Saturday, 15 September 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)


            “አዕምሮአችን በየጊዜው ካልታደሰ ይዝጋል”
               
     ከአዳዲስ ቀልዶች ባንዱ እንዝናና፡-
ልጅ፡- “አባዬ!”
አባት፡- “አቤት!”
ልጅ፡-  “መደመር ማለት ምን ማለት ነው?”
አባት፡- “አንድ ላይ መሆን ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ እኔና አንተ አንድ ላይ ስንደመር ሁለት እንሆናለን፣ እናትህ ስትመጣ ደግሞ ሦስት እንባላለን” ልጁ አንዳንድ ቀን ከአባትና ከእናቱ ጋር መተኛት ሲፈልግ…
“ዛሬ ከናንተ ጋር ልደመር” በማለት ይጠይቃል፡፡
“ና ተደመር” ይሉትና መሃላቸው ገብቶ ይተኛል። አንድ ቀን እናት ገበያ በሄዱበት አባት ሰራተኛቸውን ያስጠራሉ፡፡ ልጁ ከሚጫወትበት ቦታ ሲመለስ ሰው አልነበረም፡፡ ቢጣራም መልስ አላገኘም፡፡ እርቦታል። ማልቀስ ጀመረ፡፡ ለቅሶውን እንደሰሙ ከነበሩበት ወጡ።
“ተደምራችሁ ነው?” ሲል ጠየቀ ልጁ፡፡
“አይ አልተደመርንም” አሉ አባት፡፡
ልጁም… “ምነው አንተና እማዬ አንድ ላይ ስትሆኑ መደመር ነው አላልከኝም?” ሲላቸው…
“ልክ ነው ብዬሃለሁ፡፡ ከሌላ ሰው ጋር ከሆንኩ ግን “መቀነስ” ነው የሚባለው” አሉት፡፡ በዚህ መሃል እናት ከጉዳያቸው ተመለሱ፡፡ የልጃቸውን ፊት አይተው…
“ምን ሆነህ ነው?” እያሉ ሲደባብሱት፣ አባት ሹክክ ብለው ወጡ፡፡
“እርቦኝ ነው” አላቸው፡፡
እናትም፤ “ለምንድነው የሚበላውን ያልሰጠሽው?” እያሉ ወደ ኩሽናው ተጣሩ፡፡
“እያቀረብኩ ነው” አለች አጅሪት፡፡
በዚህን ጊዜ…
“እኔ ስመጣ ከአባዬ ጋር ተቀንሳ ነበር” አለ ልጁ፡፡
“ምን ማለት ነው እሱ?... የት ሄዳ ነበር?” ሲሉ እናት ጠየቁ፡፡…
“እዛ ነበረች… ከአባዬ ጋር”… ሲላቸው እናት ቱግ አሉ፡፡ ወደ ኩሽናው እየተቻኮሉ…
“አንቺ ምንድነው የምሰማው?... የምን መቀነስ ነው?” በማለት ሲያፈጡ፡-
“ሂሳብ የቤት ሥራ ነበረብኝ፤ እሱን እያስረዱኝ ነበር” አለች አጅሪት፡፡ (ማታ ማታ ትማራለች፡፡) በዚህን ጊዜ ሴትዬዋ መጥረጊያ ብድግ አድርገው… ምን እንዳሏት ታውቃለህ?... እስኪ ገምት፡፡
*   *   *
ባለፉት ቀናት የታጠቡት ዕድፎቻችን ብዙ ናቸው። ለዘመናት ተነክረን የኖርንባቸው ሐጢአቶቻችን፣ ሰላማችንን የበከሉ እንከኖቻችን፣ እኛነታችንን እንዳናውቅ፣ ሰው መሆናችንን እንድንረሳ፣ ዓይኖቻችንን የጋረዱ ቆሻሻዎች የተወገዱበት ቀናት ነበሩ፡፡ … ጳጉሜ ሁለት ሺ አስር!!
ወዳጄ፡- እስኪ ሁለት አዳዲስ ብርጭቆዎች ወይም ሰሃኖች ግዛ፡፡ ከፈለግህም ልብስ፣ ጫማ፣ መኪና፣ ጄነሬተር ወይም ሌላ ነገር፡፡… ሁለት ብቻ ይሁኑ፡፡ አንደኛውን ሜዳ ላይ አስቀምጠህ ተወው፡፡ አንደኛውን ግን በየዕለቱ ተገልገልበት፡፡… ብላበት፣ ጠጣበት፣ ስራበት፣ ከጨረስክ በኋላ በደንብ አጽድተህ ከንፁህ ቦታ አስቀምጠው፡፡… በተጠቀምክበት ጊዜ ሁሉ እንዲሁ አድርግ፡፡ ከዓመታት በኋላ ሁለቱን እቃዎች ጐን ለጐን አድርገህ ተመልከታቸው፡፡ በየጊዜው እየፀዳ ጥሩ ቦታ የሚቀመጠው ዕቃ ንፁህ ነው፡፡ ሜዳ ላይ የተውከው ግን ተበላሽቷል፣ ዝጓል፣ በስብሷል ወይም ነክሷል፡፡ የበፊት መልኩን ለማውጣት ትታገላለህ፡፡ ስትፍቀው ይሰነጠቃል፣ ስትፈትገው ይቀደዳል፣ ስትቀጠቅጠው ይጨራመታል፣ ይጐብጣል፣ ይሰበራል፡፡ ወደነበረበት መመለስ አይቻልም፡፡ የተከልከው ፍሬም ኮትኩተህ፣ አርመህና አቃንተህ ካላሳደግኸው ፍሬ አያፈራም፣ ይደርቃል፣ ይጐብጣል፣ በግድ ልታቃናው ብትሞክር ይሰበራል፡፡… የሰው ሃሳብም እንዲሁ!!
ወዳጄ፡- አእምሯችን በየጊዜው ካልታደሰ፣ ካልፀዳና ንፁህ ካልሆነ ይዝጋል፡፡ ይቆሽሻል፡፡ መመራመር፣ ማመዛዘን፣ አዲስ ነገር ለስልጣኔያችን ማበርከት አይችልም፡፡… ምክንያታዊም አይሆንም፡፡ ባለቤቱን ብስጩና ቁጡ፣ አኩራፊና ቂመኛ፣ አስመሳይና ጉረኛ፣ ቀናተኛና በቀለኛ፣ ድንጉጥና ተጠራጣሪ፣ ችኩልና ጀብደኛ፣ ነጭናጫና ነዝናዛ ያደርገዋል፡፡ ባልተገራ ስሜት ያናውዘዋል፡፡ የአስተሳሰብ ህመምተኛ ያደርገዋል፡፡… አንድ ቀን ግን፣ ዘግይቶም ቢሆን አጋጣሚ ይፈጠርና እንባንናለን፡፡ ስለ ራሳችንና ስለ አካባቢያችን መጠየቅ እንጀምራለን፡፡ ከዕቃዎቹ የምንለየው በዚህ ነው፡፡ … ያኔ ራሳችንን ከራሳችን ማስታረቅ፣ ራሳችንን ከራሳችን ማዋደድ፣ ውስጣችንን ማፅዳት፣ ሰላማችንን መመለስ፣ በቅዥት ስካርና በአላፊ ፈንጠዝያ ተደልለን ያመለጠንን… ‘የሚያስብ ሰው የመሆን’፣ ‘ምክንያታዊ ሰው የመሆን’፣ ‘በራሱ የሚተማመን ሰው’ የመሆንን ደስታ ለመፈለግ እንተጋለን፡፡ … ሰው ነንና!! ብንቆሽሽም… እንደ ዕቃው ባስቀመጡን ቦታ አልኖርንም፡፡ … እንደ ዛፍ አድገናል፣ ቅርንጫፎች አውጥተናል፣ ፍሬ አፍርተናል… ይህም የሆነው በተተከልንበት ቦታ ቆመን አይደለም፡፡… እየተንቀሳቀስንና እየሰራን ነው፡፡ … ሰው ነንና!!...
