸዋል፡፡ ባሌ የሬሳ ያህል ወድቆ፣ ፖሊሶቹ ሰው እንደማትረፍ፣ ወደ ሀኪም እንደ መውሰድ አጥቂዎቹን ሰብስበው፣ በራሳቸው ቋንቋ ይነጋገራሉ፡፡
ሌላው ኮርኒስ ውስጥ ተደብቆ የነበረው የባለቤቴ ወንድም፣ እኛን ሲቀጠቅጡ ድንገት ከኮርኒስ ዱብ ብሎ ሲወርድ እዛው ሲቀጠቅጡት ድንገት አምልጦ ሄደ፡፡ እሱ ሲያመልጥ የአካባቢው ሰው ጥይት ተኮሰ፡፡ እሱ ነው ተኩሶ ያመለጠው ብለው፣ ስሙን መዝግበው ያዙ፡፡ የእናቴ ልጅ፤ እኛ እንኳን ሽጉጥ ልንገዛ እንጀራ ጠግበን ያልበላን ሰዎች ነን፡፡ ከዚያ እኔም ተቀጥቅጬ፣ ባለቤቴም ማጅራቱ እግሩ ከጥቅም ውጭ ሆኖ፣ አፋፍሰው ሐኪም ቤት ወሰዱን፡፡
እዚህ ከመጣን ዕድሜ ለአዲስ አበባ ወጣትና ለህዝቡ፣ ነፍስ ዘርተን መኝታ፣ ምግብና ንፁህ ውሃ አግኝተን እየታከምን አለን፡፡ ዶርዜ ምን አደረገ? ጥበብ ሰርቶ የሚያለብስ ጥበበኛ ህዝብ እንጂ ሕግ የሚተላለፍ አይደለም፡፡ ባለቤቴ ዶርዜ፣ እኔ አማራ ነኝ። አብረን በፍቅር ነው የኖርነው፤ ልጆች ወልደናል። ምን አደረግን? ምንስ በደልን? ሰርተን ጉልበታችንን አፍስሰን፣ በአገራችን ነው የምንኖረው፡፡ መንግስት ለዚህ ሁሉ ግፍና በቃል የማይገለፅ በደል ምን ምላሽ አለው? የእኛስ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው? የሚለው ያሳስበኛል (ለቅሶ…) የባሌ ወንድም ሊጠይቀን ሲመጣ ወስደው የት እንዳሰሩት አናውቅም፡፡ አሁንም ነፍሳችንን ለታደገን የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ እንጀራ ይውጣለት፡፡ ብድራቱን በልጆቹ ያግኝ፣ ሌላ የምለው የለኝም፡፡   

