Saturday, 15 September 2018 00:00

በአርማና ባንዲራ ጉዳይ ለሚፈጠር ውዝግብ መንግስት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ

Written by 
Rate this item
(3 votes)


    በመላ ሃገሪቱ ከአርማና ባንዲራ ጋር በተያይዞ እየተፈጠሩ ያሉ ውዝግቦች ዘላቂ ሕጋዊ መፍትሄ እንደሚያሻቸው የገለፁት ሰማያዊ ፓርቲና ኦፌኮ፤ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ ወጥተው ወደ ሁከትና ብጥብጥ ከማምራታቸው በፊት መንግስት አፋጣኝ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል።
ከአርማና ሠንደቅ አላማ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ሁከቶችን ለማስቆም የሃይማኖት አባቶችና፣ አባገዳዎች፣በየአካባቢው ወጣቶችን  የማረጋጋት ስራ እንዲሰሩም ፓርቲዎቹ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጠይቀዋል፡፡
“የለውጡን ሂደት መደገፍና አገሪቱን እንደ አገር የማስቀጠል ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው ሲገባ፤ በየአካባቢው የሚታዩ ግጭቶችና ሥርአት አልበኝነት አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል” ያሉት ፓርቲዎቹ፤ “በተለይ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከባንዲራ ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ውዝግብ ከምንም በላይ አሳሳቢ ነው፤ አስቸኳይ እልባት ያስፈልገዋል” ብለዋል፡፡
ሁሉም አካል የሌላውን ባከበረ መልኩ የየራሱን አርማ መያዝ እንደሚችል የተረጋገጠ ሁኔታ መፈጠሩን የጠቀሱት ፓርቲዎቹ፤ በዚህ ሰበብ የሚፈጠሩ ግጭቶችን በፅኑ እናወግዛለን ብለዋል፡፡
በሃገሪቱ በአሁን ወቅት እየታየ ያለው ፖለቲካዊ ለውጥ ተስፋ ሰጪ መሆኑን የጠቆሙት «ሰማያዊ» እና «ኦፌኮ»፤ ሁሉም የፖለቲካ ቡድን ይህን ተስፋ ወደተሻለ ለውጥ የማሸጋገር ኃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡
ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ የትኞቹም ድርጅቶች ያለ አድልኦና መገለል በመላው ህዝብ በፍቅር አቀባበል ሊደረግላቸው እንደሚገባም ፓርቲዎቹ ገልፀዋል፡፡
የባንዲራ ጉዳይ ሃገሪቱ ካለባት ውስብስብ ፖለቲካዊ ችግሮች አንፃር በቀጣይ በህዝብ ውሳኔ እልባት ሊያገኝ የሚችል መሆኑንም በመጠቆምም ሁሉም ወገን ለውጡ እንዳይቀለበስ የበኪሉን መወጣት ይገባዋል፤ ብለዋል፡፡


Read 4774 times