Saturday, 15 September 2018 00:00

“የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ” (Thunder Stealing)

Written by  ከቃል ኪዳን
Rate this item
(1 Vote)

 Stealing someone’s thunder /የአንድን ሰው ‹ተንደር› መንጠቅ/ ወይም thunder stealing/ ‹ተንደር› ነጠቃ/ ለአንድ ሰው ሊሰጥ የተዘጋጀውን አትኩሮት/ በሆነ መንገድ ቀምቶ ለራስ ማድረግ ማለት ነው፡፡ በሀዘኑ፣ በደስታው፣ በንዴቱ፣ በቁጭቱና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከባለቤቱ ይበልጥ ስሜትን መግለፅ/ማንጸባረቅና ትኩረት መሳብ ‹ተንደር› ነጠቃ ነው፡፡ ‹ቀለበት አሠርኩ!› ብላ ደስታዋን እየገለጸች ያለች ጓደኛን፤ ‹እንኳን ደስ አለሽ! ......እኔም እኮ አረገዝኩ!› ማለት ‹ተንደር› ነጠቃ ነው፡፡ የኋለኛው ይበልጣላ!
‹ተንደር› ነጠቃ በሁሉም ቦታ አለ፡፡ ‹እንዲህ ነው ……እንዲህ ነው ጋብቻ!› እየተባለ የአድናቆት ሙዚቃ ከሚንቆረቆርበት የሠርግ አዳራሽ አንስቶ፤ ‹ምነው በአፈሩ ላይ› እየተባለ ደረት እስከሚደቃበት ድንኳን ድረስ ሞልቷል፡፡ ‹ሃፒ በርዝደይ ቱ ዩ› እየተባለ እልል ከሚባልበት የልደት ድግስ አንስቶ፤ ‹ነብስ ይማር› እስከሚባልበት ሙት ዓመት ዝክር ድረስ አለ፡፡
የ‹ተንደር› ነጠቃውን ያህል ነጣቂዎቹም በሁለቱም ዓይነት ጾታዎችና በሁሉም የዕድሜ ክልሎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከሴቱም፣ ከወንዱም፤ ከህጻኑም ከአዋቂው ውስጥ ‹ተንደር› ነጣቂዎች አይጠፉም፡፡ በገዛ ልጃችን ልደት ላይ ተገኝተው……
‹‹Are you seven?››
‹‹No!››
‹‹Are you eight?››
‹‹Yes!›› ብለው ፈረንጅነታቸውን በሚያሳብቅ የሚያምር ቅላጼ የሚመልሱ፣ ልደቱ ላይ የተገኘውን ሰው ሁሉ ትኩረት የሚስቡና ጉንጫቸውን የሚሳሙ ዳያስፖራ ህጻናት ‹ተንደር› ነጣቂዎች ናቸው፡፡
ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ በቅርቡ የታደምኩበት አንድ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ነው። ‘የታደምኩበት’ የሚለውን ቃል በድፍረት እንድጠቀም ያስገደዱኝ፣ በዕለቱ በቀብሩ ሥነ-ሥርዓት ላይ ያየኋቸው ‹ድራማዎች› ናቸው። በርግጥ እንደዚህ ዓይነት ድራማዎች በቀብር ሥነ-ሥርዓቶች ላይ የተለመዱ ናቸው (ተከታታይ ድራማዎች ባይሆኑም እንኳን ተመሳሳይ ናቸው)። ብዙ ጊዜ ለቀብር የሚሄድ ሰው፣ በአንዳንድ ለቀስተኞች አለቃቀስ ሳይናደድ ወይም ሳይስቅ አይመለስም፡፡
የነዚህ ዓይነት ድራማዎች ዋነኞቹ ተዋንያን ደግሞ የቅርብ ዘመዶች አልያም የቅርብ ዘመድ ነን የሚሉ ለቀስተኞች ናቸው፡፡ ተዋንያኑ የቀብሩ ሥነ-ሥርዓቱን እንደ‹ታለንት ሾዉ› ተጠቅመው፣ ከዘመድ አዝማድና ከለቀስተኞች ሁሉ ‹አውራ-ሀዘንተኛ› ሆነው፣ ገነው ለመውጣት ይጣጣራሉ። ይህን ለማሳካት ደግሞ ሀዘናቸውን ወጣ ባለ አለቃቀስ በማጀብ፤ ከሟቹ/ሟቺቷ ጋር የሚገናኙ ወይም የማይገናኙ አንዳንድ ነገሮችን ሁሉም እንዲሰማ አድርገው ይቀባጥራሉ (ከመቀባጠር ውጪ ምን ሊባል ይችላል?)፡፡ ቅብርጥሴአቸዉ አንዳንዴ የሟቹ ገበናዎች ይሆኑና ለቀብር የመጣውን ሰው ሁሉ ሊያሳቅቁ ይችላሉ፡፡ ‹‹ምነው ዛሬ ተሸነፍክ?......ዛሬ ለምን አትሰድበኝም? ዛሬ ለምን አትቆጣኝም? ዛሬ ለምን አትመታኝም?›› እያሉ ማልቀስ ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው?
አንዳንዴ ደግሞ ከአካባቢው ልማድና የአስተሳሰብ ደረጃ ጋር የማይገናኝ ወይ ደግሞ ‹በአወቅሁሽ ናቅሁሽ!› ውስጥ በቀላሉ ሊወድቅ የሚችል ዓይነት አለቃቀስ ይዘው ብቅ ይሉና አዝኖና ተክዞ የነበረው ቀባሪ አንገቱን ደፍቶ፣ አፉን በነጠላው ሸፍኖ እንዲስቅ ያደርጉታል፡፡ እውነት አሁን ለአምስት ዓመት ህጻን ልጅ ‹‹መካሪዬ፣ መካሪዬ›› እያሉ ማልቀስ እብደት እንጂ ምን ሊባል ይችላል? ቆይ ‹‹-- ልጄ፣ልጄ---›› እያሉ ማልቀስን ማንን ገደለ?
የቀብር ሥነ-ሥርዓቶች ሌላኛው ‹ድራማ›፤ የዕድር ቅጣት ፈርተው ወይ ጉርብትና አስገድዷቸው በሚመጡ ቀባሪዎች ‹የሚሠራው› ነው፡፡ የዚህ ድራማ ተዋናዮች የአተዋወን መንገድ ወይም ብቃት የቀባሪውን ብቻ ሳይሆን የሟቹን/ሟቺቱን የቅርብ ቤተሰቦች ትኩረት እንኳን ሊስብ ይችላል፡፡ እኔ በሄድኩበት ቀብር ላይም ያጋጠመኝ ይሄው ነው፡፡
የነዚህ ‹ድራመኞች› ዋነኛው ዓላማ ‹ተንደር› ነጠቃ ነው፡፡ ቀብሩ ላይ ሀዘንተኛው ቤተሰብ ሊያገኝ የሚገባውን አጀብ፣ አካላዊ ድጋፍና ‹አይዞህ/ሽ፣ በርታ/ቺ› የሚሉ መጽናኛዎችን ነጥቆ ለራስ ማድረግ ማለት ነው፡፡ በአፍላው ሀዘንተኛ እግር ላይ እየወደቁ ደግፉኝ፣ ተሸከሙኝ የማለት አባዜ ነው፡፡