-----------

                “ኢትዮጵያዊነቴን፣ ዜግነቴን ተጠራጥሬያለሁ”
                   ካማ ካሳ

    ቀሪ ቡራዩ ከቄራው በላይ ነው የምኖረው፡፡ ጥቃቱ የደረሰብኝ ቅዳሜ ዕለት ነበር፡፡ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ነበርኩኝ፡፡ ስፍር ቁጥር የሌላቸው በርካታ ወጣቶች መጡ፡፡ ምንድነው ስንል፣ ቄሮዎች ናቸው አሉን። ፌሮ፣ ቆንጨራና የቧንቧ ብረት ይዘዋል፡፡ እርግጥ ከልጅ እስከ አዋቂ እዛ ሰፈር የሚኖሩ በርካታ ሰዎች አብረው ከአጥቂዎቹ ጋር አሉ፤ እነሱ ግን አይማቱም፡፡ ደብዳቢዎቹ “እዚህ ቁጭ ያላችሁት ምን አለን ብላችሁ ነው? ወጥታችሁ አትሄዱም?” አሉን፡፡ እኛ መች አወቅን? የትስ እንሂድ? ብለን ጠየቅን፡፡ “ትታረዳላችሁ፤ አሁንማ በየት ታመልጣላችሁ!” አሉን፡፡ አንዱ በቀኝ እጁ ቆንጨራ፣ በሌላ እጁ የበሬ ማረጃ ቢላዋ ይዞ “ካላረድኩት” አለ - እኔን፡፡ እግዚአብሔር ይስጠውና አንዱ፣ ከሌሎቹ ጋር ተከራክሮ ነፍሴ ተረፈ፡፡
የድብደባውን ነገር አታንሺው፣ ተመልከቺ፤ አንዱ እግሬ እንዳለ አጥንቴ ድቅቅ ብሎ ብረት ገብቶልኛል። አንዱ እግሬ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ተቀጥቅጦ በጀሶ ተጠግኗል፡፡ ወገቤ አንድ የለም፡፡ ጭንቅላቴን ተመልከቺው፤ በጣም ተፈንክቶ አደገኛ ሁኔታ ላይ ነኝ፡፡ በራሴ አልንቀሳቀስም (ይህ ወጣት የቁስሉን ፋሻ ለማስቀየር በጊዜያዊነት ወደተቋቋመው ክሊኒክ ሲወሰድ በአምስት ሰው ሸክም እንደነበር ለማየት ችያለሁ) በሰው ድጋፍ ነው፡፡ በተደበደብኩበት ቦታ ለብዙ ሰዓት ራሴን ስቼ ነበር፡፡ ስነቃ ተነስቼ ስሮጥ ድጋሚ ደብድበው፣ በሞትና በህይወት መሀል ሆኜ እንደሰማሁት፤ መሪያቸው ሀጫሉ ይባላል፤ እሱ ነው እግሬን የሰበረኝ፡፡ እሱ ይመራቸዋል፤ ምቱ ሲላቸው ይማታሉ፣ ተው ሲላቸው ይተዋሉ፡፡ እሱ ሊጨርሰኝ ሲል ነው፣ አንዱ ተከራክሮ ያዳነኝ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ፖሊስ በአካባቢው አለ፡፡ ይህ የማይካድ ሀቅ ነው። ፖሊሶቹ ለወጣቶቹ ሲያቀብሉ በአይኔ አይቻለሁ፡፡ ይህ ምንድነው የሚባለው?! - ከዚያ የኦሮሚያ ፖሊስ በአምቡላንስ ጳውሎስ ሆስፒታል አመጣኝ፡፡ ታከምኩ ነገር ግን ተስፋ የለኝም፡፡
ሕግ ባለበት፣ መንግስት ባለበት ሀገር፣ እንዴት ይህ ግፍና በደል ይፈፀማል፣ ወይስ እኛ ሳናውቅ ሕግም መንግስትም የሉም? ኢትዮጵያዊነቴን፣ ዜግነቴን ተጠራጥሬያለሁ፡፡ ጥቃቱ በደረሰበት ቦታ ለ15 ዓመታት ኖሬያለሁ፡፡ ሸማ በመስራት 3 ልጆቼንና ባለቤቴን አስተዳድራለሁ፡፡ ምንም ያጠፋሁት ነገር የለም፡፡ ከስራ ውጭ ምንም አላውቅም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ለዚህ ግፍ ምን ምላሽ እንደሚሰጥ አላውቅም፡፡

-----------

               “እዛ ጫካ ውስጥ ብሆን፣ ከእነ ልጄ ሞቼ ነበር”
                  ካሎሴ ካሴ

    እኔ እኖር የነበረው ገፈርሳ ድሬ አካባቢ ነበር። እንደምታይው እግሬ በቢላዋ ተቆራርጧል፡፡ ይሄ ረብሻ ሲነሳ የምታይውን ህፃን ልጅ ይዤ፣ ጣሪያ ውስጥ ተደብቄ፣ ቤቱን ሲደበድቡት ልጄን ይዤ ከጣሪያ ላይ ወደቅኩኝ፡፡
ከዚያ በዱላ ይደበድቡኝ ጀመር፡፡ ደብዳቢዎቹ እነማን እንደሆኑ አላውቅም፡፡ “እዚህ ቤት ያሉትን ወንዶች አውጭ፤ ያለበለዚያ ከእነ ልጅሽ እናርድሻለን” አሉኝ፡፡ “ቤቱን ፈትሹ፣ እኔ ማንንም አልደበቅኩም፤” ብላቸውም፣ ከዱላ አልፈው እግሬን በቢላ ሰነጠቁኝ፡፡ ተመልከቺ፤ እግሬ ክፉኛ ተጐድቷል፡፡ “የባልሽን ስልክ ቁጥር አምጪ እንደውልለት” ሲሉ የለኝም አልኳቸው። ጥለውኝ ሲሄዱ፣ ልጄን ይዤ ጫካ ሄድከኝና ተደበቅኩኝ፡፡
በዚያ ጫካ ውስጥ ያለ ምግብ ያለ ውሃ፣ ህፃን ልጄን ይዤ አደርኩ፡፡ ከአውሬ፣ ከረሃብና ከሞት ተርፌ፣ እዚህ መጠለያ መጣሁ፡፡ ያመጡኝን እግዚአብሔር ይስጣቸው፡፡
እስካሁን እዛ ጫካ ውስጥ ብሆን ከእነ ልጄ ሞቼ ነበር፡፡ ባሌ እዚህ ከእኔ ጋር አለ፡፡ ልጄ የት እንዳለ አላውቅም፡፡ እዚህ ህክምናም ምግብም አለ፡፡ እየተንከባከቡን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ደርሶልናል፡፡ እናመሰግናለን፡፡

