Saturday, 15 September 2018 00:00

“ሕዝበኛው” ማን ይሆን? ..ያልጠረጠረ ሲመነጠር!

Written by  በጌታሁን ሔራሞ
Rate this item
(2 votes)


     ክፍል 1
አሁን ባለንበት ወቅት ፖለቲካዊም ሆኑ ሌሎች ፅንሰ ሐሳቦች የጥንቱን ቁመናቸውን በጊዜ ሂደት እያጡና እየተለጠጡ (Concept stretching) ለአያሌ ትርጓሜዎች የተጋለጡበት ዘመን ነው። ቀደም ሲል በጥቅሉ ይፈተሹ የነበሩ ሳይንሳዊ የዕውቀት ዘርፎችም፣ ዛሬ ሺህ ቦታ እየተሸነሸኑ እንደየ አካባቢው አውድ በነፍስ ወከፍ ጥናት እየተደረገባቸውም ይገኛል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በአንድ ጽንሰ ሐሳብ ላይ የሚኖረን ግንዛቤ ወቅታዊና ቀዬአዊ ብቻ ሊሆን ዘንድ በቅቷል። ነገሩ እንደዚህ ከሆነ በአንዳንድ ዕሳቤዎች ላይ የምንሰጣቸው ትንታኔዎች ቅጥ ካጣ ድፍረት፤ እርግጠኝነትና ድምዳሜ ፀድተው፣ በምትኩ ትህትናንና ቁጥብነትን ተላብሰው ሊንጸባረቁ ዘንድ ግድ ይላል፡፡ የተለወጠ ሁኔታን ባልተለወጠ አስተሳሰብ ለመጋፈጥ ማሰብ ዛሬን በትናንት ውስጥ እንደ መኖር ይቆጠራል፡፡
ለምሳሌ ያህል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን የአመራር አካሄድን በተመለከተ በተለያዩ ፖለቲከኞችና ፀሐፍት በተደጋጋሚ እየተነሳ ያለ ፅንሰ ሐሳብ አለ፡፡ ይኸውም “ዐቢይ የሕዝበኝነት አቀንቃኝ ነው” (Populist…ነው) የሚል ነው፡፡ እስቲ ሁሉንም በዝርዝር አብረን እንመልከት፡፡
ለመሆኑ ስለ ዶ/ር ዐቢይ “ሕዝበኝነት” እነማን ምን አሉ?
ሕዝበኝነት ምንድነው? በዘርፉ ሳይንስ ላይ ተመስርተን ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ከመስጠታችን በፊት በጥቂቱ ወደ አራት የሚሆኑ ፖለቲከኞችና ፀሐፍት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ በአሁኑ ወቅት እያራመዱ ያለውን ፖለቲካዊ አቋምን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከሕዝበኝነት (Populism) ጋር አቆራኝተው ያቀረቡትን አብረን እንቃኝ፡፡
የመጀመርያው የቀድሞው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው ናቸው፡፡ የ”ቀድሞው” ያልኩት አቶ ልደቱ ራሳቸውን ከፖለቲካው ትግል ስለ ማግለላቸው በግልፅ በማሳወቃቸው ነው፡፡ አቶ ልደቱ የካቲት 2010 ዓ.ም. ገና ዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው አስቀድሞ በወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታዎች ላይ አሐዱ ኤፍ ኤም ሬዲዮ 94.3 ላይ ቃለ መጠይቅ ተደርገው  ነበር፡፡ በዚህ ቃለ መጠይቅ ላይ አቶ ልደቱ አያሌው፤ አያሌ ቁም ነገሮችን እያነሱ እንደተለመደው በርቱዕ አንደበታቸው ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ በተለይም በቃለ መጠይቁ 34ኛው ደቂቃ ላይ፣ በኦህዴድ አመራሮች በኩል እየተደረገ ስለነበረው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አድናቆታቸውን ካስቀመጡ በኋላ፣ ኦህዴድ ከኢሕአዴግ በተናጠል የሚያደርገውን የለውጥ ሂደት ግን አፅንዖት ሰጥተው ተችተዋል። ከዚህም ባለፈ አቶ ልደቱ፤ የኦህዴድ (በተለይም ዶ/ር አብይንና አቶ ለማ መገርሳን ይመስለኛል) ባለሥልጣናት በሚያደርጓቸው ንግግሮች ውስጥ ቀደም ሲል በኢሕአዴግ የፖለቲካ ባሕል ባልተለመደ መልኩ፣ የእወደድ ባይነት ፖለቲካ እየተስተዋለ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡ እየተደረጉ ያሉ ንግግሮችም ስሜት ኮርኳሪና መነሻቸውም “ሕዝብ ምን መስማት ይፈልጋል?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ ናቸው በማለት አብራርተዋል፡፡ አቶ ልደቱ በዚህ ትችታቸው፤ ዶ/ር አብይንም ሆነ አቶ ለማን ሕዝበኛ እንደሆኑ በቀጥታ ባይፈርጁም፣ አንድምታው ግን ያለ ጥርጥር ወደዚያው ድምዳሜ የሚመራ ስለመሆኑ አለመጠራጠር አይቻልም፡፡ በብዙዎቻችን ዘንድ በዘልማድ ሕዝበኝነት ማለት ሕዝብ የሚፈልገውን ርዕሰ ጉዳይ እያነሱ ተከታይን ማብዛት እንደሆነ ይተረጎማልና፡፡
ዶክተር አብይን በሕዝበኝነት ካምፕ በመፈረጅ ሁለተኛው ምሁር አቶ ዓለማየሁ ወ/ማሪያም ናቸው። አቶ ዓለማየሁ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ ተመርቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም አሜሪካ ውስጥ በጆርጅታውን ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ እኚህ ምሁር በጁላይ 4 ቀን 2018  በ”ETHIOPIA OBSERVER” ላይ… Ethiopia’s charismatic Leader: Riding the Wave of Populism or Reforming Ethnic Federalism? በሚለው ርዕስ ሥር፣ የዶክተር አብይ አመራር ከሕዝበኝነት ጋር ቁርኝት እንዳላቸው ጥቆማ ሰጥተዋል። እንዲያውም ዶክተር አብይን የሕዝበኝነት ማዕበል ጋላቢ አድርገው ስለዋቸዋል፡፡ በዚህም ሳያበቁ ፀሐፊው