Saturday, 15 September 2018 00:00

መድረሻው የማይታወቅ ጉዞ! (መጣጥፍ)

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

 እርግብግቢቱ ያልጠና ህፃን የሚያከናውነው ነገር ሁሉ መጨረሻው አያምርም፡፡ ያች በልጅነቴ መኝታ ቤቴ ግድግዳ ላይ የነበረችው ፖስተር፣ አሁንም ትዝ ትለኛለች፡፡ ፖስተር ሳትሆን ፖስት ካርድ ነገር ናት። ፖስት ካርዷ ላይ የአዋቂ ሰው ጫማ (ምናልባት የአባቷን) አድርጋ፣ ያደረገችውን ጫማ ጎንበስ ብላ የምትመለከት ህፃን ሴት ልጅ ነበረች፡፡ ከምስሉ በታች “I don’t know where I am going but am on my way” የሚል መግለጫ ተፅፎበታል፡፡
እና በዘመኔ ላይ የማያቸውን ሰዎችና በአጠቃላይ ውል ያጣ ሁኔታ ስመለከት ምስሏ… በተለይ ደግሞ ምስሉን ገላጭ የሆነችው ፅሁፍ ትዝ ትለኛለች፡፡ ድሮውኑ ወደ የት እያመራ እንደሆነ የማያውቅ ህፃን…ያውም ልክ ባልሆነ ጫማ የሚራመድ--የሚያስብበት ሊደርስ አይችልም፡፡ ግን መድረስ የሚችል ይመስለዋል። ይፍጨረጨራል … ይንገዳገዳል፡፡ ወይም ክንፉ የተሰበረ ወፍ ከወደቀበት ሆኖ ለመብረር እንደሚንደፋደፈው “በት-በት” ይላል፡፡
በአጠቃላይ የዘመኔን ቀናት የሚጋሩትን የትውልድ መሰሎቼን ግለፃቸው ብባል፤ “በት-በት” የሚሉ ብዬ ነው ልገልፃቸው የምችለው፡፡ ይኼንን ሀሳብ አንዳስብ ያስገደደኝ አንድ ወጣት ነው፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በፍፁም አላማ፣ ላፕቶፑ ላይ አፍጥጦ፣ የመኖሪያ ቤት ዲዛይን ሲነድፍ ነበር የማውቀው፡፡ መነሻውን ያልረሳ፣ መድረሻውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ይመስል ነበር። ትኩረቱ ያስቀና ነበር፡፡ እያስቀና ግን ያስፈራም ነበር። እየተምዘገዘገ ወዳለበት የስኬት ሰማይ ሰተት ብሎ ከመግባት ምንም የሚያግደው ነገር ያለ አይመስልም። የሰዓት አጠቃቀሙ በዙሪያው ካሉ ወጣቶች ፈፅሞ የተለየና ሰዓት ለምን አገልግሎት እንደተፈጠረ እሱ ብቻ የሚያውቅ ያስመስለው ነበር፡፡ እየመራ ካለበት አቅጣጫ ውጭ የሚመጡ መዘናጋትን ወደ ራሱ መስመር የሚመልስበት አኳኋን በዊንበልደን የሜዳ ቴኒስ ቶርናመንት ላይ ለዋንጫ ብቁ የሚያደርገው ነበር።… እናት እንደሌለው ልጅ ሌሎችን የሚያንከራትቱ የህይወት ግቦች እሱ ራኬት ላይ ሲያርፉ በተፈለገበት የባላንጣው ሜዳ ላይ፣ በተፈለገው ስፍራ ውለው፣ ለእሱ ነጥብ ወደሚያስቆጥሩ ድሎች በቀላሉ ይቀየራሉ።
ከሁለት ዓመት በኋላ ያንን ወጣት በድጋሚ ሳገኘው አጠፋሁት፡፡ ለነገሩ ራሱ ከራሱም የጠፋበት ይመስላል፡፡ አይኑ ቡዝዝ ብሏል፡፡ ቁም ነገር መናገር አቅቶታል፡፡ የሚናገራቸው ቀልዶች ደግሞ ራሱ ሜዳ እየገቡ መልሰው ያስተክዙታል። ላፕቶፑን ሸጧል፡፡ መኪናውንም አጥቷል፡፡ በቃ እንደ ሌላው ሰው ሲንደፋደፍ ቆይቶ ተሸንፏል። በሰፊ ጫማ ወደማያውቀው አቅጣጫ የሚጓዝ ተራውን የትውልዱን አባል ሆኗል፡፡ ለካ ያ ሁሉ ‘focus’ መንደፋደፍ ነበር፡፡ በት-በት ማለት ነው በቃ!