----------

              “ለእንስሳት እንኳን የማይገባ ግፍ ነው የተፈፀመብን”
                 አቶ መንግስቱ ኦሼ

    ከታ አካባቢ መድሃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ጋ ነው የምኖረው፡፡ በቦታው ከአምስት ዓመታት በላይ ኖሬያለሁ፡፡ በሽመና ሥራ ነበር የምተዳደረው። ጥቃቱ ከመድረሱ በፊት ከአንዴም ሁለት ጊዜ መጥተው ተመልሰዋል፡፡
ቅዳሜ ጠዋት 3፡00 ሰዓት ሲመጡ ለማምለጥ መሄጃ አልነበረንም፡፡ በራችንን ደበደቡት፤ ተበረገደ። ያን ጊዜ ከቤት አውጥተው፣ በር ላይ ከጣሉኝ በኋላ መደብደብ ጀመሩ፡፡ ተመልከቺ፤ መትረፌ ተዓምር ነው፡፡ ማጅራቴን፣ ጭንቅላቴን፣ እግሬን-- ምን የተረፈኝ ቦታ አለ፡፡ ዓይኔን ሊመቱኝ ሲሉ፣ በእጄ መከትኩኝ፡፡ እንደምታይው፤ እጄ ከጥቅም ውጭ ሆነ፡፡ ሞተ ብለው ጥለውኝ ሄዱ፡፡ ከዚያ ታናሽ ወንድሜን እንጀራ ጠግቦ ያላደረ ሰው፤ ጥይት ተኩሷል ብለው ወንጀሉት፡፡ ይህን ያሉት ስላመለጣቸው ነው። በድንጋይ፣ በፌሮ፣ በዱላ ብቻ ተረባረቡብኝ፡፡ አሁን መቆም አልችልም። ሁለት ልጆችና አጠገብሽ ያለችው ባለቤቴ ናት፡፡ እሷም በሴትነቷ ሳትከበር፣ ከፍተኛ ድብደባ ደርሶባታል። አንዱን ልጄን ጐረቤት ደብቄ፣ አንዱን እዚህ ይዘን መጥተናል፡፡ ምንም በማናውቀው በገዛ አገራችን፣ በራሳችን ወንድሞች፣ እንዴት እንዲህ አይነት ጥቃት ይደርስብናል፡፡ አንድ ሰው እኮ ቢያጠፋ በሕግ ይጠየቃል፡፡ እኛ የእግዚአብሔር ፍጡሮች እንጂ እንስሳ አይደለንም፡፡
መንግስት ይህንን በደላችንን አይቶ በግፈኞች ላይ እርምጃ ካልወሰደና ለቀጣይ ኑሯችን መፍትሄ ካልሰጠን፣ ምንም ተስፋ የለንም፡፡ እዚህ መጠለያ ውስጥ የሚደረግልን እንክብካቤ፣ የአዲስ አበባ ህዝብና ወጣቱ የሚያደርግልን እንክብካቤና አይዟችሁ ባይነት ነው ተስፋ እንድንሰንቅ ያደረገን - እንጂ ተስፋ ቆርጠን ነበር፡፡ ህዝቡን በጣም እናመሰግናለን፡፡

Read 2626 times