Saturday, 22 September 2018 14:50

የኢህአፓ አመራሮች ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ «ለህዝብ መብት መሞት አኩሪ ታሪክ ነው»

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

 ከተመሠረተ ከአራት አሰርት ዓመት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) አመራሮች ዛሬ መስከረም 12 ቀን 2011 ዓ.ም አዲስ አበባ እንደሚገቡ  የአቀባበል ስነ ስርዓት አዘጋጆቹ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
ባለፉት 46 ዓመታት በሃገር ውስጥ እና በውጪ ሃገር በሚገኙ አባላቱ አማካኝነት በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ሲታገል መቆየቱን የገለፀው ኢህአፓ፣ አሁን የተፈጠረውን ምቹ የፖለቲካ ሁኔታ በመጠቀም፣ አመራሮቹ ወደ ሃገር ቤት ለመመለስ መወሰናቸውን አስታውቋል።
“በአሁኑ ጊዜ በሃገራችን እየታየ ያለው የለውጥ ብልጭታ፣ ለዘመናት ስታገልለት የቆየሁለት አቋሜ ውጤት ነው” ያለው ኢህአፓ፤ ይህን የለውጥ ሂደት ለመደገፍና የተጀመረውን የሰላም የዴሞክራሲና የአንድነት ጭላንጭል እንዳይደበዝዝ፣ የድርሻቸውን ሊወጡ፣ አመራሮቹ ዛሬ አዲስ አበባ እንደሚገቡ አስታውቋል፡፡
ኢህአፓ በዋናነት የሚታገልላቸው አላማዎችም፤ የአዲሱ ትውልድ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ፣ የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባና  ነው ብሏል ለህዝብ መብት መሞት አኩሪ ታሪክ መሆኑን በተግባር ማሳየት ጠቁሟል፡፡
ዛሬ ለረጅም ዓመታት በስደት ከኖሩበት ወደ ሃገር ቤት ከሚመለሱ ከፍተኛ አመራሮቹ መካከል ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም፣ አቶ መሐመድ ጀሚል፣ ሊቀመንበሩ አቶ መርሻ ዮሴፍና ኢ/ር ሰለሞን ገ/ስላሴ ይገኙበታል፡፡
ከጠዋቱ 1 ሰዓት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚደርሱት እነዚህ ከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች፤ መስቀል አደባባይ አካባቢ የሚገኘውን የሰማዕታት ሐውልት ይጐበኛሉ፣ ለሰማዕታቱም የአበባ ጉንጉን ያስቀምጣሉ ተብሏል፡፡
«ዛሬ ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱት ኢህአፓዎች ከዶ/ር አቢይ ጋር ሲወያዩ የተናጋና  ሠሚ  ዓይነት  መሆን የለበትም፤ ጠንካራ ውይይት ነው የሚያስፈልገው» ያለው የቀድሞ የኢህአፓ አባል፣ ገጣሚና ተርጓሚ ነብይ መኮንን «አመጣጡ ላይ ብዙ ደጋፊ ሊቀበላቸው ይችላል፣ ነገር ግን ለህዝቡ  ምን ለውጥ ሊያመጡ ነው የተዘጋጁት የሚለው ነው መሠረታዊ ጥያቄው» ብሏል፡፡

Read 8709 times