ምን አይነት “ሾተላይ” ነው የወጣን ሁሉ አውርዶ የሚጥል? የሰውን ትግል ወደ “በት-በት” የሚቀይር? ሀሳብ ከተሳካ በኋላ ሶኬቱን ነቅሎ፣ባለ ሀሳቡን መና የሚያስቀረው፡፡ ማንኛውም መጓዝ የፈለገ አካል ማወቅ ያለበት ነገሮች አሉ፡፡ ስለ ጉዞው፣ ስለ መጓጓዣውና ስለ ተጓዡ የበለጠ በታወቀ ቁጥር ወደ ግብ የሚደረገው ሙከራ በቀላሉ ወደ መንደፋደፍ አይቀየርም፡፡
ጉዞው ሁሉ በዕጣ ፈንታና እድል እጅ ሲወድቅ እንገፍ-እንገፍ … ደፍ-ደፍ… ዱብ-ዱብ… በት-በት ማለት ይሆናል - የስኬት ሙከራው ሁሉ። ስኬቱ በእድል እጅ ሲሆን የስኬት በሩ ቀዳዳ… ቀዳዳው ደግሞ ስንጥቅ… ስንጥቁን ደግሞ ደርሰው ሊጨብጡት ሲሞክሩ የበረሃ ውሃ… (ሚራዥ) ሆኖ ያርፋል፡፡ እድልን በእጁ ለማድረግ ጉዞውን በልበ-ሙሉነት የጀመረውን፣ በእድል እጅ ወድቆ “ከመታገል መታደል” እንደሚሻል ያሳምነዋል። በማወቅ ያደረገ የመሰለው የስኬት ጉዞ፣ ለካ መፍጨርጨር ነበር? በት-በት ማለት ወደ ቀቢፀ ተስፋ ይጥለዋል፡፡
እና ያንን ወጣት ሳስተውለው አዘንኩለት፡፡ ምንም የምለግሰው ምክር የለኝም፡፡ እኔም ከዚህ በፊት በሁለት የሙያ ዘርፎች፣ ከእውቀት በፊት ተስፋን አስቀድሜ፣ በልጅ ጉልበት ዘምቼ ነበር። የተስፋ ፈረሴ ላይ ተቀምጬ በምጋልብበት … ጦሬን ሰብቄ የድሉን የመሀል ነጥብ (bulls eye) ለመውጋት የተምዘገዘግሁበት ፈረስ ከሥሬ ሟሙቶ መሬት ጥሎኝ ያውቃል፡፡ ከዛ ግን፤ መሬት በወደቅሁበት ሆኜ፣ አወዳደቄን ከመንስኤና ውጤት ጋር ለማስተሳሰር ስሞክር አዲስ እውቀት አገኘሁ፡፡ ምነው ፈረሱን ከመፈናጠጤ በፊት የግስጋሴዬ ኃይል ሳይባክን በፊት ይሄንን እውቀት አስቀድሜ ብይዝ ኖሮ የሚያሰኝ የዘገየ እውቀት አገኘሁ፡፡ ለካ እኔ ፈረሴን ወደ ፍላጎቴ በተስፋ ተፈናጥጬ ጋለብኩ እንጂ መሬቱ የሚጋልበው ለካ እኔ ወደምተጋበት አቅጣጫ አልነበረም፡፡
“መሬቱን” ምሳሌያዊ ወይም ተለዋዋጭ ዘይቤ አድርጋችሁ ልትመለከቱት ትችላላችሁ፡፡ መሬቱን የሀገሩ ነባራዊ ፖለቲካ ወይም ባህል ወይም “Status quo” ብላችሁ ተክታችሁ አንብቡት፡፡ ግን ዋናው ቁም ነገር፣ ተስፋ ከእውቀት ከቀደመ ሩጫ ሁሉ ወደ እንገፍ-እንገፍ ወይም በት-በት መለወጡ አይቀርም፡፡ በማታውቀው ህዝብ ላይ የውጭ ሀገር የስኬት ግብን አንጠልጥለህ ብትሮጥ የመጨረሻው ውጤት የሚሆነው ያላወቅከውን (ቫሪያብል) ያህል ጎደሎ ነው፡፡
ብዙ የሮጡ አይቻለሁ፡፡ ጥቂት ወደ ግብ ደርሰዋል። ወደ ግብ የደረሱት አሯሯጣቸው፣ ከሀገሩ የመሬት አዟዟርና መንፈስ ጋር ተናበው በመሆኑ ምክንያት ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ “ሀቀኛ” ከመሆን “ብልጣብልጥ” መሆን፣ ብዙ ሳይሮጡ ወደፊት የተሻለ መሄድ ያስችላል፡፡ ከተስፋ ይልቅ እውቀት ወደ ግብ ያደርሳል። ብልጠትና ተንኮል፣ በሀገራዊ መሬት አዟዟር አንፃር ከተረጎምነው፣ “እውቀትን” ተክቶ ሊገባ ይችላል። ንፁህ እውቀትን ከመሬቱ የአዟዟር ባህርይ ጋር ካላስማማህ፣ እንደዚያ ወጣት የሄድክበትን ያህል ተመልሰህ ታገኘዋለህ፡፡ ስትመለስ ግን ተስፋን በተስፋ መቁረጥ ወይም ምቀኝነት ቀይረህ ነው፡፡ ተስፋን ከእውቀት ጋር ማዳበል የግድ ነው፡፡ ተስፋ በሀገራዊ መሬት ላይ እውን እንዲሆን ምን አይነት “እውቀትን” ነው መጠቀም የሚያሻው?...
ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ሀገራዊው መሮጫ ሜዳ ራሱ በማይሆን የብልጠት እውቀት እየተሮጠበት ተቦዳድሶ አልቋል፡፡ ብልጦቹንም ከእንግዲህ አያስሮጥም፡፡ ድሮ የዋሁ ነበር ወደ ስኬት የማይደርሰው---ከእንግዲህ ወዲያ ግን ብልጡም አይደርስም፡፡ ከእንግዲህ ሄዶ የሚደርስ የለም፡፡ ሁሉም በት-በት ማለት፣ ፅኑ እጣ-ፈንታው የሆነ ይመስላል፡፡
በዚህ ዓይነት ሀገራዊ የመሬት ስበት ላይ ተወልደው… በመከራ ተፍጨርጭረው ድኸው… ከዚያ ተንገዳግደው… ተደግፈው… ተውተርትረው መራመድ ጀምረው… ድክ-ድክ ብለው፣ አጥንታቸውን በብዙ ተሞክሮ አጠንክረው፣ ለመሮጥ በመዘጋጀት ላይ ላሉ አዝንላቸዋለሁ። “በርቱ” እያልኳቸውም ግን አዝንላቸዋለሁ። በተስፋ ከእኔ በጣም ቢበልጡኝም… የእነሱ የየዋህነት ብርታት በእኔ ተሞክሮ እንድደፍር ፈፅሞ የማይፈቅድልኝን ነገሮች ለመጋፈጥ ሲዘጋጅ እያየሁ አዝንላቸዋለሁ፡፡
እኔ በደረስኩበት የተሞክሮ ንቃት ላይ ሆኜ ስመለከት፣ከተስፋ እውቀት ይበልጣል፡፡ ተስፋ የሚቆልለው ወይም ተስፋ የሚቆርጠው በእውቀት እጦቱ መጠን ነው፡፡ The extent of your Disappointment is the direct result of your expectation …. ልላቸው እፈልጋለሁ። ግን ሰው ተስፋ ሳያደርግ ኑር ማለት አይቻልም። ወጣት ሳትሆን አርጅ ብሎ ከመምከር አይተናነስም፡፡
ስለዚህ ለመሮጥ ሲወጡ እመለከታቸዋለሁ። ከሮጡት መሀል አንዱ ወደ አቀደበት፣ በአቀደበት ቀጥታ መንገድ እንዲደርስ እመኛለሁ፡፡ ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ምኞቴ ደርሶ አያውቅም፡፡ በተስፋ የተጫማውን ሰፊ የህልም ጫማ አድርገው ወይ ጥለው ሲመለሱ ነው የማየው፡፡ ከሁለት አመታት በኋላ እንዳገኘሁት አርኪቴክቱ ወጣት፡፡ ሰፊ የ“ego” ጫማቸውን ጥለው ባዶ እግራቸውን ይመለሳሉ፡፡ ሲመለሱ ይቀላሉ። (“ቀ”ይላላል)። ለካ ተስፋ ነው ሰውን ከባድ የሚያስመስለው… አቅጣጫ የሌለውን የህይወት ዙረት ግብ የሚሰጠው ለካ ተስፋ ነው!