ትናንት አመሻሽ ላይ የሞተ የቅርብ ዘመዱን ሞት ማመን እንኳን ተስኖት፤ በአጀብና በድጋፍ ሊቀብር፤ አስክሬን ተሸክሞ የመጣ ትኩስ ሀዘንተኛ እያለ፤ ከዓመታት በፊት የሞተ ዘመዱ ሃውልት ላይ ተደፍቶ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚል ‹ተንደር› ነጣቂ ቁጥር አንድ፣ ሁለት ብቻ የሚባል አይደለም። የሞተው አፈር ካልቀመሰ ምግብ አልቀምስም በሚል ማህበረሰብ ውስጥ እየኖረ፤ በሸክም ያለው አስክሬን ሳይወርድና ሳያርፍ፤ የዛገ ሃውልት አቅፎ፣ ያዙኝ ልቀቁኝ እያለ፣ የአዲሶቹን ሀዘንተኞች ‹ተንደር› የሚነጥቅ ብዙ ነው፡፡
‹በተንደር› ነጠቃ ተዘፍቆ ምጣዱ ላይ የሚቆላው እያለ እንቅቡ ላይ ያለው ከተንጣጣ ደግሞ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ በርግጥ ሀዘን አይለቅምና እንቅቡ ላይ ያለውን አትንጣጣ ማለት አይቻልም፡፡ ምጣዱ ላይ ካለው በላይ አትንጣጣ፣ ‹ተንደር› አትንጠቅ ማለት ግን ግድ ይለናል፡፡ ደግሞ ሌላው ቢቀር እንኳን ጉርብትናውን አስበልጦ ወይ በእድሩ ተገዶ ሥራ አስፈቅዶ፣ ለቀብር የመጣው ሰውም እንዳይጉላላና እንዳያዝንብን መጣር አለብን፡፡
ማንኛውም ሰው የወዳጅ ዘመዱን የመቃብር ቦታ ሲመለከት እረስቼዋለሁ/ቆርጦልኛል ብሎ ያሰበው ሀዘን ሊያገረሽበትና ተንሰቅስቆ እስኪያነባ ድረስ በሀዘን ሊሸነፍ ይችላል፡፡ በተለይ እንደዚህ ዓይነት ክፉ አጋጣሚዎችን እየጠበቀ የቀብር ቦታን የሚጎበኝ ሰው፣ የረሳው የመሰለው ሀዘኑ ሳይቀሰቀስበት አይመለስም፡፡ አጅበውት የመጡት አስክሬን አፈር ከቀመሰና ቀባሪው ከተበተነ በኋላ የወዳጅ ዘመዱን መቃብር አፈላልጎ ሄዶ፣ እንባውን የሚያፈሰው ለቀስተኛ ቁጥር ጣት አይበቃውም፡፡
የአገራችንን ለቅሶ በእንባ ከሚያደምቀው አንዱ ለቀስተኞች የቅርብ ዘመዶቻቸውን ህልፈት እያሰቡ የሚያፈሱት እንባ ነው (በድንኳን ውስጥም ሆነ በቀብር ቦታ)፡፡  ሀዘንተኞችም ቢሆኑ ‹ተንደራቸውን› እስካልተነጠቁ ድረስ በዚህ ቅሬታ የላቸውም፡፡ እነሱም ሲያደርጉት የኖሩትና ነገም ሲያደርጉት የሚኖሩት ነው፡፡ ሀዘን ያልደረሰበት ሰው፣ እንዴት የሰውን ሀዘን ሊረዳ ይችላል? ከአይዞህ ባዩም እኮ መከራ የደረሰበት በደንብ ያጽናናል!
