Saturday, 15 September 2018 00:00

እውነትንና እውቀትን፣ የጥረት ስኬትንና ብቃትን የማንቋሸሽ ዘዴ!

Written by  ዮሃስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 • ለማንቋሸሽ የሚያገለግሉ አባባሎች የትኞቹ ናቸው? “የግለሰብ ሃሳብ”፣ “ራስ ወዳድነት” የሚሉ አባባሎች።  
 • ግን ለምን ማጥላላትና ማንቋሸሽ?! አእምሮና እውቀት የግል ስለሆነ፤... ሕይወትና ብቃት የግል ስለሆነ!
1. “ራስ ወዳድ” ብሎ ማውገዝ ትርጉሙ ምንድነው?...
 • ቤት ሰሪ እና ቤት ሰርሳሪ፣... የራሱን ኪስ የሚያስከብርና የሰውን ኪስ የሚበረብር፣ አምራችና አምታች፣... ልዩነት የላቸውም እንደማለት ነው። “ልዩነታቸውን የሚያይ አይን አይስጠኝ” አይነት ጭፍንነት!
2. “የግል ሃሳብ” የሚለው አባባልስ?
 • እውቀትንና ቅዠትን ማስተማርንና ማሳከርን፣ እኩል እንድናስተናግድና እንድንቀበል የሚገፋፉ
3. እየገነነ የመጣ ፈሊጥ!
• በእውነተኛ መረጃ ምትክ፣... ምን መጣ? “ትርክት” በሚል ፈሊጥ፣... ተረትንና ታሪክን፣... የአሉቧልታ ወሬዎችንና እውነተኛ መረጃዎችን እኩል ማስተናገድ፣.. እንደ ምሁርነት እየተቆጠረ ነው።

• በእውነተኛ መረጃ፣ በትክክለኛ ሃሳብና በእውቀት ምትክ፣... እንደ አልፋና ኦሜጋ የሚቆጠሩ የዘመናችን መፈክሮች የትኞቹ ናቸው? “ትርክት፣ የሃሳብ ብዝኃነት፣ የሃሳብ ፍጭት”... የተሰኙ መፈክሮች!
     

    “የግል አእምሮ” ብንል፣ ትርጉሙ ምን ሊሆን ይችላል? በአጭሩ፣ “አእምሮ” እንደማለት ነው። የግል አእምሮ፣ የእከሌ አንጎል፣ የእከሊት አእምሮ እንጂ፣... ጋን የሚያክል “የጋርዮሽ አእምሮ”፣ “የአቶ ሕዝብ አእምሮ”፣ “የወ/ሮ ብሔረሰብ አእምሮ”... የሚባል ነገር የለማ። “የግል ሃሳብ” ስንልም፣ በቃ፣ “ሃሳብ” እንደ ማለት ነው።
ታዲያ፣ ለምን ይሆን፣ “የግል ሃሳብ” የሚል አባባል፣ ጭፍን የማጣጣያ ፈሊጥ እየሆነ የሚያገለግለው?