ሲመለስ ግን ሩጫም መፍጨርጨር እንደነበር ተገልጾ ይወጣል፡፡ ወደማይታወቅ አቅጣጫ፣ ለእግር በማይመጥን ሰፊ ጫማ፣ ከመሬቱ ዙረት በተቃራኒ የተሮጠ ሩጫ፡፡ አቅምንና እድሜን አዳብሎ የሚጨርስ የህልም ሩጫ፡፡
ሲመለሱ ነው የሚያውቁት፡፡ ሲመለሱ ነው የሚነቁት፡፡ የሚነቁት ጥርሳቸውን እያፋጩ ነው፡፡ እየተበሳጩ፡፡ ጨለምተኛ እየሆኑ፡፡ ቁም ነገረኝነትን በቀልድ ወደ መለወስ ነው የሚነቁት። ወደ ስነልቦና ስብራት፡፡ ወደ ሱስና መሰል ራስን ሸሽቶ ወደ ማሳበሪያ የአግድም እድገት አማራጮች፡፡
በተለይ ይሄ አርባ ዓመት ይሄንን አሻራ በተስፋ ወደ ምኞቱ የሮጠን ሁሉ እያሰናከለ መልሷል። ከሀገር ውጭ፤ የመሬት ስበቱ ቀለል ወዳለበት ፖለቲካዊ መያዣና መጨበጫ ወዳለበት… የተሻለ ትምህርትና እውቀት ወደሚገኝበት ሄደው፣ የሮጡት የተሻለ ስኬታማ ሆነዋል፡፡ በሌላ ሰው ሜዳ ላይ ለራሳቸው የሚሆን ጎል አስቆጥረዋል። ግን ወደ ሀገር ሲመለሱ የመሬት ስበቱ ያው ነው። ፖለቲካው ያው ነው፡፡ ህዝብና ባህሉ ያው ነው። እንደ ህፃን ሌላ ተስፋ ይዘው ይመጣሉ፡፡ ግን ውጤቱ ብልጠት ካልታከለበት፣ ወደ ስኬት በዚህ የመሬት ስበት ላይ አያደርስም፡፡ ግን የመሬት ስበቱ ራሱ ከዚህ በኋላ፣ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የብልጠት ጥርስ ሞርደው ቢመጡም አያገለግላቸውም፡፡ …. በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ሰዎችን አገኛለሁ፡፡ ከልጅነት ተወልደው ወደ አፍላ ወጣትነት ሲያድጉ ተስፋቸው ይታየኛል… ሁሉ ነገራቸው ንቁ ይሆናል… እርምጃቸው ይቀለጥፋል ያኔ፡፡ … ከሁለት ወደ ሦስት አመት በኋላ መልሼ ሳያቸው፣ ተስፋቸው ከፊል ደመናማ ሆኖ እጣ ፈንታቸው አዝሎ እያንሳፈፋቸው መሆኑን ራሱን አያውቁትም፡፡ አለማወቅ ዋናው ጉዳት ነው። ተስፋን አለማወቅ ሲዳበለው፣ በእኛ አይነቱ የመሬት ስበት የሄደ ሁሉ መመለሱ እንደማይቀር ያስረሳዋል፡፡
“I don’t know where I am going but am on my way” የሚለውን ጽሁፍ፣ ትልልቅ ጫማ አድርጋ የምትጓዘው ልጅ፣ በዛ እድሜዋ ፎቶዋ ስር የተፃፈውን ገላጭ ፅሁፍ (Caption) አታነበውም። እሷ ጫማው ልኳ እንዳልሆነም ሆነ የምትጓዘው መንገድ ወደ ግብ ፈፅሞ እንደማያደርሳት አታውቀውም፡፡ ምናልባት ፖስት ካርዱ ላይ የተፃፈውን የጉዞዋን ግብ በእድሜ ከበሰለች በኋላ ነው አድጋ የምታነበው። ተስፋ በእውቀት ሲተካ። ህልም በእውነታ፡፡… “በት-በት” ማለቱ ሲያበቃና ሁለት እግር ይዞ መሄድ የሚቻለው፣ የመሬት ስበቱ እስከሚፈቅደው ርቀት ብቻ መሆኑ ሲገባት፣ ያኔ አቅሟን አውቃ ምኞቷን በልኳ ታሳርፋለች፡፡ በሰፊ ጫማና በማይሆን ህልም መጓዝ የሚቻለው አርክቴክቱ እስከተጓዘበት ድረስ መሆኑ ይገባታል። አቅሟን ያሳውቃታል፡፡  


Read 1025 times