ጠ/ሚኒስትሩ በሕዝበኝነት ማዕበል ላይ ከመጋለብ እንዲቆጠቡ ምክር ብጤ እስከ መስጠትም ዘልቀዋል። “If Abiy can avoid riding the populists wave, he can make a fine Ethiopian leader” ከዚህም ባለፈ በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዋርም እየታየ ያለ ለውጥ አንዳንዶች እንደገመቱት፤ በአብዮታዊ ዲሞክራሲና በሊብራል ዲሞክራሲ መካከል እየተደረገ ያለ ፉክክር ሳይሆን ቀውሱን ተከትሎ፣ የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚን ተጠቅሞ ለሥልጣን የሚጋልብ ሕዝበኛ መሪ በዲሞክራሲው መድረክ ያመጣው ውጤት ነው ይላሉ፡፡ “…However, arguably it is not so much a competition between revolutionary democracy and liberal democracy as it is the outcome of an opportunistic populist jockeying for power on a democratizing platform.” እንግዲህ “opportunistic populist” የሚለው ቃል የሚያመለክተው ዶ/ር አብይን መሆኑ ነው፡፡    
በነገራችን ላይ አቶ ዓለማየሁ የፖለቲካ ንድፈ ሐሳብም ምሁር ናቸው፡፡ እኚህ የዘርፉ ምሁር፤ ዶ/ር አብይን የሕዝበኝነት ማዕበል ጋላቢ እንደሆኑ ያሰመሩት የዶ/ሩን የ100 የአመራር ቀናትን ሂደት በገመገሙበት ፅሑፋቸው ነው፡፡ በእኔ በኩል የአቶ አለማየሁን ጥርት ያለውን ምደባ (Crystal clear categorization) ካነበብኩ በኋላ ጠብቄ የነበረው ወደዚህ መደምደሚያ ይደርሱ ዘንድ ያስቻላቸውን አመክንዮአዊ ዝርዝርን ነበር፡፡ ነገር ግን ዶ/ር ዐቢይ ሕዝበኛ መሪ ስለመሆናቸው የሚያስረግጡና በሕዝበኝነት ፅንሰ ሐሳብ ላይ የተደረጉ ጥናቶችን እንዲሁም ሚዛን የሚደፋ ማስረጃን ፅሑፋቸው ውስጥ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ብቻ ግን እሳቸውም በአብዛኛው ያተኮሩት ልክ እንደ አቶ ልደቱ፣ በዶክተር አብይ ንግግሮች ላይ ነው። …ዶክተር አብይ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እየተዘዋወሩ ያደረጓቸው ንግግሮች(Rhethoric) አነቃቂ፤ የፍቅርና የአንድነት ቃና የነገሰበት እንደሆነ በመግለጽ፡፡ እንዲያውም አቶ አለማየሁ፤ ዶ/ር አብይ በ100 የአመራር ቀናት ውስጥ እንደፈፀሟቸው ከዘረዘሩት በጎ ተግባራት ውስጥ አንዳንዶቹ ከአንድ “ሕዝበኛ” የሚል ስያሜ ከተለጠፈበት መሪ የሚጠበቁ አይደሉም፡፡ በእርግጥ አቶ አለማየሁ፤አንድን መሪ ሕዝበኛ ሊያስብለው ከሚያስችላቸው መስፈርቶች አንዱን ፅሑፋቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡ ይኸውም ዶክተር አብይ አግላይ መሪ እንደሆኑ አድርገው የፃፉት ነው፡፡ ያገለሉትም ደግሞ ህወሓትን ነው፡፡ “His rhetoric of love and unity should start at home with his own political base. TPLF , for example, it seems to be still wondering whether Abiy is doing EPRDF’s bidding, or his ego’s….It will also be wise to include the TPLF leadership in the dialogue with Eritera…” በመጨረሻም አቶ አለማየሁ ፅሑፋቸውን ያጠናቀቁት እንደዚህ በማለት ነው፦  “Ultimately, Abiy needs to prove that he is the reformist, not the populist, that Ethiopians have long been waiting.” ነገር ግን ዕውን ዶክተር አብይ ሕዝበኛ ናቸው? አግላይስ ሊባሉ ይችላሉ? እስቲ የዶክተር አብይን ሕዝበኛ መሆን ያለመሆንን፣ ለጊዜው ገታ  አድርጌ ተጨማሪ ጥያቄዎችን ልጠይቅ፡፡ ሕዝበኛ ማለት አቶ አለማየሁ በፅሑፋቸው እንዳስቀመጡት፣ መርህ,አልባነት ነው? ሕዝበኛስ “Refromist” መሆን የሚችልበት አጋጣሚ አይኖር ይሆን? እነዚህ ጥያቄዎች ትንሽ ቆይቼ የምመለስባቸው ይሆናሉ፡፡
ዶ/ር አብይን በሕዝበኝነት የሚፈርጀው ሦስተኛው ፅሑፍ የሚገኘው በ”Tigray Online” ላይ ነው፡፡ ዘዐተ መድህን በተባለ ፀሐፊ ጁላይ 22 ቀን 2018 የተሰናዳ ፅሑፍ ነው፡፡ ርዕሱ “Abiy Ahmed Leading Ethiopia to Oblivion” ይሰኛል…”አብይ አህመድ ኢትዮጵያን ዳግም ወደማትታወስበት ጥፋት ውስጥ እየመራት ነው” እንደ ማለት! እኚህም ፀሐፊ ቢሆኑ የዶክተር አብይን የሕዝበኝነት ምደባን ገና ከጅምሩ ያገናኙት ከንግግራቸው ይዘት ጋር ነው፦ “His populist oratory mesmerized his base and innocent Ethiopians who were yearning for peace and stability” (አብይ በሕዝበኛ ንግግሮቹ ላይ ተመስርቶ ለሰላምና መረጋጋት ድምፃቸውን የሚያሰሙትን ኢትዮጵያዊንን እያፈዘዛቸው ነው)፡፡ ዘአተ የአብይ አጀንዳ ሕዝባዊ እንደሆነም በድፍረትና በእርግጠኝነት ጠቁሟል፡፡ ለዚህም አጀንዳ እነ አሜሪካና አረቦቹ የጀርባ ደጀን እንደሆኑላቸው አስምሯል፦ “USA, UAE and