እውነትን መስካሪ እና ውሸትን ቀባጣሪ።

አዎ፤... እውነተኛ መረጃን፣ ትክክለኛ ሃሳብንና እውቀትን፣... ከአሉቧልታ ጋር፣ ከጭፍን እምነት ጋር፣ ከተሳከረ ሃሳብ ጋር በእኩል አይን እንዲታዩ የሚያገለግል አጥፊ መሳሪያ ሆኗል - “የግል ሃሳብ” የሚለው አባባል። ይህም ብቻ አይደለም።
እውነትንና ሐሰትን፣ ትክክልንና ስህተትን፣ እውቀትንና ቅዠትን ማስተማርንና ማሳከርን፣ እኩል እንድናስተናግድና እንድንቀበል የሚገፋፉ ሌሎች አጥፊ አባባሎች አሉ - የእውነትንና የእውቀትን ብርሃን የሚያጠፉ አባባሎች።
እውነትን መስካሪ እና ውሸትን ቀባጣሪ፣...  እነዚህ ሁለት ሰዎች፣ ያለልዩነት፣... እኩል የሚስተናገዱት፣ የሁለቱም ሰዎች ንግግር የሁለቱ”የዚህኛው ሰውዬ ንግግር፣ የግል ሃሳብ ነው። የዚያኛው ሰውዬ ንግግርም የግል ሃሳብ ነው” በሚለው አባባል አማካኝነት፣ የሁለቱንም ሰዎች ንግግር እኩል በማውገዝ ወይም በማወደስ ብቻ አይደለም። ይሄ አንድ አጥፊ ዘዴ ነው።
እውነተኛውንና አሉባልተኛውን፣ አዋቂውንና ዘባራቂውን በእኩል ዓይን እንድናይ የሚያገለግል ሌላ አጥፊ አባባልስ? “የዚህኛው ሰውዬ ንግግር፣ አንድ ትርክት ነው።... የዚያኛው ሰውዬ ንግግርም፣ ሌላ ትርክት ነው”....
ይህ አባባል፣... እውነትንና ውሸትን እኩል እንድናስተናግድ ይገፋፋል። “ትርክት” የሚለው ቃል፣ በቅርቡ እየገነነ የመጣውም፣ ከዚህ አይነት አጥፊ አባባል ጋር ተያይዞ ነው።
“የግል ሃሳብ ነው”... የሚለው አባባል፣ አንዳንዴ፣ ውሸትን ከፍ ከፍ፣... ሌላ ጊዜ ደግሞ እውነትን ዝቅ ዝቅ አድርጎ ለማውረድ፣ ያገለግላል - ውሸታምን ለመካብ ወይም እውነተኛን ለማዋረድ።
1. “እውነት፣... ከውሸት አይበልጥም” ብሎ ሁለቱንም እኩል ለማውገዝና ለማዋረድ ሊያገለግል ይችላል - “የግል ሃሳብ” ብሎ ሁለቱንም እኩል በማጣጣል።
2. “ውሸት፣... ከእውነት አያንስም”... ብሎ ሁለቱንም እኩል ለመቁጠርና ለማስተገናገድም ሊያገለግል ይችላል - “የግል ሃሳብ” ብሎ ለሁለቱም እኩል ቦታ በመስጠት።