የለቅሶ ባህላችንን የሚያስረዳ በአንድ የቤተሰባችን ሀዘን ላይ የታዘብኩትና እስካሁን በአእምሮዬ ተቀርጾ የተቀመጠ ነገር አለ። ድንኳን ውስጥ በተሠራ መድረክ ላይ እናቶች (ቤተሰቦችና ጎረቤቶች) ተቀምጠው ለቅሶ ደራሹን ያስተናግዳሉ (የመጣና ያልመጣውን ይቆጣጠራሉ)፡፡ ቀብሩ ላይ መድረስ ያልቻሉ፤ በአብዛኛው ሴቶች የሆኑ ለቅሶ ደራሾች፤ እያለቀሱ ነው ወደ ድንኳኑ የሚገቡት፡፡ እናቶቹ የሚገቡትን እያዩ አብረው ያለቅሳሉ ወይ ደግሞ እስኪጨርሱና ‹ምናግኝቷት ነዉ?...ታማ ነበር?› የመሳሰሉ ጥያቄዎችን እስኪጠይቋቸው ይጠብቃሉ፡፡ ይሄንን ነገር ቁጭ ብዬ ለሰዓታት በግርምት ተመለከትኩኝ፡፡ የቅርብ ሰው የሆነችና ከልቧ ያዘነች ናት፤ ሀዘናችን የእውነት ተሰምቷታል የሚሉትን ነው እንግዲህ አብረው አጅበው የሚያለቅሱት፡፡ ሰምቼ እንዴት እቀራለሁ ብላ ለቅሶ ልትደርስ የመጣችውንና የሴትነቷት የምታለቅሰውን ደግሞ ቁጭ ብለው ይመለከቷታል (አለቃቀሷን ይገመግማሉ)፡፡ በርግጥ የሷም ቢሆን ማልቀሷ ይፈለጋል፡፡
እንደዚህ ዓይነቱ የሰውን እንባ ትክክለኝነት የመረዳት ክህሎታችን ይመስለኛል፣ ‹ተንደር› ነጣቂውን ከእውነተኛው ለይተን በነጣቂው ነገረ ሥራ እንድንናደድ ወይ ለቅሶው ሳይበግረን በድብቅ እንድንሥቅ የሚያደርገን፡፡ አልያማ የትኛው ጤነኛ ሰው ነው፣ የሰው ቀብር ላይ ሄዶ እንባ እያየ የሚሥቀው? የቀብር ላይ ‹ተንደር› ነጣቂዎች እባካችሁ ተው፡፡ አፍላ ሀዘንተኞች ሀዘናቸውን በቅጡ እንዲወጡና እረፍት እንዲያገኙ ቦታና ጊዜ ስጧቸው፡፡ ምናልባት እኮ እናንተን እንዲህ በየሰው ለቅሶ ‹ተንደር› እንድትነጥቁ የሚያደርጋችሁ በጊዜያችሁ ሀዘናችሁን በአግባቡ ሳትወጡ ‹ተንደራችሁን› ተነጥቃችሁ ይሆናል፡፡  
ከሀዘኑ ውጪም በደስታም፣ በንዴትም፣ በቁጭትም ‹ተንደር› ንጥቂያ አለ፡፡ የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ከተንጣጣ ‹ተንደር› ንጥቂያ ነው፡፡ እነሱ በጠጡት መጠጥ እነዚያ ሠክረዉ የሚወላገዱ ከሆነ ‹ተንደር› ንጥቂያ ነዉ፡፡ በተጠሩበት ግብዣ ላይ ደጋሹ እያለ ብሉ ጠጡ ማለት፣ ‹ተንደር› ንጥቂያ ነው፡፡ ብድር ለመበደር ስላሰብን ብቻ የጓደኛችን ደሞዝ ሲገባ፣ ከእሱ በላይ የምንደሰት ከሆነ ‹ተንደር› ንጥቂያ ነው፡፡ ሚዜዋ ከሙሽሪት የበለጠ ካማረባት ‹ተንደር› ንጥቂያ ነው፡፡ ጨለማን ተገን አድርጎ አንገታችንን ሊያንቅ የሚጣጣርን ማጅራት መቺን ‹‹ማጅራት እኮ እንደዚህ አይደለም የሚመታው!›› ብለን አሽከርክርን አንገቱን የምናንቅ ከሆነ ተንደር ንጥቂያ ነው፡፡ የጓደኛችን ሚስት ልትውለድ ስታምጥ ‹ማርያም! ማርያም!› ከማለት አልፈን ቀበቶ የምንፈታ ከሆነ ‹ተንደር› ንጥቂያ ነው (ኧረ እንደውም የዲ.ኤን.ኤ ምርመራ ያስፈልገዋል)፡፡

Read 2261 times