Saudi Arabia  are bankrolling Abiy Ahemed’s populist agenda” ይህም ብቻ አይደለም፤ ከላይ አቶ አለማየሁም እንዳሰፈሩት፣ አቶ ዘአተም በአብይ አህመድ የሚመራው ሕዝበኛው ቡድን፣ ህወሓት-ጠል እንደሆነም ያስገነዘበው እንደዚህ በማለት ነበር፦ “The populist group led by Abiy Ahmed found its constituency in a group of people and entities who hate TPLF. They hate TPLF because they perceive it as the vanguard of the Federal order. Typical of a populist leader, the new prime minister has brought together a demagogic coalition with incompatible ideologies and aspiration to rally around his primary mission of weakening or destroying TPLF” ለልዩ ልዩ ርዕዮተ ዓለማዊ ዕሳቤዎች ምህዳርን አስፍቶ፣ ብዝሃነትን ማስፈን፣ እንዴት ሆኖ የህዝበኝነት ልዩ ምልክት ሊሆን እንደቻለም ግራ ያጋባል፡፡ ዶ/ር አብይ የርዕዮተ-ዓለም ብዝሃነትን ያሰፈኑት፣ ህወሓትን ሆን ብሎ ለማጥቃት ነው የተባለውም ከእውነታው ጋር የሚጣረስ የሀሰት ውንጀላ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ሁሉ ፍረጃ ውስጥ ግን አቶ ዘአተ ልክ እንደ ልደቱና አቶ ዓለማየሁ፣ የዶክተር አብይ ንግግር ሕዝበኛ መሆኑን ከመጠቆም ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የህዝበኛ መሪ ተምሳሌት ሊያደርጋቸው የሚያስችላቸውን አመክንዮአዊ መነሻዎችን በወጉ አስቀምጦ፣ ሲሞግተን ማየት አልቻልንም፡፡ ዘአተም ቢሆን ልክ እንደ አቶ አለማየሁ፣ ዶክተር አብይ ሕዝበኛ እንደሆነ ካስቀመጠ በኋላ ዝርዝሩ ውስጥ ግን ከአንድ ሕዝበኛ መሪ ባሕርይ ጋር የሚጣረስ ነገር ይጠቃቅሳል፡፡ በዚህኛውም ዝርዝር ላይ እመለስበታለሁ፡፡
ቀጣዩ ባለተራ ክቡር አቶ አስመላሽ ወ/ሥላሴ ናቸው፡፡ አቶ አስመላሽ በዝክረ-መለስ 6ኛ አመት መታሰቢያ ላይ ዶክተር አብይ ሕዝበኛ እንደሆኑ በገደምዳሜ አስገንዘበዋል፡፡ በእሳቸው ገለፃ መሠረት፤ ሕዝበኝነት ማለት፦ የሕዝብን ስሜት እየተከተሉ መምራት፤ መርህ አልባነት፤ ኢ-ተቋማዊነት (Anti-institutional)፤ የህዝብን ቀልብ ለመሳብ ሲባል ስሜት ኮርኳሪ ንግግሮችን ማድረግ፤ ሕዝብን በውሸት ቃል መደለል፤ ፀረ ዲሞክራሲ፤ ፀረ ልማት፤ ፀረ ሰላም፤ ኋላ ቀርነት፤አድሀሪነትና መጨረሻውም ጥፋት ነው። ከዚህም ባለፈ መለስ ዜናዊ ሕዝበኝነትን አጥብቆ እንደሚቃወመው፣ አቶ አስመላሽ በጥናታዊ ፅሑፋቸው ላይ አስምረዋል፡፡
ስለ ሕዝበኝነት ፅንሰ ሐሳብ የዘርፉ ምሁራን ምን ይላሉ?
የ21ኛውን ክፍለ ዘመን የፖለቲካውን መድረክ ካጨናነቁ ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የሕዝበኝነት ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ምንም እንኳን የሀገራችን ፀሐፍትና ፖለቲከኞች፣ ሕዝበኝነትን በአብዛኛው ከንግግር ጥበብ (Rhetoric) ጋር አገናኝተው ፅንሰ ሐሳቡን ቢገድፉትም፣ ዝርዝሩ ውስጥ ሲገባ ብዙ ውጣ ውረዶች ያሉበት ነው፡፡ ነገሩ ሁሉ ታላቁ ፈላስፋ ቅዱስ አውግስጢን “If no one asks me, I know what it is. If I wish to explain it to him who asks, I do not know.” በማለት እንዳስቀመጠው ነው…እውነቱን ነው፤ ብዙዎቹን ፅንሰ ሐሳቦች የምናውቃቸው የሚመስለን ጠያቂ ስላላጋጠመን ብቻ ነው፡፡ የሕዝበኝነት ጽንሰ ሐሳብም በፖለቲካው ሳይንስ ወጥ ማብራርያ ከማይሰጥባቸው አወዛጋቢ ጽንሰ ሐሳቦች (Contested concepts) ተርታ ይሰለፋል። Gellener እና Ionescu የተባሉ ፀሐፍት በ” Populism: Its meaning and National Characterstics” መጽሐፋቸው፤ የፅንሰ ሐሳቡን ውስብስብነት በተመለከተ የገለጹት እንደዚህ በማለት ነበር፦ “There can at present, be no doubt about the importance of populism. But no one is clear just what it is. As a doctorine or as a movement, it is elusive and protean.” (“Protean” የሚለው ቃል የመጣው በግሪኩ ሚቲዮሎጂ “Proteus” ወይም የውኃ (ባህር፤ ወንዝ ውቅያኖስ) አምላክ ከሚለው ቃል ሲሆን የሚያመለክተውም ለመገመትም ሆነ ለመተንበይ አስቸጋሪ የሆነ የቅርፅ መለዋወጥን ነው፡፡) እንግዲህ የሕዝበኝነት ፅንሰ ሐሳብም ልክ እንደ “Proteus” በጊዜና በቦታ ሁኔታ ተለዋዋጭ ነው ማለት ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ በሕዝበኝነት ላይ ጥናት በማድረጋቸው የሚታወቁ እንደ “Cas Mudde” እና “Cristobal Rovira”ም ያሉ ምሁራን ሕዝበኝነትን በቀጥታ መተርጎም ለብዙ ግራ መጋባትና ስልቹነት ሊዳርግ እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡ ስለዚህም አዋጪ የሚሆነው የገለፃው ሂደት ከክስተቱ ላይ መንደርደር እንዳለበት ይጠቁማሉ… በእንግሊዘኛው “Phenomenological Definition” ብለን ልንጠራው እንችላለን፡፡ ይህም ሕዝበኝነት በተለያየ የጊዜና የቦታ አውድ (Time-space context) ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ ከሚያሳየው ባሕርይ እየተንደረደሩ ትርጓሜን መስጠት ነው፡፡ ለምሳሌ የእስስት ቀለም ምን ዓይነት ነው? ለዚህ ጥያቄ የሚኖረን ምላሽ ክስተታዊ  (Phenomenological… how it appears) ብቻ ነው መሆን የሚችለው! እስስት ወጥ የሆነ ቀለም የላትምና፡፡ ሕዝበኝነትም እንደዚሁ ነው፦ ለምሳሌ ሕዝበኝነት በአውሮፓና በላቲን አሜሪካ ያለው ትርጉምና ቁርኝት ለየቅል ነው (Space dependent definition)፡፡ እንዲሁም ሕዝበኝነት፣ ትናንትናና ዛሬ ያለውም ትርጉም ለየቅል ነው(Time Dependent definition)፡፡  
አንድን ፖለቲከኛ “ሕዝበኛ” ነው ካልን በኋላ ምደባውን በማስረጃ ለማስደገፍ እንደ መንደርደርያ የሚያገለግሉን ሦስት መሠረታዊ ፅንሰ ሐሳቦች አሉ፡፡ እነርሱም ሕዝብ፤ልሂቃን እና አጠቃላይ ፈቃድ (The People, The Elite and The General will) የተሰኙ ፅንሰ ሐሳቦች ናቸው።  
ሕዝብ፦ የሁሉም ፖለቲከኞች ህልውና የተመሠረተው ሕዝብ በሚለው ቃል ላይ ነው። ፖለቲከኞች ሳያቋርጡ ከሚነግሩን ርዕሰ ጉዳዮች አንዱና ዋናው ለሕዝብ ስለሚከፍሉት መስዋዕትነት ነው፡፡ ሕዝበኛ መሪዎች ዘንድ ሲመጣ ደግሞ ሕዝብ-ተኮር ስብከቱ ይብሳል፤ ለሕዝብ ያላቸው ውክልናም መቶ ፐርሰንት ስለመሆኑ በእርግጠኝነት ያነሳሉ፡፡ ስለዚህም በነርሱና በሕዝብ መካከል ልዩነት ብሎ ነገር የለም፤ አንድ ናቸው፡፡ በወቅታዊው የሕዝበኝነት ፅንሰ ሐሳብ ላይ አያሌ ምርምሮችን በማድረጉ የሚታወቀው ጀርመናዊው Jan Werner Muller በ”What is Populism” መፅሐፉ ላይ “Populists claim that they, and they alone, represent  the people” በማለት ይህንኑ የመቶ ፐርሰንት ውክልና ሙግታቸውን ይፋ ያደርጋል፡፡
ልሂቃን፦ እንግዲህ ሕዝበኛ መሪዎች ሕዝቡን በብቸኝነት የሚወክሉ ከሆነ፣ ከነርሱ አስተሳሰብ የተለየ ሐሳብና አማራጭ ለሕዝቡ ለማቅረብ የሚፈልግ የትኛውም የልሂቃን ቡድን ካለ፣ ጉድ ሊፈላበት ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ሕዝበኛ መሪዎች፤ ሕዝቡ ከነርሱ ውጪ ሌላ አማራጭ ሊኖር እንደሚችል ለአፍታ እንኳን ተስፋ እንዳያደርግ ለልሂቃኑ ልዩ ልዩ ስያሜዎችንና ቅፅሎችን እየሰጠ፣ ከሕዝቡ ሰፈር ያርቃቸዋል… ለምሳሌ ፀረ-ሕዝብ፤ ሙሰኛ ልሂቃን፤ ፀረ-ልማት ወዘተ እያለ ያገልላቸዋል፡፡ እነዚህ በሕዝበኛ መሪዎች ቁም ስቅላቸውን የሚያዩ ልሂቃን የፖለቲካ (ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጨምሮ)፤ የኢኮኖሚ፤ የሚዲያና የሥነ ጥበብ ልሂቃን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም ሕዝበኛ መሪ አግላይ ነው፡ አሳታፊ አይደለም። የፀረ ብዝሃነት (Antipluralist) አመለካከት አቀንቃኝም ነው፡፡ ሕዝበኛ መሪ በተለይም ተቃዋሚ ፓርቲን፣ በየትኛውም መስፈርት እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ አይቆጥርም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕዝቡ ዘንድ ያላቸው ውክልና ዜሮ በመሆኑ ትግላቸው ሁሉ ትርጉም አልባ እንደሆነ አበክሮ ይነግራቸዋል፡፡ ለምሳሌ ሕዝበኛውና የወቅቱ የቱርክ ፕሬዝዳንት ጠይብ ኤርዶገን፤ ተቀናቃኞቹን የሚያሸማቅቅበትና አፋቸውን የሚያስይዝበት፣ “We are the people. Who are you?” የሚል ታዋቂ ሕዝበኛ አባባል አለው። ..አያድርስ ነው! እንግዲህ እነ አቶ ዓለማየሁ ወ/ማሪያም፣ ዶክተር አብይን በሕዝበኛ መሪነት ሲፈርጁት፣ የፖለቲካ ባሕርዩ እንደዚህ ዓይነት ነው እያሉን አንደሆነ ልብ በሉልኝ!
አጠቃላይ ፈቃድ፦ በነገራችን ላይ ሕዝብ የሚለው ፅንሰ ሐሳብ እንደ አንድ ሆኖ በገሃዱ ዓለም የለም፡፡ ሕዝብ ስንል የሚሊዮኖች ስብስብ ነው፡፡ ሚሊዮኑ ደግሞ ሚሊዮን ፍላጎት ሊኖረው ይችላል። ስለዚህ ሕዝበኛ መሪዎች፤ የመቶ ፐርሰንት የሕዝቡ ውክልና አለን ካሉ፣ ሕዝቡ በሙሉ አመለካከቱም ሆነ አስተሳሰቡ፣ “ከፋብሪካ ተመርቶ እንደወጣ ሳሙና”  ምርት፣ ወጥ ነው ማለት ነው። ይህ ግን ውሸት ነው… የለየለት ቅጥፈት! ስለዚህም ሕዝበኛ መሪዎች፤ ሕዝቡን ሁሉ በአንድ የፍላጎት ማዕቀፍ ውስጥ ለመክተት ከወደ ፈላስፎቹ ሰፈር ጎራ ማለት ሊኖርባቸው ነው፡፡ እንግዲህ እዚህ ጋ ነው፣ ሕዝበኛ መሪዎች የፈረንሳዊ ፈላስፋ “Jean Jacques Rousseau” ፍልስፍናዊ ግኝትን ጥቅም ላይ የሚያውሉት፡፡ “Rousseau” አንድ ማሕበረሰብ ሁለት ዓይነት ፈቃድ አለው ይለናል። የመጀመሪያው፤ የእያንዳንዱ ሰው በአንድ በተወሰነ የጊዜ አንጓ ውስጥ ሊኖረው የሚችለው ግለሰባዊ ፈቃድ ድምር (The Will of All) ሲሆን ሁለተኛው ግን ግለሰባዊ ፍላጎቶች ተቀናንሰው፣ ማሕበረሰቡ በሙሉ እንደ አንድ ሕዝብ በጋራ ሊኖረው የሚችለው አጠቃላይ ፈቃድ (General will)  ነው፡፡ ሁለተኛው የፈቃድ ዓይነት ለሕዝበኛ መሪዎች አገዛዝ ምቹ አመክንዮአዊ መሣሪያ ነው። ከዚህም ተነስተን፣ ሕዝበኛ መሪዎች ቅድሚያ የሚሰጡት ለግለሰብ ሳይሆን ለቡድን መብት ስለመሆኑ ማስተዋል ይቻላል፡፡ ሕዝበኝነት በተለይም የሊብራል ዲሞክራሲ ጠንቅ እንደሆነ የሚነገረው ከዚሁ የተነሳ ነው፡፡ (ሊብራል ዲሞክራሲ ባልሰፈነባቸውና አምባገነን ሥርዓቶች በናኙበት ሀገራት ግን ሕዝበኝነት፣ የሕዝቡን ተሳትፎ አመንድጎ፣ ለጅምር ዲሞክራሲው ማበብ፣ አዎንታዊ ተጽዕኖን ሊያበረክት ይችላል፡፡ ይህን እውነት ክፍል 2 ላይ የምናጤነው ይሆናል፡፡)
እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ሦስቱ የሕዝበኝነት አላባዎች፤ በሁሉም ዘመንና በአብላጫው የዘርፉ ምሁራን ተቀባይነት ያላቸው ጽንሰ ሐሳቦች ናቸው፡፡ አንድን መሪ “ሕዝበኛ” ነው ካልን በኋላም ሙግታችንን ማቅረብ ያለብን፣ ከነዚህ ጽንሰ ሐሳቦች እየተንደረደርን መሆን አለበት። ከዚህ ባሻገር አንድ መሪ፣ የእነ እማሆይን ቤት ስለጎበኘ ብቻ “ሕዝበኛ” ነው ማለት፣ ውቅያኖስ የሚያክለውን ፅንሰ ሐሳብ፣ ወደ አንድ ትንሽ ኩሬ እንደ ማሳነስ(Reductionism) ይቆጠራል፡፡
እስቲ አሁን ደግሞ ከፖለቲካ አስተሳሰብነት አንፃር የሕዝበኝነት ምደባ ምን ሊመስል እንደሚችል አብረን እንመልከት፡፡ ማለትም ሕዝበኝነት ርዕዮተ ዓለም ነው ወይስ ሌላውን ርዕዮተ ዓለም ለማሳካት ጥቅም ላይ የሚውል አንድ የፖለቲካ ስትራቴጂ ነው? ሐቲት ነው ወይስ ፖለቲካዊ አመክንዮ? ከዕሳቤው ምደባ ጋር በተገናኛ እ.ኤ.አ. ከ1990ዎቹ ወዲህ በምሁራን መካከል  ጠለቅ ያሉ ክርክሮችና ውይይቶች ተደርገዋል። ከነዚህም ምሁራን ውስጥ የዙሪክ ዩኒቨርሲቲው “Hans-Georg Betz”, አሜሪካዊው የታሪክ ምሁር “Michael Kazin”, እንግሊዛዊው የፖለቲካ ፕሮፌሰር “Paul A. Taggart” እና አሜሪካዊው “Kenneth M. Roberts” ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ምሁራን፤ ሕዝበኝነትን ከላይ በጥያቄ መልክ ጠቀስ እንዳደረኩት፣ በአራት ዓይነት ዕሳቤዎች መድቦ ማጤን እንደሚቻል ያስገነዝባሉ፡፡
ሕዝበኝነት እንደ ርዕዮተ ዓለም፦  ሕዝበኝነትን እንደ አንድ ርዕዮተ ዓለም(Ideology) ቆጥረው፣ ጥናት ከሚያደርጉ የዘርፉ ምሁራን ውስጥ አሜሪካዊው Cas Mudde ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ይህም አካሄድ “Ideational Approach” ተብሎ ይጠራል። ሕዝበኝነትን በዚህ መልኩ ማጥናት ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ የሚታወቅ ቢሆንም፣ በተለይም በአውሮፓዎቹ የሕዝበኝነት ፖለቲካም ሆነ በላቲኖቹ ዘንድ በአሁኑ ወቅት ይህ አካሄድ ሰፊ ተቀባይነትን እያገኘ ስለመምጣቱ Cas Mudde አፅንዖት ሰጥቶ ይገልጻል፡፡
በእርግጥ ይህን ዕይታ የሚያንፀባርቁ ምሁራንም ቢሆኑ ሕዝበኝነት ለሁሉም የፖለቲካ ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጥ ዓይነት ርዕዮተ ዓለም አይቆጥሩትም። ነገር ግን እንደ አንድ የፖለቲካ አጀንዳ፣ ከሌላ ዋና ርዕዮተ ዓለም (Full Ideology) ጋር ተዳብሎ ሊከሰት የሚችል ርዕዮተ ዓለም(Thin-centered Ideology) እንደሆነ አበክረው ይገልጻሉ፡፡ “Cas Mudde” ከዚህ ጋር በተገናኛ ስለ ሕዝበኝነት የሰጠው ታዋቂው ገለፃ በእንግሊዝኛ ይህን ይመስላል፡፦ “Populism is a thin-centered ideology that considers society to be ultimately separated into two homogeneous and antagonistic groups, ‘the  pure People’ and ‘the corrupt elite’ and which argues that politics should be an expression of the general will of the People” እናም በአጭሩ እዚህ ጋ ለማስገንዘብ የፈለኩት፣ ፖለቲከኞቻችን፣ ሕዝበኝነት መርህ አልባነት እንዳልሆነ ልብ እንዲልሉኝ ነው፡፡ ርዕዮተ ዓለም ሊሆን በሚችልበት አግባብ ጥናት ያደረጉ አያሌ ምሁራን እንዳሉም ለመጠቆም ያህል ነው፡፡     
ሕዝበኝነት እንደ አንድ የፖለቲካ ስትራቴጂ፦  በሁለተኛው ምድብ ያሉ ምሁራን፤ ሕዝበኝነት በየትኛውም መስፈርት ከርዕዮተ ዓለም ጋር ንክኪ ሊኖረው ዘንድ አይገባውም በማለት ይከራከራሉ። ይልቁን ሕዝበኝነት፤ ሕዝበኛ መሪዎች ዋናውን የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማሳካት ሲሉ ከህዝቡ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት ለመፍጠር የሚጠቀሙት የስትራቴጂ(Strategy) ዓይነት ነው ይላሉ፡፡ አብዛኞቹ የላቲን አሜሪካ ሀገራት ሕዝበኛ መሪዎች፤ ሕዝበኝነትን የሚጠቀሙት እንደ እስትራቴጂ ነው፡፡ እናም በዚህኛው ምድብም ቢሆን ሕዝበኝነት ፈጽሞ መርህ አልባነት እንዳልሆነ፣ ይልቁን ዋናውን የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ መሣሪያ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል፡፡  
