Print this page
Saturday, 22 September 2018 14:42

ከጅብ ጅማት የተሠራ ክራር ቅኝቱ ልብላው ልብላው ነው!

Written by 
Rate this item
(13 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን ጅቦች በጠፍ ጨረቃ ተርበው የሚበላ ፍለጋ ሲዘዋወሩ አንድ ግዙፍ ዝሆን ገደል ገብቶ ሞቶ አዩ፡፡
አንደኛው ጅብ - በረሀብ ከምንሞት እንግባና እንብላው
ሁለተኛው ጅብ - ገደሉ በጣም ሩቅ ነው፡፡ እንኳን ገብተን ሆዳችን ሞልቶ እንዲሁም ለመውጣት አዳጋች ነው፡፡ ስለዚህ መዘዋወራችንን እንቀጥልና የረፈደበት አህያ እንፈልግ፡፡
ሦስተኛው ጅብ - እንግባና ከበላን በኋላ እንደጋገፍና አንዳችን አንዳችን ትከሻ ላይ እየወጣን ከገደሉ እንወጣለን፡፡
አራተኛው ጅብ - ከገባን በኋላ እናስብበታለን
አንደኛው ጅብ - በድምፅ ብልጫ እንለየው
ሁሉም በድምፅ ብልጫ ይሁን በሚለው ሀሳብ ተስማሙ፡፡
አንደኛው ጅብ - እሺ፤ እንግባና በልተን እናስብበታለን የምትሉ?
ሁሉም እጃቸውን አወጡ፡፡
በሙሉ ድምፅ እንብላው አሉና ተግተልትለው ገቡ፡፡
ለአንድ ሁለት ሦስት ቀን ፈንጠዝያ ሆነ፡፡ ዋለ አደረና የዝሆን መቀራመቱ ጥጋብ አበቃና፣ ረሀብ በተራው ይሞረሙራቸው ጀመር፡፡
እንደተገመተውም ከገደሉ መውጫው ዘዴ ሊገኝ አልተቻለም፡፡
እየተራቡ መተኛትም ሆነ ዕጣ-ፈንታቸው፡፡ አንድ ሌሊት አንደኛው ጅብ ጐኑ ላለው ጅብ፤ “በጣም የተኛውንና ዳር ያለውን ጅብ ለምን አንበላውም?” ሲል ሀሳብ አቀረበ፡፡ አንዱ ለአንዱ እያማከረ፣ ዳር ላይ ለጥ ያለው ላይ ሰፈሩበት፡፡ ለአንድ ሁለት ቀን ፈንጠዝያ ሆነ፡፡
እንደገና ረሀብ ሆነ፡፡ በዚያው ተዘናግቶ በተኛው ተረኛ ጅብ ላይ እየፈረዱ፣ በመጨረሻው ሁለት ቀሩ፡፡ ብዙ ለሊት እየተፋጠጡ አደሩ፡፡ ሆኖም መድከም አይቀርምና አንዱ ደክሞት ተኛ። የነቃው በላው፡፡ ጥቂት ሰነበተና እራሱም በረሀብ ሞተ!
*   *   *
የሀገራችን የሙስና ደረጃ ገና ያልተጠረገ በረት ነው፡፡ “አህያም የለኝ ከጅብም አልጣላ” ብለን የምንዘልቀው እንዳልሆነ ካወቅነው ውለን አድረናል፡፡ “ሙስናው በአዲስ መልክ ሥራ ቀጥሏል፡፡” እንዳንል፣ መረር ከረር ብሎ መገታት እንዳለበት መገንዘብ ያሻል፡፡ ብርቱ ጥንቃቄና ብርቱ እርምጃ ግድ ነው፡፡ “ግርግር ለሌባ ያመቻልና” የህዝቡን ፀጥታ የሚያደፈርስን ሁኔታ በችኮላም ሳንደናገር፣ በመኝታም ሳንዘናጋ በአስተውሎት መጓዝና ፍሬ ያለው ሥራ መስራት ያሻል፡፡ በየትኛውም አገር ለውጥን ተከትሎ የሚመጣ አደናጋሪ ሁኔታ ይከሰታል፡፡ “የምጣዱ እያለ የእንቅቡ መንጣጣቱም” ሆነ፤ “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች” መባሉ የነበረ፣ ያለና ወደፊትም የሚኖር በመሆኑ፤ ነፃ አስተሳሰቡን እጅግ ልቅ ሳናደርግ፣ ግትርነቱንም (die-hardism) እጅጉን ሳናከርረው፣ በሥነ ሥርዓትና በዲሲፕሊን መራመድ ብቻ ነው የሚጠበቅብን። የረፈደ ነገር ያለ ቢመስለን አይገርምም! የአጭር ጊዜ ለውጥ ነውና! አመለካከታችን እስኪጠራ፣ በሀገራችን ህዝብ ዘንድ ብትሰራም ትኮነናለህ - ባትሰራም ትኮነናለህ (Do, damned! Don’t damned) ነውና፣ የያዝነውን መንገድ አለመልቀቅ ረብ ያለው እርምጃ ነው፡፡ ሰላምን ማደፍረስም ለሙስና ማራመጃም መከላከያም ሊሆን የሚችል አደገኛ መሣሪያ ነው! ዞሮ ዞሮ “ከጅብ ጅማት የተሰራ ክራር ቅኝቱ ልብላው - ልብላው ነው” ከሚለው ተረት አይዘልም! ወንጀሎችን እንቆጣጠር! የመሣሪያ ዝውውርን በሕግ የበላይነት ሥር እናድርግ! “ጦር ሜዳ ማህል ግጥም አታነብም” እንደሚባል አንዘንጋ! ዘረፋን እንቋቋም! ያለ መስዋዕትነት ድል የለም! ከመጠምጠም መማር ይቅደም! የዕውቀትንና የባለሙያን ግብዓት በየፕሮግራሞቻችን ውስጥ ቀዳሚ እናድርግ፣ ከዘርና ከጐሣ ግጭት ወጥተን፣ በዲሞክራሲና በሕግ የበላይነት ራሳችንን እንገንባ! የዴሞክራሲያዊነት እንጂ የገዥነትና የተረኝነት ስሜት የትም አያደርሰንም!

Read 7804 times
Administrator

Latest from Administrator