እውነትና ውሸት፣ እኩል ሲስተናገዱ፣... ውሸት ይንሰራፋል።

ሁለት ሰዎች፣ በየፊናቸው የየራሳቸውን ሃሳብ ሲናገሩ፣... አዎ፣... የዚያኛውም፣ የዚህኛውም ሰውዬ ሃሳብ፣... ያው “የግል ሃሳብ” ነው። ግን በዚህ አያበቃም።
የእያንዳንዱን ሰው ንግግር ሰምተን፣ ሃሳቡን መመርመር ይቻላላ። እያንዳንዱን ሃሳብና ንግግር፣... ከእውነታ ጋር እያመሳከርን፣... ከተያያዝ ማስረጃ ጋር እያገናዘብን፣... ለሕይወት ያለውን ፋይዳ እያመዛዘንን፣... ትክክለኛ ሃሳብ ይሁን ወይም የተሳሳተ ሃሳብ ይሁን፣ በቅጡ መለየት እንችላለን።
የዚህኛው ሰውዬ ሃሳብ በውሸት የተሳከረና የተሳሳተ ሃሳብ ከሆነ፣... ይህንኑን አረጋግጠን ስህተቱን እንዲያስተካክል ማስረዳት፣... አልያም ትተነው ዞር ማለት አይከብድም።
የሌላኛው ሰውዬ ሃሳብ፣ እውነተኛና ትክክለኛ ሃሳብ መሆኑን ካረጋገጥን ደግሞ፣... ሃሳቡን እንደ ትምህርት መጨበጥና የየግላችን ሃሳብ ማድረግ እንችላለን። “ተመሳሳይ ትክክለኛ ሃሳብ መያዝ” ማለት ይሄው ነው። በርካታ ሰዎች፣ በየግል አእምሯቸው እውነትን መገንዘባቸውንና፣ ይህንኑን ትክክለኛ ሃሳብ በየግላቸው መጨበጣቸውን የሚያመለክት አባባል ነው።
ውሸታም ሰው፣ ከእውነተኛ ሰው የበለጠ ተሰሚነት ማግኘት አያስፈልገውም። ሁለቱንም እኩል ሰምቶ እኩል ማስተናገድ፣ እውነትን ወደ ዝቅታ አውርዶ፣ ውሸትን ደግሞ ከፍ ከፍ እንደማድረግ ነው።
ከእውነታ ጋር ያልተመሳከረ የሌጣ ስሜት አሉቧልታ፣... በማስረጃ ያልተረጋገጠ ጭፍን እምነትን፣... ተያያዥ እውነታዎችን ያላገናዘበ የተሳከረ ሃሳብና የዘፈቀደ ንግግር፣... እየገነነ ይሄዳል (እውነትና ውሸት እንደ እኩል ከተቆጠሩ። እውቀትና ጭፍን እምነት እንደ እኩል ከተስተናገዱ)።
የመስተንግዶው አይነት ለውጥ አያመጣም። እውነትና ውሸት፣ እንደ እኩል ተስተናግደው ከተወደሱ ወይም እንደ እኩል ተቆጥረው ከተወገዙ... ያኔ፣... ውሸት ይንሰራፋል።
እውቀትና ጭፍን እምነት እኩል ቢወደሱ፣ ጭፍን እምነት እየገነነ ይሄዳል። እኩል ቢወገዙስ? ውጤቱ ተመሳሳይ ነው - የዘፈቀደ ንግግርንና የሳይንስ ግኝትን... እኩል ለማውገዝ “የግል ሃሳብ” እያሉ የማጣጣል ፈሊጥ ሲዘወተር፣... ጭፍን እምነት ይነግሳል። ለምን? እውተኛውም ሃሰተኛውም፣ ንፁሁም ጥፋተኛውም፣... እኩል በጭፍን የሚወነጃጀሉበት መድረክ፣ “ውይይት፣ የሃሳብ ፍጭት” እየተባለ ይወደስ የለ?
ነገር ግን፣ ጨዋና ባለጌ፣ አዋቂና አላዋቂ በጭፍን እኩል የሚስተናገዱበትና የስድብና የብሽሽቅ መድረክ... ለማን ይመቻል? - ለወንጀለኛው፣ ለሃሰተኛው፣ ለአላዋቂው፣ ለባለጌው።
ሰራስ
እውነትንና ሐሰትን እኩል ከማስተናገድ ጎን ለጎን፣...  ቤት ሰሪንና ቤት ሰርሳሪንም እኩል የማስተናገድ በሽታም አለላችሁ። የራሱን ኪስ የሚያስከብርና የሰውን ኪስ የሚበረብር፣ አምራችንና አምታችን ለይቶ የሚያይ አይን አይስጠኝ የሚል አይነት በሽታ ነው!
ንብረት ያፈራውን ሰውና ንብረት የዘረፈውን ሰው... እኩል የመወንጀል ሱስ የተፀናወተውና ስር የሰደደበት ባህል ነው ጎልቶ የሚታየው - “ራስወዳድ” በሚለው አባባል ውስጥ።
ራስ ወዳድ የሚለውን ጭፍን ውግዘትና ውንጀላ ስንቀበል፣... ሌላ ትርጉም ሊኖረው አይችልም።
አምራቹ ሰውዬ እና አምታቹ ሰውዬ፣ ተመሳሳይ ሆነው ይታዩናል ማለት ነው። ንብረት የሚያፈራ ታታሪ ሰራተኛና፣ የጎረቤቱን ንብረት ለመመንተፍ የሚያሰፈስፍ ቀበኛ፣... እኩል ሆነው  ይታዩናል - “እኩል ራስ ወዳድ”።
ኑሮውን በጥረቱ ለማሻሻል የሚተጋና ለመስረቅ የሚያምታታ፣... አምርቶ ንብረት የሚያፈራና ንብረት የሚዘርፍ ሰው መካከል ያለውን ልዩነት የሚያገናዝብ የስነምግባር መመዘኛና ፍሬሃሳብ የለንም ማለት ነው?
በተቃራኒው፣ አምራቹንና አምታቹን፣ ንብረት ያፈራውንና ንብረት የዘረፈውን... እኩል የሚወነጅል ባህል ነው ጎልቶ የሚታየው - “ራስወዳድ” በሚለው አባባል።

Read 2616 times