Print this page
Tuesday, 18 September 2018 09:59

“የሄድንበትን ቦይ እንጠይቅ እንመርምር፤ ጅምሩን ሳንጨርስ አዲሱ አይጀመር!” (የአገራችን ገጣሚ)

Written by 
Rate this item
(3 votes)


    አንድ የፋርስ ገጣሚና ነገን ተንባይ (Philosophizing the Future) ከአንድ ሌላ የጊዜው ባለሙያ ጋር፤
አንደኛ - “የመጣነውን መንገድ ጨርሰነዋል ወይ?”
ሁለተኛ - ጥያቄዎቹን አንጥረን ስናወጣ (Crystallized Questions)፤ መፍትሄ የሚያገኙ ንጡር ጥያቄዎች ናቸው ወይ?
ሦስተኛ - “ድንገት ወደ መልስ ካመሩ ወዴት ያምሩ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ባለሙያውም፤
1ኛ/ “ትናንትን ለመጨረስ ዛሬን መጀመር ብቻ በቂ ማረጋገጫ አይሆንም፡፡ ቢያንስ ነገን ማሰብን ይጠይቃል! ስለዚህ ካሁኑ ስለ ነገ መመራመር ጀምር!”
2ኛ/ የነጠረ ጥያቄ ለማውጣት አስቀድመን ፍላጐታችን ምንድነው? ብለን እንጀምር፡፡ ከዚያ ጥያቄዎቻችንን እናሰባስብ፡፡ ቀጥለን አንኳር አንኳሮቹ የትኞቹ ናቸው? እንበል፡፡
3ኛ/ “አንኳር አንኳሮቹን ጥያቄዎች ለማን እናቅርባቸው? ስትል ወዴት ማምራት እንዳለባቸው ራሳቸው ይመሩሃል፡፡ ሁሉንም ስታደርግ ግን በሁለት ቢላዋ ከሚበሉ ሰዎች ተጠንቀቅ!” ብሎት ባለሙያው መምህር ሄደ፡፡ ፋርሳዊው ገጣሚም “ነገን ለመጀመር ትናንትናን ጨርስ” የሚለውን ሀሳብ ዕድሜ ልኩን ይዞት ኖረ!
*   *   *
የነገ ጉዟችን ትላንትና እንደተጀመረ አንርሳ፡፡ ለዚያ ጅምር አስተዋፅኦ ያደረጉትን ሁሉ አንዘንጋ፡፡ የነገ ጉዟችን አጭር ርቀት እንዳልሆነ እናስተውል፡፡ ይህ ጉዞ ከባድ የዕውቀት መሰናዶን ይጠይቃል፡፡ መማር፣ መማር፣ አሁንም መማር ሲባል የነበረው ለትምህርት ጥማት ብቻ ሲባል አልነበረም፡፡ አንድም ትላንትናን ለመማርና ልምድን ለማካበት፣ አንድም በዛሬ ላይ ለመንቃት፣ አንድም ድግም ነገን ለመተንበይ ነው። መማርን ወደ ዕውቀት፣ ዕውቀትን ወደ ጥበብ ስናሳድግ የተግባር ብልሃት ይገባናል። ያኔ አገርን ማሳደግ ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡ ከአሮጌው አስተሳሰብ መፅዳት እንዴት እንደሚቻል ግንዛቤው ከእነ ዘዴው ይመጣልናል! የትምህርትን ነገር ዘንግቶ ስለ ዕውቀት ማውራት ዘበት ነው፡፡ ትምህርታችንን በየዕለቱ መቀጠል እንዳለብን አስተውለን፣ ምን እናድርግ? እንበል፡፡ “ከመጠምጠም መማር ይቅደምከ የሚሉት አበው፣ ጧቱኑ ነገሩ ገብቷቸው ነው፡፡ አውቀናል ብለን ከተኮፈስን፣ አዲስ ዕውቀት ያመልጠናል፡፡ አስበን መኖር ይጠፋናል፡፡ ነገን መጨበጥ ዛሬውኑ ከእጃችን ይወጣል፡፡ ሥጋቶቻችንን እንምከርባቸው እንጂ አንሽሻቸው፡፡
ከአገረ-ዳንኪራ በጊዜ እንገላገል፡፡ የጥንቱ ሥነ-ተረት ስድስት ቅዳሜና አንድ እሁድ ስለነበራቸው ድንክዬዎች የሚያወጋ ነው፡፡ ወደ ሥራ፣ ወደ ማሰብ፣ ወደ ተግባር ለመሄድ ሰባት የሥራ ቀንም አይበቃንም፡፡ በአሉባልታና በጫጫታ የፈረሰችውን እያሪኮ ሳይሆን የጠንካራዋን ኢትዮጵያን አዲስ መሠረት ለመጣል እንነሳ፡፡ አዕምሮ ለአዕምሮ በመናበብ አዕምሮ ላይ እንሥራ፡፡ ሌትና ቀን እንጣር፡፡ የማይታየንን ለማየት እንሞክር፡፡ እንዳናይ ማን ጋረደን እንበል፡፡ በግርግር ጊዜ አናጥፋ፡፡ ከአገረ-ዳንኪራ ወደ አገረ-ኮሰታራ እንቀየር፡፡ አዲስ የተባለን ሁሉ በመነካካት የተለወጥን አይምሰለን፡፡ ለውጥ ጊዜ-ወሳጅና አዳጊ ሂደት እንጂ ሙቅ ማሞቅ አይደለም! ሼከስፒር “Uneasy Lies the head that wears the crown” ይለናል፡፡ ዘውድ የጫነ ጭንቅላት ጭንቀት ይጫነዋል፤ እንደማለት ነው፡፡ ለመጪዎቹ የምናደርገው መስተንግዶ ሁሉ ዘውድ ለመጫን ከሆነ፣ ጭንቀቱንም መጋራት አይቀሬ ነው፡፡ ይህን ልብ እንበል! እግረ-መንገዳችንን ገጣሚው፡-
የሄድንበትን ቦይ፣ እንጠይቅ እንመርምር
ጅምሩን ሳንጨርስ፣ አዲስ አይጀመር
ያለውን በአዕምሯችን እንያዝ!!

Read 4231 times
Administrator

Latest from Administrator