ሕዝበኝነት እንደ አንድ የፖለቲካ ሐቲት፦  ሦስተኛው ምድብ፤ ሕዝበኝነት፣ ሐቲት(Discourse) እንደሆነ ብቻ የሚያምን ነው፡፡ ሕዝበኝነት እንደ ሐቲት በሚቆጠርበት ወቅት ጥቅም ላይ የሚውለው፣ አልፎ አልፎ ሕዝበኛው መሪ፤ ፖለቲካዊ ገለፃውን በፅሑፍ ወይም በንግግር በሚገልፅበት ወቅት ነው፡፡ የ”The Globlal Rise of Populism” መፅሐፍ ደራሲ ስዊድናዊው ቤንጃሚን ሞፊት፤ ሕዝበኝነትን ከሐቲት ጋር ብቻ የሚያገናኙ መሪዎች፣ ከላይ ካየናቸው ሁለቱ ምድቦቹ በተለየ፣ ሕዝበኝነታቸው እንደ ሁኔታው ተለዋዋጭ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ ስለዚህም ሕዝበኝነትን እንደ ሐቲት ብቻ የሚጠቀሙትን መሪዎችን ማወቅ የሚቻለው፣ በየወቅቱ የሚደርጓቸውን የንግግራቸውን ይዘትና ድምጸት በመፈተሽ ነው፡፡ ሕዝበኝነትን እንደ ሐቲት ከሚጠቀሙት መሪዎች ውስጥ የቬኑዙዌላው ሁጎ ቻቬዝ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው፤ የቻቬዝ ርዕዮተ ዓለም ሶሻሊዝም ነው፤ ሕዝበኝነትን ግን እንደ ሐቲት ይጠቀሙታል፡፡ የሚገርመው ግን ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ አንዳንድ መሪዎች የሕዝበኝነት ስያሜ ሳይሰጣቸውና እነርሱም ሕዝበኛ መሆናቸውን ሳያስነቁ፣ ነገር ግን በንግግራቸው ውስጥ ሕዝበኝነትን እንደ ሐቲት ሲጠቀሙ መገኘታቸው ነው፡፡ እንደ “Kirk A. Hawkins” እና “Koopmans Muis” ያሉ ምሁራን፤ የመሪዎችን ንግግርና ፅሑፍ ይዘት፣ እግር በእግር እየተከታተሉ፣ ሕዝበኝነታቸውን የሚደርሱበትና የሚገልጡበት የጥናት መዋቅር (Classical Content Analysis) አላቸው፡፡
ሕዝበኝነት እንደ አንድ ፖለቲካዊ አመክንዮ፦ የመጨረሻውና አራተኛው የሕዝበኝነት ምድብ፣ ፅንሰ ሐሳቡን እንደ ፖለቲካዊ አመክንዮ የሚቆጥር ነው፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይ የበለጠ ግንዛቤ ለመጨበጥ የ”Enersto Laclau”  On Populist Reason (2005b) መፅሐፍ ማንበብ በቂ ነው፡፡   
የእኛ ሀገር ፖለቲከኞችና ፀሐፍት፤ “ሕዝበኛ” የሚለውን ቃል የሚጠቀሙት፣ የሚቃወሙትን ፖለቲከኛ ለማሸማቀቅ አሊያም ለማኮሰስ (Deragatory) ብቻ ነው፡፡ በሌላው ዓለም ግን ከላይ እንደተመለከትነው፤ ሁኔታዎች ተቀይረው፣ ሕዝበኝነት በዋናው የፖለቲካ ፅንሰ ሐሳቦች መስመር በመግባቱ፣ ትኩረት ተሰጥቶት፣ የሚጠናበት ዘርፍ ሊሆን ችሏል፡፡  
ስለ ሕዝበኝነት ዓይነቶች ደግሞ ጥቂት እናንሳ፦ ከነዚህም ውስጥ ገበሬን መሠረት ያደረገ ሕዝበኝነት (Agrarian Populism); ምርጫን መሠረት ያደረገ ሕዝበኝነት (Electroate Populism) እና ለተጨቆኑ ብሔር ብሔረሰቦች የቆመ ሕዝበኝነት (ethnopopulism) በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡
የመጀመሪያውና ግብርናን መሠረት ያደረገው ሕዝበኝነት፣ ከቃሉ ሥርወ አመጣጥ ጋር ቁርኝት ያለው ነው፡፡  ሕዝበኝነት... Populism …የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው እ.ኤ.አ በ1890ዎቹ በደቡብና በማዕከላዊ ምዕራብ አሜሪካ፣ ገበሬውን ማዕከል ያደረገውን የሕዝብ ፓርቲ (People’s Party) የፖለቲካ ንቅናቄን ለማመላከት ሲባል ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ እ.ኤ.አ. በ1860-70ዎቹ በራሺያ ለወቅቱ ፖለቲካ የገበሬው ሚና ወሳኝ መሆኑን ባመኑ ሕዝበኛ ምሁራን የተጀመረው ንቅናቄም፣ “ሕዝበኛ” ተብሎ እንደተሰየመ የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ በሌላ አንፃር የቻይና መሪ የነበረው ማኦ ሴቱንግ፤ ግብርናን እንደ ሕዝበኝነት እስትራቴጂ እንደተጠቀመው ማንሳት ግድ ይላል፡፡ ስንቶቻችን ማኦ ሴቱንግ ከሚከተለው የማሌ ርዕዮተ ዓለም ጎን ለጎን፣ ሕዝበኝነትን እንደ አንድ የፖለቲካ ስትራቴጂ እንደተጠቀመው እንደምናውቅ እጠራጠራለሁ፡፡ ነገሩ እንደዚህ ነው፦  ማኦ፤ ማርክሲስታዊ ርዕዮተ ዓለምን ከራሺያ ሲያስገባ፣ ከሀገሩ ከቻይና ኢኮኖሚያዊ አውድ ጋር አልገጥም ብሎ አሰቃየው፤ ማለትም የማሌ ርዕዮተ ዓለም ሥጋና አጥንቱ የተዋቀረው በላብ አደሩ ላይ ነው፡፡ ቻይና ደግሞ በወቅቱ ላብ አደር የሚባል መደብ ከነአካቴው አልነበራትም…ገና ኢንዱስትሪዋ አላደገም ነበርና፡፡ ስለዚህም ያሉትን ጥቂት ላብ አደሮች ይዞ ወደ ፖለቲካው ገበያ ዘው ብሎ መግባት አደጋኛ ኪሳራን ያስከትላል፤ ስለዚህም ማኦ በእነ ማርክሲስት ርዕዮተ-ዓለም ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ተገደደ፡፡ “ሕዝብ” የሚለውን ስሜት ለመፍጠር ከላብ አደሩ ይልቅ የሚጠቅመው ገበሬው ሆኖ ተገኘ፡፡ እናም የማኦ ዋና ርዕዮተ-ዓለሙ ሶሻሊዝም ቢሆንም፣ ግብርና ተኮር ሕዝበኝነትን እንደ እስቴራቴጂ ለመጠቀም ወስኖ፣ የፖለቲካ አጀንዳውን ወደ ገበሬው አዛወረ፡፡  ይህን በተመለከተም የ”Political Ideologies” መፅሐፍ ደራሲዎች Lean P. Baradt እና John A. Phillips