የቆሸሽነው ጥፋትን ባህል በማድረጋችን ብቻ አይደለም፡፡ ተሳስተናል ከማለት ይልቅ ‘ልክ ነን’ ብለን በማሰባችን፣ ‘ዐዋቂ እኛ ብቻ ነን’ ብለን በመገበዛችን፣ ዓይናችንን ጨፍነን፣ ጆሮአችንን ደፍነን፣ ተደላድለን በመቀመጣችን ነው፡፡ ዝገት የሚመጣው እዚህ ስንደርስ ነው፡፡
ወዳጄ፡- አእምሮህ ጤነኛ እንዲሆን ከፈለግህ ልትንከባከበው ግድ ይልሃል፡፡ አእምሮን መንከባከብ ማለት፤ አእምሮህ በትክክል እንዲያስብ ማብቃት ነው፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ለዕውቀት ስትተጋ፣ አካባቢህን መርምረህ እውነትን ለመረዳት ስትጥር ነው፡፡ ፍሬ ነገሩ፡- የቆሸሸን ዕቃ ወይም የጐበጠን ተክል ወደነበረበት መመለስ አስቸጋሪ መሆኑን ማሳወቅና የሰው ልጅ አፈጣጠር ግን ከዚህ በእጅጉ የራቀ እንደሆነ ለማስታወስ ነው፡፡ ሰው ሁሌም በእንቅስቃሴ ውስጥ በመኖሩ፣ በፊት ወደነበረበት እሱነቱ ሊመለስ እንደማይችል የማያጠራጥር ጉዳይ ቢሆንም፤ በይቅርታ የመታረም፣ በዕውቀት የመቃናት፣ በፍቅር የመታደስ፣ ለጋራ ሰላም፣ ለአገር አንድነትና ብልፅግና ለመቆም ራሱን ማስተካከል የሚችልበት ዕድልና ተስፋ እንዳለው ተፈጥሮው ያስገድደዋል ለማለት ነው፡፡
ወደኛም ጉዳይ ስንመጣ፤ የሁለት ሺ አስር ጳጉሜ ይህን አጋጣሚ ፈጥራልን በማለፏ ውድድ አድርገናታል። “ከመቅረት መዘግየት ይሻላል”… እንዲሉ!!
*   *   *
ወደ ቀልዳችን ስንመለስ፡- ሠራተኛዋ ለእመቤቷ፣ ባላቸው ሂሳብ ሲያስጠኗት እንደነበር ስትነግራቸው ‘ብው’ አሉ፡፡ መጥረጊያቸውን አንስተው እያንቆራጠጧት፤ “የኔ አልጋ ብላክ ቦርድ ነው ያለሽን ንገሪኝ” ነበር ያሏት፡፡ ደክሟቸው ከሶፋቸው ላይ ቁጭ ብለው፣ ሰውየው ሲመጡ እንዴት ጉዳቸውን እንደሚያፈሉ ሲያሰላስሉ የዜና ሰዓት ደረሰና፤ “ዛሬ የይቅርታ ቀን ነው”… አለ ቴሌቪዥናቸው፡፡ “ውይ!” አሉ ሴትየዋ፡፡ መጥረጊያቸውን ጥለው ማልቀስ ጀመሩ፡፡ አዲሱ ‘ሰውዬ’ የሚቀየማቸው መሰላቸው፡፡ ይወዱታል፡፡… “የልጅ ወሬ ሰምቼ ጉድ ሆኜ ነበር!!”… ሲሉ አጉተመተሙ፡፡
ሠላም!!

Read 1152 times