እንደዚህ ይላሉ፦ “An Agrarian country lacking even the small industrial base available to Russia in 1917, China was overwhelmingly rural,so Mao turned to the peasants for political strength…Mao and others realized that the future of the Chinese Revolution was in the hands of the peasantry. The problem of reconciling this practical reality with Marxism, a theory that sees the proletariat as centeral inspired him to develop a unique variation on the Marxist theme፡ Populism…Mao gave the peasants a leading position in the society.” ማኦ በዚሁ ሂደት ገበሬውን ወደ ላብ አደርነት ቀይሮ…Proltarianize አድርጎ.. ከርዕዮተ ዓለም ጋር ላለመላተም ቁም ስቅሉን አይቷል፡፡
እስቲ አሁን ደግሞ ወደ ምርጫ ተኮር ሕዝበኝነት (Electroate Populism) እንሂድ። ሕዝበኛ መሪዎች፤ የሕዝብ ብቸኛ ተወካዮች መሆናቸውን ለማስረገጥ ከሚጠቀሙት እሴቶች ውስጥ አንዱ የምርጫ ውጤት ነው፤ ቀደም ሲል እንዳስቀመጥኩትም፤ …Populists claim that they alone, represent the people. ስለዚህም ውክልናቸው 99% ማለት በእነርሱ ዘንድ የሚታሰብ አይደለም፤ ነውር ነው፤ ነገር ግን ሕዝበኛ መሪዎች ያለ አንዳች ሐፍረት ሽንጣቸውን ገትረው 100% እንዳሸነፉ ይፋ ያደርጋሉ፡፡ ይህን በተመለከተም Jan Werner Muller እንደዚህ ይላል። “Put simply, populists do not claim ‘We are the 99 percent.’ What they imply instead is ‘We are the 100 percent.” ሆኖም ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት፤ በፖለቲካ ሳይንቲስቶቹ ዘንድ እንደዚህ ዓይነቱ ቅጥፈት ቦታ የለውም፤ የ100 ፐርሰንት ውክልናው ሙሉ በሙሉ ቅዠት (Fantasy) እንደሆነ ሁሉም በአንድ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ በአንድ ወቅት ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ከፋብሪካ ከተመረተ ወጥ ምርት ጋር ያመሳሰሉት የሕዝብ ሞዴል፤ በየትኛውም ዘመንና ማሕበረሰብ ውስጥ አይኖርም፤ “Jan Werner Muller”ም ቢሆንም ከላይ ያስቀመጥኩትን አስከትሎ ያለው ይህንኑ ነው፦ “The idea of the single, homogeneous,authentic people is  a fantasy ,as the philosopher Jurgen Habermas once put it ,the people can only appear in plural.”
በሦስተኛ ደረጃ ሕዝበኛ መሪዎች፤ የሕዝብ ወኪል መሆናቸውን ለማመላከት የብሔር ብሔረሰብ ውክልናን “Ethnopopulism”ን እንደ አማራጭ የሚወስዱበት ጊዜ አለ፡፡ በአጭር ቃል “Ethnopopulist” መሪዎች፣ በአንድ ሀገር ያሉትን ብሔሮች ለሁለት ይከፍላሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ፣ የእነርሱ ውክልና ያላቸው የተጨቆኑ ብሔሮች (The People) ሲሆኑ በሌላው ጽንፍ ደግሞ ጨቋኝ ብሔር (The corrupt political Elit) እንዳለ ያመላክታሉ፡፡ እዚህ ጋ “Ethnopopulist” መሪ ሁሌም በቁጥር ብዙ ከሆነው ብሔር እንደማይወጣ ልብ ልንል ይገባል፡፡ በታሪክ እንደታየው፤ እንደዚህ ዓይነት መሪዎች አንዳንዴም በቁጥር አናሳ ከሆኑ ብሔሮችም ብቅ ሊሉ ይችላሉ፡፡ ለዚህም የፔሩ መሪ ፉጂሞሪ በዋቢነት ይጠቀሳል፦ ይህን በተመለከተም Cas Mudde እንደዚህ ይላል፦ “But the populist leader does not even have to be part of the ethnic majority. As we have seen, Fujimori became one of the most popular politicians in Peru despite being part of the small Japanese minority in the country”
በመጨረሻም ሕዝበኛ መሪዎች፤ የሕዝብን ሙሉ ውክልናን በብቸኝነት እንደተጎናጸፉ ለመቆየት ሲሉ ስለሚጠቀሟቸው ዘዴዎች ጥቂት ልበል፡፡ አሜሪካዊው የፖለቲካ ፕሮፌሰር “Jan Werner Muller” ሕዝበኞች ሥልጣናቸውን ላለማስነጠቅ በጥቂቱ ሦስት ዓይነት ዘዴዎችን እንደሚጠቀሙ በስፋት ይዘረዝራል፡፡  
የመጀመሪያው ዘዴአቸው፤ መንግስታዊ ተቋማትን፤ ፍርድ ቤቶችን፤ የሲቪል መሥርያ ቤቶችን በቁጥጥር ሥር ማድረግ ነው፡፡ ይህን ሂደት ደራሲው…Colonizing or Occupying the state…በማለት ይገልጸዋል፡፡ ለዚህም የሐንጋሪው ሕዝበኛ መሪ ቪክቶር ኦርባንና የፖላንዱ ጠ/ሚኒስትር ማቲዎሽ ሞራዊያኪ መሪ ጥሩ ማሳያ ናቸው፡፡ እነዚህ ሕዝበኛ መሪዎች፣ ወደ ፖለቲካው ሥልጣን እንደመጡ፣ የመንግስት የሲቪል መሥርያ ቤቶችን ሳይቀሩ በነርሱ ታማኝ ካድሬዎች አጥለቀለቁ፤ ቀደምት የፍርድ ቤት ዳኞችንም ከሹመታቸው አውርደው፣ ለሥርዓቱ ታማኝ በሆኑ አዳዲስ ዳኞች ተኳቸው፡፡ የመንግስት ጋዜጠኞችም፤ በመንግስት ዕውቅና ያላገኘውንና የመንግስትን ፖሊሲ የሚፃረር ምንም ዓይነት ዘገባ እንዳይሰሩ ማዕቀብ ተጣለባቸው፦ “Media authorities were also immediately capatured, the clear signal went out that journalists should not report in ways that violate the interests of the nation.” በእርግጥ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ሕዝበኛ ባልሆኑ ፖለቲከኞችም የሚዘወተር ነው፡፡ የሕዝበኞቹ መሪዎች የሚለየው መንግስታዊ ተቋሞችን በግልጽ መውረራቸውና ለነርሱ ታማኝ የሆኑ ካድሬዎች የሲቪል ተቋማትን ማጥለቅለቃቸውን፣ ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት ከመሆኑ ጋር አያይዘው ግልጽ ማብራሪያን መስጠታቸው ነው፡፡
ሁለተኛው ሕዝበኛ መሪዎች በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚወስዱት እርምጃ፣ በሕዝቡና በነርሱ መካከል የደንበኝነትን ግንኙነት መፍጠራቸው ነው - “Clinetelism” ይባላል፡፡ ማለትም ለሕዝቡ በዓይነትም ሆነ በገንዘብ ሊሰላ የሚችለውን ጥቅማ ጥቅም በመስጠት ለመደለል ይሞክራሉ፤ ገንዘብ እየሰጡት ሰላማዊ ሰልፍ ያስወጡታል፤ በምርጫ ወቅትም ፓርቲያቸው እንዲመረጥ፣ ብር በነፍስ ወከፍ በጠራራ ፀሐይ ያድላሉ፡፡ “Clientilism” በእንግሊዝኛው…”The exchange of material and immaterial favors by elites for mass political support”….ተብሎ ሊገለፅ ይችላል፡፡  ሕዝበኛ መሪዎች ጥቅማ ጥቅሙን ከገንዘብ ባለፈ በሌላ ልዩ ልዩ ዘዴዎችም ሊከውኑ ይችላሉ። ለምሳሌ የእነርሱን የፖለቲካ አጀንዳ ለሚፈጽሙና ለሚደግፉ፣ በመንግስት መስርያ ቤቶች እድገትና  ሹመትን ለቦታው ባይመጥኑ እንኳን በአፋጣኝ ይሰጣሉ፤ ተማሪዎችም ከሆኑ ከዩኒቨርሲቲ እንደተመረቁ ከማንም ቀድመው የሥራ ዕድል እንደሚያገኙ ቃል ይገባላቸዋል። ይህ ሁሉ የ”Clientilism” ሁነኛ መገለጫዎቹ ናቸው። ከዚህም ባለፈ ለደጋፊዎቻቸው ልዩ የሆነ የሕግ ከለላ ያደርጋሉ፤ አፈንጋጭ ደግሞ የሕዝብ ጠላት ተብሎ ይፈረጅና አስፈላጊ ከሆነም የህግ አንቀፆችም በአፋጣኝ ተከልሰውና ተቀይረውበት ቁም ስቅሉን ያያል፦ ይህም “Discrminatory legalism” ተብሎ የሚጠራው ነው፦ ማለትም፦ …For my friends, everything for my enemies the Law. ለ “Clinetelism” እንደ ምሳሌ ከሚጠቀሱት መሪዎች ወስጥ የቬኑዙዌላው ሕዝበኛ መሪ ሁጎ ቻቬዝ፣ ከነዳጅ ሽያጭ ከሚገኘው ገቢ የተወሰነውን ለዚሁ ዓላማ እንደሚመድቡ ይታወቃል። የኦስትሪያው ጆርጅ ሃይደርም፤ በምርጫ ወቅት የሕዝቡን ድጋፍ ለማግኘት፣ በመቶ ዩሮዎች የሚቆጠር ገንዘብ፣ ጎዳና ላይ በጠራራ ፀሐይ፣ ለሕዝብ በነፍስ ወከፍ ያድል ነበር፡፡ በእርግጥ ይህም ቢሆን የሕዝበኛ መሪዎች ልዩ ባሕርይ አይደለም፤ ነገር ግን ሕዝበኛ መሪዎች ይህን ሁሉ ሲያደርጉ በግልጽ ነው፤ ገንዘብ መስጠታቸውንም የሚያገናኙት፣ ሕዝቡ በምርጫው ተሳትፎ እንዲያደርግና ዲሞክራሲያዊ መብቱን እንዲጠቀም ከማበረታታት ጋር ነው፡፡
ሦስተኛውና የመጨረሻው የሕዝበኛ መሪዎች ዘዴ፤ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ካላቸው ቁርኝት ጋር ይገናኛል፡፡ መንግስታዊ ያልሆኑ(NGO) ድርጅቶች፣ ከሕዝበኛ መሪዎች ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ከገቡ አለቀላቸው ማለት ነው…”Populists in power tend to be harsh with nongovernmental organizations(NGOs) that criticize them” (Jan- Werner Muller ). የራሺያውን የቭላድሚር ፑቲንንና የሐንጋሪውን የቪክቶር ኦርባን አገዛዝን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ማውገዝ በጀመሩበት ጊዜ፣ ሁለቱም መሪዎች ከመቅፅበት ድርጅቶቹን ከውጪ ሃይሎች ጫና ጋር አገናኝተው፣ በሕዝብ  ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ለማሳጣት እርምጃ እንደወሰዱ ይታወሳል፡፡
ውድ አንባቢያን፦ ክፍል 2 ሳምንት ይቀጥላል። በክፍል 2 መጣጥፌ፣ በክፍል 1 መግቢያ ላይ የጠቀስኳቸውና ዶ/ር አብይ ሕዝበኛ እንደሆኑ የገለፁት ፀሐፍትና ፖለቲከኞች አመለካከት፣ ከወቅቱ የሕዝበኝነት ጽንሰ ሐሳብ ጋር የቱን ያህል እንደሚላተም ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡ በመቀጠልም ዶ/ር አብይ አሁን እየተከተሉ ያለው የአመራር ስትራቴጂ፣ ምን እንደሆነ በጥቂቱም ቢሆን እንቃኛለን፡፡ በመጨረሻም ከላይ የጠቃቀስናቸውን የሕዝበኛ መሪዎች ባሕርይን ከቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊና ከፓርቲያቸው ድብቅ የሕዝበኝነት ባሕርይ ጋር እያመሳከርን፣ “ያልጠረጠረ ሲመነጠር” አብረን እንመለከታለን፡፡
መልካም ሳምንት!

Read 2018 times